2015 ጃንዋሪ 9, ዓርብ

አባቶችና ምእመናን ‹‹ሸኚው ሸኚ ሲያጣ›› እስኪሉ ድረስ በመጣደፉ በእጅጉ ያዘኑበት የ106 ዓመት አረጋዊው የብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ



funeral of Abune Aregawi
ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን

ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ አረጋዊ

ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በ1901 ዓ.ም. ወልደው በፀለምት /ሰሜን ጎንደር/ ተወልደው ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገብተው ንባብና ዳዊት እንዲኹም እስከ ፀዋትወ ዜማ አጠናቅቀው ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ማዕርገ ዲቁናና ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ገብተው ለዘጠኝ ዓመታት ያኽል (ከ1933 – 42 ዓ.ም.) ሥርዓተ ገዳሙን ከአጠኑና በግብዝና ከአገለገሉ በኋላ በዚኹ ገዳም መዓርገ ምንኵስናን ተቀብለዋል፡፡ ትምህርታቸውን በመቀጠል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሚገኘው በደብረ ዓባይ ገዳም የደብረ ዓባይ መዝገበ ቅዳሴ ዜማ ተምረው በመምህርነት በቅተዋል፡፡
በ1943 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ፈቃድና ትእዛዝ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን እንዲያገለግሉ ተልከው ለአራት ዓመታት ያኽል አገልግለዋል፡፡ አኹንም በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ወደ ግብጽ ሔደው ለ16 ዓመታት ያኽል ነገረ መለኰትን በዓረብኛ ቋንቋ አጥንተው ተመርቀዋል፡፡funeral of Aba Aregawi 
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት ለማገልገል ተልከው ለስድስት ዓመታት ያኽል በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል፡፡ በዚኹ ሓላፊነት ሳሉም በ1968   ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኹነው በተሾሙ ጊዜ በሱዳን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመምጣት ለበዓሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በመኾን አገልግለዋል፡፡
በጥቅምት ወር 1983 ዓ.ም. በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኾነው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ተሾመዋል፡፡
ከመጋቢት 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ለአንድ ዓመት ያኽል ሠርተዋል፡፡
ከየካቲት 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳምና ት/ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከሐምሌ 1968 ዓ.ም. ጀምሮ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከግንቦት 1992 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም በዚኹ ሥራ ላይ ሳሉ ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በተወለዱ በ106 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
funeral of Aba Aregawi03
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም በዚኹ ዕለት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበትና የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ ከተፈጸመ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ አቡነ አረጋዊን ነፍስ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ሰጥቶ በአብርሃም በይሥሐቅ በያዕቆብ አጠገብ ያኑርልን፤ በማለት እንሰናበታቸዋለን፡፡
About these ads

ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ



  • ሥርዐተ ቀብሩ ዛሬ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
His Grace Abune Aregawi
በተባሕትዎአቸውና በተመሰገነው ምንኵስናቸው የሚታወቁት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ፡፡ ብፁዕነታቸው ዛሬ፣ ዓርብ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ያረፉት ለተሻለ ሕክምና በገቡበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡
ብፁዕነታቸውን ለኅልፈት ያደረሳቸው፣ ከአንድ ወር በፊት ለሐዋርያዊ ተልእኮ ወደ ደቡብ ሱዳን በሔዱበት ወቅት ያጋጠማቸው ቢጫ ወባ በኩላሊታቸውና በሳምባቸው ላይ ያስከተለው ጉዳት ነው፡፡
ከጉዟቸው መልስ ‹‹እኔ ንግግሬ ከእግዚአብሔር ጋራ ነው›› በማለት ያለሕክምና ርዳታ ለኹለት ሳምንት ያኽል በተዘጋ ማረፊያቸው የቆዩት ብፁዕነታቸው፣ በብፁዓን አባቶችና በቅርብ ወዳጆቻቸው ተማኅፅኖ በዘውዲቱ ሆስፒታል እና በሳንቴ የጤና ማእከል በተደረገላቸው ከፍተኛ ክትትል የተጎዳው ኩላሊታቸው አገግሞ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በተሻለ ኹኔታ ላይ ይገኙ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ይኹንና ከዕድሜ አንጋፋነታቸው ጋራ ሕመሙ በሳምባቸው ላይ ባደረሰው ጉዳት የተፈጠረው ኢንፌክሽን ለኅልፈት እንደዳረጋቸው ተመልክቷል፡፡
በቅርበት የሚያውቋቸው ወገኖች÷ የዋልድባው መነኰስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሀብት ምክር ያላቸው፣ ታሪክ ዐዋቂና የታያቸውን በግልጽ የሚናገሩ መምህር ወመገሥጽ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
www-st-takla-org-abune-paulos-in-alex-15-july-2007-017
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በግብጽ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ሐምሌ ወር ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.፣ ሐምሌ ፰ ቀን በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም በተሠራው ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት ወቅት፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የቅዱስነታቸውን ንግግር በልሳነ ዓረቢ እየመለሱ አሰምተው ነበር፡፡
የቀደምት ቅዱሳን አበውን ትውፊት በመከተል በግብጽ ገዳማት ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያኽል በመቀመጥ ከአኃው መነኰሳት ጋራ መንፈሳቸውን ያስተባበሩት ብፁዕነታቸው፣ ልሳነ ዓረቢን አቀላጥፈው በመናገርም ይታወቃሉ፡፡ የቅድስት ሀገር ተሳላሚ ለመኾን የበቁትም በወጣትነታቸው ማለዳ ሳሉ ነበር፡፡
በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ አቡነ አረጋዊ ተብለው ጥቅምት ፲፰ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት በአራተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ነው፡፡
ብፁዕነታቸው ቀድሞ ሊቀ ሥልጣናት በተባሉበት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በበላይ ጠባቂነት ከመወሰናቸው በፊት፣ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲኹም የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን አገልግለዋል፡፡
የብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር ዛሬ፣ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለረጅም ዓመታት በአገለገሉበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በ9፡00 እንደሚፈጸም ተገልጧል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለብፁዕ አባታችን ዕረፍተ ነፍስን ይስጥልን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...