2015 ማርች 19, ሐሙስ

በተመሳሳይ ኃጢአት እየወደቅኩ ተቸገርኩኝ፡፡ ምን ላድርግ?


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሑደ አምላክ አሜን!!!
        ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችኁ? በዛሬው ጽሑፋን ከአንባብያን ከተላኩልን ጥያቄዎች አንዱን ካህናትን ጠይቀን መልስ ይዘን መጥተናል፡፡ መልሱን የሚሰጡን በቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙር የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ ለርሳቸው ተናጋሪ አንደበት ለእኛም ሰሚ እዝነ ልቡና ያድለን፡፡ አሜን!!!
ጥያቄ፡- “እንደምን አላችኁ መቅረዞች? እባካችሁ አንድ ኃጢአት በተደጋጋሚ እሠራለሁ፡፡ ንስሐ አባቴ ጋር በተደጋጋሚ ብሔድም ኃጢአቴን መተው አልቻልኩም፡፡ ምን ላድርግ? እባካችሁ ጉልበት የሚኾነኝ ምክር ስጡኝ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡”
 
        ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- አንድ ሰው “ምን ላድርግ?” ብሎ ሲጠይቅ መንፈሳዊ ሕይወትን መፈለጉ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን “ምን ማድረግ ይገባኛል?” የሚል ጥያቄ ካነሣ ለማደግ መፈለጉን፣ መንፈሳዊ መፍትሔ መሻቱን፣ እግዚአብሔር እንደሚረዳው በማያጠያይቅ መንገድ ማመኑን ያመለክታል፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሚያስተምርበት ጊዜ ሕዝቡ፣ ቀራጮች እንዲኹም ጭፍሮች እየመጡ፡- “ምን እናድርግ?” ይሉት ነበር /ሉቃ.3፡10-14/፡፡ ስለጠየቁም “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ብሏቸዋል /ማቴ.3፡8/፡፡ ሐዋርያት ሲያስተምሩ፡- “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” ያሉት የገባቸው ናቸው /ሐዋ.2፡37/፡፡ ስለዚኽ ምንም ደካሞች ብንኾንም ድካማችንን ከእኛ የሚያርቀው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር “በርሱ ቃል እታነፃለኁ፤ እመከራለኁ” ብሎ “ምን ላድርግ?” ብሎ መጠየቅ ታላቅነት፣ አንድም ትሕትና፣ አንድም የመንፈሳዊ ሕይወት ፍላጎትን የሚያሳይ ነውና ኹል ጊዜ ጠያቂዎች ለካህናት፣ ለቤተ ክርስቲያን መምህራን “ምን ማድረግ ይገባኛል?” ብለው ሲጠይቁ ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡ በመኾኑም ውድ ጠያቂያችን ምሥጢራቸውን በማካፈል የኃጢአት ልምምድ ድል መንሻ ጥበባትን እንድንማማር ምክንያት ስለኾኑን በልዑል እግዚአብሔር ስም ላመሰግናቸው እወዳለኁ፡፡
ጥያቄው የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ፡- “ሰው ኾኖ የማይበድል እንጨት ኾኖ የማይጤስ” እንዲሉ እንደየኑሮአችን ደረጃ፣ እንደየሥራችን ዓይነት ይለያይ እንደኾነ እንጂ ክርስትና ሕይወታችን ስንመላለስ አንድ ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ ኃጢአት የሚስማማን መኾኑ ነው፡፡ ጥያቄአችንም ጠያቄአችን እንዳነሡት “ምን እናድርግ?” ነው፡፡ በርግጥም “ምን እናድርግ?”፡-
1.     የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ማወቅ፡- አንድ ሰው የሚወድቅበት ሌላኛው የማይወድቅበትና ትኩረት የማይሰጠው ሊኾን ይችላል፡፡ ከዚኽ አንጻር ጠያቂው “በተመሳሳይ ኃጢአት ደጋግሜ እወድቃለኁ” ያሉት ኃጢአት ምንድነው? እየተደጋገመ ያስቸገራቸው ምንድነው? ከምንም በፊት የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ያጢኑት፡፡ መፍትሔው የሚዠምረው ከዚኽ ነው፤ የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ከማወቅ፡፡
2.    የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ከለዩ በኋላ ለዚያ ከሚዳርጉን ቦታዎች፣ ወይም ጓደኞች፣ ወይም ኹኔታዎች መሸሽ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ወደምንወድቅበት ኃጢአት የሚገፋፉ ኹኔታዎችን፣ ቦታዎችን ወይም ጓደኛን በአጠቃላይ እንደየኃጢአቱ መነሻነት መራቅ ያስፈልጋል፡፡ “ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ኾነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ኾነህ ትገኛለህ” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት /መዝ.18፡26/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- “አትሳቱ፤ ክፉ ባለንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል /1ኛ ቆሮ.15፡33/፡፡ በዚኽ መሠረት ጠያቂያችን ብቻ ሳይኾኑ ኹላችንም ኃጢአትን ደጋግመን የምንሠራው በኹኔታዎች ተጽዕኖ ነው? ወይስ በጓደኞች ግፊት? ወይስ በምንሰማው፣ በምናየው፣ በምንዳስሰው ተጽዕኖ? ይኽን በአግባቡ ከለየን በኋላ ከምንጩ ለማድረቅ ለዚያ ከሚዳርጉ ኹኔታዎች መሸሽ ነው፡፡ ይኽን ስናደርግም ከምንም በፊት ኅሊናን ማሳመን ይጠይቃል፡፡ በመቀጠልም አካላዊ ውሳኔ መስጠትን ነው፡፡ ለኃጢአት በሚዳርግ ቦታ ተቀምጠን “በፍጹም አይነካኝም፤ አይደርስብኝም” ማለት መመጻደቅ ነው፡፡ ሰይጣንም እኛን ለመጣል አያርፍምና የምንወድቅበትንም መንገድ ያዘጋጃልና በኅሊናም በአካልም ከዚያ መሸሽ ያስፈልጋል፡፡ የጴጢፋራ ሚስት ዮሴፍን ለክፉ ሥራ ስትከጅለው ቆሞ አልተሟገተም፤ ጥሏት ሸሸ እንጂ /ዘፍ.39/፡፡ ስለዚኽ ለተደጋጋሚ ኃጢአት ከሚዳርጉንና ከሚገፋፉን ነገሮች “እችለዋለኁ፤ እቋቋሟዋለኁ” ብሎ መመጻደቅ ሳይኾን መሸሽ ካለብን መሸሽ ያስፈልጋል፡፡ እንደየኹኔታው በይበልጥም ከክፉ ቦታዎች፣ እንደየኃጢአቱ መነሻነት መሸሽ ያስፈልጋል፡፡
3.    ኃጢአቱ በሥጋም በነፍስም ጎጂ እንደኾነ ማስተዋል፡፡ ይኽ በተመሳሳይ እየወደቅንበት ያለው ኃጢአት በሥጋም ጭምር የሚጎዳን ይኾናል፡፡ ከክርስትና ሕይወት ባሻገር ስብእናን የሚያጎድፍ፣ ጤናን የሚያውክ ሊኾን ይችላል፡፡ ከዚኽ አንጻር የዚኽ ጉዳት በጥልቀት ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ጉዳት ማሰብ ለመጠንቀቅ ይረዳልና፡፡
4.    ከመምህረ ንስሐ፣ ከመምህራን እንዲኹም ከመጻሕፍት ትምህርት ማግኘት፡፡እድገት በደረጃ ነው፡፡ በአንድ ጀምበርም ለውጥ ላይመጣ ይችላል፡፡ በመኾኑም በሒደት ያንን የመተው መስመር ውስጥ እንድንጠነክር ከዚኽ ኹኔታም ፈጽመን ለመራቅ በራሳችን ጉልበት ብቻ አንችልም፡፡ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሎናልና /ዮሐ.15፡5/፡፡ በዚኽም መሠረት ከመምህራን የምንሰማው የእግዚአብሔር ቃል፣ ከመጻሕፍት የምናገኘው፣ ከመምህረ ንስሐም በጸሎትና በምክር የምናገኘው ሐሳብ ያ እያጠቃንና እየጣለን ያለውን እንዲኹም የምንደጋግመውን ኃጢአት ለማስወገድ ኃይል ይኾነናል፡፡
5.    መንፈሳዊ ተግባራትን ማዘውተር፡፡ እንግዲኽ እንደየ ክስተቱ ለየትኛውም የኃጢአት ተግባር መንፈሳዊ ሕይወት፣ መንፈሳዊ ተግባር ድል መንሻው ነው፡፡ ይኽም “እንዲኽ ያለውን ክፉ መንፈስ ያለ ጾም ያለ ጸሎት ከእናንተ አይወጣም” እንዳለ /ማር.9፡29/ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ንስሐን የሕይወታችን መሠረት ማድረግ ነው፡፡
6.    መተውን መለማመድ፡፡ ይኽም ማለት ጠቢቡ “ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” እንዳለ /ምሳ.23፡17/ “እስኪ ዛሬ ተቆጥቤ ልዋል” ብሎ መወሰን ማለት ነው፡፡ ከዚያ ከምንጠላው ግን ደግሞ እየወደቅንበት ካለው ስሕተት ተቆጥበን ከዋልን ማታ ላይ ተመስገን ብሎ ጸልዮ ማደር ነው፡፡ ነገም ሲነጋ “ዛሬም እንዲኹ እንደ ትናንትናው መንፈሳዊ መንገድና ሒደት ልዋል፡፡ ዛሬም እንዲኽ ካለው ተግባር ፍጹም ተቆጥቤ መዋል አለብኝ፡፡ ደግሞም እችላለኁ፡፡ እግዚአብሔር ያስችለኛል፡፡ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ኹሉን እችላለኁ፡፡ እግዚአብሔር ያበራታኛል” ስንልና ዕለት ዕለት ኹኔታውን እየኰነንነው፣ እያወገዝነው፣ “በዚያ መንፈስ ዛሬ አልውልም፡፡ ይልቁንም በመንፈሳዊ መንገድና በጥንካሬ እውላለኁ” ብለን ስንወስን ያን ውሳኔአችንን እያደነቅን ስለተደረገልን ጥንካሬም ተመስገን እያልን ልምምድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ደጋግመን የምንሠራው ኃጢአት እጅግ ብዙ ዘመናት ከእኛ ጋር የቆየ ሊኾን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ኃይል በላይ የኾነ ኃጢአት የለም፡፡ ዋናው የእኛ ውሳኔ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምንታለለው እዚኽ ጋር ነው፡፡ ለመተው እንፈልጋለን፤ ለመተው ግን በተግባር አንወስንም፡፡ ንስሐ መግባት የማይፈልግ ሰው የለም፤ በተግባር ወስኖ የሚገባ ግን ጥቂት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ መኖር የማይፈልግ ክርስቲያን አይኖርም፡፡ ብዙዎች መቁረብ ይፈልጋሉ፤ ወስነው የሚቆርቡት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ከዝሙት ኃጢአት መራቅ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ዝሙትን የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ምስሎችን እንዲኹም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ዘፈኖችን እንዲኹም ጽሑፎችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ንግግሮችን ሲያደርጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚኽን ሰዎች ስናያቸው በውስጣቸው ከዚያ ኃጢአት የመራቅ ፍላጎት አለ፤ ተግባሩ ላይ ግን ከዚያ የሚያሸሻቸው አይደለም፡፡ ለዚኽም ነው ጌታ፡- “ብዙዎች ይፈልጋሉ፤ አይችሉምም” ያለው /ሉቃ.13፡24/፡፡ ስለዚኽ ከኃጢአት መራቅ የሚፈልግ ሰው የመተው ልምምድን አኹንኑ መዠመር አለበት፡፡ “ዛሬ ዘፈን አላዳምጥም፡፡ ዛሬን በዚኽ ምትክ መዝሙር አዳምጣለኁ” ብሎ መለማመድ አለበት፡፡ በዚኽ ውሳኔው ጸንቶም ዛሬን ይውላል፤ ያድራልም፡፡ ሌሎች ነገሮችም እንደዚኽ ናቸው፡፡ የመጠጥ ልምድ ያለው ሰው “ዛሬ አልጠጣም፤ ዛሬ በምጠጣበት ሰዓት እዚኽ ቦታ እሔዳለኁ፡፡ እዚያ ሒጄ እውላለኁ፡፡ በበጎ ነገር አሳልፈዋለኁ” ሲል ዛሬን ይውላል፡፡ ማታ ላይ ሲመሽ “ለካ ይቻላል፡፡ ለካስ እኔ ከበረታኁ እግዚአብሔር ያስችለኛል” የሚለውን በኅሊናው ያሳምናል፡፡ ነገሮችን የመተው ልምምድ በተግባር ማሳየት ማለት ይኸው ነው፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያ ያስቸግረን የነበረው ተደጋጋሚ ኃጢአት ታሪክ ይኾናል፤ ለሌላ ሰው መካሪ ኾነን ራሳችንን በለውጥ ቦታ ላይ እናገኟለን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡         

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...