2014 ማርች 5, ረቡዕ

ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደር የማሻሻል አቋሜ ‹‹አልተበረዘም፤ አልተከለሰም›› አሉ


  • ‹‹የፀረ ሙስና አቋማቸው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ያለፈ ውጤት አላመጣም›› /ተቺዎች/
(ሰንደቅ፤ የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
Sendek front pageየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፍትሕ፣ ርትዕና እኩልነት የሞላባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ለማድረግ በዕለተ ሢመተ ፕትርክናቸው የተናገሩት ቃል ኹሉ እንደጸና መኾኑንና ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናን ጋር በመኾን እንደሚያጠናክሩት ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ስድስተኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙበት አንደኛ ዓመት ከትላንት በስቲያ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረበት ወቅት ‹‹ሙስና ካልጠፋ ሕይወት አይኖርም›› ሲሉ የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰበሰበው ገንዘብ ከድኾች የተገኘ ሀብት ስለኾነ የድኾችን ገንዘብ በከንቱ የሚያማስነውን እግዚአብሔር እንደሚፈርድበት፣ በዚኽም እግዚአብሔርን ማታለልና በእግዚአብሔር ላይ መቀለድ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእውነትና የሐቅ መገኛ ትኾን ዘንድ መንፈሳዊ ባሕርይዋ የሚያስገድዳትና አገልግሎትዋም በእግዚአብሔር ስም የሚሠራ በመኾኑ አሠራርዋ ከአድሏዊነትና ወገንተኝነት መጽዳት፣ ታማኝነትንና ፍትሐዊነትን መጎናጸፍ ይኖርበታል ብለዋል ፓትርያርኩ፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሲባል ሕንፃ ቤተ መቅደሱ ብቻ ሳይኾን የካህናትና የምእመናን አንድነትም መኾኑን ያስረዱት አቡነ ማትያስ፣ በይበልጥም ቤተ ክርስቲያኒቷን በሓላፊነት ለመጠበቅ ጥሪው ያላቸው ካህናት በአበው ሥርዐት በተደነገገው መሠረት÷ ቀኖናዋንና ትውፊቷን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ምእመኖቿን በስብከተ ወንጌል ማርካትና በግብረ ገብነት እንዲታነፁ ማድረግ የዉሉደ ክህነት ሓላፊነት ነው፤ ከዚኽ አንጻር ዉሉደ ክህነት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮ ፈሩን ሳይስት እንዲፈጸም የማድረግ መንፈሳዊ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዓለ ሢመቱ የአንድ መሪ ግለሰብ በዓል እንዳልኾነ ያስገነዘቡት ፓትርያርኩ፣ በዓሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኹለንተናዊ ልዕልናና ክብር በፊት እንዴት እንደነበር፣ አኹን ምን ላይ እንዳለና በቀጣይ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በስኬት ለማከናወን ምን መደረግ እንዳለበት እየታሰበ እንደሚከበር አብራርተዋል፡፡ ከሥርዐተ ሢመታቸው ወዲህ ባለፈው የአንድ ዓመቱ ጉዞ ውስጥ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራት ፓትርያርኩ በንግግራቸው ዘርዝረዋል፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ እየተሻሻለ ነው፤ በመልካም አስተዳደር፣ በመሪ ዕቅድ እንድትመራ ጥረት እየተደረገ ነው፤›› በማለት ክንውኑን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ችግሩ ለዘመናት የተከማቸና በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ስለሚያዳግት በትዕግሥት መጠባበቁ መልካም ይኾናል፤›› ብለዋል፡፡ በበዓለ ሢመታቸው ቀን የአስተዳደር መዋቅር ማሻሻያን አስመልክቶ ተናግረዋቸው የነበሩ ቃላት ኹሉ ‹‹እንደጸኑ ናቸው፤ አልተበረዙም፤ አልተከለሱም፤ እንዲያውም ከሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናን ጋር በመኾን አጠናክራቸዋለኹ›› ያሉት አቡነ ማትያስ፣ ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለድርሻ አካላት ኹሉ መነሣት እንደሚኖርባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፤ ‹‹ይህ ግዴታ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር እንዲሁም አደረጃጀትና አሠራር ከመሠረታዊ ክህነታዊና የስብከተ ወንጌል ተልእኮዋ ጋራ እንዲጣጣም፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ የተደረጉ የሙከራ ትግበራዎችና በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶች፣ ‹‹ይኹንታ ካገኙበት የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በተፃራሪ ዕንቅፋት ገጥሟቸዋል፤›› የሚሉ የቅርብ ታዛቢዎች በበኩላቸው÷ ፓትርያርኩ ሙስናን በየአጋጣሚው በመቃወምና ስለመልካም አስተዳደር ደጋግሞ በመናገር ራሳቸውን አስተዋውቀው እንደኾነ እንጂ ያመጡት ተስፋ ሰጭ ውጤት የለም፤ እንዲያውም በደሉና ጥፋቱ መልኩን ለውጡ እየረቀቀና እየተባባሰ መምጣቱን በምሬት ይናገራሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ሥር ሰዷል ያሉት ጎሰኝነት ከቀድሞም ጀምሮ ስማቸው ሲጠቀስ በቆዩና በተለይ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ዙሪያ በተሰባሰቡ ግለሰቦች ተጽዕኖ እየገዘፈ መምጣቱን ታዛቢዎቹ ከማስረዳታቸውም በላይ፣ ፓትርያርኩ ‹‹እንደ ጸና ነው›› የሚሉት አቋማቸው በላቀ አመራርና የውሳኔ ሰጭነት አቅም ተፈትኖና በተግባር ተገልጦ ማየት እንደሚሹ ለሰንደቅ ገልጸዋል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...