2014 ኖቬምበር 23, እሑድ

.ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ሦስት ገዳማት የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ


•ለፕሮጅክቶቹ ማስፈጸሚያ ከ3 ሚሊዮን 180 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡
ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.


በእንዳለ ደምስስ
gundagundi 02ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡


በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት እነዚህ ፕሮጅክቶች ከኅዳር 3/2007 ዓ.ም. - ኅዳር 8/2007 ዓ.ም. ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለየገዳማቱ አስረክቧል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ፅብላ ወረዳ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም በ630 ሺሕ ብር የተሠራ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ 150 ሺሕ ሊትር መያዝ ይችላል፡፡ ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በገዳሙ ውስጥ ተገንብቶ በመጠናቀቁ ማኅበረ መነኮሳቱ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በቀን ከ4-5 ሰዓት በመጓዝ የሚባክንባቸውን የአገልግሎትና የጸሎት ጊዜያቸውን እንደሚያስቀርላቸው የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡

abune tomas zehayda 02 1ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ገዳሙ ጥንታዊና ገዳማዊ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ የሚገኝበት ሲሆን፤ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

gundagundi 03በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡

ሕንፃው በ416.49 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ማኅበሩ የሠራው የምድሩን ወለል ብቻ ነው፡፡ መሠረቱ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃን መሸከም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ገዳሙ ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ይገነባል፡፡

ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ቀድሞ በርካታ መነኮሳት የነበሩባት ቢሆንም በደርግ መንግሥት የነበራት ሰፊ ይዞታ በመነጠቋ የመነኮሳቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በችግር ምክንያት እየተመናመነ ሄዶ ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ እነሱም በገዳሟ ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ገዳማት የማይገኙ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ለማን ጥለን እንሔዳለን በማለት ችግሩን ተቋቁመው ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡

ወደ ገዳሟ ለመድረስ መንገዱ አስቸጋሪና መኪና የማይገባ በመሆኑ የአንድ ቀን ሙሉ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ለመመለስም እንዲሁ የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ገዳሟ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሲሆን፤ የሁለገብ ሕንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመነኮሳቱ ቁጥር ከሁለት ወደ ሰባት ከፍ ለማለት ችሏል፡፡

dibo 02በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡

የሽመና ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው በገዳሟ ውስጥ ለሚገኙት መነኮሳይያት ሲሆን፤ መነኮሳይያቱ ቁጥራቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የሽመና ውጤቶችን ማምረት ያስችላቸዋል፡፡

ደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ ከሚባሉ ገዳማት መካከል የምትመደብ ስትሆን በውስጧም ጥንታዊ ሥዕላትን ጠብቃ ለትውልድ በማቆየት ትታወቃለች፡፡ ለትኅርምት እና ለጽሞና የምትመረጥም ገዳም ናት፡፡

ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍሉ አማካይነት ለበርካታ ገዳማትና አድባራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ገዳማት የልማት ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡

በደ/ኦሞ: በሀ/ስብከቱ እና በማኅበረ ቅዱሳን መተባበር ከ16 ሺሕ በላይ ምእመናን ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተጨመሩ፤ ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ደስታ ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/


baptism and church inaguration Jinka 2007the newly consecrated Jinka Dabre Keraniyo Medhanielm church
  • ከ1300 በላይ አዲስ አማንያን በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተጠመቁ
  • በዓመቱ 17‚000 አዲስ አማኞችን ለማፍራት በመርሐ ግብር የተያዘው ዕቅድ አካል ነው
  • ከተጠማቂዎቹ፣ ከባዕድ አምልኮ የተመለሱ አርብቶ አደሮች እንደሚገኙበት ተመልክቷል
*              *              *
ተጠማቂዎች ከየስብከት ኬላዎች ወደ ጂንካ ለጥምቀተ ክርስትና ሲገጓዙ
ተጠማቂዎች በታላቅ መንፈስ ከየስብከት ኬላዎች ወደ ጂንካ ለጥምቀተ ክርስትና ሲያመሩ
ተጠማቂዎች ወደ ጥምቀተ ክርስትና በጉዞ ላይበዲዛይን ሥራው የማኅበረ ቅዱሳን ሞያዊ አስተዋፅኦ ከተገለጸበት አዲሱ የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት (ምረቃ) ጋራ ጥምቀተ ክርስትና የተፈጸመላቸውና ከሰባት የስብከት ኬላዎች የተውጣጡት 1350 ምእመናን ጂንካ የደረሱት ከየስብከት ኬላዎቻቸው (ሼፒ ጋኢላ፣ አልጋ ኪለት፣ ዛቢ፣ ጉርጨት፣ ሰንሰለት፣ አይዳ እና ጋራ) ለሰዓታት በእግራቸው ተጉዘው ነው፡፡
የሀገረ ስብከቱን ነባር አብያተ ክርስቲያን በመደገፍና አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማነፅ ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰው የደቡብ ኦሞ የስብከተ ወንጌል፣ የልማት እና ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ለጥምቀተ ክርስትናው መከናወን የገንዘብና ከፍተኛ የቁሳቁስ እገዛ አድርጓል፡፡
ኮሚቴው በጂንካ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በ45 ሚልዮን ብር ወጪ ለሚያሠራው የአብነት ት/ቤት ግንባታ እና ለሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ፓትርያርኩ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠዋል፡፡
*                *               *
the newly convert cathecumen being baptized
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጥምቀተ ክርስትና
ጠረፋማ የአገራችን አካባቢዎች አተኩሮ በሚካሔደውና ከ፳፻፫ – ፳፻፲፩ ዓ.ም. የተዘረጋው የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተጨመሩት አዲስ አማኞች ጠቅላላ ቁጥር ከ26 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገልጧል፡፡
በ፳፻፭ ዓ.ም. የአገልግሎት ዓመት መርሐ ግብሩ በሸፈናቸው የጉምዝ፣ ካፋ(ጫራ) እና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች በተከናውነው ጥምቀት ክርስትና 8,744 አዲስ አማኞች የቅድስት ሥላሴ ልጅነት እንዲያገኙ የተደረገ ሲኾን በተያዘው የ፳፻፯ ዓ.ም. የአገልግሎት ዓመት በአምስት ቦታዎች 17‚000 አዲስ አማንያንን ለማፍራትና የተጨመሩትን ምእመናን ለማጽናት ከብር አምስት ሚልዮን በላይ በጀት በመርሐ ግብሩ ተይዟል፡
being baptized
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በጥምቀተ ክርስትና
ሀብተ ውልድና ጥምቀተ ክርስትና አግኝተው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱትን ምእመናን የሚያጸኑ የትግበራ ዕቅዶች ከአህጉረ ስብከት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንና ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ በመቀናጀት ይፈጸማሉ፡፡
ተጠማቅያኑ የሚገለገሉበት ቤተ ክርስቲያን መትከል፣ በቋንቋቸው የሚያስተምሯቸውን ሰባክያንና ካህናት ማሠልጠን፣ በቋንቋቸው የሚማሩባቸውን ጉባኤያት እና ሐዋርያዊ ጉዞዎች ማካሔድ፣ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን (የትምህርት መጻሕፍትንና በራሪ ጽሑፎችን፣ የስብከት እና የመዝሙር ካሴቶችንና ሲዲዎችን) ማዘጋጀትና ማሰራጨት ተጠቃሽ የመተግበርያ ስልቶች ናቸው፡፡
one of sibket kelas(Merafe Sibket)
ቤተ ክርስቲያን ባልተተከለባቸው የገጠር ቀበሌዎች የሚቋቋሙት የስብከት ኬላዎች÷ በቅድመ ጥምቀት የተጠማቂ ምእመናን ቅስቀሳና ሥልጠና፤ በጊዜ ጥምቀት የተጠማቂ ምእመናን ዝግጅት እና በድኅረ ጥምቀት ተጠማቂ ምእመናንን በተከታታይ ትምህርትና የአብነት ትምህርት የማጽናት አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ የስብከት ኬላዎች/ምዕራፈ ስብከት/ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያስፈልጓቸው የትግበራ ቁሳቁሶች በማስፋፊያ መርሐ ግብሩ ወጪ የሚሸፈን ሲኾን አዲስ ምእመናን እንዲጨመሩና የተጨመሩትም እንዲጸኑ በየቋንቋው የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልም የገንዘብ ድጎማ ይደረግላቸዋል፡፡

አዲስ አማኞችን በማጥመቅ፣ ያሉትን በማጽናትና የካዱትን በመመለስ ላይ ባተኮረው የማስፋፊያ መርሐ ግብሩ÷ የምእመናንን ቁጥር ጨምሯል፤ በቋንቋ የሚያገለግሉና ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑ ካህናትን ለማፍራትና የሰባክያንን ቁጥር ለማሳደግ ተችሏል፤ የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት ተጠናክሯል፡፡ በቋንቋ የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርት እጥረት፣ የገንዘብ አቅም ማነስና በቂ መጓጓዣ አለመኖር የፕሮግራሙ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡
*               *                *
Lique Tiguhan Wondewosen Gabre Sellassieይህ ያለእግዚአብሔር ርዳታ ከፍጻሜ አይደርስም፡፡ በክንዳችን ውስጥ የእግዚአብሔር ክንድ ስላለ በኻያ ዓመት የማያልቀውን ይህን ሕንፃ በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ የረዳን እግዚአብሔር ነው፡፡
ሌላም ብሥራት አለ! የሚገርመው ነገር፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በሚመረቅበት በዚኽ ዕለት 1350 ሕንፃ ሥላሴ በዛሬው ዕለት ተጠምቀው የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ኾነዋል፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ ሕንፃ ሥላሴን ሊባርኩ፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ሊመርቁ የመጡት ቅዱስ አባታችን ከዚኽ የበለጠ ደስታ የላቸውምና እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡
እንደምታውቁት ስብከተ ወንጌሉን በዞኑ[በሀገረ ስብከቱ] ኹሉ ለማዳረስ ሀገረ ስብከታችን አቅም የለውም፤ ነገር ግን የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል ከብፁዕነታቸው[አቡነ ኤልያስ] መመሪያ በመቀበልና ከሀገረ ስብከቱ ጋራ በመተባበር ከ፳፻፬ – ፳፻፯ ዓ.ም. 16‚630 ሰዎች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተጠምቀዋል፡፡ ደስ ይበላችኹ! በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከ፳፻፬ – ፳፻፯ ዓ.ም. የዛሬውን ጨምሮ 16‚630 ሰዎች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጨምረዋል፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡
/የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ/

the convert fathfuls being baptizedበዛሬው ዕለት ሀብተ ውልድና ጥምቀተ ክርስትና የተቀበላችኹ ወገኖች ኹሉ፣ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ትብብር ስላለ ነው ለዚኽ ውጤት የበቃችኹት፡፡ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ደስታዋ የተፈጸመበት ቀን ነው፡፡ ይኸውም አንደኛ፡- ገንዘባችኹን፣ ዕውቀታችኹን፣ ጊዜአችኹንና ጉልበታችኹን መሥዋዕት አድርጋችኹ ግሩም ድንቅ የኾነ ቤተ ክርስቲያን በመሥራታችኹ ደስ ብሎናል፤ ደስ ሊላችኹ ይገባል፡፡ ከዚኽ በላይ ደግሞ 1350 አዲስ ክርስቲያኖች ተጨምረዋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ እንዲኹ እያለ ያድጋል ማለት ነው፡፡ በእውነቱ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ እናንተን ይዘው ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ትጉህ አባት፣ ትጉህ ሐዋርያ ናቸው፤ በእናንተ ፊት ላመሰግናቸው እወዳለኹ፡፡
ጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን Jinka dabre Keraniyo Medhanialem
ቅዳሴ ቤቱ የተከናወነው የደ/ኦሞ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን
ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋራ የሚገናኙበት ቤተ ክርስቲያን አምሮ ሠምሮ በመሠራቱ አዲስ ምእመናን መጨመራቸው ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሰባክያን፣ መምህራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሕዝቡን ጠንክራችኹ ማስተማርና ወደ ክርስቶስ ጉባኤ እንዲጨመሩ ማድረግ አለባችኹ፡፡ ትልቁ ሥራችኹ ስብከተ ወንጌል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ሥራዋ ስብከተ ወንጌል ስለኾነ በስብከተ ወንጌል ኹላችን መጠንከር አለብን፡፡ ሕዝብን ኹሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት የመሳብ፣ የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ዜጎች እንዲኾኑ የማድረግ ሓላፊነት አለብን፡፡ ሃይማኖታችኹ ጸንቶ ምግባራችኹ ቀንቶ ስናይ ለእኛ ሕይወት መድኃኒት ነው፤ በየጊዜው እንዲጨመሩ ማድረግም ሓላፊነታችን ነው፡፡
የሠራችኹት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለእናንተ ብቻ ሳይኾን ለልጅ ልጆቻችኹ የሚተላለፍ ሥራ ስለኾነ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ ከዚኽ በኋላ ሐሳባችኹ ትምህርት ቤት ወደ መሥራት መኾን አለበት፡፡ ልጆቻችኹ ቋንቋቸውን አጥንተው የጸናችውንና የቀናችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምልኮቷን፣ ሥርዐቷን፣ ቀኖናዋን፣ ምስጢሯን እንዲጠይቁና እንዲያውቁ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡
/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከስድስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ተገኝተው የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤትና የ1350 ምእመናን ጥምቀተ ክርስትና በተፈጸመበት ወቅት ከተናገሩት/
About these ads

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...