2015 ሜይ 30, ቅዳሜ

4ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ


አትም ኢሜይል
ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ002sundayቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተጀመረ፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት፤ የከንባታ ሀዲያ የስልጤ ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ጉባኤውን በጸሎት ከፍተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ከዚህ በፊት ሰንበት ት/ቤቶች ተጣምረው የጋራ ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው በተናጠል ዕቅዶችን በማውጣትና የአፈጻጸም ስልቶች በመንደፍ ይጓዙ እንደነበር ገልጸው፤ የተናጠል ጉዞውም ውጤታማ ባለመሆኑ ከሰ/ት/ቤቶች ወጣት ምሁራን ጋር በመነጋገርና በመገምገም የአገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በማቋቋም ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ፤ ቅዱስ ሲኖዶስም የቀረበው ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥቅም በማረጋገጥ ደንብ ወጥቶ መጽደቁን ጠቅሰዋል፡፡

የሰ/ት/ቤትን ጥቅም ባልተረዱ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች መባል እንደ ነቀፋ ይቆጠር የነበረውን ስም ማስቀረት የሚቻለው በሥራ መሆኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው የወጣቱን አእምሮ ለሃይማኖታዊ ልማት በማነሳሳት ረገድ የአንድነቱ መቋቋም ጉልህ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ አባላቱም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥቅም በማስቀደም ከቡድናዊና ጐሣዊ አስተሳሰብ በመራቅ የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

001sunday003sunday
የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መምህር ዕንቁባሕርይ ተከስተ ባቀረቡት ሪፖርትም በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ 37,332 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ20,000,000 በላይ ወጣቶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፤ እሰካሁን በ8,610 አብያተ ክርስቲያናት በሥርዓት ተመዝግበው አገልግሎት በማግኘት ላይ ያሉ ወጣቶች 2,701,253 ብቻ መሆናቸውን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ገልጸው ይህንንም መሠረት በማድረግ ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችንም በተመለከተ መምህር እንቁባሕርይ ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሀገር አቀፍ አደረጃጀት በመላው ሀገሪቱ አደራጅቷል፤ ያልተቋቋመባቸውም ቦታዎች ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፤ የ2007 ዓ.ም. እና የ2008 ዓ.ም. ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብር በማውጣት በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ መደረጉ፤ ከ2005 እስከ 2010 የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ፤ በማደራጃ መምሪያው ድረ ገጽ በመላው ዓለም ለሚገኙ ምእመናን እያሰተማረ መሆኑ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀትን እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፤ የተለያዩ ስልጠናዎችንና ጉባኤያትን እንዲሁም ስብሰባዎች ማድረጉ፤ የፋይናንስ አሠራር ረቂቅ ተዘጋጅቶ በውይይጥ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርታቸው ውስጥ ተካትተዋል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችን በመተመለከተም የበጀት እጥረት፤ ብቁ የሰው ኃይል አለመመደብ፤ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ እጦት የፈጠረው ችግር፤ ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ መሆናቸው፤ ሕጋዊ የወጣት ሰንበት ትምህርት ቤት እያለ ከመዋቅር ውጭ የደብር አለቃና ጸሐፊ በተጓዳኝ የጽዋ ማኅበራትን እያደራጁባቸው እንደሚገኙ፤ የማኅበራት ወሰን የለሽ እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት ሓላፊው እንደ ችግር ካነሷቸው መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በተመለከተም ግልጽ የሆነ የወጣቶች ራዕይና ስትራቴጂ ማስቀመጥ፤ከሀገር አቀፍ ጠቅላላ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እስከ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ድረስ ማጠናከር፤ የሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች አሠራር እንቅስቃሴ በማእከል ደረጃ መቆጣጠርና መከታተል እንዲቻል የሀሳብ ልውውጥና ስልት መንደፍ፤ የትምህርትና የመዝሙርን ወጥነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ እንደመፍትሔ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ምክትል ሓላፊ ወ/ሮ ማርታ ኃ/ማርያም ባቀረቡት ሪፖርት የአንድነቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ ከተመረጠ ሁለት ዓመታት ቢያስቆጥርም የአመራር አባላቱ ከተለያዩ አህጉረ ስብከት የተመረጡ በመሆናቸው ተሰባስቦ ወጥ የሆነ አገልግሎት ለመፈጸም እንደተቸገሩ ገልጸው፤ በዚህ ዓመት ግን የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች እያጋጠሟቸው ከሚገኙ ችግሮች መካከል ሲገልጹ የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት በየደረጃው ያለመኖር፤ የመመህራን ችግር፤ የፋይናንስ እጥረት፤ ከውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲንን የሚያጠቁ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲሁም የአስተዳደር ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በተነሱትና ሌሎችም ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ጠቅላላ ጉባኤው ተወያይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

ቀጥሎም የሀገረ ስብከታቸውን ሰንበት ትምህርት ቤቶች  አንድነት ወክለው በመጡ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር አባላት የ2007 ዓ.ም. ሪፖርታቸውን በቅደም ተከተል አቅርበዋል፡፡

መምህር በለጠ ብርሃኑ የሰው ኃል አያያዝ በሰንበት ትምህርት ቤት በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታ ቀናት ሲካሔድ ይቆያል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...