2013 ኖቬምበር 17, እሑድ


በደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት በሥራ አስኪያጁ ላይ የተላለፈውን የማሰናበት ውሳኔ የተቃወሙ መላው የጽ/ቤት ሠራተኞች ሥራ አቆሙ፤ ሀ/ስብከቱ ‹‹የመንበረ ጵጵስና ልዩ ጽ/ቤት›› እስከ ማቋቋም በደረሱ ሙሰኞች እና ጠንቋዮች እየታወከ ነው

  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሥራ አስኪያጁ ላይ የተላለፈውን የስንብት ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ወደ ሓላፊነታቸው እንዲመለሱ ለሊቀ ጳጳሱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይኹንና ትእዛዙ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ተፈጻሚ ባለመኾኑ የሀ/ስብከቱን ሥራ በማቆም የተወሰደው የመላው ሠራተኛ ርምጃ፣ በአሜሪካ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ በሐዋርያዊ ጉብኝት ላይ የሚገኙትን የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስን መመለስ እየተጠባበቀ ነው፡፡
  • ራሳቸውን ‹‹የሊቀ ጳጳሱ የግል አማካሪ›› ብለው የሠየሙት ሙሰኞቹና ጠንቋዮቹ በሀ/ስብከቱና በሊቀ ጳጳሱ ስም ባስቀረፁት ማኅተምና ቲተር ጽ/ቤቱ የማያውቃቸውን ሕገ ወጥ ደብዳቤዎች ያዘጋጃሉ፡፡
  • ሥራ አስኪያጁ ከሓላፊነታቸው መሰናበታቸው የተገለጸው፣ ሊቀ ጳጳሱን የከበቡት ‹‹የሊቀ ጳጳሱ የግል አማካሪ›› ነን ባዮች በሐሰተኛ ማኅተምና ቲተር ባዘጋጁት ደብዳቤ ነው፡፡
  • በሀ/ስብከቱ በስምንት ዓመት ውስጥ 13 ሥራ አስኪያጆች ከሓላፊነታቸው መሰናበታቸው ሙሰኞች እና ጠንቋዮች በሊቀ ጳጳሱ ዙሪያ እየፈጠሩት ለሚገኙት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳያ ኾኗል፡፡
Participants of the 32nd SGGA 02
አላግባብ ከሓላፊነታቸው የተሰናበቱት የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት በመ/ፓ/አጠ/ሰ/መ/ጉባኤ ፴፪ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት በተሳትፎ ላይ
  • ሥራ አስኪያጁ÷ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን ድጋፍ በማስተባበር በሚያዘጇቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ ከሌሎች አህጉረ ስብከት ጋራ በሚካሄዱ የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብሮች፣ በወቅታዊ ግምገማዎችና በግምገማዎቹ ላይ በተመሠረቱ የማስተካከያ ርምጃዎች በሀ/ስብከቱና በዐሥራ ሁለቱም የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የዘለቀ መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎች የባለቤትነት መብት በሕግ አግባብ በፍትሕ አካል በማስከበር ሞያዊ ጥረታቸው ሀ/ስብከቱን በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ‹‹የአህጉረ ስብከት የሥራ ብቃት ዓመታዊ ውድድር›› ላይ ተሸላሚ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
  • በሕግ ዲፕሎማ ያላቸውና ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት በሀ/ስብከቱ በሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነት የቆዩት አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፣ የመሬት ይዞታቸውን በሕገ ወጥ መንገድ የተነጠቁ የ12 አብያተ ክርስቲያንን የባለቤትነት መብቶች እንደጠበቃ በተለያዩ ፍ/ቤቶች በራሳቸው እየተሟገቱ አስመልሰዋል፡፡
  • ከእኒህም መካከል÷ በፎገራ ወረዳ መነጉዞር ኢየሱስ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ግንባታ የታቀደበትና በሀገር በቀል ደን የተሸፈነ አራት ሄክታር መሬት፣ በሊቦ ከምከም የዋሻ ተክለ ሃይማኖት አራት ሄክታር መሬት፣ በደብረ ታቦር ፀጉር ኢየሱስ 2.5 ሄ/ር መሬት፣ በፋርጣ ወረዳ የሞክሼ መርቆሬዎስ 2 ሄ/ር መሬት እና በስምና ጊዮርጊስ አንድ ሄክታር መሬት እንዲሁም በደብረ ታቦር እና ላይ ጋይንት ከተሞች ስፋታቸው 7012 ካሬ ሜትር የኾኑ የሕፃናት ማሳደጊያዎች የይዞታ መብቶች መረጋገጥ ይገኙበታል፡፡ የሀ/ስብከቱ የ፳፻፭ ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው 623 አብያተ ክርስቲያን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
  • በሥራ አስኪያጁ ላይ የተወሰደውን አላግባብ ከሓላፊነት የማሰናበት ርምጃ በመቃወም የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች ከኅዳር ፫ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም አንሥቶ ሥራ በማቆማቸው ሳቢያ ከፍተኛ የባለጉዳዮች መጉላላት እየታየ ነው፡፡ በሥራ እንቅሰቃሴው እና የሠራተኞች ቁጥጥሩ ቀናት ይፈጁ የነበሩ ሥራዎችን በሰዓታት ያሳጠረው ሀ/ስብከቱ በጽ/ቤት ደረጃ የቅሬታ ሰሚ ሠራተኛ በመመደቡ ክፍተት የሚታይባቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና አሠራሮች በቅሬታ መልክ በድጋሚ ቀርበው አፋጣኝ መፍትሔ ያገኛሉ፡፡
  • የጽ/ቤቱ ሠራተኞች ራሳቸውን ‹‹የሊቀ ጳጳሱ የግል አማካሪ›› ብለው በሠየሙና ለሥራ አስኪያጁ አላግባብ መታገድ ምክንያት ከኾኑ ግለሰቦች ውስጥ በሦስቱ ላይ ክሥ መሥርተዋል፡፡ ከእነርሱም መካከል በታች ጋይንት እና አዲስ ዘመን ከተሞች ሁለት ጊዜ በሥርዐተ ተክሊል ጋብቻ የፈጸመው የወረታ ወረዳ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል ሓላፊ መ/ር ዕንባቆም ዘርዐ ዳዊት ዋነኛው ሲኾን ካህናትንና ሊቃውንትን በመከፋፈልና በማጋጨት፣ የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያትን በጣልቃ ገብነት በመበጥበጥና ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ በማጋጨት በሚገባ ይታወቃል፡፡
  • ሌላው አዋኪ፣ በፎገራ ወረዳ የደራ ቅ/ጊዮርጊስ አስተዳዳሪው መልአከ ሰላም አፈ ወርቅ ወንድማገኝ የሚባሉ ሲኾን በመጋቢት ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ በከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር ተከሠው የታሰሩና ከሓላፊነታቸው የታገዱ ናቸው፡፡ መሪጌታ መፍቀሬ ሰብእ መኰንን እና መሪጌታ ኅሩይ ደመወዝ የተባሉት ግለሰቦች ደግሞ በደራ ወረዳ አንበሳሜ ከተማ እና በንፋስ መውጫ ቅድስት ሥላሴ በጥንቆላ ሥራ የሚተዳደሩ እንደኾኑ ተነግሯል፡፡
  • በሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያ ላይ የተላለፈው የማሰናበት ርምጃ አግባብነት የሌለው መኾኑን በመግለጽ ለሁለት ዓመታት ያህል ወደቆዩበት ሓላፊነታቸው እንዲመለሱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለመቀበል ሁለተኛ የማሰናበት ደብዳቤ የጻፉት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ÷ በአማካሪ ነን ባይ ነገረ ሠሪዎች ላይ እንዲያውቁባቸውና ሀ/ስብከቱን ‹‹መቋጫ ከሌለው መካሠሥና ከፋ ብጥብጥ›› እንዲታደጉት የሀ/ስብከቱ አካላት በመምከር ላይ ናቸው፡
  • ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በአንድ መልእክታቸው፣ ‹‹ሐላፊነት፣ ሐቀኝነትና ተጠያቂነት የተሞላበት መልካም አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ እንዲሰፍን ማድረግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ መልካም አስተዳደር ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ እንደኾነ እናምናለን›› እንዳሉት፣ በሥራ አስኪያጅነት በሚመሩት ሀ/ስብከት የመልካም አስተዳደር አብነት እንደኾኑ የሚነገርላቸው እንደ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት ያሉ ሓላፊዎች በተቋማዊ ለውጥ አመራራቸው ይጎለብቱ ዘንድ ዕድል ሊሰጣቸውና አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
  • ሀ/ስብከቱ÷ ባለፈው ዓመት መነሻቸውን አዲስ አበባ ባደረጉና ራሳቸውን ደቂቀ ኤልያስ በሚል ሲቀስጡ የተገኙ ሁለት ዲያቆናት ነን ባይ ግለሰቦችን ለፍትሕ አካል አቅርቦና እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ተከራክሮ በስድስት ወራት እስራት እንዳስቀጣው ሁሉ በቡድን ተደራጅተው አስተዳደሩንና መንፈሳዊ አገልግሎቱን በሚያውኩት ሙሰኞች እና ጠንቋዮች ላይም የሚወስደውን ርምጃ አጠናክሮ በመቀጠል ከመዋቅሩ ማጽዳት ይጠበቅበታል፡፡
  • የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት የአራቱ የምስክር ጉባኤ ቤቶች መገኛ እንደመኾኑ መጠን የበርካታ ቋሚ መንፈሳዊ ት/ቤቶችና የአብነት ት/ቤቶች ምንጭ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ብዛታቸው 7,167 የኾነ የንባብ፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የዝማሬና መዋስዕት፣ የድጓ፣ አቋቋምና የመጻሕፍት መምህራን እንዲሁም ከ27,928 በላይ ደቀ መዛሙርት እንደሚገኙበት የሀ/ስብከቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ እኒህን የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት ለመደጎም በገቢ ምንጭነት የሚያገለግል ባለአራት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ በደብረ ታቦር ከተማ ለመገንባት ዲዛየኑ አልቆ፣ የመሠረት ደንጊያው ተጥሎ ወደ ግንባታ ሥራው በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ የድጓ ምስክር የሚገኝበት የቅድስት ቤተ ልሔም ጉባኤ ቤት እና ሙዝየም በብፁዕ ሊቀ ጳጳ አቡነ እንድርያስ የቅርብ ክትትልና በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት መርጃና ማቋቋሚያ ድጋፍ ለፍጻሜ መብቃቱ ይታወሳል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...