2015 ጁን 24, ረቡዕ

ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም (ክፍል ኹለት)


በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
(መዝረቅ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 16 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡             - በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ኹለተኛው በይሁዳ ነው!
ይሁዳ የኢየሩሳሌም አውራጃው ነው፡፡ የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማም ኢየሩሳሌም ነች፡፡ ከኢየሩሳሌም ይሁዳ ይከፋል፤ ከሰማርያ ግን ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ኢየሩሳሌም ዋና ከተማዋ ነች፣ ጌታም የተወለደው በይሁዳ አውራጃ በቤተ ልሔም ነው፡፡ የተሰቀለው፣ የሞተው፣ የተቀበረው፣ ያረገው፣ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከው በኢየሩሳሌም ከተማ ነው፡፡ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ነገር በይሁዳ አውራጃ የተሻለ ይወራል፤ ይነገራል፡፡ የሚያውቁት ዘመድ ይኖራል፡፡ የሐዋርያትና የይሁዳ ቋንቋ ተመሳሳይ ነው፡፡ የይሁዳ ባሕልና የኢየሩሳሌም ባሕል ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሰማርያ ቢሻልም ከኢየሩሳሌም ግን ይከፋል፡፡

ይሁዳ ምንድነው ይሁዳ? ይሁዳ አከባቢያችን ነው፡፡ ይሁዳ መንደራችን ነው፡፡ ይሁዳ ጓደኞቻችን፣ የምንሠራበት አከባቢ፣ የምንማርበት አከባቢ ነው፡፡ በየመንደሩ የሚሰበሰቡ ሰዎች ለወንጌል እንዲሰበሰቡ ማድረግ ይቻላል፡፡ አባቶቻችን ጽዋን፣ ሰንበቴን የመሠረቱት አንዱ ትልቁ ጥቅም በቅዱሳን ስም ተሰብስበን እንድንማር፣ እንድናውቅ፣ በይሁዳ ወንጌል እንዲሰበክ ነው፡፡
ታላቁ ሐዋርያ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ማኅበረ ጽዮን የተሰኘችውን የመጀመሪያዋን የጽዋ ማኅበር በአክሱም ጽዮን ሲመሠርት ሦስት ዓላማ ነው የነበረው፡፡ የመጀመሪያው ዓላማ ከዚያ ከቅዱሱ ረድኤት በረከት ማግኘት፤ ኹለተኛው ዓላማ ወንጌልን መማር፤ ሦስተኛው ዓላማ ድኾችን መርዳት፡፡ ዛሬ ጽዋዎቻችን እነዚህን ዓላማዎች ይተግብራሉ? ትምህርት አለ? ድኾች ይረዳሉ? ወይስ ከተለያየ ቦታ ተሰብስበን በቤታችን የሰለቸነውን ምግብ እንደገና አምጥተን በልተን ነው የምንለያየው? አብያተ ክርስቲያናት ይረዳሉ? የሐዊረ ሕይወትንና የመሳሰለውን ጉባኤ’ኮ ማዘጋጀት ያለባቸው በየከተማው ያሉ ሰንበቴዎች፣ ጽዋ ማኅበራት፣ የጉዞ ማኅበራት አንድ ላይ ኾነው ነው፡፡ ይኼ ነዋ ዓላማቸው! ወንጌል እንዲሰበክ ማድረግ ነዋ ዓላማቸው! አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የሾማቸው የመጀሪያዎቹን ሰባት ኢትዮጵያውያን ሐዋርያት የሚያስፈልጋቸውን አሟልታ “ሒዱ፤ አስተምሩ” ብላ የላከችው’ኮ ያቺ ማኅበረ ጽዮን የተባለችው የጽዋ ማኅበር ናት፡፡ ዛሬ ጽዋዎቻችን ሐዋሪያዊነት አላቸው? ስብከተ ወንጌል ላይ ይሠራሉ? የጽዋ ማኅበርተኞች ይማራሉ? በየመንደራችንስ ትምህርት አለ?
በይሁዳ ማለት ይኼ ነው፡፡ ኹለተኛው ስምሪት ይኼ ነው፡፡ ጥቂት የሚያውቁ፣ ጥቂት የተማሩ፣ ጥቂት የገባቸው፣ መንደሩን የሚያውቁ ምእመናን አከባቢያቸውን ሰብስበው የሚያስተምሩበት ነው፤ ይሁዳ፡፡ ነጋዴዎች በንግድ አከባቢ ያሉትን ሰብስበው፣ ሾፌሮቹ በዚያ በሙያቸው ያሉትን ሰብስበው፣ ፓይለቶቹ በዚያ አከባቢ ያሉትን ሰብስበው፣ ሊስትሮዎቹ በሙያ የሚቀርባቸውን ሰብስበው፣ የመንግሥት ሠራተኞቹ በዚያ የሚቀርቧቸውን አሰባስበው፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንደዚሁ፤ ሌሎችም የሚቀርቧቸውን ሰብስበው የሚያስተምሩበት ነው፡፡ “ኑ እንወቅ፤ ኑ እንማር፡፡ እኛ መጀመሪያ እንወቅ፤ ከዚያም እንሒድ፤ ሌላ ቦታ እንድረስ” የሚሉበት ነው፤ ይሁዳ፡፡
ምናልባት ሔደን ቆመን ላናስተምር እንችል ይኾናል፡፡ ነገር ግን ሞራል መኾን እንችላለን፡፡ የሐዊረ ሕይወትና የበእንተ ወንጌል ጉባኤ ተዘጋጅቶ ወደ ሌላ አከባቢ ስንሔድ እኛን ያዩ የዚያ አከባቢ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ በአጠቃላይ ምእመናን ምን እንደሚሰማቸው እስኪ አስቡት? ሰው’ኮ ከዕውቀት ከትምህረት እጥረት በላይ የሞራል እጥረት ይጎዷል፡፡ በተደጋጋሚ እርሱ ከሚያምነው የተለዩ ሰዎች የሞራል ጫና ሲያሳድሩበትና “አንተ’ኮ የለህም፤ የሚጠይቅህም የለም” ሲሉት በጣም ነው የሚጎዳው፡፡ እስረኛና በሽተኛ ትልቁ የሚርበው ጠያቂ ነው፡፡ አንድ በሽተኛ ተኝቶ፣ አንድ እስረኛም ታስሮ ሔዶ የሚጠይቀው ሰው ነው የሚርበው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በማቴዎስ 25 ከጠየቃቸው ጥያቄዎች አንዱ፡- “ታስሬ አልጠየቃችሁኝም፤ ታምሜ አልጎበኛችሁኝም” የሚለው፡፡ ምክንያቱም አንድ የታመመና የታሰረ ሰው መጀመሪያ የሚፈልገው ምግብ ወይም ገንዘብ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሔዶ “እግዚአብሔር ያበርታህ፤ ደኅና ነህ ወይ?” የሚለውን ነው የሚሻው፡፡ የታመም ሰው “አይዞህ፤ በርታ! እግዚአብሔር ያጽናህ፤ እግዚአብሔር መድኃኒቱን ይላክልህ” የሚለው ሰውን ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ ምንም ባናደርግም መምጣት በራሱ ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡ መጥቶ “እኛ የእናንተ አካል ነን፤ አብረናችሁ ነን፤ ከእኛ ጋር ናችሁ፤ ወገኖቻችን ናችሁ፤ ወገኖቻችሁ ነን” ማለት በራሱ ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡
አሁን ትንሽ ተስፋ የምናየው በይሁዳ ያለው አገልግሎት ነው፡፡ ሰዎች ይሰበሰባሉ፤ የሚቀር ግን አንድ ነገር አለ፡፡ ብዙዎቻችን ለእንዲህ ዓይነቱ የመሔድ አገልግሎት የበረታን አይደለንም፡፡    
ሦስተኛው በሰማርያ ነው!
ለምንድነው ሰማርያ ያለው? ሰማርያ ከአይሁድ በብዙ ይለያል፡፡ በቋንቋ ይለያሉ፤ በባሕል ይለያሉ፡፡ በእምነት ይለያሉ፤ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነውና የሚቀበሉት /ዮሐ.4/፡፡ ስለዚህ ወደ ሰማርያ መሔድ ማለት በባሕል፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በአስተሳሰብ፣ በአለባበስ፣ በአመጋገብ ወደሚለዩ ሰዎች መሔድ ነው፡፡ ጣዖት የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፤ ባሕላዊ እምነት የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፤ ሌላም ነገር የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ ወደነዚያስ መቼ ነው የምንሔደው? “በይሁዳ እንዳትቀሩ፤ ወደ ሰማርያ ሒዱ” ነዋ የተባልነው፡፡
ብዙ ሐዋርያት ከሰማርያም አልፈው ነው የሔዱት፡፡ እነ ቅዱስ ቶማስ ሕንድ ሔደዋል፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሮም እስከ ስፔን ድረስ ሔደዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሐዋርያትም እንደዚሁ ከሰማርያ አልፈው ሔደዋል፡፡ ዛሬ የተነሡ አንዳንድ ሰዎች ሰማርያ አልፋ የሔደች አይመስላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማይክራፎን ከመጣ ወዲህ ማስተማር የጀመረች ነው የሚመስላቸው፡፡ ከሞንታርቦ ዘመን ወዲህ ነው ታሪኳን የሚጀምሩት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን የሞንታርቦ ዘመን ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ ብዙዎች ሐዋርያት ተሰማርተዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ወደማይታወቅ ቦታ ስምሪት ነበረ፡፡ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሰባት ሐዋርያትን እስከ ሱዳን ድረስ ልኳል፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳንም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ እንኳን በአክሱም ከተማ የተቀመጡት ኹለቱ ብቻ ናቸው፤ አባ ሊቃኖስና አባ ጰንጤልዮን፡፡ እርሱም ንጉሡ፡- “እኔንማ ትታችሁኝ ከሔዳችሁ ማን ይባርከኛል? ማን ይጸልይልኛል? እኔ ክፉ ከኾንኩ የእናንተ የወንጌል አገልግሎትም ክፉ መኾኑ አይደለም ወይ? እኔንምኮ ማስተማር አለባችሁ፤ እኛ መኳንንቱ እኛ ነገሥታቱ ሐላፊዎቹ ከከፋን አገር ትከፋለች፡፡ ስለዚህም እኔንም ማስተማር ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው” ብሏቸው ነው፡፡ የቀሩት ሰባት ግን አክሱም መቀመጥ እንኳን እንደ ቅንጦት እንደ ምቾት ቈጥረዉት ወጥተው ነው የሔዱት፤ ከሔዱ ደግሞ አልተመለሱም፡፡ 
ከእነርሱም በኋላ የመጡት ሐዋርያት ወደማያውቁት አገር ነው የሔዱት፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መጀመሪያ 17፣ በኋላ (በአቡነ ፊልጶስ ዘመን) ያፈሯቸው 12ቱን ሐዋርያት ሀገረ ስብከት አካፍለው ነው የላክዋቸው፡፡ ማንም ወደተወለደበት አከባቢ አልሔደም፡፡ ተመልሶ በሰላም የመጣም የለም፡፡ በክፍል አንድ ትምህርታችን ያነሣነው አቡነ አኖሬዎስ ባሌን ተሻግሮ በዚያው ዐርፎ፡ ዐፅሙ ነው በደቀመዛሙርቱ የተመለሰው፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤል ዐፅሙ ነው ወደ ገዳሙ የተመለሰው፡፡ አቡነ ፊልጶስ ዐፅሙ ነው ወደ ገዳሙ የተመለሰው፡፡ ማንም የላመ የጣመ ያለበት የተመቸ ቦታ ላይ ልቀመጥ ያለ የለም፡፡ እንደሔዱ ነው የቀሩት፡፡ እንደተጓዙ ነው የቀሩት፡፡ ይኼ ነው ወደ ሰማርያ መሔድ፡፡
አሁን የሚቀረንና የምንወቀስበት ትልቁ አገልግሎት ይኼ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኹለት ሺሕ ዓመት ታሪክ አፍሪካ በሙሉ ክርስቲያን መኾን ነበረበት፡፡ መሔድ ማስተማር ነበረብን!
ዛሬ በጠረፉ አከባቢ ያለው መልክ ትክክለኛ መልክ አይደለም፡፡ የሠሩ ሰዎች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም፤ ሠርተዋል፡፡ እነ ዕጨጌ ዕንባቆም ከየመን ተነሥቶ፣ ሃይማኖቱን ቀይሮ፣ ክርስቲያን ኾኖ፣ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ፣ መንኩሶ፣ መንኖ፣ ከዛ ደግሞ 12ኛው የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ ኾኖ፣ እንደገና ተሰማርቶ በዐባይ በረኻ በወለጋ ያስተማረው ትምህርት የሚደግመው ጠፋ፡፡ እስከ አሶሳ ድንበር ድረስ አስተምሮ ነበር፤ ነገር ግን የሚደግመው ጠፋ፡፡ እነ አቡነ አኖሬዎስ እስከ ባሌ ድረስ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ በመተሐራና በወንጂ እነ አቡነ ኢዮስያስ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ በዳሞት፣ በከንባታ፣ በሀድያ እስከ ጋሞጎፋ ድረስ እነ አቡነ ታዴዎስ ተሰማርተው አስተምረው ነበር፡፡ በምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የሶማልያ ሀገረ ስብከት እስከምንለው ድረስ እነ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ (የአቡነ ሳሙኤል ዋናው ገዳማቸውኮ ደብረ ወገግ አይደለም፡፡ ደብረ ኪሩብ የሚባል ነው፡፡ ዛሬ ምንም ነገር የለውም፡፡ አሰቦት ላይ ቆማችሁ ደብረ ኪሩብ ይታያችኋል፡፡ እርሳቸውም ሲያስተምሩ ያረፉት እዚሁ ደብረ ኪሩብ ላይ ነው፡፡ ዐፅማቸው በኋላ ነው የተመለሰው፡፡) ዛሬ ዓፋር የምንለው አከባቢ የእነ አባ አንበስ ዘደብረ ዓዘቦ ሀገረ ስብከት ነበር፡፡ (ደብረ ዓዘቦ ዛሬም ፍርስራሹ አለ፡፡ በረዶ የሚያፈላበት ትልቁ ተራራ ጫፍ ላይ ነው ገዳማቸው የነበረው፡፡ እዛ ላይ ኾነው ነው አከባቢውን ሲያስተምሩ የነበሩት፡፡) ማን ይተካቸው? ማን ይውረሳቸው? የለም! ኹላችንም የተመቸ ቦታ ላይ ተቀምጠን ያለነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለነው ሰዎች ከኢየሩሳሌም ከከፋም ከይሁዳ ላለመውጣት ወስነናል፡፡
ምእመናንም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለንን ሩጫ ያኽል ስብከተ ወንጌል ላይ የለንም፡፡ እስኪ ማን ነው ገንዘቡን፡- “እዚህ አከባቢ ያለው ሕዝብ ሊማር ይገቧል፡፡ ሐዋርያ ሊደርሰው ይገባል፡፡ የኛ ገንዘብ እዛ መዋል አለበት” የሚል? ያንን ስምሪት የሚተካ አልመጣም፡፡
ኹሌ የምንኮራበት፣ “እርሱም ለወገኖቹ ሐዋርያ ኾነ” ብሎ አውሳብዮስ የተናገረለት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ’ኮ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም ብዙውን ያስተማረው፡፡ መጀመሪያ ኢትዮጵያ - አክሱም አከባቢ፣ ከዛ ኑብያ - የዛሬዋ ሰሜን ሱዳን፣ ከዚያ ቀጥሎ ናግራን - የዛሬዋ ደቡብ የመን፣ ከርሱ ቀጥሎ ፋርስ - የዛሬው ኢራንና ዒራቅ፣ ከዚያ ቀጥሎ ሕንድ፣ ከሕንድ ቀጥሎ ቻይና አጠገብ ሲኖል የምትባል ደሴት አስተምሮ ነው ተሰማርቶ ያረፈው፡፡ ይህን ዛሬ ማን ይተካው? ማን ነው የሚሰማራው? ይህ ስምሪት ስለጎደለ ነው ዛሬ ትልቅ አደጋ ውስጥ የገባነው፡፡
ሠርተው ነበር አባቶቻችን!!! ወንዶቹ ብቻ አይደሉም፤ ሴቶቹም ጭምር!!! ሴቶችን ለመቀበል በማይደፍረው ዘመን እንኳን ኦርኒና መክብዩ የሚባሉ የአቡነ ፊልጶስ ደቀ መዛሙርት ተሰማርተው ነበር፡፡ እነዚህ ኦርኒና መክብዩ እሳት የላሱ ወንጌላውያን ነበሩ፡፡ ጥቅምት 23 ነው የሰማዕትነትን ጽዋ የተቀበሉት፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው የንጉሥ ወታደር ተሰልፎ፣ አንዱ ባታሌውን ጠርቅሞ፡- “ማስተማር የለባችሁም” ሲላቸው “እኛኮ ተናገሩ እንጂ ዝም በሉ አልተባልንም፡፡ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም፡፡ ታዲያ ለምን እንፈራለን? ጌታችን በጲላጦስ አደባባይ በንጉሡና በወታደሮቹ ፊት አልፈራም፤ እኛም ልጆቹ አንፈራም፡፡ እንዲያውም ቁሙ፤ እናንተንም እናስተምራችኋለን፡፡ ቁሙ! እኛን ለመግደል አይደል የመጣችሁ? ለማሰር አይደል የመጣችሁ? እንደዉም ባላችሁበት ቁሙ፤ ይኼን ትምህርትማ ሰምታችሁ መሔድ አለባችሁ” ነው ያሉት፡፡ በዚያ ዘመን ሴቶች እንዲህ የሚናገሩበት ዘመን ስላልነበረ “ምንድነው የመጣብን?” ብለው እጅግ ደንቋቸው ቆሙ፤ ሰሟቸው፡፡ ወደ 23 የፈጀ ትምህርት ነው ያስተማሯቸው፡፡ እናቶች ዛሬ ለ23 ቀን የሚኾን ትምህርት አላችሁ? ወይስ ለ23 ቀን የሚኾን የቡና …. አልጨርሰውም፡፡ አርኒና መክብዩ ግን ቆሙ፡፡ አስተምረዋል፡፡ እስከ ጠረፍ ድረስ ሔደው መስክረዋል፡፡
እነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ሱስንዮስ “አገሪቱን ወደ ካቶሊክነት እቀይራታለሁ” ባለ ጊዜ፣ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ሲገደሉ፣ ታላላቆቹ ሊቃውንት ሲታሰሩ፣ መምህራኑ በየገዳማቱ ሲሰደዱ ዞራ አስተምራለች፡፡ ባሏ የሱስንዮስ የጦር አዛዥ ነበር፡፡ ሊቀ ጳጳሱን ገድሎ፣ አክሊላቸውን (አስኬማቸውን) እና ልብሳቸውን እንደ ግዳጅ ይዞት ሲመጣ፡- “ይኼውልሽ! ዛሬኮ በጦርነት ላይ ዋልኩ፡፡ ካቶሊክነትን አልቀበልም ያሉትን ጳጳስ ገደልኩ” ሲላት፡- “አባቴን ገድለህ ከእኔ ጋር መኖር አትችልም፡፡ የእኔና የአንተ ግንኙነት በዚህ ላይ አበቃ፡፡ ሃይማኖት ነው የመሠረተው፤ እዚህ ላይ አበቃ፡፡ የአንተን ሚስት ነኝ እላለሁ፤ ግን የማን ልጅ ነኝ እላለሁ?” ብላ ነው ወጥታ በመላ ትግራይ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር ዞራ ያስተማረችው፡፡ ንጉሡ የሚያደርገው እስኪጠፋው ድረስ ድረስ ነው ያስተማረችው፡፡ እንዳይገድላት ወንድሞቿ የንጉሡ የቀኝ ግራ አዛዦች ናቸው፡፡ እርሷን ገድሎ ከእነርሱ ጋር መኖር ፈራ፡፡ ዝም እንዳይላት “እንዴ! ሴቷ እንኳን እንደዚህ ስታስተምር” ብለው ሊቃውንቱ ሞራል እየኾነቻቸው ተነሡበት፡፡ ዙራ አስተምራለች፡፡ እርሷ እንድታስተምር ትልቁን እገዛ ያደረጉት በተለይ በጣና ሐይቅ ይሠሩ የነበሩ ባለ ጀልባዎች ናቸው፡፡ ከዕንጨት ጋር እየደበቁ፣ ከሌላ ነገር ጋር እየደበቁ አገር አገር እያሻገሯት እንድታስተምር ያደረጉት፡፡ ዛሬ ወደየገዳማቶቻችን አድርሰው እንደሚመልሱን ሹፌሮች ማለት ነው! ከተጠቀምንበትኮ ይህም ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡
ቢጨንቀው ንጉሡ “እስኪ አስተምራት” ብሎ ወደ አልፎንስሜንዴዝ ወሰዳት፡፡ እጅና እግሯን ታስራ ኹልጊዜ የኑፋቄ ትምህርት እንዲነበብላት ተደረገች፡፡ “ቀይራት፤ ባትሰማህም ንገራት” ተባለ፡፡ ደከመ፤ ነገር ግን ምንም ሊቀይራት አልቻለም፡፡ እንደዉም መጨረሻ ላይ እዚያ ቦታ መታሰሯን ያወቁ ሌሎች ጀግኖች መጡና እርሱ በሌለበት በሩን ሰብረው ገመዷን በጥሰው ይዘዋት ጠፉ፡፡ “ቀየርካት?” አለው፡፡ “የምትቀየር አይደለችም” አለው፡፡ ይዘዋት ከሔዱ በኋላ ደቀ መዛሙርቷ ጠየቋት፡፡ “ይኼን ያህል ጊዜ እርሱ የኑፋቄ ትምህርት ሲያስተምርሽ ከልብሽ ውስጥ አልገባም” ሲሏት “እርሱ የኑፋቄውን ሲያነብ እኔ ጸሎቴን አደርጋለሁ፤ ሰምቼው አላውቅም፡፡” እስኪ በየመሥሪያ ቤታችን፣ በየንግድ ቦታችን የሚጮኽ ነገር የለም ወይ? የሚወራ ነገር የለም ወይ? ታዲያ ያን ጊዜ ስንቶቻችን ነን ያቺን ሰዓት ለጸሎት የምንጠቀምባት? ነገር ግን ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ወደ ካቶሊክነት ከመለወጥ የታደጋት የእነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ሐዋርያነት ነው፡፡  
ምእመናን ሆይ! ይኼን ነው በሰማርያ ማምጣት ያለብን! ጉሙዝ ሕዝብ ሔዳ አስተምራለች፡፡ ታስራ ወደ ጉሙዝ ሔዳለች፡፡ የሚያስራት ሰውዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላላወቀ አሰራት፡፡ በኋላ ግን ሃይማኖቷን፣ ምግባሯን ቢያይ “ምን አድርገሽ ነው? ለምንድነው እኔ ጋር እሰራት ብለው የላኩሽ?” አላት፡፡ “እኔ ሃይማኖቴን ስለጠበቅኩ ነው፡፡ የአባቶቼን ሃይማኖት ስላከበርኩ ነው የታሰርኩት” ስትለው “እስኪ ይኼ ሃይማኖቴ የምትዪውን ንገሪኝ” አላት፡፡ መጀመሪያ ያስተማረችው እርሱን ነው፡፡ የለወጠችው እርሱን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እርሷ ሦስት ዓመት እዚያ ስትታሰር እርሱ የእርሷ ደቀ መዝሙር ነው የኾነው፡፡ እስር ቤት ልንገባ እንችላለን፤ ግን ስንት ደቀ መዛሙርትን እናፈራለን?
ሰማርያ ማለትኮ ይኼ ነው፡፡ እስርቤቶቹ፣ ሆስፒታሎቹ፣ የተለያዩ ቦታዎች፣ ከሀገር ወጥተን የምንሔድባቸው ቦታዎች ሰማርያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዙ ዓለማት ተሰማርተዋል፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ በየአጥቢያው ስትሔዱ እኛው ብቻ ነን፡፡ አንድ ቻይናዊ አምጥተናል? አንድ ሕንዳዊ አምጥተናል? አንድ ሜክሲኮአዊ አምጥተናል? እኛ ብቻ ነን፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በውጪው ዓለም መባላትና መናከስ ያለው፤ እኛው ብቻ ነና! ትንሽ ብንቀላቀል ኖሮኮ ያም ቋንቋው ስለማይችል መሰዳደባችንን እንኳን ስለማይገባው ተስማምተን እንኖር ነበር፡፡ አላመጣንም፡፡ በሰማርያ ግን አስተምሩ ተብለናል፡፡ ለእነርሱ የሚኾን መዝሙር አለን? አዲስ ሰው ቢመጣ ለእርሱ የሚኾን መጽሐፍ አለን? ለእነርሱ የሚኾን ትምህርት አለን? ለእነርሱ የሚኾን ዝግጅት አለን?
ሰሜን ኬንያ የነበሩ ሕዝቦ በስደተኞቹ ካምፕ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲያዩ ከጎሳው መሪ ጀምረው ተጠመቁ፡፡ “አሁን እኛ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. አማኞች ነን” አሉ፡፡ እምነታቸውን ትተው መምጣት፤ መጠመቁ አልቸገራቸውም፡፡ ነገር ግን የሚቀበላቸው ዝግጅት አልነበረም፡፡ ለእነርሱ የሚኾን ሰው አልነበረም፡፡ የሚበሉትን በልቶ፣ የሚጠጡትን ጠጥቶ፣ የሚኾኑትን ኾኖ የሚያስተምራቸው ሰው አልነበረም፡፡ አባቶቻችንኮ ወደ ባዕድ አገር ስትሔዱ “እንደነርሱ ኹኑ” ነበር ያሉን፡፡ “የሚበሉትን ብሉ፤ የሚጠጡትን ጠጡ፤ የሚለብሱትን ለብሳችሁ በቋንቋቸው ተናገሩና መልሷቸው” ነበር ያሉን፡፡ እንደዛ የሚኾን ሰው ግን አላተረፍንም፡፡ ብዙ ደቡብ አፍሪካውያን መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ለእነርሱ የሚኾን አላዘጋጀንም፡፡ ይኼ ነው ሰማርያ ማለት፡፡ ነገ ትልቁ ሥራችንም ይኼ ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ሰዎች እንዲሁ አንብበን “በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ጥሩ ጽሑፍ ነው” ብለን አይደለም መሔድ ያለብን፡፡ የቤት ሥራ ነው ይዘን የምንሔደው፡፡ ኹላችንም ይህን ጽሑፍ አንብበን በየመስካችን ካልተሰማራን ዝም ብለን ነው ከንፈር የምንመጠው፡፡ “እዚ ቦታ ላይ መናፍቃን እንዲህ አደረጉ፤ እዚህ ቦታ ላይ ከሐዲያን እንዲህ አደረጉ” ብንል ምን ያደርጋል? እንደ ሽሮ ወጥ ለጊዜው ከመቆጣት አልፈን ይኼ ነገር ነገ እንዳይደገም ምን እናድርግ ማለት አለብን፡፡ ይኼ ነው የሰማርያ ስምሪት፡፡ በሰማርያ ሒዱ የተባለው ይኼ ነው፡፡
አራተኛው ደረጃ በዓለም ዳርቻ ነው!
እስከ አሁን ያየናቸው ሦስቱም ይታወቃሉ፡፡ ኢየሩሳሌም ትታወቃለች፡፡ ይሁዳ ትታወቃለች፡፡ ሰማርያም ትታወቃለች፡፡ የዓለም ዳርቻ ግን የት ነው? አይታወቅም፤ ሰፊ ነው፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ማለት እስከማትመለሱበት ቦታ ድረስ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት ከሔዱበት አልተመለሱም፡፡ የሐዋርያት ልጆችም አልተመለሱም፡፡ በኪደተ እግራቸው የባረኩት አገራቸው ኾኖ በዚያ አስተምረው ነው የቀሩት፡፡ የአንዳንዶቹ ዐፅማቸው፣ የአንዳንዶቹ ተረፈ ዐፅማቸው ነው የተመለሰው፡፡ የዓለም ዳርቻ ማለት ይኼ ነው!
በጠረፉ አከባቢ ትልልቅ ጉባኤዎች እጅግ የበዛ ዋጋ አላቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ዓፋር፣ ወደ አሶሳ፣ ወደ ቦረና፣ ወደ ሶማሌ፣ ክርስቲያኖች ወደሚያንሱበት፣ አምስት ስድስት ኾነው ወደሚያስቀድሱበት መሔድ አለብን፡፡ ዕጣንና ጧፍ አንሷቸው “በቃ ማለቃችን ነው” ወደሚሉት መሔድ አለብን፡፡ “አይዟችሁ አለን፤ ብቻችሁ አይደላችሁም፡፡ ቦታ አራራቀን እንጂ ሃይማኖት አልለያየንም፡፡ ቦታ አራራቀን እንጂ ሥርዓት አንድ ነው፡፡ የእናንተ አገልግሎት የእኛ አገልግሎት ነው፤ የእናንተ ማስቀደስ የእኛም ማስቀደስ ነው” ብለን መሔድ አለብን፡፡ ሲኾን ከዛ አልፈን ወደ አፍሪካ አገራት፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን አይቷት ሰምቷት ወደማያውቁት መሔድ አለብን!
ዛሬ በንግድ የሚሔደው ቻይና፣ ጃፓን፣ ዱባይ፣ ሕንድ፣ ወደ ሌሎችም እንሔዳለን፡፡ ታዲያ ስንት አስተማርን? ስንት አጠመቅን? ወይስ ዕቃ ብቻ ይዘን ነው የምንመጣው? የኦሪትን እምነት እንድናገኝ ያደረገንኮ ታምሪን የተባለ ነጋዴ ነበር፡፡ ዛሬም ታምሪን የኾኑ ነጋዴዎች ያስፈልጉናል፡፡ ቶማስን ሕንድ ድረስ የወሰደው ነጋዴ ነው፡፡ ስለዚህ የነጋዴ ሐዋርያት፣ የሹፌር ሐዋርያት፣ የምሁር ሐዋርያት፣ የባለሙያ ሐዋርያት ያስፈልጉናል፡፡ ሱቅ ከፍታችሁ የምትሸጡ፣ ሻይ ቤት ከፍታችሁ የምትሸጡ፣ ምግብ ሠርታችሁ የምትሸጡ ሑሉ ሐዋርያ ለመኾን መዘጋጀት አለባችሁ፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ! እኛ ወደማናውቀው ድረስ መሔድ አለብን፡፡ ብዙ ይቀረናል፡፡ ጀመርነው እንጂ ገና ነን፡፡ ያለቀ እንዳይመስላችሁ! ዛሬ በጉባኤ ስለተሰባሰብን በዝተን ስንታይ የጨረስነው እንዳይመስላችሁ! ገና ብዙ አለ፡፡ ይኼን ተስፋ የሚያደርጉ በጣም ብዙ ሕዝቦች አሉ፡፡ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም፡፡
እንዴት እንሒድ?
አባቶቻችንን ሒደታቸውን በአራት መንገድ ነው የሔዱት፡፡
v  የመጀመሪያው በአካል መሔድ ነው፡፡  
v  ኹለተኛ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጽፈው አስተምረዋል፡፡የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ተቃጥሎ፣ ተሰርቆ፣ አይጥ በልቶት፣ ምድር ቀብሮት እንኳን ሊያልቅ ያልቻለውን መጻሕፍት ጽፈዋል፡፡ ለዚህ ሐዋርያዊ ተልእኮ ሦስት አካላት ነበሩ፡፡ አንድ ሊቃውንቱ፤ ኹለት ጸሐፍቱ (የሚጽፉት)፤ ሦስት ደግሞ የሚያስጽፉት፡፡ ገድሉ መጨረሻ ላይ አይታችሁ ከኾነ “የጻፈ፣ ያስጻፈ” ይላል፡፡ ዛሬ እንደነዚህ ዓይነት ሐዋርያት ያስፈልጉናል፡፡ ለምንድነው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በየቋንቋው የማይተረጐመው? ሲቻል ሳይሸጥ (በተለይ ለዕጣንና ለጧፍ እንኳን መግዣ ለሌላቸው ምእመናን) ለምን አይሰጥም? ምን አለበት እኔና እናንተ ዐሥር ኾነን አንዳችን የአንድን መጽሐፍ፣ አንዳችን ሌላውን መጽሐፍ ማሰተሚያ በተለያየ ቋንቋ በኦሮምኛ፣ በሀዲያኛ፣ በከንባትኛ፣ በጉራጊኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በጀርመንኛ፣ በየቋንቋ ለምን አናስጽፍም? እዛ ሔደን ማስተማር ባንችል ለምን እንዲህ አድርገን የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ወደየ አገራቱ እንዲደርስ አናደርግም? ለምን የካሴት ሐዋርያት አንኾንም? ለምን ትምህርቱ በካሴት ተባዝቶ በነጻ እንዲሔድ አናደርግም? ዛሬ እንደዉም የዲሽ ዘመን ነው፡፡ በዲሾቻችን ምን እየመጣ እንደኾነ እናውቃለን፤ ወረራው ቀላል አይደለም፡፡ ይኼም ዓይነት ሐዋርያ መምጣት አለበት፡፡ በቀላሉ የሚሔድ ሐዋርያ! አንድ ሰው ወደ እኛ እንዲመጣ አስተርጓሚ መጠበቅ የለበትም፡፡ እኛ ቶሎ ደርሰንለት ቶሎ አምኖ ቶሎ መጽደቅ አለበት፡፡ ጊዜ የለም አሁን፡፡ እርሱን መቼ ነው የምንሠራው?     
v  ሦስተኛው ማእከል የመመሥረት ሐዋርያነት፡፡ አባቶቻችን ለምን ይመስላችኋል ከሰሜን እስከ ደበቡ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፡ በየቦታው ገዳማትን የተከሉት? ዛሬ ካሉት ገዳማትኮ በተለያዩ ጦርነቶች ምክንያት የጠፉ ገዳማቶቻችን ይበልጣሉ፡፡ በታሪክ የምናውቃቸው ዛሬ ግን በአካል ያላገኘናቸው በጣም ብዙ ሺሕ ገዳማት ነበሩ፡፡ አባቶቻችን እነዚህን ገዳማት የተከሉበት አንዱ ዓላማ ለስብከተ ወንጌል ስምሪት ማእከል እንዲኾኑ ነው፡፡ እዛ ያስተምራሉ፤ እዛ ይጸልያሉ፤ እዛው የምንኩስናው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከዚያ የወጡ ደቀ መዛሙርትም ይሔዳሉ፤ ያስተምራሉ፤ ይሔዳሉ፤ በተራቸውም ገዳም ይተክላሉ፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሸዋ ነው የሔዱት፡፡ መጀመሪያ አባ በጸሎተ ሚካኤል አምሐራ፣ ከዚያ ሐይቅ፣ ከዛ ደብረ ዳሞ፣ ከዛ ኢየሩሳሌም፣ ከዚያ ግብጽ ሔደዋል፡፡ ተመልሰው መጥተው ግን የስምሪት ማእከል ነው ያቋቋሙት፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም እንዲሁ የተተከለ እንዳይመስላችሁ፡፡ ወደ ደቡቡም፣ ወደ ሰሜኑም፣ ወደ ምዕራቡም፣ ወደ ምሥራቁም ለመሔድ እጅግ እስትራቴጂያዊ ቦታ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ወደ አራቱም አቅጣጫ የሔዱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳሙን ለወንጌል አገልግሎት እንዲመች አድርገው ስለገደሙት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የስምሪት ቦታ ያስፈልገናል፤ ማእከል፡፡ በሰሜኑም፣ በደቡቡም፣ በምሥራቁም፣ በምዕራቡም የምንኩስና ሕይወትን፣ የአብነት ትምህርትን፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን አንድ ላይ የሚሰጡ ማእከላት ያስፈልጉናል፡፡ ያለ ማእከል ሐዋርያ ማፍራት አንችልም፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ ገንዘባቸውን ሲያወጡ የነበሩትኮ ዝም ብለው አይደለም፡፡ የሕንፃ ፍቅር ስላላቸው አይደለም፤ በፍጹም አይደለም! ያንን ማእከል አድርጎ ለማስተማር ነው፡፡ ሰዉ እንዲሰበሰብ እንዲሰማ ነው፡፡ እስኪ ገድላቱን አንብቧቸው፡፡ ወይም ሲነበቡ አድምጧቸው፡፡ ወይም ስታነቡ አስተውሏቸው፡፡ ገና ሲጀምሩ “በዚህ ቀን በቅዱስ እገሌ በዓል የተሰበሰባችሁ ወንድሞቼ ሆይ ስሙ፡፡ እገሌ የተባለውን ታሪክ እነግራችኋለሁ” ነው የሚሉት፡፡ ስሙ ለምን አለ? ሕዝቡ ተሰብስቦ ይነበብ ስለነበር፡፡ ዛሬኮ ወደነዚህ ማእከላት መጥተን ከቻልን በሰዓታቱ ተኝተን፣ ጎበዝ ነን ከተባልን ደግሞ እኛ ሌላ መዝሙር እየዘመርን፣ አንዳንዶቻችን የራሳችንን ቴፕ፣ አንዳንዶቻችንም ምን ምን የሚያክል ፍራሽ ለአንድ ሌሊት ይዘን ነው የምንሔደው፡፡ እንዴ! እንዲህ ከሆነ ለምን እንሔዳለን? አባቶቻችን ለንግሥ እንድንሰበሰብ ያደረጉን ዋና ዓላማቸው እንድንሰማ ነው፡፡ ሰምተንም ሐዋርያ እንድንኾን ነው፡፡ ዛሬ እነዚህን ማእከላት መሥራት አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንሠራ ይኼን ታሳቢ ያደረገ መኾን አለበት፡፡ ይኼ ነውኮ ሰማርያ የዓለም ዳርቻ የተባለው!
v  በየቋንቋው የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርትን የማሰማራት ሐዋርያነት፡፡ ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደማያውቁት ቋንቋ፣ ወደማያውቁት ባሕል እየሔዱ ማስተማር አይቻልም፤ በአስተርጓሚ እያስተማርን አንችለውም፡፡ አያዛልቅም፡፡ ይልቁንስ ታላቁ ሐዋርያዊ አባት ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳደረገው መኾን አለብን፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን የኾነው አባ ሰላማ ልሾም ብሎ ስለሔደ ወይም አብርሃና አጽብሃ እንደዚያ ብለው ስለላኩት አይደለም፡፡ የተላከው ጳጳስ ይዞ እንዲመጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ አትናቴዎስ ኹለት ዓመት አስተምሮ ነው ቋንቋውን፣ ባሕሉን በሚያውቀው አገር ጳጳስ አድርጎ ነው የላከው፡፡ ስለዚህ ከየቋንቋው እናምጣ፡፡ ከየባሕሉ እናምጣ፡፡ ከየአከባቢው እናምጣ፡፡ ከየሰዉ እናምጣ፡፡ አምጥተንም እናስተምራቸው፤ አስተምረንም እናሰማራቸው፡፡ በምታውቁት ቋንቋ፣ በምታውቁት ባሕል፣ በምታውቁት አሠራር አስተምሩ እንበላቸው፡፡ ገንዘብ ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ መጽሐፍ ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ የማስተማሪያ ነገሮች ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ ግን እናንተ ሐዋርያት ኹኑ፤ ሒዱ እንበላቸው፡፡ ይኼ ስምሪት ያስፈልጋል ዛሬ፤ የደቀ መዛሙርት ስምሪት፡፡ እነዚህን መጀመሪያ ማሠልጠን ከዚያ ለተልእኳቸው የሚያስፈልጋቸውን መስጠት ከዚያም መጎብኘት ያስፈልጋል፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ስለዚህ እናሰማራ! ከአዲስ አበባ መዘምራን፣ ሰባክያን እየላክን አንችለውም፡፡ በዓመት ልንሠራ የምንችለውን ለምን ወደ ዐሥር ዓመት እናራዝሟለን? ሕዝቡም በቋንቋው ሲነገረው በቀላሉ ደስ ብሎት ነው የሚቀበለው፡፡ ሐዋርያት 72 ቋንቋ የተሰጣቸው አንዱ ዓላማኮ ለዚህ ነው፡፡
ይኼ ነው ኃላፊነታችን! በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ የተባለው ይኼ ነው፡፡
እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ተሰማርተን፣ 30 60 100 ያማረ ፍሬ አፍርተን፣ ያለ ሐፍረት ቆመን “ጌታ ሆይ! ኹለት መክሊት ሰጥተኸን ነበር፤ እነሆ አራት አደረግነው፡፡ አምስት ሰጥተኸን ነበር፤ እነሆ ዐሥር አደረግነው” የምንልና “ና አንተ ታማኝ ባርያ ወደ ደስታው ግባ” ከተባለው ወገን እንዲያደርገን፣ ያ መክሊቱን ቀብሮ “አንተ ክፉና ሐኬተኛ፤ እኔ ካልዘራሁበት የምሰበስብ ካልተከልኩበት የማጭድ መኾኑን ካወቅክ ለምን ለሌላ አትሰጠውም ነበር? እሳትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወርውሩት” ከተባለው እንዲጠብቀን የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!!!  

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...