2015 ኦክቶበር 16, ዓርብ

ለዘብተኛነት/ሊበራሊዝም/፡የክርስትና ዘመናዊው ጠላት - ክፍል 2

ባለፈው ጽሑፍ የሊበራል ክርስትናን ምንነት እና ጠባያት ተመልክተናል፡፡ በዚህ ቀጣይ ጽሑፍ ደግሞ ያመጣውን መዘዝ እና መፍትሔውን እናያለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ሊበራል ክርስትና ምን አመጣ?

ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳይፈሩ አደረገ

ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር የተባለው ተዘንግቶ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ የሚያሾፉ ፊልሞችን እንዲሠሩ፣ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን እንኳን የማይለውን የዳቪንቺን ኮድን የመሰሉ አስተሳሰቦችን እንዲያራምዱ፣ በስቅለት ቅርጽ የፋሲካ ካንዲ እንዲሠሩ፣ ወዘተ አደረጋቸው፡፡ በየዘፈኖቻቸው ስመ እግዚአብሔርን እያነሡ እንዲቀልዱ አበረታታቸው፡፡ የጌታችን የስቅለት ሥዕል ከየቦታው እንዲነሣ ፣ አሠርቱ ትእዛዛት ከአሜሪካ ፍርድ ቤት በር እንዲነሣ አስደረጉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ቅዱሳንን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና የቤተ ክርስቲያን አካላትን እያነሡ መቀለድ እና ማቃለል በሀገራችን እየተለመደ ነው፡፡ ምሁራን፣ባለ ሥልጣናት፣ጋዜጠኞች እና ሌሎችም በይፋ በቤተ ክርስቲያን ነገሮች ላይ መቀለድ ልማድ አድርገውታል፡፡ የሚገርመው ነገር እነርሱም አይሰቀቁ፣እኛም ለምደነው እንስቃለን፤ አናዝንም፡፡ ለሌሎች አርአያ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ አገልጋዮች፣የእምነት አባቶች እና ገዳማውያን ሳይቀሩ በሥነ ምግባር ብልሹነት እና በሙስና እስከ መዘፈቅ ደርሰዋል፡፡

ለአክራሪ እስልምና አጋለጠን

አክራሪ እስልምና እጅግ በጣም ወግ አጥባቂ እምነት ነው፡፡ ይህ እምነት ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲዘምት በሊበራሊዝም የተቦረቦረ ኅብረተሰብ ነው ያገኘው፡፡ ይህ የራሱ ማንነት የሌለው እና ሁሉም ትክክል ነው ብሎ የሚያምን ኅብረተሰብ ደግሞ በፍጥነት እና በፍላጎት ለሚሠራው አክራሪ እስልምና የተመቸ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ ፓትሪክ ሱኬዶ የተባሉ «የእስልምና እና ክርስትና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር» እንደ ተናገሩት 200 ከፍተኛ የአሜሪካ ኩባንያዎች የሸሪያ ሕግን አጣጥመው ይሠሩበታል፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያም ለዋና ዋና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ ርዳታ በመስጠት የትምህርት ሥርዓቱ ከተቻለ ለእስልምና አመቺ ካልተቻለም ለዘብተኛ እንዲሆን ታደርጋለች ብለዋል፡፡

እጅግ ታዋቂ የሆኑ አሜሪካውያን ክርስትናው አላረካቸው ብሎ እስልምናን ሊቀበሉ የቻሉት፣ መጀመርያውኑ ርግጠኛውን ክርስትና ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የምዕራብ ዜጎች ከነ አልቃይዳ ጎን ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውን እና ወገናቸውን እስከማጥፋት የደረሱት ያሳደጋቸው ለዘብተኛ ክርስትና ሊያረካቸው ባለመቻሉ ነው፡፡

የሞራል መላሸቅን አስከተለ

ክፉ እና ደጉን ለይቶ የማያውቅ፣ ማንንም የማይፈራ፣ ለሱስ፣ ለመገዳደል፣ ለመጠጥ፣ ለሐሺሽ፣ ለዝሙት፣ ለጭፈራ፣ የተጋለጠ ለማኅበረሰባዊ እሴቶች ግድ የሌለው፣ ሀገሩን እና ወገኑን ለመርዳት የማያስብ፣ ከትምህርት ይልቅ መዝናናትን የሚመርጥ ትውልድ እንዲያፈሩ አደረገ፡፡ ዛሬ አሜሪካን ውስጥ ድራግ የማይቀምስ ወጣት የለም፡፡ በድንግልና መቆየት ነውር ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ አሜሪካውያን ለሂሳብ፣ ለፊዚክስ እና ለኢንጂነሪንግ ፍቅር የሌላቸው በሙዚቃ ግን የተለከፉ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይሄ ነው፡፡ ቅዱሳንን ንቀው ታላላቅ ሰዎችን የሚያመልኩ፣ የፈለግኩትን ባደርግ ምን አለበት? በሚል ስሜት ለወንጀል የሚዳረጉ እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡

ቅድመ ጋብቻ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደ ኃጢአት ሳይሆን እንደ መብት በመታየቱ ዛሬ ወጣቶቻቸው እምብዛም አይጨነቁበትም፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት ዕድሜያቸው 20 ዓመት ከሞላቸው ወጣቶች መካከል ቢያንስ 75% ቅድመ ጋብቻ የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬ 2 ዓመት በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገ ጥናትም ከ50% በላይ ተማሪዎች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ጾታዊ ግንኙነት ማድረጋቸውን አመልክቷል፡፡

ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የሚኖር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን መሆኑ እየቀረ በተፈለገ ጊዜ ሊቀር የሚችል መሆኑ ስለተሰበከ ፍቺ በርክቷል፡፡ ጋብቻ በአንደ ወቅት የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት እንጂ የቅድስና ምንጭ መሆኑ እየተረሳ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሳይጋቡ በደባልነት መኖር እንደ ጋብቻ ኑሮ እየተቆጠረ መጥቷል፡፡

በአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናቱ የጽንስ ማስወረድ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች ተብለው እስከ መለየት ደርሰዋል፡፡

አገልግሎትን እንደ ሞያ ማየት

በሊበራሊዝም አስተሳሰብ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደ አንደ ሞያ ብቻ ይታያሉ፡፡ ጵጵስና፣ ካህንነት፣ ዘማሪነት፣ወዘተ ሞያዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት ሥነ ምግባርን እና አርአያ ክህነትን አይጠይቁም፡፡ አገልግሎት እንደሞያ ከታየ ፈሪሃ እግዚአ ብሔር ጠፍቶ ድፍረት ቦታውን ይይዛል፡፡ የሚያስተምሩትን ራሳቸው የማይፈጽሙ፣ለክብር ፣ለዝና እና ለገንዘብ ብቻ ሲሉ የሚያገለግሉ፣ በመንፈሳዊነት ስም ኃጢአትን የሚፈጽሙ አገልጋዮች እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በአሜሪካ እና በአውስ ትራሊያ በካቶሊክ መነኮሳት ላይ የታየው የሞራል ዝቅጠት በሽታው የደረሰበትን ደረጃ ያመለክተናል፡፡

በሀገራችንም ቢሆን ዛሬ ዛሬ ምንኩስናን ለፍጹምነት መብቂያ መንገድ ሳይሆን የድብር አስተዳዳሪ ለመሆን፣ውጭ ሀገር ለመሄድ፣ የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ አድርገው የሚቆጥሩት እየበዙ መጥተዋል፡፡ ሰባኪነት እና ዘማሪነትም ቢሆን ተሰጥኦ እና ትምህርት፣ሃይማኖት እና ምግባር የሚጠይቅ መሆኑ እየተዘነጋ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ቀላል እና ክፍት የሥራ ቦታም ይመስላል፡፡

የማይጾም፣ የማይጸልይ፣ የማያስቀድስ፣ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የራቀ፣ የሌለበትን ሕይወት የሚያስተምር እና የሚዘምር አገልጋይ እየመጣ ነው፡፡ እንደ ባለሞያ ለእንጀራው ሲል ብቻ የማያምንበትን የሚያስተምር አገልጋይ እየመጣ ነው፡፡ ሰዓታት መቆም፣መቀደስ፣መመንኮስ፣ኪዳን ማድረስ፣ ጠዋት ተገብቶ ማታ የሚወጣበት ሥራ እየሆነ መጥቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የማያውቃቸው ምእመናንን እና ካህናትን አፈራ

ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የማያስቀድሱ፣ የንስሐ አባታቸውን አግኝተው የማያውቁ፣ በአዳራሽ እንጂ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ለመሰብሰብ የማይፈልጉ፤ አንድም ቤተ ክርስቲያን የማያውቃቸው ካህናት፣ ገዳም የማያውቃቸው መነኮሳት እየበዙ መጥተዋል፡፡

ከዚህም ብሶ ከአጠቃላዩ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተነጠሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ጳጳሳት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ «እኔን ከመሰለኝ» የሚለውን የሊበራል አስተሳሰብ በመከተል በአንድ በኩል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እየተሰበሰቡ በሌላ በኩል ደግሞ የግላቸው ቤተ ክርስቲያን መሥርተው የሚንቀሳቀሱ ጳጳሳት ተፈጥረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት የግል እና የመንግሥት ተብለው እንደ ሚከፈሉት ሁሉ አገልጋዮችም የግል አገልጋዮች እና የቤተ ክህነት አገልጋዮች ተብለን እስከ መከፈል ደርሰናል፡፡

የሊበራሊዝም ግርፍ የሆኑ አንዳንዶች ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ሊያድን እንጂ ሃይማኖት ሊመሠርት አልመጣም የሚል ፍስፍና ያስፋፋሉ፡፡ ለመሆኑ ሃይማኖት ምንድን ነው? ሃይማኖት ማለትኮ በቀላሉ ሲተረጎም እግዚአብሔርን የማምለኪያ መንገድ ማለት ነው፡፡ ታድያ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን መንገድ አልዘረጋም? ሐዋርያው ይሁዳስ «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠች ሃይማኖት» በማለት የገለጠው ምንድን ነው?/ይሁዳ 1÷3/ ቅዱስ ጳውሎስስ በኤፌሶን መልእክቱ «አንድ ሃይማኖት አለ» ያለው/ኤፌ 4÷5¼ ተሳስቷልን? ልጁ ቲቶን «ስለዚህም ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም እኔ አንተን እንዳዘዝሁህ» ቲቶ 1÷5 በማለት የገለጠው ክርስትና የራሱ አደረጃጀት ስላለው አይደለምን?

ምን ይደረግ ?

ሊበራል ክርስትና ዛሬ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን እየተፈታተኑ ካሉት የዘመኑ ፈተናዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ፈተና በሁለት መልኩ ይገባል፡፡

የመጀመርያው አስተሳሰቡን በማራመድ ሆን ብሎ በሚደረግ ወረራ ነው፡፡ በሀገራችን ፕሮቴስታንቶች እና ተሐድሶዎች ሞክረውት የነበረው ይሄንን መንገድ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ፓስተሮች እና ተሐድሶዎች ይህንኑ አስተሳሰብ ያራምዱታል፡፡ የሁለት ሺ ዓመት መሠረትን በማጥፋት ቤተ ክርስቲያንን ያልተጣሩ አስተሳሰቦች መናኸርያ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሺ ዓመታት ወንጌል የገባው ሕዝብ አልተፈጠረም፣ ክርስቲያኑ ክርስቶስን አያውቅም ነበር ብሎ ማሰብ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋው ተርጉሞ እና ከዮዲት እና ግራኝ ጠብቆ ያቆየን ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አታውቅም ነበር ብሎ በድፍረት ማስተማር መሠረትን ለማናጋት እንጂ እውነቱ ጠፍቶ አይደለም፡፡ አንድ ምሁር እንዳለው ይህ «ክርስቲያንን መልሶ ክርስቲያን ማድረግ  re  christianization of the Christians » ማለት ነው፡፡

በተለይም አሜሪካ የዚህ ወረራ ዋነኛ ቦታ ሆናለች፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት፣ትውፊት እና ባሕል እያቃለሉ ማስተማር፣ወይንም ደግሞ በጭራሽ ርእሰ ጉዳይ አድርጎ አለማስተማር እና ማስረሳት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ከ30 በላይ ገድላትን እና ድርሳናትን የሚሳደቡ ጽሑፎች በተሐድሶአውያን ታትመው በነጻ እየተሠራጩ ይገኛሉ፡፡  አክራሪ እስልምናን በተመለከተ ግን ትንፍሽ ብለው አያውቁም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ አስተሳሰቡ ሳይታወቅ ይገባና ውስጥ ለውስጥ ይሸረሽራል፡፡ ከዚያም በሃይማኖት ለዘብተኛ ያደርጋል፡፡

ቅዱሳንን እና ክብራቸውን ማቃለል፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስሕተት ለመፈለግ መኳተን፣ የጸሎት መጻሕፍትን አለመጠቀም፣ በሰበብ በአስባቡ ከጾም መሸሽ፣ በየምክንያቱ ከቤተ ክርስቲያን መራቅ፣ ለንዋያተ ቅድሳት ያለን አክብሮት መቀነስ፣ ምን አለበት በሚል ምክንያት ነገሮችን በፈለግነው መንገድ ማድረግ፣ ጳጳሳትን፣ ካህናትን እና አገልጋዮችን መናቅ፣ እና በድፍረት መናገር፤ ቤተ ክርስቲያን ባልሄድም በልቤ መልካም ሰው ከሆንኩ ይበቃኛል እያሉ መጽናናት፣ በሃይማኖት ጉዳዮች ሳቅ እና ቀልድ ማብዛት፣ በሃይማኖት ማፈር፣ አንዲት እምነት ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወጥቶ፣ ለሌሎቹ ያዘኑ በመምሰል፣ ሁሉም ልክ ነው የሚል አዝማሚያ መያዝ ከበሽታው ምልክቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሽታው ሌላም ምልክቶች አሉት፡፡ የሊበራል ክርስትና «እኔ እኔ» አስተሳሰብ ወደ መዝሙሩም፣ ወደ ትምህርቱም ይገባና ሁሉም በዚሁ ይቃኛል፡፡ እግዚአብሔርንም የኔ ማለት ይጀመራል፡፡ በትምህርታችን ውስጥ እኔ እንዲህ ሆኜ፣ ይህንን አድርጌ፣ እንዲህ ያለ ነገር ታይቶኝ፣ ወዘተ እያሉ ራስን ከፍ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን መጨማመር፣ በመዝሙሮቻችንም ራስን መስበክ ይመጣል፡፡ በምሥራቃውያን ትውፊት ሰው ስለ ራሱ ይናገር የነበረው ታናሽነቱን፣ ትኅትናውን ወይንም በደለኛነቱን ለመግለጥ ነበር፡፡ ሊበራሊዝም ዘልቆ ሲገባ ግን የራስን ታላቅነት እና ክብር መናገርም ይጀመራል፡፡

ሊበራሎች ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔር ነው ብለው አያምኑም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለሰዎች ሕይወት «ሞዴል ነው» ይላሉ፡፡ ስለዚህም እንደ አንድ ፍቅረኛ፣ ጓደኛ፣ አርአያ ያዩታል እንጂ በአምላክነቱ አይቀበሉትም፡፡ በመሆኑም ናፈቀኝ፣ እወደዋለሁ፣ ጓዴ ነው፣ አብሮ አደጌ ወዘተ ብሎ መጥራት ያዘወትራሉ፡፡ ይህ አስተሳሰባቸው ገብቶብን እንደሆነም አላውቅም «ስትናፍቀን እንዘምራለን» የሚል መዝሙር በሰንበት ት/ቤቶች ሲዘመር የሰማሁ ይመስለኛል፡፡

ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከሁለት አቅጣጫ በሚመጣ ፈተና ተወጥራለች፡፡ ከምሥራቅ ወግ አጥባቂው እና በከፍተኛ ሁኔታ ኃይልን፣ ገንዘብን እና ነውጥን በሚጠቀመው አክራሪ እስልምና፣ ከምዕራብ በኩል ደግሞ ለሃይማኖት ግድየለሽ፣ በፈጣሪ በሚቀልደው እና ጠንካራ እና ጽኑዕ እምነትን ለመሸርሸር በተነሳው ሊበራል ክርስትና፡፡ አንዱ በኃይል ሌላው በፍልስፍና - ኦርቶዶክሳዊነትን ለማጥፋት ዘምተዋል፡፡

ይህንን ከሁለት ወገን የመጣ እና ሳንዱዊች ሊያደርገን የተዘጋጀ ፈተና «መንፈሳውያን ሃይማኖታውያን» በመሆን ብቻ ነው ድል የምንነሣው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የተበታተነች፤ በአሠራርዋ የተዳከመች ከሆነች፤ ልጆቿ በመንፈስ የዛሉ፣ በሃይማኖት ዕውቀት ያልበረቱ ከሆኑ ፈተናውን መቋቋም አይችሉም፡፡

«በክርስትና እና በሳይንስ መካከል ያለው ዐቢይ ልዩነት፣ በሳይንስ የቅርቡ በጣም የተሻለ ሲሆን፣በክርስትና ግን የጥንቱ በጣም የተሻለ መሆኑ ነው in science the latest is the best, but in Christianity the oldest is the best» በማለት ይስሐቅ አል ባራኪ የተባሉ ሶርያዊ ሊቅ እና ሳይንቲስት ተናግረዋል፡፡ ክርስቲያን የሆንነው እኛ አባቶቻችንን ለመምሰል እንጂ አባቶቻችን እኛን እንዲመስሉን አይደለም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም የመጣነው እኛ በቤተ ክርስቲያንዊ ትምህርት እና ሕግ ልንመራ እንጂ ቤተ ክርስቲያን በኛ ትምህርት እና ሕግ ለመምራት አይደለም፡፡

በመሆኑም ትክክለኛውን ክርስትና ለመኖር እኛም ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያንም ወደ እኛ መግባት አለባት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና በሦስት መልኩ መገለጥ አለበት ትምህርታዊ፣ ሊተርጂያዊ፣ እና ትውፊታዊ፡፡ ትምህርታዊ ማለት መጽሐፍ ቅዱስን አባቶቻችን በተረዱበት መንገድ እና መሠረት መረዳት፣ መመስከር እና መኖር ማለት ነው፡፡  በክርስትና አዳዲስ ማብራርያዎች እንጂ አዳዲስ መሠረተ ሃሳቦች ሊኖሩ አይችሉም፡፡

ሊተርጂያዊ ማለት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚገኙትን ጾም ፣ጸሎት፣ ቅዳሴ፣ የምሥጢራት ተሳትፎ፣ ዝማሬ፣ ወዘተ ገንዘብ ማድረግ እና የእነዚህ ፍሬዎች የሆኑትን የምግባር ፍሬዎች ማሳየት ማለት ነው፡፡ ትውፊታዊ ማለትም በቤተ ክርስቲያን ያገኘናቸውን የቀደሙ አበው የሕይወት መንገዶች፣ትሩፋቶች፣ጸጋዎች፣ ቅርሶች በመያዝ፣በመጠበቅ እና በመጠቀም መኖር ነው፡፡

ዋናን ከውኃ ውጭ መዋኘት እንደማይቻለው ሁሉ ክርስትናንም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ መኖር አይቻልም፡፡ በመርከቧ ሲጓዙ ማዕበል በተነሣባቸው ጊዜ በዚያው መርከብ ውስጥ ሆነው አድነን ነበር ያሉት ሐዋርያት፡፡ እኛም በየምክንያቱ ከቤተ ክርስቲያን መውጣታችንን ትተን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመኖር ችግሮችን መጋደል እና መቋቋም ያስፈልጋል፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «ሸረሪት አትሁኑ» ይሉ ነበር፡፡ ሸረሪት ድር አድርታ የኖረችበት ቤት ሲቃጠል ውኃ አምጥታ ከማጥፋት ይልቅ ቤቱን ለቅቃ ሌላ ቦታ በመሄድ ድር ታደራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ፈተና በገጠማት ቁጥር እየሸሹ የራስን ኅሊናዊም ቁሳዊም ጎጆ መቀለስ ሸረሪትነት ነው፡፡

ሃይማኖት የትርፍ ጊዜ ሥራ መሆን የለበትም፡፡ መንፈሳዊነትም ባሕል እና ልማድ ብቻ ሆኖ ያለ ልቡና እንዲሁ የሚኖርበት መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ቀጥ ብሎ ራስን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ እንደዋዛ የምንናገራቸው እና የምናደርጋቸው ነገሮች ቤተ ክርስቲያንን ሸርሽረው ሸርሽረው በምእመናን ላይ የማይጠገን ቁስል ከመጣላቸው በፊት በቀደሙት አበው ትምህርት እና ኑሮ መነጽርነት መንገድን እና ልብንም መመርመሩ የተሻለ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ከቡር

ለዘብተኛነት/ሊበራሊዝም/፡የክርስትና ዘመናዊው ጠላት



ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን ዕወቅ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፣

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፡፡ 2ኛጢሞ. 3÷5

ለዘብተኛነት/ሊበራሊዝም/ በ18ኛው መክዘ መጨረሻ እና በ19ኛው መክዘ መጀመርያ ብቅ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በፖለቲካው መስክ ግራ ዘመም አስተሳሰብ በመባል ይታወቃል፡፡ በደምሳሳው ልቅ በሆነ መብት እና ነጻነት የሚያምን፤ ነባር ባሕሎችን፣ ልምዶችን እና እምነቶችን በየጊዜው በመናድ ሰዎች ራሳቸውን አማልክት አድርገው እንዲያስቡ የሚያበረታታ አመለካከት ወይም ርእዮተ ዓለም ነው፡፡

ዛሬ በፖለቲካው መስክ ያለው ለዘብተኛነት ርእሰ ጉዳያችን አይደለም፡፡ የምንወያየው ስለ ለዘብተኛ/ሊበራል/ ክርስትና ነው፡፡

ሊበራል ክርስትና የግራ ዘመምን አስተሳሰብ በመያዝ በዚያው በ18ኛው መክዘ መጨረሻ እና በ19ኛው መክዘ መጀመርያ ብቅ ያለ አስተምህሮ ነው፡፡ ይህ አስተምሮ ፕሮቴስታንቲዝምን ሳይቀር አክራሪ /conservative/ ነው ብሎ የሚያምን እና በሃይማኖት ለሰው ልጅ ልቅ የሆነ መብት እና ነጻነት ሊሰጠው ይገባል በሚል የተነሣ ነው፡፡ በአሜሪካ እና በአውሮፓ አብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች እና ፓስተሮቻቸው በዚህ አመለካከት የሚመሩ ናቸው፡፡

ይህ አመለካከት የፕሮቴስታንቱን ዓለም ሃይማኖት አልባ ማድረጉ ሳያንሰው የካቶሊካውያንን እና የምሥራቅ እና የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናትን በር በማንኳኳት ላይ ይገኛል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን እና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው በየጊዜው ስለሚለፈፍ፣ ታላላቅ የሚባሉ ፖለቲከኞች እና የተከበሩ ሰዎች በየአጋጣሚው ስለሚያነሡት የሊበራል ክርስትና አስተሳሰብ እንደ ተስቦ በየሰው እየሠረፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሊበራል ክርስትናን እንዲህ እና እንዲያ ነው ብሎ ከመበየን መገለጫዎቹን ማቅረቡ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፡፡

የሊበራል ክርስትና አመለካከት ዋና ዋና መገለጫዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ይላሉ

ሊበራል ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት የነበሩ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ምን እንደሚያምኑ የገለጡበት መጽሐፍ እንጂ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ሊተች፣ ሊስተካከል፣ ሊታረም እና ሊቀየር የሚችል ጽሑፍ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰባቸው ምክንያትም ዛሬ ዛሬ ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት አስተማሪዎች በትምህርታቸው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ማለት አልነበረበትም እያሉ ይተቻሉ፡፡ ወይም አንድ ሰው እንዳለው they want to re-write the bible፡፡ ሃይማኖታቸውም የግድ መጽሐፋዊ መሆን እንደሌለበት እና መጽሐፍ ቅዱስ የሃሳብ መነሻ ብቻ መሆን እንደሚችል ያስተምራሉ፡፡ በመሆኑም በየጊዜው አዳዲስ እና የተሻሻሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጅዎች እንዲታተሙ ያበረታታሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ወጥ ትርጓሜ አያስፈልገውም ይላሉ

ሊበራሎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንም ሰው እንደተመቸው እና እንደገባው መተርጎም ይችላል፡፡ አንድ ወጥ የሆነ እና «ትክክል ነው» ተብሎ ሊመሰከርለት የሚችል ትርጓሜ የለም ይላሉ፡፡ ይህም በሃይማኖት እና በአስተሳሰብ የተለያዩ ሚሊዮን ዓይነት የክርስትና ክፍልፋዮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ዶግማ እና ቀኖና የሚባል ነገር ስለሌላቸው ስለሚያመልኩት አምላክ እንኳንስ ሁሉም፣ በአንድ ጉባኤ የተገኙት እንኳን ተመሳሳይ እምነት የላቸውም፡፡ በማናቸውም ትምህርታቸውም ቢሆን የቀደሙ አበውን ትምህርት፣ ትርጓሜ እና ሐተታ አያካትቱም፡፡ ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሱ ካልሆነ በቀር፡፡ የቅዱሳንን ሕይወትም አስረጂ አድርገው አይቆጥሩትም፡፡

በሃይማኖት ጉዞ ውስጥ አንድ ሊቋረጥ የማይገባው አንድነት «አሐተኔ» አለ፡፡ ይኸውም በአንድ ዘመን በሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል፣በአንድ ዘመን በሚኖሩ ወይንም በነበሩ ክርስቲያኖች እና ከእነርሱ በፊት በነበሩ ክርስቲያኖች መካከል፣እንዲሁም በአንድ ዘመን በሚኖሩ ወይንም በነበሩ ክርስቲያኖች እና ከእነርሱ በኋላ በሚመጡ ክርስቲያኖች መካከል የሃይማኖት አንድነት መኖሩ ነው፡፡ እኛ ከቀደሙ ክርስቲያኖች እና ወደፊት ከሚመጡ ክርስቲያኖች ጋር የሃይማኖት አንድነት ከሌለን «አንዲት ሃይማኖት፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን» ብለን መጥራት አንችልም፡፡

ሊበራሊዝም መጽሐፍ ቅዱስን እያንዳንዱ ሰው በራሱ መንገድ እንደፈለገ እንዲተረጉመው በመፍቀዱ የተነሣ በአንድ ዘመን በሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል የሃይማኖት አንድነት የለም፡፡ በአንድ ዘመን በሚኖሩ ክርስቲያኖች እና ከእነርሱ በፊት በነበሩ፣በኋላም በሚመጡ መካከል ያለውም አንድነት ፈርሷል፡፡

ትክክለኛም ሆነ የተሳሳተ ሃይማኖት የለም ይላሉ

ሊበራሎች «አንድ ሰው ትክክል ነው ብሎ እስካመነበት ድረስ ማንኛውም እምነት ትክክል ነው» ብለው ያስተምራሉ፡፡ ከኤፌሶን ምዕራፍ ሁለት «አንዲት እምነት» ከሚለው ትምህርት በተቃራኒ «የተሳሳተ ሃይማኖት የለም፤ ሁሉም ሃይማኖት እኩል እና ትክክል ነው፡፡ ልዩነቱ የሰዎች አስተሳሰብ ነው» ብለው ያስተምራሉ፡፡ በመሆኑም ልዩ ልዩ አመለካከት ያላቸው አማኞች በአንድ ጊዜ፣ በአንድ ቦታ ፣በጋራ ማምለክ ይችላሉ ብለው ያስባሉ፡፡

ይህ አስተሳሰባቸውም ሰዎች የራሳቸውን ፍልስፍና እንደ ሃይማኖት ትምህርት እየቆጠሩ በየጊዜው እንዲበታተኑ አድርጓቸዋል፡፡ ወደ ትክክለኛዋ መንገድ ከመመለስ ይልቅ ሁላችንም ትክክል ነን በሚል ፍልስፍና በስሕተቱ ጎዳና እንዲበረቱበት ረድቷቸዋል፡፡

የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ወንጌል ብቻ ነው ይላሉ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለማኅበራዊ ኑሮ፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት እና ለእኩልነት መዳበር ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር እንጂ በመሠረተ እምነት/ዶግማ/ ላይ ማተኮሩን ይቃወማሉ፡፡ ለስብከቱ ማራኪነት፣ አስደሳችነት እና ሳቢነት እንጂ ለትምህርቱ ትክክለኛነት አይጨነቁም፡፡ የነገረ ሃይማኖት ጉዳዮችን ማንሣት ሊለያየን ስለሚችል «ከዚህም ከዚያም ያልሆነ አቀራረብ» /neutral approach/ መጠቀም ያስፈልጋል ባዮች ናቸው፡፡ ትምህርታቸው መንፈሳዊ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ፣ ለማዳን ሳይሆን ለማስደሰት፣ እውነቱን ለመመስከር ሳይሆን ሰው እውነት የመሰለውን እንዲመርጥ ለማድረግ የታሰበ ነው፡፡ የዶግማ እና የቀኖና ትምህርት አይሰጡም፡፡

ዛሬ ዛሬ ይህ በሽታ እኛም ውስጥ ገብቶ ነው መሰለኝ ሰባክያን የተባልን ሰዎች ከዶግማ ትምህርት እየወጣን በስብከት ላይ ብቻ ወደማተኮር እየቃጣን ነው፡፡ በትምህርታችን ውስጥ እንኳን መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርትን በተገቢው መንገድ አናቀርብም፡፡ ምእመናንም ይህንኑ ለምደው መሠረታዊ ትምህርት ሲሰጥ እንደ ባከነ ጊዜ ይቆጥሩታል፡፡ በትምህርት አሰጣጣችንም ውስጥ የአበው ትምህርት፣ ትርጓሜ እና ሐተታ እየተረሳ፣ የቅዱሳንም ሕይወት በአስረጅነት መጠቀሱ እየቀረ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን አልባ ክርስትናን ያስፋፋሉ

ሊበራል ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ለድኅነት የግድ አስፈላጊ አይደለችም፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያን መሆን ይቻላል፤ ብለው ያምናሉ፡፡ አንድ ሰው ካመነ ክርስቲያን ለመሆን በቂው ነው፡፡ ስለዚህም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ መጠመቅ፣ መቁ ረብ፣ መማር፣ መዘመር ወዘተ የግድ አያስፈልገውም ብለው ያስተምራሉ፡፡ ፕሮቴስታንቲዝም ሲጀመር «ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከተራ ቤት እኩል ነው» ብሎ ተነሣ፣ ቀጥሎ ደግሞ ሊበራሎቹ «ያም ቢሆን አያስፈልግም» ብለው ደመደሙት፡፡ ውሻ በቀደደው አይደል ድሮስ ጅብ የሚገባው፡፡

በዚህ የተነሣም ብዙ ፕሮቴስታንቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም፣ አይሳተፉምም፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝ ሀገር 10% የሚሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው ቤተ ክርስቲያን እሑድ እሑድ የሚሄዱ፡፡ በስካንዴኒቪያን ሀገሮች ደግሞ ከ2 እስከ 3% ብቻ ይሄዳል፡፡ በአሜሪካ 60% ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም፡፡ ከሚሄዱት ከ40% ብዙዎቹ ማኅበራዊ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የሚሄዱ ናቸው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ዘመን ደግሞ «የኮምፒውተር ቤተ ክርስቲያን» online church የሚባል እየተከፈተ ነው፡፡ ስለዚህም በዳታ ቤዙ ላይ የኃጢአት ዝርዝር አለ፤ የሠሩትን ኃጢአት ከዳታ ቤዙ ውስጥ ገብተው ክሊክ ሲያደርጉ ቅጣቱን ይነግርዎታል፡፡

መዋቅር አልባ እምነትን ያስፋፋሉ

ሊበራሊዝም ማንኛውም ክርስቲያን በፈቀደው መንገድ እንዲያምን ስለሚያስተምር ማናቸውንም ዓይነት የሃይማኖት መዋቅሮች አይቀበልም፡፡ ሃይማኖታዊ መዋቅሮች ይኑሩ ከተባለም በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚመረጡ የቦርድ አባላት የሚመሩ እና ለብዙኃኑ ድምጽ ተገዥ የሆኑ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ በዚህም የተነሣ የክህነትንም ሆነ የአስተዳደር እርከኖችን አይቀበልም፡፡ ጳጳሳት በካህናት ላይ፣ ካህናት በምእመናን ላይ ያላቸውን ሃይማኖታዊ ሥልጣን፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳይ በመወሰን ረገድ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሥልጣን አይቀበልም፡፡

በአሜሪካን ሀገር በ1960 እኤአ መሥመራውያን አብያተ ክርስቲያናት /main line protestants/ ከጠቅላላ ክርስቲያኑ 40% ይሸፍኑ ነበር፡፡ በ40 ዓመታት ውስጥ ግን በሊበራሎች ተነጥቀው ዛሬ 12% ብቻ ናቸው፡፡

ኑፋቄ የሚባል ነገር የለም ይላሉ

ሊበራሎች «የሁሉም ሰው ሃይማኖታዊ አመለካከት ትክክል ነው» ብለው ስለሚያምኑ ኑፋቄ የሚባል ነገር የለም ይላሉ፡፡ እንዲያውም ጥንት የተወገዙ መናፍቃን መብታቸው ተነክቷል ብለውም ያስባሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት የተለዩ የግኖስቲኮች መጻሕፍትን እንደ ገና ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስገባትም ይጥራሉ፡፡ መናፍቃንን በተመለከተ ምናልባት በዚያ ጊዜ የነበሩ አባቶች ተሳስተው ከሆነ ነገሩን እንደ ገና ማየት አለብን የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ የበርናባስ ወንጌል፣ የይሁዳ ወንጌል፣ የማርያም መግደላዊት ወንጌል ወዘተ የተባሉና በግኖስቲኮች የተጻፉ የክህደት መጻሕፍት ዛሬ ዛሬ እንደ አዲስ ግኝት በመቸብቸብ ላይ ናቸው፡፡

መናፍቃንን መናፍቃን ማለተ ሰውን ማራቅ ነው፡፡ ስለ መናፍቃን ማውራት መለያየትን ማባባስ ነው፡፡ ስለ ራሳችን ብቻ እንናገር እንጂ ስለሌሎች አናንሣ፡፡ የሚሉት አመለካከቶች የልዩነቱን ድንበር አፍርሰው ክርስቲያኖች ስንዴውን እና እንክርዳዱን መለየት እንዳይችሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ለአዳዲስ አስተሳሰቦች ክፍት በር ይከፍታሉ

ሊበራሎች ለአዳዲስ አስተሳሰቦች በራችን ክፍት መሆን አለበት፣ አንድ ነገር አሳማኝ እስከሆነ ድረስ ልንቀበለው ይገባል ይላሉ፡፡ ዋናው ነገራቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት መሠረት ሳይሆን ምን ያህል ሕዝቡ ይቀበለዋል? በሚለው መሠረት ነው፡፡ በዚህ የተነሣም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን፣ የሴቶችን ክህነት፣ የእንስሳትን አባልነት ወዘተ በመቀበል ላይ ናቸው፡፡ የሊበራሎች አንዱ መሠረታዊ አስተሳሰብ ዘመኑን በቅዱሳት መጻሕፍት መዋጀት ሳይሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን ለዘመኑ ማመቻቸት ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እና በአባቶች ትምህርት ሳይመረመሩ አዳዲስ አስተሳሰቦች እንዲሁ የሚገቡባት ቤት መሆን አለባት ይላሉ፡፡

ግዴለሽነትን ያስፋፋሉ

ሊበራሎች ለጾም፣ ለጸሎት፣ ለሥነ ምግባር እና ለባሕል ግዴለሾች ናቸው፡፡ ሥርዓታዊ እምነት አይመቻቸውም፡፡ አንድ ሰው ክርስቲያን ለመሆን ከማመን እና ከማወቅ በላይ አያስፈልገውም ስለሚሉ ሌላ ዓይነት ሥርዓተ አምልኮን እንዲፈጽም አይገደድም፡፡ ጋብቻን ማክበር፣ ከሱስ ነጻ መሆን፣ ንጽሕናን መጠበቅ፣ ድንግልናን ማክበር፣ ወዘተ የሰው በጎ ፈቃድ እንጂ የሃይማኖት ትምህርት ናቸው ብለው አይወስዷቸውም፡፡ ስለዚህም አማኞች ትክክለኛ ኑሮ እና የተሳሳተ ኑሮ፣ሥነ ምግባራዊ እና ኢሥነ ምግባራዊ የሚባለውን ለይተው እንዲያውቁ እና እንዲኖሩ አይነገራቸውም፡፡

ሊበራል ክርስትና ምን አመጣ?
               ይቀጥላል
                                                           

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...