መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/
በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት’ የዓለሙ ፍሳሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/’ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲህ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባህል፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክትአንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣
1. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡- ”አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አትፍልስ” ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ሁኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ”እስመ ብዙሃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በኔ ስም ይነሣሉና” /ማቴ. 24፣5/፡፡ ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት፣ ከክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በኋላ የሚመጣ፣ ክርስቶስን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብሎ የማይሰብክ ሁሉ፤ ሌላ አምላክን የሚሰብክ ሁሉ መደቡ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው የተነሡ እንደ ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ሥራ. 5፣36-37/ የመሰሉ ሁሉ ከዚያም በኋላ በየጊዜው የተነሡና በዚህም ወቅት የዋሁን ሕዝብ ”ኢየሱስ ነኝ፣ ኢየሱስ በኛ ዘንድ አለ” እያሉ የሚያጭበረብሩ ሁሉ ሐሳውያነ መሲሖች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ፣ ”ሎቱ ስብሐት” ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት /ቁሳውያን/ ወይም በኢቮሉሽን /በዝግመተ ለውጥ/ ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ ሁሉ፣ ወዘተ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ”ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” /1ዮሐ. 4፣3/ በማለት ይመሰክርባቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም በመልእክቱ ”ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” /1ዮሐ. 2፥18/ ይለናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መሆኑን የማያሻማ ሀሳብ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ የሚያመለክቱ፣ ስለ ሐሳዊው መሲሕ እና ከርሱ ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ተዛማጅ የሆኑትን የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣
ሀ. ”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” /ራእ. ዮሐ. 13፥16-18/ የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይን ሊፈታ ከሚችልበት ትርጉም አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ’የሚናገር የአውሬው ምስል’ ማለትም ለሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል አሁን ባለን ወቅታዊ የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሰለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መንገድ የተደራጀ በመሆኑ፣ እዚያ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር እዚያ ሀገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ እዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ ሰው የትም ዓለም ቢሄድ በጣቱ አሻራ ይታውቃል፡፡ በትንቢቱ” አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” የሚለው ይህን የሚያደራጀው ጉዳዩን የሚያስተሳስረው ሌላ አካል ሳይሆን ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት የሚለው ቁጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡ ለ. ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስሎ የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ባጠቃላይ በሰማይ የሚያድሩትን መስደብ ነው፡፡ እነዚህም ተግባራት በተለያዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው ዛሬም ተጠናክረው እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶ ሤራ ዋናው ተቃውሞው የወልድን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፣ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፣ የቅዱሳንን ክብርና አማላጅነት ነው፡፡ በመሆኑም ተሐድሶ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ ”ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” /ራእ. ዮሐ. 13፣4.8/ እንዲል፡፡ ሐ. ሌላው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብር፣ ዝናና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቁጠር ከሐሳዊው መሲሕ ያስመድባል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናሰተውል የተነሡበት ዋናው ነጥብ ’ስማችንን እናስጠራ’ የሚለው ነበር፡፡” ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።” /ዘፍ. 11፥4/ ነው የሚለን፣ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትናየተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራቸው፣ ሲያደንቃቸው መኖርን ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
2. የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ አንዱ የጊዜው መቃረብ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡እንስሳትና ተክሎችን ለማባዛት የማያደርገው ጥረትና የማዳቀል ዘዴ የለም፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ በመሆኑም ውጤቱ የሰውን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ሕክምናዎች ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሚደረገውም ማበረታታት በሠለጠኑት ዓለም ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ”ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ” /ዘሌ. 19፣ 19፤/ ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው።” /ዘሌ 20፣ 13/ በማለት ያሰተምረናል፡፡
3. በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትን ስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎች ባንድ ላይ እንዳይኖሩ አውሬው /አስማንድዮስ/ የጋብቻ ጠላት በመሆን ስለነገሠ ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና ነው፡፡ ስለዚህ አስማንድዮስ ከዛ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው” ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣” ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” /ሮሜ.1፥24-ፍጻሜ 4. መንፈሳዊ ባህል፣ የክህነት ክብር፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ፣ በሚለው ዙሪያ ስንመለከት በቀላሉ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ያለውን ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ እነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” / 2ጢሞ. 3፥1.7/ በማለት በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ፀባይን ይነግረናል፡፡ ይህንን ትምህርተ ጥቅስ ለማገናዘብ እግዚአብሔርን የማያምነውን ህዝብ ትተን፣ አሁን በዓለም ሁሉ ካለው የቤተ ክርስቲያንዋ አማኞች ብቻ አንጻር በመጠኑ እንይ ደግሞ፤ ሀ. መንፈሳዊ ባህል ማፍረስን ስንመለከት፣ የሁሉንም ባይሆን፣ የአንዳንዶቹ አማኞች ሰዎች ጸባይ ቅ. ጳውሎስ ”ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደሆነ ያስረግጥልናል፡፡ እንደ አማኝ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው ’የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል’ ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት መሆን ነው ያለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙዎቹ በመንፈሳዊው ባህል የጠነከሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ሥራ ፈቶች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ዘረኝነት፣አሉባልታ፣ ወዘተ በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይታያል፡፡ ቅ. ሉቃስ በተመሳሳይ አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን ”አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥” /የሐዋ. ሥራ 17፣ 5/ በማለት እንደገለጸው ያሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ”ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።” ይላቸዋል፡፡ ለ. የክህነት ክብርን ማፍረስ በተመለከተ፣ ቅ. ጳውሎስ ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” እንዳለው ሁሉ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሰጥቷቸው በአንብሮተ እድ እየተሾሙ ሲወርድ መጥቶ ለኛ የደረሰውን ታላቁን የድኅነት መፈጸሚያ ክህነት እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ዛሬ በብዙዎች ተንቆና ተዋርዶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከሚፈጸሙ ስህተቶች ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመለከት፣
ሐ. ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ለሚለው ሌላ ብዙ ከማለት ይልቅ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ”ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ” በማለት የዘረዘረው ለርእሰ ጉዳዩ ተስማሚና በቂ ነው፡፡/1ጢሞ.3፥1-3/ ባጠቃላይም የምጽአት ምልክቶች የሚያሳዩት ሁኔታዎች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከተማረው እስከ መሀይሙ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ያላገባው፣ ያገባው፣ መነኩሴው ሳይቀር ሁሉም ሁሉም ባንድ ላይ ከቅድስና ርቀት፣ ከጥፋት ርኩሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋደሽ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው እንደመሰከሩልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንገት ይመጣል አይዘገይም፡፡ ቅዱስ ዳዊት ”ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።” /መዝ.49፥2-3/ ብሎ እንደተናገረው፡፡ ከላይ እንደተዘረዘረው የሰው ልጆች ሁለ ጊዜ ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ በተጠመዱበት የዓለማዊ ሥራ እንደ ተወጠሩ ነው ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሄዳሉ እንጂ መንፈሳዊ ወደ ሆነው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመጽ እየበረታ እስከ መቅደስ ድፍረቱን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጸዋል፤”ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።” /2ተሰ.2፥3-4/ ይለናል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁሉ የጥፋት ትንቢቱ እኛ ላይ እንዳይፈጸም አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኩሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡ |
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የሚቀርቡ መንፈሳዊ ትምህርቶች ፤መረጃዎች እና የመሳሰሉት የሚስተናገዱበት ገጽ ነው
ቅዳሜ 14 ማርች 2015
ደብረ ዘይት
ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ 24፤44
መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዲ/ን ተመስገን ዘገየ
ይህ ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ለደቀመዛሙርቱ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ሲጠይቁት የተናገረው ኃይለ ቃል ነው፡፡ “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፤ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ፣ ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የዓለም ፍጻሜ ምልክቱስ ምንድን ነው?” አሉት፡፡
ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ 800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ቤተፋጌና ቢታንያም ከግርጌው የሚገኙ መንደሮች ናቸው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውም የተሰጠው በላዩ ከሚበቅሉት (ተራራውን ከሸፈኑት) የወይራ ዛፎች የተነሳ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የመላበት (በብዛት የሚገኝበት) ተራራ ማለት ነውና፡፡
የደብረ ዘይት ተራራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት እንደወጣ በ2ኛ. ሳሙ. 15፤30 “ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ” ይላል፡፡ ይህ ተራራ በሕዝቅኤል ትንቢት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደሚያርፍበት ተነግሮአል፡፡ የእግዚአብሔር ክብርም ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ፡፡ ት.ሕ11.23
ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ ዐደባባይ ደብረ ዘይት 75 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚበሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡ÂÂÂ
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11.1 ላይ “ወአልጺቆሙ ኢየሩሳሌም ኀበ ቤተ ፋጌ ወቢታንያ በኀበ በደብረ ዘይት ፈነወ ክልኤተ እምአርዳኢሁ ፤ወደ ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደ አሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ከደቀ መዘሙርቱ ሁለቱን ላከ” ይላል፡፡ አይሁድም ጌታን የያዙት በደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ በምትገኘው ጌቴሴማኒ ነው፡፡
አንቢቦሙ ወሰቢሖሙ ወጽኡ ወሖሩ ውስተ ደብረ ዘይት ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክሕዱኒ በዛቲ ሌሊት፣ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው፡፡ ማቴ. 26.30
ጌታችንም ሲያስተምር ውሎ ማታ ሔዶ የሚያድረው በደብረ ዘይት ተራራ ውስጥ ባለችው ኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሳዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጡ የገባውም ወደ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ማር 11.1 በዚህ ዓለም የፈጸመውን አገልግሎት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሰማይ ያረገውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ወደፊትም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ላይ መገለጫው ደብረ ዘይት እንደሆነች ተገልጿል፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ቀን ይመጣል ብዝበዛሽንም በውስጥ ይከፍላሉ፡፡ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምን ይወጉአት ዘንድ እሰበስባለሁ ከተማይቱም ትያዛለች ት. ዘካርያስ 14.1
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ በደብረ ዘይት ተራራ) ላይ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በቤተ መቅደስ ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻ ጠየቁት፡፡ እንዲህም አሉት ንገረን ይህ መቼ ይሆናል (ማር 13.3፣ማቴ 24.1-51) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ዘበሰማያት የሚለውን ጸሎት ያስተማረውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ከ62 ሀገሮች በላይ ልሳን(ቋንቋ) በሞዛይክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚዘመርበት፤ የሚሰበክበት ዕለት ስለሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል፡፡ ሰያሚውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ 24.1-36 ነው፡፡
ÂÂÂ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ፡፡ “አማን እብለክሙ ኢይትኀደግ ዝየ እብን ዲበ እብን ዘኢይትነሠት፣ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስና ዳግም መምጣትን አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊ ንጉሥ ፊት ያለ ምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በአሕዛብ ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚህ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል” (ማቴ.24.14) በማለት በስፋት አስተምሮአቸዋል፡፡ እምበለስ አእምሩ አምሳሊሁ፣ ነገሩን በበለስ እወቁ፡፡ የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው የእስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት 11ኛ ምልክት ነው፡፡ ማቴ 24.32
ከዚህ በኋላ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር በደመና ይመጣል፡፡ “ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩላ ዐይን ወእልክቱሂ እለ ወግእዎ ይበክዩ በእንቲአሁ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር እወ አማን፣ እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል ዐይን ሁሉ ታየዋለች የወጉትም ሁሉ ያለቅሳሉ የምድር ወገኖች ሁሉ የኀዘን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፡፡” (ራእይ 1.7)
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ካስጠነቀቀበት ዐቢይ ኃይለ ቃል መካከል ስለ ሐሰተኞች መምህራን መምጣት ነበር፡፡ “እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን” የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ በማለት (በማቴ 24.5) አስጠንቅቋል፡፡ ክርስቲያኖች አሁንም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማል? በማለት እውነተኛ የወንጌል መምህራንን በመምሰል ብዙዎችን እንደሚያሳስቱ ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 7.15 ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 16.17 “ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምንቹሃለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉና” ይላል፡፡
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ “እኛስ ያለማወላወል የደጋግ አባቶችን ሃይማኖት እንይዛለን” (ሃይማኖተ አበው ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያውን እምነታችን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተከፋዮች ሆነናልና፡፡ (ዕብ 3.14) ይላል፡፡ ስለዚህ በጊዜው ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል (2ኛ ጢሞ4.2)
የዓለም መጨረሻውና የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች በማቴ 24.1 በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡
ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ምጽአቶች እንዳሉት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “….በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሥዋት ኃጢአት ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል… አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸውም ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታዩላቸዋል” (ዕብ 9.26-28 ) በማለት ተናግሮአል፡፡ የመጀመሪያው ምጽአቱ ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትህትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ በሚሞት በሚሰደድ በሚዳከም ፤በሚበረታ፤ በሚራብ፤ በሚጠማ ፤ በሚዝል በሚወድቅ በሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) እንደ አንድ ኃጥእ ሞት፣ እስኪፈረድበት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጐ መጣ፡፡ ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሸጋግረን በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ስለ እኛ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመሰቀል ሞት ታዘዘ፡፡ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ተነሳ ወደ ሰማይም በዐርባኛው ቀን አረገ በየማነ አብ ተቀመጠ፡፡ ይህ ነው የመጀመሪያው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳንና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡ ዳግማዊ ምጽአቱ፡- በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪያ ምጽአቱን) ባልተቀበሉት ላይ ሊፈርድ ዐይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል፡፡ “እግዚአብሔርስ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል (መዝ 50.3)
መጥቶም ዝም አይልም (ኤሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደልዋን፤ ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ወዮላቸሁ) እያለ ይወቅሳል ወንጌልንም ያስተምራል፡፡ ጻድቃንን “እናንተ የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ ብሎ ይጠራል ኃጥአንንም እናንተ ርጉማን ሐሩ እምኔየ፤ ከእኔ ወግዱ” ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ በፊቱ እሳት ይነዳል ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መዓት በባሕርዩ አለ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ! የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት?
ጌታችን በደብረ ዘይት ያስተማራቸው ትምህርቶች በመሠረታዊነት በ3 ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡
1. ምልክት፡- በዚያ ዘመን እንዲህ ይሆናል እያለ በፍጻሜ ዘመን የሚከሰቱትን ድርጊቶች፡፡
2. ትእዛዝ፡- በዚያ ዘመን ከጥፋት እንድን ዘንድ የሰጠን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ እያለ ፡፡
3. ማስጠንቀቂያ በፍጻሜ ዘመን እንዲህ ሁናችሁ የተገኛችሁ “ወዬላችሁ” እያለ የተናገራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ “ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” የሚለው እርጉዝ ማለት የኃጢአት ዐሳብ የጸነሱት ሲሆኑ የሚያጠቡ ያላቸው ኃጢአትን ጸንሰው በንግግር የወለዱትን ነው”ÂÂ
በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ (ማቴ 24.16) በዚህ ቃል መሠረት በይሁዳ በዓለም ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ ተብሏል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ትሩፋት እየሠሩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ ይሽሹ ነው፡፡ÂÂ
ለመሆኑ ተራራ ምንድን ነው?
1. ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው “መዝ. 124.2 ይላል፡፡ በዚህ ቃል የእግዚአብሔር ረድኤት በተራራ ተመስሎ ቀርቧል፡፡ ምክንያቱም ተራራ እንደሚከልል እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይከልላልና፡፡ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡ 2. ተራራ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
3. ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች “አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፣ በጽዮን በደብረ መቅደሱ ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጽዮን ላይ ” መዝ.2.6 ስለዚህ ትውልድ ድንግል ማርያምን ዓምባ መጠጊያ ያደርግ ማለት ነው፡፡
4. ተራራ የተባሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው፡፡ መዝ.86.1 መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን ፤መሠረቶቿ በቅዱሱ ተራሮች ናቸው” ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ወደ ቅዱሳን አባቶቻችን ቅረቡ በአማላጅነት ሥልጣናቸው አምናችሁ ተማጸኗቸው ሲል ነው፡፡
በሰገነት ያለውም በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ ይላል (ማቴ 24.17) ሰገነት ከፍ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቃል በሠገነት የተመሠለ በምግባር በሃይማኖት የበረታ የወጣትነት ዘመን አልፎ ከማዕከላዊነት የደረሰ ማለት ሲሆን፤ በዝቅታ የተመሠለ ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ የነፍስ ተዋርዶ ነው፡፡ÂÂÂ
ዴማስና ይሁዳ በሰገነት ነበሩ በኋላ ግን በዝቅታ ሥፍራ ተገኙ፡፡ መዋል በማይገባቸው ቦታ ውለው ተገኙ፡፡ በክርስትና ከፍ ከፍ ብለው በመንፈሳዊነት መጽናት አቃታቸው፡፡ እኛስ ከየትኛው ስፍራ እንሆን?
በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላ አይመለስ (ማቴ24.18) በእርሻ የተመሰለ የመነነ ወይም በምንኩስና ሕይወት ያለ ማለት ነው፡፡ በእርሻ ያለ አይመለስ ማለት በምነና በምንኩስና ያለ ይህንን ሕይወት የጀመረ አይመለስ፡፡ ስለዚህ ስደታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ አለ (ማቴ 24 .20) ክረምት የፍሬ የአጨዳ ሳይሆን የሥራ የመዝሪያ ወቅት ነው፡፡ ሰንበትም የዕረፍት ቀን ናት፤ በሠንበት ሥጋዊ ሥራ አይሠራም፡፡ አንድም በክረምት ቅጠል ካልሆነ ፍሬ አይገኝም እናንተም ሃይማኖት ይዛችሁ ምግባር ከሌላችሁ ዋጋ የላችሁም ማለቱ ነው፡፡
ሽሽት የተባለ ዕለተ ምጽአት ሲሆን በሽሽት የተመሰለው ሞት ድንገት እንደሚመጣ ዕለተ ምጽአትም በድንገት ስለሚሆን ነው፡፡ ትርጉሙ ንስሓችሁን ሳትጨርሱ የንስሐ ፍሬ ሳታፈሩ በድንገት ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ጸልዩ የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ሲኖር “ድልዋኒክሙንበሩ፤ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ማቴ 24:24 በተባለው አማናዊ ቃል መሠረት ራሱን በንስሓ አዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ÂÂÂ
|
ረቡዕ 11 ማርች 2015
እረፍቱ ለአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ
Written By Hulubante Abebe
“የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።”
መጋቢት 5 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞች ዘንድ የፃድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል ።
በዚህ እለት እምናከብረው የእረፍት መታሰቢያቸውን ሲሆን ከገድላቸውም እንዲህ ተፅፎ እናገኘዋለን ።
ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ግብፅ ንሂሳ በምትባል ቦታ ከአባታቸው ስምዖን ከእናታው አቅሌስያ ነው። በአጠቃላይ የኖሩበት ዕድሜ 562 አመት ሲሆን 300 ዓመቱን በግብጽ 262 ቱን በኢትዮጵያ 100 ዓመት በዝቋላ በተጋድሎ ያሳለፉ ታላቅ አባት ናቸው።ኢትዮጵም የአስራት ሐገራቸው ሆና በቃልኪዳን ተሰጣቸዋለች። እናታቸው ሳትታቀፋቸው ወተት ሳይጠጡ በመንፈስ ቅዱስ አድገው በ፫ ዓመታቸው ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ እስከ ሰባቱ ሰማያት አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረበው፤ ባረከውም፤ ድንግል ማርያም ጻድቃን ሰማዕታት ወዳሉበት ተወስዶ ተባርኮ በጌታችን ቃል ተቀብሎ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳሉበት አውርዶ በዚያም አድጎ መንፈሳዊ ሥራን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተጋድሎውን ጀምሯል። በበረሃ ሲኖሩ 60 አንበሳና ነብር የተሰጣቸው ሲሆን አንበሳ እና ነምሮቹም የሚበሉትም የቅዱሱን እግር ያረፈበትን ቦታ በመላስ ነው። የአባታችን ገድል እንደሚያስረዳው እንደ ሰው ልብስ ለብሰው ሳይሆን ልብሳቸው በጸጋ የተሰጣቸው ጠጉር ነበር እሱም ልክ እንደ ልብስ ያገለግላቸው ነበር።
ከሚያስገርመው ገድላቸው ውስጥ አባታችንን ለመጠየቅ የመጡት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር መጥተው እንግዶቹን አንበሶቹ በልተው አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ መምጣታቸውን አውቆ ሲነግሯቸው ለምን ያልተፈቀደላችሁን በላችሁ ብለው የበሉትን አንበሶች የበላችሁትን አንድም ሳታስቀሩ ትፉ ብሏቸው ወደ እግዚአብሔር ጸልየው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሱ ባሉ ጊዜ የተበሉት ነፍስ ዘርተው እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባም በሰላም ወደ ባእታቸው በአባታችን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸሎት በሠላም ገብተዋል።
መጋቢት 5 በገድለ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ
ዕለቱ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ህመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግን አልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚያብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት
ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አለው፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው፤ ከመጋቢት አምስት ቀን ጀምሮ ዝክርህን ያድርጉ በአማላጅነትህም ይማጸኑ አለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዱ በእየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በዛሬዋ ቀን ሩጫውን ጨረሰ። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።
የአባቶችን የቅዱሳንን ታሪክ እንድናውቅ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከነርሱ ገድል ተምረን እኛም ወደአምላክ መንገድ እንድንቀርብብበት ነውና አምላከ ገ/መንፈስ ቅዱስ መንገዱን ያብራልን ። ገድሉንም ሰሚወች ብቻ ሳንሆን እምንማርበት ያድርግልን ።
መጋቢት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ /አባ ገብረ ሕይወት/ 2.ቅዱስ አባ ሰረባሞን /በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ/ 3.አባ ግርማኖስ ጻድቅ /ሶርያዊ/ 4.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት /ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት/
5.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ /የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች/
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ማክሰኞ 10 ማርች 2015
እየደመሰሱ መቅዳት
ለረዥም ዓመታት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ
የሠራ ጋዜጠኛ ለአንድ ጥናት ወደ ጣቢያው ይሄዳል፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት እርሱ ራሱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር፡፡ ቃለ መጠይቁ
የተደረገላት ሴት አሁን በሕይወት የለቺም፡፡ ለዚህ ነበር እርሷ የሰጠቺውን ቃል ፍለጋ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሄደው፡፡ ያገኘው ግን
የጠበቀውን አልነበረም፡፡ የተቀዳው ቃለ መጠይቅ የለም፡፡ ምነው? አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ብዙ ካሴቶችን እየደመሰስን ቀድተንባቸዋል፡፡
በዚያ ምክንያት ያንን ቃለ መጠይቅ አሁን አታገኘውም›› አሉት፡፡ እርሱም በዚህ አዝኖ ወጣ፡፡
ለነገሩ እርሱ በካሴቱ አዘነ እንጂ
ከኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫዎች አንዱ እየደመሰሱ መቅዳት ነው፡፡ የሚመጣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን፣ ዐዋቂ ወይም ታዋቂ፣ ታሪክ ጸሐፊ
ወይም ዐቅድ ነዳፊ ከእርሱ በፊት ለነበረው ነገር ዋጋ ሰጥቶ፣ የየራሱን ሥራ ከመሥራትና የዘመኑን አሻራ ከማኖር ይልቅ ያለፈውን መደምሰስ ይቀናዋል፡፡
ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለ
ቆየ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡ የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም አሣምሮ የሚጨምር
ከሆነ ሀገር እያደገች፣ እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን
ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡
ባቢሎን
በታሪክ ቀድመው ከሠለጠኑ ሀገሮች ተርታ ነበረቺ፡፡ ነገር ግን የገዛት ሁሉ ከመሠረቷ እያፈረሰ እንደገና ሲሠራት፣ የመጣዉ ሁሉ እየደመሰሰ
ሲቀዳባት ይሄው ዛሬም አላልፍላት ብሎ የጦር አውድማ ሆናለቺ፡፡ ስለ ኢራቅ ጥንታዊ ታሪክ የሚተረከውና የዛሬዋ ኢራቅ አይጣጣሙም፡፡
የመጡት ሁሉ በባቢሎን ካሴት ላይ እየደመሰሱ ሲቀዱ፣ መሠረት አልባ ጣራ ሊያቆመ ሲደክሙ፣ አሁን የመጡባት አሸባሪዎች ደግሞ ጨርሰው
ታሪካዊ ቅርሶቿን በድጅኖ መናድ ጀመሩ፡፡ እየደመሰሱ መቅዳት ካንሰር መሆን ሲጀምር ይሄው ነው፡፡
ይኼ እፉኝታዊ ጠባይ ነው፡፡ እፉኝት የምትባል የእባብ ዘር አለች አሉ፡፡
አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ነው፡፡ ከወንዱ ጋር ስትገናኝ የወንዱን አባለ ዘር ትቆርጠውና ወንዱ ይሞታል፡፡ ልጆቿን በማኅፀኗ ፈልፍላ ስትወልዳቸው
ደግሞ ለመውጣት ስለማይችሉ ሆዷን እየቀደዱ እናታቸውን ገድለዋት ይወጣሉ፡፡ ልጆቹ ልጅ የሚሆኑት አባትና እናታቸውን ገድለው ነው፡፡
ያለፈውን ካልደመሰሱ መኖር አይችሉም፡፡
የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን
እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር
አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡
ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን
ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡
አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡፡
ቅቤን ማንም አያነጥረውም፤ ባለሞያ ይጠይቃል፡፡ አንጉላውን የማስወገጃ
መንገዱ ራሱ ልዩ ሞያ ጠያቂ ነው፡፡አንጉላ መስሎን ቅቤዉን ጭምር እንዳያስወግደው እንደ ዶሮ ላባ ባለ ስስ ነገር እየለዩ ማንጠርን
ይጠይቃል፡፡
ታሪካችንንና ባሕላችንን፣ ወጋችንንና ልማዳችንን ስንመረምርና አንጉላውን
ስንለይ፣ እንደ ቅቤ አንጣሪው በሞያ መሆን አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ሊያገኝ አይገባም፡፡ ቅቤ አንጣሪ ስሜት ውስጥ ከገባ ምች ይመታዋልና፡፡
አረሙን እንነቅላለን ብለን ስንዴውን ጨምረን እንዳንነቅለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ብለን የምንሠራቸው
ሥራዎች አዙሪት ውስጥ እንዳይጥሉን ጉዳዩን የሞያና የዕውቀት ጉዳይ ማድረግ ይገባናል፡፡ ‹ዕውቀት አጠር፣ ስሜት መር› ከሆነው ጉዟችን
ይልቅ ‹ዕውቀት መር፣ ስሜት አጠር› ወደሆነው ሥልጣኔ ካልወጣን በስተቀር እዚያው ጨለማው ውስጥ ስንኳትን እንኖራለን፡፡
ቅቤ አንጣሪ ሰው ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ያስፈልገዋል፡፡ ምች እንዳይመታው፡፡
የቅቤ ምች ያጠናግራል ይባላል፡፡ ቅቤውን በጥንቃቄ ያነጠረቺ ባለሞያ ናት ‹‹ቅቤ አንጣሪዋ እያለቺ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት›
ብላ የተሳለቀቺው፡፡ ነባሩን ነገራችንን ስናነጥር ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ወሳኝ ነው፡፡ የዘመን ምች መትቶ እንዳያጠናግረን፡፡
ጎጠኛነት፣ የፖለቲካ ፍጆታ፣ የሥልጣን ፍቅርና ጊዜያዊ ጥቅም የሚባሉ ምቾች አደገኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ምቾች የመቱት ሰው ቅቤውን
በሚገባ ማንጠር ቀርቶ ሌላ በሽታ በራሱ ላይ ይጨምራል፡፡ ጤነኛ የነበረው አንጣሪ ተጣሞ፣ ዓይኑ ጠፍቶ፣ ፊቱ ቆሳስሎ ይወጣል፡፡
ከዚያ በኋላ እርሱ ያለፈው ታሪኩን ሁሉ የሚያየው በማንጠሪያ ዓይኑ ሳይሆን በተጠናገረ ዓይኑ ነው፡፡
አሁን በደምስሶ መቅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩት ብዙዎቹ ወገኖቻችን ምች
የመታቸው ናቸው፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን ምች ስለ መታው ቅቤውንና አንጉላውን መለየት አልቻሉም፡፡ አንጉላ መስሏቸው ሁሉንም ነባር ቅቤ
ሊያስወግዱ የቋመጡ ናቸው፡፡ የዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ
አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡
ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡
አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡
ሰው በአንድ ቦታ ስለተሰበሰበ ብቻ ሀገር አይሆንም፡፡ እንዲያ ቢሆን
ኖሮ እሥራኤላውያን አሜሪካና ፖላንድ መኖር ይበቃቸው ነበር፤ ለፍልስጤማውያንም ዮርዳኖስና ሊባኖስ የሚኖሩት የካምፕ ኑሮ በቂ ነበር፡፡
ሰፊ መሬት ብቻውንም ሀገርን አይመሠርትም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ
ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ሀገር ግን ከሰውም ከመሬትም በላይ ናት፡፡ ሰው በመሬቱ ላይ ሲኖር የሠራው ታሪክ፣ ያካበተው ባሕል፣ የደነገገው
ወግና ሥርዓት፣ ያዳበረው ቋንቋ፣ ያመጣው ለውጥ፣ የፈጠረው ዘዴ፣ የገነባው ሥነ ልቡና፣ የተከተለው እምነት፣ የእርስ በርሱ መስተጋብር፣
ዓለምን የሚያይበት ርእዮተ ዓለም፣ ሥነ ቃሉ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም ተዋሕደው የሚፈጥሩት ነገር ነው - ሀገር፡፡
እነዚህን የተሠራንባቸውን ነገሮች ነው ማንጠር የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ
እንሰብስባቸው፣ እንመዝግባቸው፣ እንለያቸው፣እንዘግባቸው፣ እንቀርሳቸው፣ እንወቃቸው፡፡ ከዚያ እናጥናቸው፣ እንመርምራቸው፡፡ በመጨረሻም
እናንጥራቸው፡፡ ገመዱ ውስብስብ ነው፡፡ ለዘመናት የተፈተለና የተገመደ፡፡ ርጋታ፣ ትዕግሥትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ወስነን አይደለም
ማወቅ ያለብን ዐውቀን ነው መወሰን እንጂ፡፡ አንዳንዴ መጀመሪያ እንወስናለን፣ ከዚያ እንሰይማለን፣ ቀጥለንም እንፈርጃለን፣ በመጨረሻም
እንመታለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ዕውቀት፣ ጥናትና ማንጠር ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ ‹ስቅሎ ስቅሎ› ነው፡፡
‹ትዕዛዝ ከበላይ፣ እግር ወደላይ› ይሆናል መመሪያው፡፡
በዚህ መንገድ ስንቱን እየደመሰስን ቀዳን፡፡ ስንቱን ነባር ዕውቀት
ሳንጠቀምበት እንደ ገናሌ ወንዝ ፈስሶ ፈስሶ ቀረ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን
የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ
ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡
በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር
አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡
የኢሬቻ በዓል በደብረ ዝቋላ እንደሚከበር የተላለፈው ዘገባ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ተወሰነ
- ለአፈጻጸሙ የወረዳው እና የዞኑ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሓላፊነት ወስደዋል
- ከመጋቢት ፭ ክብረ በዓል በፊት ማስተባበያው እንዲተላለፍ ከስምምነት ተደርሷል
- ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ የችግሩን ቆስቋሾች ያጣራል
- በክብረ በዓሉ ቀን የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል
* * *
- ‹‹ለእኛ ዐዲስ ነገር ነው፤ እዚኽ ቦታ ኢሬቻ የለም፤ በአራት ወይም በስምንት ዓመት አንዴ ዝናም እምቢ እንዳይለን ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዐት ውጭ በተነገረው መልኩ የሚከበር በዓል የለም፡፡ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡››
/የአባ ገዳ ተወካዮች/
- ‹‹ኅብረተሰቡን ከእኛ ጋራ ሊያጣሉ የሚፈልጉ ግለሰብ አመራሮች አሉ፡፡… ለተላለፈው መልእክት ሓላፊነት የሚወስድ አካል ካልተገኘ፣ የመጋቢት ፭ ክብረ በዓል ከመድረሱ በፊት በስሕተት የተላለፈ መኾኑ ይገለጽልን፡፡››
/የገዳሙ አስተዳደር/
- ‹‹እናንተ ሰላም ፍጠሩ፤ [በክብረ በዓሉ] ከተለመደው ውጭ አንዳችም የሚደረግ አይኖርም፤ ጥበቃውም እንዲጠናከር ይደረጋል፤ የተላለፈውን ዘገባ አጣርተን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፡፡››
/የዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ሓላፊዎች/
ሐሙስ 5 ማርች 2015
በዝቋላ ገዳም ዙሪያ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ እየተዛመተ ነው
- የሄሊኮፕተር እገዛ አልያም የውኃ ቦቴ መኪኖች ድጋፍ እየተጠየቀ ነው
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ትላንት ጠዋት የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ አሞራ ገደልበሚባለው አቅጣጫ መዛመቱ ተገለጸ፡፡
በሰሜን በኩል ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው የገዳሙ መውጫ ትላንት ጠዋት 2፡00 የተቀሰቀሰው ቃጠሎ፣ በአዱላላ ወረዳ ሠራተኞችና በነዋሪው ሕዝብ ርብርብ ማምሻውን መጥፋቱ ከተገለጸ በኋላ ነው አሞራ ገደል በሚባለው የገዳሙ ደቡባዊ ገጽ በዛሬው ዕለት 5፡00 ላይ ዳግመኛ መቀስቀሱ የተሰማው፡፡
በገዳማውያኑ የጥሩንባ ልፈፋ በተሰባሰበው የገጠሩ ነዋሪና የወረዳው አስተዳደር ሠራተኞች እሳቱን አፈር በማልበስና በቅጠል በመተምተም ለማጥፋት የተቻለ ቢመስልም አንድ የገዳሙ መነኰስ በስልክ እንዳስረዱት፣ ‹‹በደንብ ሳይጠፋ ቀርቶ የታፈነ ነበር፡፡ ዛሬ አሞራ ገደል ጫካ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዛፉ እርጥበት አለው፤ ጢሱ ያፍናል፡፡››
ቃጠሎው፣ በአካባቢው ከባድ ነፋስ እየበረታ ከገደሉ ሽቅብና ወደ ጎን ወደ አዱላላ አቅጣጫ የተወሰነ የደኑን ክፍልና እዳሪ መሬት እየበላ በአስጊ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ አኹን ባለው አካሔድ ሳይገታ ወደ ምሥራቅ ከዞረና ጠበል ሜዳውን ካገኘ ወደ ደኑ በጥልቀት ስለሚገባ በእጅጉ አውዳሚ እንደሚኾን የገዳሙ መነኰስ ተናግረዋል፡፡
ከቦታው ገደላማ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንጻር የሚያፍነው ጢስና የቃጠሎው ፍጥነት የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት የገዳሙ መነኰስ፣ አመቺ የሚኾነው አስቸጋሪውን ዐቀበት በመውጣት ለሰው ኃይሉ ውኃ ማቅረብ በሚችሉ መኪኖች አልያም በአየር ርጭትበመኾኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል የሄሊኮፕተር አልያም የቦቴ መኪኖች እገዛ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲጠየቅ አመልክተዋል፡፡
የትላንቱን ቃጠሎ ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ከደብረ ዘይት ከተማ ተጉዘው ሌሊቱን ቃጠሎው በጀመረበት ስፍራው የደረሱ ምእመናንየእሳቱን መስፋፋት የሚገቱ የመከላከል ሥራዎችን ሲሠሩ አድረው መመለሳቸው ተገልጧል፡፡ የከተማው ሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን የወረዳው ማእከል አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲኹም ምእመናን÷ መሬቱን ቆፍሮ በአፈር የመከተር፣ ተቀጣጣይ ጉቶዎችንና ቁጥቋጦዎችን የመመንጠር የመከላከል ሥራ እስከ ንጋት ድረስ ሲሠራ ማደሩ ታውቋል፡፡
ዛሬ ቀትር ላይ መዛመቱ የታወቀውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከገዳማውያኑ የድረሱልን ጥሪ መተላለፉን የገለጸ አንድ ምእመን፣ በከተማው በስምንቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችና በሠርክ ጉባኤያት ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በመቅስቀስና በማስተባበር በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ለመድረስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የገዳሙ መነኰሳት እየተናገሩ ነው፡፡
ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው የጀመረው ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው በገዳሙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ነው፡፡
ይህ አቅጣጫ፣ የገዳሙ ሞፈር ቤት የሚገኝበት መውጫ መንገድ ሲኾን በአኹኑ ሰዓት በበርካታ ቦታዎች ጭስ እንደሚታይ በመነኰሳቱ ተገልጧል፡፡
የቃጠሎው መንሥኤ በውል ባይታወቅም እሳቱ በአካባቢው ባለው ከባድ የነፋስ ኃይል ወደ ገዳሙ መውጫና በገዳሙ ዙሪያ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል፡፡
የአቅራቢያው ነዋሪ ኅብረተሰብ በጥሩንባ በተላለፈው የድረሱልን ጥሪ የተሰባሰበ ሲኾን ወደ ወረዳው ጽ/ቤትም ተደውሎ የአስተዳደሩ አባሎችና የፖሊስ ኃይል በስፍራው መድረሳቸው ተገልጧል፡፡ ‹‹ቃጠሎውን በቅጠልና በአፈር ለመከላከልና መዛመቱን ለመቀነስ የነፋሱን ጋብ ማለት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፤›› አንድ የገዳሙ መነኰስ፡፡
በጥንታዊውና ታሪካዊው ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ ሲደርስ የአኹኑ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እንደ አርዘ ሊባኖስና የሐበሻ ጥድ ያሉት አገር በቀል ዛፎች በስፋት ወድመዋል፡፡ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ደግሞ ተኣምራዊና ግራ አጋቢ ጠባይዕ የታየበት ነበር፡፡ በምሥራቃዊ አቅጣጫ በሚገኘው የመንግሥት ደን ውስጥ ተከሥቶ በአንድ ገጽ ኃይሉ ሲቀንስ በሌላ አቅጣጫ እየተዛመተ ገዳሙን ጨርሶ ለማጥፋት በተቃረበበት ኹኔታ ከአዲስ አበባ፣ ከቢሾፍቱና ከአዳማ በተመሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና አካላት መተባበር እንዲኹም በመከላከያና በፖሊስ ኃይሎች እገዛ መገታቱ የሚታወስ ነው፡፡
በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በገዳሙ የጠበል – ሐይቅ የኢሬቻን በዓል ለማክበርና በደብረ ዝቋላ የአባ ገዳ ሐውልት ለመትከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታቀዱንና በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ መገለጹን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር በጻፈችው ደብዳቤ ተቃውሞዋን በማሰማት ላይ እንዳለች ይታወቃል፡፡ጥንታዊውና ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በገዳሙ ደጅ ጠኚውን፣ አፈር ጠባቂውንና የአብነት ትምህርት መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ሳይጨምር እስከ 350 መነኰሳትና መነኰሳዪያት እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡
ሰበር ዜና:- በዝቋላ ገዳም ዳግም የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ
የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ደን ላይ በዛሬው እለት የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን ከገዳሙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ከተራራው ሥር ከወንበር ማርያም እና አዱላላ አቅጣጫ የተነሳው ቃጠሎ በገዳሙ ደን ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ ማኅበረ መነኮሳቱና ተማሪዎች፤ እንዲሁም የአካባቢው ምእመናንን ባደረጉት ርብርብ ለጊዜው አፈር በማልበስ ለማጥፋት ተችሏል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ካለው ነፋሻማና ሞቃታማ አየር ምክንያት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ገዳማውያኑ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረ ማርያም ገልጸዋል፡፡ |
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
ልጥፎች (Atom)
በአውሮጳ የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ የተውጣጡ ካህናት፡” የ...
-
June 1, 2015 ከሐራ ዘተዋሕዶ በሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ዕድገት ፊት ከተጋረጡትና አፋጣኝ እልባት ከ...
-
‹‹…ወንድማችንን እናውቃቸዋለን፤ በእውነቱ ለፌ ወለፌ የማይሉ ደረቅ ሊቅ ናቸው፤ በሃይማኖቱ ዘርፍ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንዲቱም ነጥብ እንዳትዛባ...