2015 ማርች 11, ረቡዕ

እረፍቱ ለአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ


Written By Hulubante Abebe 

 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።” 
                                 
 መዝ ፴፫፡፲፭-፲፯ 
መጋቢት 5 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞች ዘንድ የፃድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል 
በዚህ እለት እምናከብረው የእረፍት መታሰቢያቸውን ሲሆን ከገድላቸውም እንዲህ ተፅፎ እናገኘዋለን 
ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ግብፅ ንሂሳ በምትባል ቦታ ከአባታቸው ስምዖን ከእናታው አቅሌስያ ነው። በአጠቃላይ የኖሩበት ዕድሜ 562 አመት ሲሆን 300 ዓመቱን በግብጽ 262 ቱን በኢትዮጵያ 100 ዓመት በዝቋላ በተጋድሎ ያሳለፉ ታላቅ አባት ናቸውኢትዮጵም የአስራት ሐገራቸው ሆና በቃልኪዳን ተሰጣቸዋለች  እናታቸው ሳትታቀፋቸው ወተት ሳይጠጡ በመንፈስ ቅዱስ አድገው በ፫ ዓመታቸው ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ እስከ ሰባቱ ሰማያት አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረበው፤ ባረከውም፤ ድንግል ማርያም ጻድቃን ሰማዕታት ወዳሉበት ተወስዶ ተባርኮ በጌታችን ቃል ተቀብሎ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳሉበት አውርዶ በዚያም አድጎ መንፈሳዊ ሥራን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተጋድሎውን ጀምሯል። በበረሃ ሲኖሩ 60 አንበሳና ነብር የተሰጣቸው ሲሆን አንበሳ እና ነምሮቹም የሚበሉትም የቅዱሱን እግር ያረፈበትን ቦታ በመላስ ነው። የአባታችን ገድል እንደሚያስረዳው እንደ ሰው ልብስ ለብሰው ሳይሆን ልብሳቸው በጸጋ የተሰጣቸው ጠጉር ነበር እሱም ልክ እንደ ልብስ ያገለግላቸው ነበር
 ከሚያስገርመው ገድላቸው ውስጥ አባታችንን ለመጠየቅ የመጡት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር መጥተው እንግዶቹን አንበሶቹ በልተው አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ መምጣታቸውን አውቆ ሲነግሯቸው ለምን ያልተፈቀደላችሁን በላችሁ ብለው የበሉትን አንበሶች የበላችሁትን አንድም ሳታስቀሩ ትፉ ብሏቸው ወደ እግዚአብሔር ጸልየው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሱ ባሉ ጊዜ የተበሉት ነፍስ ዘርተው እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባም በሰላም ወደ ባእታቸው በአባታችን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸሎት በሠላም ገብተዋል።
መጋቢት 5 በገድለ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ
ዕለቱ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ህመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግን አልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚያብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት
ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አለው፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው፤ ከመጋቢት አምስት ቀን ጀምሮ ዝክርህን ያድርጉ በአማላጅነትህም ይማጸኑ አለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዱ በእየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በዛሬዋ ቀን ሩጫውን ጨረሰ። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።
የአባቶችን የቅዱሳንን ታሪክ እንድናውቅ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከነርሱ ገድል ተምረን እኛም ወደአምላክ መንገድ እንድንቀርብብበት ነውና አምላከ ገ/መንፈስ ቅዱስ መንገዱን ያብራልን ። ገድሉንም ሰሚወች ብቻ ሳንሆን እምንማርበት ያድርግልን ።
መጋቢት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ /አባ ገብረ ሕይወት/                                     2.ቅዱስ አባ ሰረባሞን /በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ/                 3.አባ ግርማኖስ ጻድቅ /ሶርያዊ/                                                         4.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት /ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት/ 
5.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ /የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች/

                       ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...