2016 ሴፕቴምበር 28, ረቡዕ

ካህናት በደመራ ላይ
  በፊንላንድ ሄልሲንኪ ለመጀመሪያ ጊዜ የመስቀል ደመራ በዓል በአደባባይ ተከበረ                                                                 ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት  ቤተክርስቲያን ለመጀምሪያ ጊዜ በአደባባይ የመስቀል ደመራ በዓል መስከረም 16. 2009 ዓ.ም ተከበረ::በዕለቱ የሄልሲንኪ ደብረ ሰላመ መድኃኔ ዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ካህናት ዲያቆናት ምእመናን ከከተማው አስተዳደር ጀምሮ የባህል እና የሌሎችም ተቋማት ሓላፊዎች ጋዜጠኖች በቦታው ተገኝተዋል የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  እና የሌሎቹም ቤተ እምነት መሪዎች ታድመዋል  በሃገራችንም እንደተለመደው በዓበይት በዓላት ብቻ የሚገኙ ምእመናን በዚሁ በስደት ሀገር መኖራቸው የሚገርም ቢሆንም  ያን ዕለት  ተገኝተዋል በተለይ በስደት ያለ ሰው በጣም የሚከፋው ለጥምቀትና  ለመስቀል ደመራ በዓል ጊዜ ነው ይባላል ሁለቱም የአደባባይ በዓላት ናቸው  ያን ዕለት እቤቱ የሚቀር ሰው የለም በሀገር ቤት  ሄልሲንኪም  ያ ትዝ አለኝ ይህ ሁሉ ሰው ነበረ ከሚለው ጥያቄ ጋር የሚገርመው የፈረንጆቹ ደስታ ከ ሐበሻው ቢበልጥ እንጂ አያንስም  ነበረ  ከልብ የመነጨ ልዩ ደስታ ከፊታቸው ይነበባል  አንዳንዶቹም በሀገራችን እንዲህ ያለ ሃይማኖትና ሥርዓትና ሃይማኖት በመኖሩ መደሰታቸውን በመግለጥ  እስካሁን በፊንላንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይምኖት ቤተ ክርስቲያን ያለች ሲሆን   በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ከተመሠረተች  አምስት ዓመታት ያህል አስቆጥራለች የሄልሲንኪ ደብረ ሰላመ መድኃኔ ዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በዚሁ ከተማ ይገኛል የካህናቱና       የምእመናኑ ፍቅር የተለየ ነው ያዝልቅልን እንጂ  የደመራውንም በዓልም በደስታ በጋራ  ማክበራችን  በፈረንጆች ዘንድ ልዩ ትዝታን ፈጥሯል

                       ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ ለሚቀጥለው ዓመት  ጸልዩ
  በፊንላንድ ሄልሲንኪ ለመጀመሪያ ጊዜ የመስቀል ደመራ በዓል በአደባባይ ተከበረ   ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት  ቤተክርስቲያን ለመጀምሪያ ጊዜ በአደባባይ የመስቀል ደመራ በዓል መስከረም 16. 2009 ዓ.ም ተከበረ::በዕለቱ የሄልሲንኪ ደብረ ሰላመ መድኃኔ ዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ካህናት ዲያቆናት ምእመናን ከከተማው አስተዳደር ጀምሮ የባህል እና የሌሎችም ተቋማት ሓላፊዎች ጋዜጠኖች በቦታው ተገኝተዋል የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  እና የሌሎቹም ቤተ እምነት መሪዎች ታድመዋል  በሃገራችንም እንደተለመደው በዓበይት በዓላት ብቻ የሚገኙ ምእመናን በዚሁ በስደት ሀገር መኖራቸው የሚገርም ቢሆንም  ያን ዕለት  ተገኝተዋል በተለይ በስደት ያለ ሰው በጣም የሚከፋው ለጥምቀትና  ለመስቀል ደመራ በዓል ጊዜ ነው ይባላል ሁለቱም የአደባባይ በዓላት ናቸው  ያን ዕለት እቤቱ የሚቀር ሰው የለም በሀገር ቤት  ሄልሲንኪም  ያ ትዝ አለኝ ይህ ሁሉ ሰው ነበረ ከሚለው ጥያቄ ጋር የሚገርመው የፈረንጆቹ ደስታ ከ ሐበሻው ቢበልጥ እንጂ አያንስም  ነበረ  ከልብ የመነጨ ልዩ ደስታ ከፊታቸው ይነበባል  አንዳንዶቹም በሀገራችን እንዲህ ያለ ሃይማኖትና ሥርዓትና ሃይማኖት በመኖሩ መደሰታቸውን በመግለጥ  እስካሁን በፊንላንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይምኖት ቤተ ክርስቲያን ያለች ሲሆን   በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ከተመሠረተች  አምስት ዓመታት ያህል አስቆጥራለች የሄልሲንኪ ደብረ ሰላመ መድኃኔ ዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በዚሁ ከተማ ይገኛል የካህናቱና       የምእመናኑ ፍቅር የተለየ ነው ያዝልቅልን እንጂ  የደመራውንም በዓልም በደስታ በጋራ  ማክበራችን  በፈረንጆች ዘንድ ልዩ ትዝታን ፈጥሯል

                       ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ ለሚቀጥለው ዓመት  ጸልዩ

2016 ሴፕቴምበር 23, ዓርብ

 የመስቀል ደመራ በዓል ለመጀምሪያ ጊዜ በፊንላንድ ሄልሲንኪ  በአደባባይ  እንደሚከበር ተገለጸ

ፊንላንድ በሰሜን አውሮፓ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት 5.5 ሚሊየን ሕዝብ እንድሚኖርባት የሚነገርላት ፊንላንድ ወደ ሰሜን ዋልታ ጠጋ ያለች ሀገር በመሆኗ በቅዝቃዜዋም ትታወቃለች  ነዋሪዎቿ በሥነ ምግባራቸውና  በዝምታቸው ይታወቃሉ። ረዘም ያለ ጊዜ በሀገሪቷ የቆዩ የውጪ ዜጎችም ይህንኑ ጠባይ ይጋሩታል   በሃይማኖት በኩል ሲታይ በሀገሪቱ 2 % ያህሉ የፊንላንድ ኦርቶዶክስ  ሃይማኖት ተከታይ ሲሆኑ የቀሩት በአብዛኛው ሉተራውያን  ናቸው  የውጪ ዜጎች ሁሉም  አኃት አቢያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም ክፍተኛ እንቅስቃሴ ያላቸው  ግን  የኢትዮጵያና እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው   በፊንላንድ ዋና ከተማ  ሄሊሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እና የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም  የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቢያተ ክርስቲያናት  ይገኛሉ ። ሁለቱም አድባራት መንፈሳዊ እና ምኅበራዊ አገልግሎቶችን በጋራ ይፈጽማሉ ። በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ  በ2009 ዓ.ም መስከረም 16 ቀን በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር  ከ 1730  ጀምሮ እንደ ሀገራችን ሁሉ በአደባባይ / መስቀል አደባባይ / ይከበራል  የፊንላንደ ኦርቶዶክስ የከተማው ከንቲባ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መጋበዛቸው ተገልጧል በአሁን ሰዓት ምእመናኑ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ ምንም በስደት ሀገር ብንኖርም  ልክ እንደ ሀገራችን ሕዝቡ የሀገር ባህል ልብሱን ለብሶ ሕፃናትም ሁሉ ተሰልፈው በዝማሬ የደመራው ሥነ ሥረዓት  በልዩ  ሁኔታ እንደሚከበር  ይጠበቃል ።                                                       እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ

2016 ማርች 7, ሰኞ

የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት


በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 28 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፤- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ይህ ትምህርት የተወሰደው የተወደደ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በ388 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ጀምሮት በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ እየተረጎመ ከጨረሰው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህን ትምህርት ይከታተሉ የነበሩትን ምእመናን ከሊቁ አጠቃላይ ንግግር አንጻር ስናያቸውም የቤት እመቤቶችና በተለያየ የሙያ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ሲኾኑ የሚማሩትም በዐቢይ ጾም ምንም እኽል ሳይቀምሱ ነው፡፡   
(1) የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በልጆቿ ስትደምቅእናንተም ጉባኤውን ለመታደም ደስ ብሏችሁ ተሰባስባችሁ ስትመጡ ዐይቼሐሴት አደረግሁኝ፤ ደስም አለኝ፡፡ ፊታችሁ እንዴት በደስታ እንደ ተመላስመለከት ጠቢቡ “ልብ ደስ ሲለው ፊት ይበራል” እንዳለው ልባችሁ ምን ያህልእንደ ተደሰተ ተገነዘብሁኝ /ምሳ.1513/፡፡ በመኾኑም፥ ዛሬ ማለዳ የተነሣሁት ከወትሮው በተለየ ትጋት ነው፡፡ ይኸውም ይህን መንፈሳዊ ደስታ ከእናንተ ጋርእንድካፈልና ቀጣዩ ወራት ቁስለ ነፍሳችሁ ድኅነት የሚያገኝበት ወርሐ ጾመኾኑን አበሥራችሁ ዘንድ ነው፡፡ የኹላችንም ጌታ ልዑል እግዚአብሔር፥ ልክእንደ ደግ አባት ባለፉት ወራት ለሠራነው ኃጢአት ሥርየት እናገኝበት ዘንድ ሽቶመድኃኒት የሚኾን ቅዱስ ጾምን አዘጋጅቶልናልና፡፡

(2) ስለዚህ የነፍሳችን ጠባቂ (እግዚአብሔር) የሕመማችንን ፈውስየምናገኝበትን መድኃኒት ስላዘጋጀልን እያመሰገንን ወርሐ ጾሙን ደስ ብሎንልንቀበለው ይገባናል፡፡ ከእኛ መካከል ጾም በመግባቱ አንድስ እንኳን የሚከፋውወይም የሚበሳጭ ሊኖር አይገባም፡፡ ወርሐ ጾሙን እንዲህ ደስ ተሰኝተንመቀበላችንን ዐይተውም አሕዛብ ይፈሩ፤ አይሁድም ይራዱ፡፡ በእኛና በእነርሱመካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ዐይተውም ይማሩ፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንበዓል የምትሠራው ምእመናን ራሳቸውን መግዛት እንዲችሉ፣ በበጎ ምግባር ያጌጡያሸበረቁ እንዲኾኑ እንደ ኾነ፥ እነርሱ ግን በዓላትን የሚያደርጉት በዘፈንና በስካርይህንም በመሰለ በሌላ ጸያፍ ግብር ለመንከባለል እንደ ኾነ ለይተው ይወቁ፡፡በእርግጥም በዓል ተከበረ የሚባለው፡ሰዎች ነፍሳቸውን ካዳኑበት፣ ውስጣዊሰላምንና ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ካደረጉበት፣ ዕለት ዕለት ከሚያጋጥማቸው የነፍስመታወክ ካረፉበት፣ ያለ ሁካታና ጋጋታ እንዲሁም እንስሳትን በማረድ ከልክበላይ ከኾነ መብልና መጠጥ ርቀው ያከበሩት እንደ ኾነ ነው፡፡ ከዚህምበተጨማሪ በዓል ተከበረ የሚባለው፡- አርምሞንና ጸጥታን፣ ፍቅርንና ደስታን፣ሰላምንና ራስን መግዛትን፣ እንዲሁም ሌሎች እዚህ መዘርዘር የማንችላቸው ብዙምግባር ትሩፋቶችን ገንዘብ ያደረግንበት እንደ ኾነ ነው፡፡
(3) እንኪያስ እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይከኹሉም በፊትእነዚህን ነገሮች በስፋት እንነጋገርባቸው ዘንድ፣ ዳግመኛም አንዳች የሚረባንንነገር ይዘን ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ ቃላችንን በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችሁትቀበሉት ዘንድ አሳስባችኋለሁ፡፡ ኹላችንም ወደዚህ ጉባኤ ስንመጣ እንዲሁናያለ ዓላማ አይደለም፡፡ ወሬ ለማውራት፣ ምን እንደ ተባለ እንኳን ሳንሰማለማጨብጨብ፣ ከዚያም ምንም የሚረባ ነገርን ሳንይዝ ወደ ቤታችን ለመመለስወደዚህ ጉባኤ አልመጣንም፡፡ እኔም የመጣሁት ለነፍሳችሁ ድኅነት የሚጠቅምአንዳች ነገርን ለመናገር ነው፤ እናንተም ስትመጡ በእኔ በባሪያው አድሮእግዚአብሔር የሚናገረውን ነገር አድምጣችሁ ለመጠቀምና አንዳች የሚረባነገርን ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ለመመለስ ነው፡፡ ተመልከቱ! ቤተ ክርስቲያን ማለትቤተ ድኅነት ናት፡፡ ወደ እርስዋ የሚመጡትም ለችግራቸው ተገቢውን መድኃኒትአግኝተው መሔድ አለባቸው፡፡ ተግባራዊ የኾነ ለውጥ ሳያመጡ ቃለ እግዚአብሔርን መማር ብቻ ምንም ጥቅም እንደሌለው ሲናገርም ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡- “በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁት ሕግንየሚያደርጉት እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደሉም” /ሮሜ.213/፡፡ በቃል መነገሩ፣በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችንክርስቶስም ሲያስተምር፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ብሏል /ማቴ.721/፡፡ ስለዚህ ተወዳጆች ሆይቃሉን በመስማታችን ብቻ አንዳች የምንጠቀመው ነገር ስለሌለ የሰማነውን የምናደርግ እንጂ የምንሰማ ብቻ አንኹን፡፡ እንዲህ ከኾነም እምነታችን ሕይወት ያለው እምነት ይኾናል፡፡
(4) በመኾኑም፥ ስለ ጾም የሚሰጠውን ስብከት ለማዳመጥ እዝነ ልቡናችሁን ክፈቱ፡፡ ከትሕት እና ዓይናፋር ሙሽሪት ጋር አነጻጽሬ እንድነግራችሁ ትወዳላችሁን? ሙሽሪቱን በሰርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች አስቀድመው ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይጠርጉታል፡፡ የቆሸሸ ልብስን የለበሰ ሰው ወደ ሰርጉ አዳራሽ እንዳይገባ ያደርጉታል፡፡ ወደ አዳራሹ መግባት የሚችለው የሰርግ ልብስ የለበሰ ሰው ብቻ ነው፡፡ እናንተም እንዲህ ልታደርጉ ይገባችኋል፡- ልቡናችሁን በማንጻት፣ አብዝቶ ከመብላትና ራስን ካለመግዛት በመራቅ - የምግባር እናት፣ የማስተዋልና የሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ደጀ ልቡናችሁን በመክፈት ልትቀበሏት ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደ ኾነ ታላቅ ሐሴት ታደርጋላችሁ፤ እርስዋም ቁስለ ነፍሳችሁን ትፈውስላችኋለች፡፡ ሌላ ምሳሌ መስዬ ብነግራችሁ፡- ሐኪሞች በሕሙማን ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻና መርዘኛ ፈሳሽን ማስወገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ ሕሙማኑ ምግበ ሥጋን ከመውሰድ እንዲቈጠቡ ያደርጉዋቸዋል፡፡ ሕሙማኑ ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከሉ ግን ሐኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት የተፈለገውን ያህል ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም የነፍስንና የሥጋን ቁስል የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚህ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ድኅነትን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹህና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፤ እንዲህ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡
(5) የዛሬው ንግግሬ ለአንዳንዶቻችሁ አዲስና እንግዳ እንደሚኾንባችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በዓላማ (ድኅነትን ለማግኘት ብለን) እንጹም እንጂ እንዲሁ የልማድ ባርያዎች አንኹን ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ በየቀኑ ከልክ በላይ በመብላትና በሆዳምነት የምታገኙት ጥቅም ምንድን ነው? ጥቅምስ ይቅርና ጭራሽ የከፋ ጉዳትን የሚያመጣባችሁ ነው፡፡ ተመልከቱ! ከልክ በላይ በመጠጣትና በመስከር የማስተዋል ልቡና ሲታወር የጾም ጥቅምዋም ምንም ምልክትን ሳያስቀር ያጠፏል፡፡ እስኪ ልጠይቃችሁ፡- እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብዙ ወይንን ከሚጠጡ፣ በየመሸታ ቤቱ አድረው ፀሐይ ከምትወጣባቸው፣ ለሚያገኛቸው ሰው ኹሉ ደስ ከማያሰኙ፣ ለቤተ ሰቦቻቸው ግድ ከሌላቸው፣ ሕፃን ዐዋቂው ከሚሳለቅባቸው፣ ራሳቸውን ባለመግዛታቸውና ያለጊዜው በኾነ ደስታ ደስ በመሰኘታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ካጡ ከእነዚህ ሰዎች በላይ ማን ጎስቋላ ሰው አለ? ቅዱስ መጽሐፍስ እንዲህ የሚል አይደለምን?፡- “ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” /1ኛ ቆሮ.6፥10/፡፡ ወዮ! እንደ ጠዋት ጤዛ ለሚጠፋ፥ ያውም እጅግ ከባድ ጉዳትን የሚያመጣ እርካታን ለማግኘት ብለው፥ የዘለዓለምን መንግሥትን የሚያጡት እነዚህ ሰዎች ከሚያገኛቸው መከራ በላይ ምን መከራ አለ?
(6) እዚህ ጉባኤ ከተሰበሰባችሁ ምእመናን መካከል አንድም ሰው እንኳን ቢኾን በዚህ ዓይነት ስንፍና መያ’ዝ የለበትም፤ እግዚአብሔር ይህን በፍጹም አይወደውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዷን ቀን በትዕግሥትና ራስን በመግዛት እንዲሁም አብዝቶ መብላት ከሚያመጣው የመከራ አውሎ ነፋስ ተጠብቃችሁ ወደ ነፍሳችሁ ወደብ - ይኸውም ወደ እውነተኛ ጾም - ልትደርሱ ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነም ከእርስዋ የሚገኘውን ጥቅም በብዙ ታገኛላችሁ፡፡ በሌላ አነጋገር አብዝቶ መብላት የብዙ ውርደቶችና ኃጢአቶች ምንጭ እንደ ኾነ ኹሉ ጾምም የብዙ በረከቶችና ክብር ምክንያት ነው፡፡ እንደምታስታውሱት መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲፈጥር ለነፍሳቸው ድኅነት የሚኾን አንድ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር፡፡ በመኾኑም፥ ገና ከመነሻው አንሥቶ ለመጀመሪያው ሰው (ለአዳም) አንድ ትእዛዝ ሰጠው፤ እንዲህ በማለት፡- “በገነት ካለው ዛፍ ኹሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” /ዘፍ.2፥16-17/፡፡ ይህ ስለ መብላትና ስለ አለመብላት የተገለጠው ኃይለ ቃል በምሥጢር ስለ ጾም የሚናገር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰው ይህቺን ትእዛዝ ይጠብቃት ዘንድ ቢታዘዝም እርሱ ግን አልጠበቃትም፡- ራሱን መግዛት አቃተው፤ ባለመታዘዝ ኃጢአት ውስጥ ወደቀ፤ በራሱ ላይም የሞት ፍርድን አመጣ፡፡ እንደምታስታውሱት ዲያብሎስ ክፉ መንፈስና የእኛ ጠላት ስለ ኾነ የመጀመሪያው ሰው አዳም በገነት ሲኖር እንዴት በነጻነት እንደሚኖርና ሥጋ ለብሶ ሳለ እንዴት የመላእክትን ኑሮ በምድር ላይ እንደሚኖር ተመለከተ፡፡ በመኾኑም፥ እንዴት እንደሚጥለው አሰበ፤ ታላቅ የኾነ ተስፋ በመስጠት ከልዕልናው አዋረደው፤ በዚህ ሽንገላዉም የነበረውን ሀብት ኹሉ ሰረቀው፡፡ በመጠን ያለመኖርና ከዓቅም በላይ የኾነን ነገር የመመኘት ክፋቱ ይኽን ያህል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰውም ይህንን እንዲህ በማለት ግልፅ አድርጎታል፡- “በዲያብሎስ ቅንአት ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ” /ጥበ.2፥24/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ገና ከጥንቱ የሞት መግቢያው ራስን አለመግዛት መኾኑን ታያላችሁን? በኋላ ዘመን ላይም መጽሐፍ ቅዱስ አብዝቶ መብላትን እንዴት ደጋግሞ እንደሚነቅፈው አስተውሉ፡፡ በአንድ ስፍራ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” /ዘጸ.32፥6/፤ በሌላ ቦታም፡- “በላ፥ ጠጣም፤ ወፈረ፥ ደነደነም፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” ይላል /ዘዳ.32፥15/፡፡ የሰዶም ኗሪዎችም እንደዚሁ ያን የማይበርድ ቍጣ በራሳቸው ላይ ያመጡት በዚህ ኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ ሌላውን በደላቸውን እንኳን ሳንገልጠው የነቢዩን ቃላት አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡- እንጀራን መጥገብ” /ሕዝ.16፥49/፡፡ በአጭር አነጋገር መብል ብዙውን ጊዜ እንደ ምንጭ ውኃ ነው፤ ወይም የክፋት ኹሉ ሥር ነው፡፡
(7) እንግዲህ አሁን ራስን አለመግዛት እንዴት አደገኛ እንደ ኾነ ተገነዘባችሁን? አሁን ደግሞ ጾም እንዴት ያለ በረከትን እንደሚያመጣ እንመልከት፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አርባ ቀን ስለ ጾመ የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ጽላት ሊቀበል ችሏል /ዘጸ.24፥18/፡፡ ከተራራው ሲወርድ ግን አብዝቶ የሚበላና ኃጢአተኛ የኾነ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢቀበል ምንም ትርጉም የለውም በማለት በብዙ ምልጃ የተቀበለውን ጽላት ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበረው /ዘጸ.32፥19/፡፡ በመኾኑም፥ ይህ ታላቅ ነቢይ በሕዝቡ ኃጢአት ምክንያት በሰበረው ጽላት ፈንታ እንደ ቀድሞ ያለ ሌላ ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾም ነበረበት /ዘጸ.34፥28/፡፡ በእሳት ሠረገላ ተነጥቆ ወደ ሰማያት የተወሰደው፣ እስከ ዛሬ ድረስም ሞትን ያልቀመሰው ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ልክ እንደ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል /1ኛ ነገ.19፥8/፡፡ ልክ እንደዚሁ መንፈሰ ብርቱው ዳንኤልም አያሌ ቀናትን ይጾም ነበር፤ እንደ ሽልማትም እጅግ የሚያስደንቅ ራእይን ተቀብሏል፡- ቍጡዎቹን አንበሶች እንደሚያስለምዳቸው፣ ጥንተ ተፈጥሯቸው ተለውጦ ሳይኾን ከእነ ተናጣቂ ባሕርያቸው እንደ የዋህ በጎች እንደሚኾኑለት ዐየ፡፡ የነነዌ ሰዎችም እንደዚሁ በጾም መድኃኒትነት ከእግዚአብሔር ዘንድም ምሕረትን አግኝቷል፡፡ እንዲያውም በነነዌ የጾሙት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ እንስሳቱም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ሊያደርገው ከተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም /ዮና.3፥10/፡፡ ከብሉያትና ከሐዲሳት እንዲህ በመጾማቸው ምክንያት የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን - ነገር ግን የኹላችንም ጌታ ወደ አደረገው መምጣት ሲገባን አገልጋዮቹን የምናየው ለምንድን ነው? እንደምታውቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል /ማቴ.4፥2፣ ሉቃ.4፥2/፡፡ ሲጾምም ዲያብሎስን ድል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ይኸውም የጾምን ትጥቅ ልንታጠቅ እንደሚገባንና ከዚህ በምናገኘው ኃይልም ብርቱ የሚኾን ጠላታችንን ድል ማድረግ እንደሚቻለን አርአያ ሲኾነን ነው፡፡
(8) እዚህ ላይ ምናልባት ነገሮችን ጠለቅ አድርጎ የሚመረምርና ሐሳበ ልቡናዉን ንቁ ያደረገ ሰው፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር የጾመው ስለ ምንድን ነው?” ብሎ ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል፡፡ ጌታችን ይህንን ያደረገው ያለ ምክንያት ሳይኾን ከጥበቡና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ወደዚህ ምድር የመጣው ሥጋን ሳይለብስ ነው፤ ሰውም የኾነው በምትሐት ነው” ብለው ለሚነሡ ዐብዳን ሐሳባቸውን ይገታ ዘንድ አስቦ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር ጾመ፡፡ እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ በገቢር ጾሞ ሳለ እንኳን እንደዚህ ያለ ምክንያት የሚያመጡ ከኾነ ከቸርነቱ የተነሣ ሊያመጡት የሚችሉትን ሰበብ አስቀድሞ ባይጥለው’ማ እንደ ምን የከፋ ነቀፋን ባመጡ ነበር? በመኾኑም፥ የእኛን ባሕርይ ገንዘብ እንዳደረገና ከእኛ የራቀ እንዳልኾነ ሲያስተምረን ከቀደሙት አባቶች ሳያተርፍ አርባ ቀን ጾመ፡፡
(9) እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይ! የጾም ጥቅምዋ ምን ያህል የበዛ እንደ ኾነና ነፍሳችን ከዚህ ብዙ ጥቅምን እንደምታገኝ ከጌታችን እና ከአገልጋዮቹ ተምረናል፡፡ ስለኾነም የጾም ወራት ሲቃረብ ግድየለሽነትንና ሞራለ ቢስነትን ከእኛ አስወግደን ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ፡- “የውጭው ሰውነታችን ይበልጥ ሲጠፋ የውስጡ ሰውነታችን ይበልጥ ይታደሳል” ብሎ እንዳስተማረን እጅግ ደስ ተሰኝተን ልንቀበለው ይገባናል ብዬ እማልዳችኋለሁ /2ኛ ቆሮ.4፥16/፡፡ ጾም የነፍስ ምግብ ነው፡፡ ምግበ ሥጋ ሰውነታችን እንዲወፍር እንደሚያደርግ ኹሉ ጾምም ነፍስን ያበረታል፤ ፈጣንና መንፈሳዊ ክንፍን ይሰጣታል፤ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር ገብታ በፅሞና እንድትያዝ ያደርጋታል፤ የዚህን ዓለም ተድላና ደስታ እንድትንቅ ያስችላታል፡፡ ቀላል ጭነትን የተሸከሙ መርከቦች ፈጥነው ባሕሩን እንደሚሻገሩ፣ እጅግ ብዙ ጭነትን የተሸከሙት ግን ባሕሩንና ወጀቡን ቶሎ ማለፍ እንደሚያቅታቸው ኹሉ ልክ እንደዚሁ ጾምም ውሳጣዊ ዓይናችን እንዲበራ፣ የዚህ ዓለም ፈተናዎችን በቀላሉ መቋቋም እንድንችል፣ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር እንድንገባ በዚያም ስላሉ አይነገሬ በረከቶችን እንድናስብ፣ በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ኹሉም ነገሮች እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥነው የሚያልፉ እንደ ኾኑ እንድንገነዘብ ታደርለች፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ አብዝቶ መብላትና ራስን አለመግዛት ደግሞ አእምሯችን የጠፋ፣ ሥጋችን የወፈረ፤ ውስጣችን በእግር ብረት የተጠፈረ፣ በዚህ ኹሉ ተከበንም እጅግ በከፉ ምግባራት የተያዝን፣ የዘለዓለማዊ ሕይወታችን ጠላቶች ኾነን እንድንጓዝ ያደርጉናል፡፡
(10) ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! መብልንና ራስን አለመግዛት ተከትለው የሚመጡትን ኃጣውእ በማወቅ ከድኅነታችን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ቸልተኞች አንኹን፡፡ ራስን አለመግዛት አእምሮን እንደሚያጠፋና አብዝተን ልንጋደለው እንደሚገባን፣ ይህን ያደረግን እንደኾነም አክሊል ሽልማቱ የበዛ እንደ ኾነ የተማርነው በዘመነ ሐዲስ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በዚያ በጨለማ የተቀመጡ፣ የብዙ ጧፎች ጥገኛ የነበሩ፣ ሕፃንን ቀስ በቀስ ወተት አስትተው ፅኑ መብልን እንደሚያስለምዱት ቀስ በቀስ ወደ አማናዊ ብርሃን የተሻገሩ ቢኾኑም፥ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ሰዎችም አብዝተው እንዲበሉ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ራስን አለመግዛት ይህን ያህል አደገኛ እንደ ኾነ ስነግራችሁ የራሴ ሐሳብ እንዳይመስላችሁ ግን ነቢዩ የተናገረውን አድምጡ፤ እንዲህ በማለት፡- “ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፣ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፣ ከፍየሎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፣ ከበገናው ድምጽ ጋር አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች፣ በጽዋ የቀላ ወይንን ለሚጠጡ፣ እጅግ ባማረ ሽቱም ለሚቀቡ - ይኸውም ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው ወዮላቸው” /አሞ.6፥3-6/፡፡ እንግዲህ ነቢዩ፡- በስንፍና፣ በፍትወትና መብልን በማብዛት የነበሩትን አይሁዳውያንን እንዴት አድርጎ እንደወቀሳቸውና እንደገሠፃቸው ተመለከታችሁን? ኃይለ ቃላቱን በደንብ አስተውሏቸው፡- አብዝተው መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ከወቀሳቸው በኋላ እንዲህ ብሎ ይጨምራልና፡- “ይኸውም ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው፡፡” ይህም ማለት፡- ደስታቸውና ፈንጠዝያቸው የሚያበቃው በከንፈራቸውና በላንቃቸው ላይ ብቻ ነው፤ ከዚያ ወዲያ መሔድ አይችልም፡፡ ደስታው ከመገኘቱ የሚጠፋ ነው፤ የሚያገኛቸው ምረረ ገሃነም ግን መቼም መች የሚያበቃ አይደለም፤ ፍጻሜ ያለው አይደለም፡፡ “ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው” የሚለው ደስታ ገና ከመገኘቱ የሚጠፋ መኾኑን አማናዊ ትርጓሜ የምናውቀው ያኔ ነው፡፡ 
(11) አሁን በዚህ ምድር ላይ የምንመለከታቸው የሰው ሰውኛና ሥጋዊ ነገሮች ልክ እንደ ደስታውና ፈንጠዝያው የሚጠፉ ናቸው፡፡ ክብርና ሥልጣን፣ ሀብትና ንብረት፣ በዚህ ዓለም ላይ የምናገኛቸው ብልጽግናዎች ኹሉ ጸንተው የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ኹሉም ከወራጅ ውኃ በፈጠነ ፍጥነት የሚያልፉ ናቸው እንጂ ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ዘለዓለማዊ የለም፡፡ የሙጥኝ ብሎ ሊይዛቸው የሚሞክር ሰው እንኳን በፍጹም ሊያቆያቸው አይችልም፤ የሚቀረው ባዶውን ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ግን እንደዚህ አይደሉም፤ የዚህ ተቃራኒ ናቸው እንጂ፡- እንደ ጽኑ ዐለት የማይንቀሳቀሱ ናቸው፤ ሕልፈት ውላጤ የለባቸውም፡፡ ታዲያ ጸንቶ የሚኖረውን እጠፋ እጠፋ በሚለው፣ የማይነቃነቀውን በሚንገዳገደው፣ ዘለዓለማዊዉን በጊዜያዊው፣ የማያልፈውን በሚያልፈው፣ ዘለዓለማዊ ደስታ የሚሰጠዉን ዘለዓለማዊ ስቃይ በሚሰጠው መቀየራችን እንደ ምን ያለ ሞኝነት ነው?
(12) ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! ድኅነተ ሥጋን ድኅነተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ ራስን አለመግዛትን ከእኛ ዘንድ እናርቀው፤ ጾምንና ከእርስዋ ጋር ያሉትን ሌሎች በጎ ምግባራትን እንውደዳቸው፤ ከዛሬ አንሥተን አዲስ ኑሮን እንጀምር፤ ዕለት ዕለት በጎ ምግባራትን መሥራትም የሚያስደስተን እንኹን፡፡ እንዲህ መንፈሳዊ ተግባራትን የምንፈጽምና የበጎ ምግባር ሀብትን አከማችተን ዐቢይ ጾሙን የምናሳልፍ ከኾንንም ወደ ጌታ ቀን (በዓለ ትንሣኤ) ለመድረስ የተገባን እንኾናለን፤ ወደዚያ ወደ አስደናቂው ማዕድ (ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ) መቅረብ ይቻለናል፡፡ በጌታችን ቸርነትና ሰው ወዳጁ አምላካችን ክርስቶስን ደስ ባሰኙ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃም ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ ከእርሱም ጋር ለባሕርይ አባቱ ለአብ፣ ለባሕርይ ሕይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር፣ ኃይልና ጌትነት ይኹን፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ትውልደ ትውልድ ድረስ አሜን፡፡†††
ምንጭ፡- ኦሪት ዘፍጥረት፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው፣

2016 ጃንዋሪ 16, ቅዳሜ

ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ .ሕዝ.36› 25 -33

                                                                         

                                  
ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ  ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ ጥሩ ውሃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኩሰታችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ  አዲስ ልብ እስጣችኋለሁ አዲሰ መንፈስ በወስጣችሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ  መንፈሴን በወስጣችሁ አኖራልሁ .......
ነቢያት በተሰጣቸው ፀጋ  መሠረት ያለፈውንና   የሚመጣውን   ትንቢት የመናገር  ኃብት ተሰጥቶአቸዋል
ነቢዩ  ሕዝቅኤልም ከላይ እንደተጠቀሰው   ስለ ጥምቀት ተናግሮአ ፤  እስቲ !ኃይለ ቃሉን  በዝርዝር እንየው
        1 . ጥሩ ውሃ ምንድነው?
ውሃን  እግዚአብሔር  ሲፈጥረው  ለበጎ ነገር የሰው ልጅ  እንዲጠቀምበት አድርጎ ፈጥሮታል ። ለመጀመሪያ ጊዜ የእግዚአብሔርም  መንፈስ ያደረው በውኃ ላይ ነው ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር ። ዘፍ .1  ፤ 2   ይሁን እንጂ  የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን እየጣሰ ሲመጣ ለሰው ልጅ መጠቀሚያ  የነበርው ሁሉ  መጥፊያም መሆን ጀመረ ።  በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ  በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል ። ዘፍ .6  ፣ 18  ተብሎ ተጽፎአል
ታዲያ ውኃ ከምሥጢረ ጥምቀት ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት  ለምሥጢረ ጥምቀት በሚገባ  ቋንቋ  ነቢዩ ሕዝኤል ገልፆታ።
  ጥሩ ውኃ  ሲል የጠራ፣ ንጹህ የሆነ ውኃን  እረጭባችኋለሁ ማለቱ ጌታ በወንጌል  ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር መሆኑን ተገልፆለት ተናግሮታል ፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ይህውም ተግባራዊ የሚሆነው በውኃ ነው።ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የምስጢረ  ጥምቀት አመጣጥ  የተገለጸው በውኃ ነው። አማናዊውን ጥምቀት በሐዲስ ኪዳን የጀመረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ግልጽ መሆኑ ቢታወቅም ከዚያ በፊት ግን በብዙ ምሳሌ ይታወቅ ነበረ።አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 1417/
v  ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
v  ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 514 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
v   የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 613 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችንኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 320/
v   እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 1415/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 101/
v   ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 179/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 211/
                                             ጥምቀት ለምን?
                 1.የእግዚአብሔርን ልጅነት ለማግኘት
ከላይ በመነሻ ላይ እንደተገለጸው  “ ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ” የሚለው ኃይለ ቃል  የሚገልጸው ከሌሎች በጥምቀት ኃብተ ወልድና ሥመ ክርስትና ከሌላቸው ሰዎች መለየትን ነው  ። ”ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን “ ሮሜ .8 ፤ 17  ስለዚህ የመጠመቃቸን አንዱ ምክንያትም ሆነ ጥቅም የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን  ከሌሎች መለየት ነው ። ልጆች ደግሞ ስለሆን ገድልን  ከነቅድስናው  በረከተ ሥጋ ወነፍስን  ለመውረስ  ያስችላል።
              2. አገረ ሕይወት መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ
ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” የሰው ልጅ ከፈጣሪው በኃጢያት ምክንያት  ከተለየ በኋላ ያልተስተካከል የተዘበራረቀ ያልተረጋጋ  ጭንቀት የበዛበት እና የተበታተነ ሕይወት በመኖር 5500 ዘመናትን አሳልፎአል  ወተትና ማር የምታፈስ ገነትን ያህል  ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አጥቷል ። ይሁን እንጂ ወደ ቀደመው ቦታችን ለመመለስ  ያቺን የሕይወት አገር ለመውረስ እንችል ዘንድ የተሰጠን ልዩ ስጦታ ጥምቀት ነው ። በጥምቀት የተበታተን ሕይyanወታችን ይሰበሰባል ወደቀደመ አገራችን እንመለሳለንና ነቢዩ ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” በማለት ተናገረ። ጥምቀት የምናገኘውን ፀጋ  ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “ በጥምቀት ከርሱ ጋር ተቀብራችሁ ፤ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” ቆላ. 2 ፤ 12 ትንሣኤ ዘለክብርን አግኝቶ መንግስተ ሰማያትን መውረስ የሚቻለው በጥምቀት ነው። ‘’ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።እንዲል.  ሕዝ. 36 ፤ 28
                                                     3. አዲስ ሕይወት ለማግኘት
ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ  በቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ላይ እንደገለጠው “ ሰው እንደ አዲስ ጨርቅ ነው አዲስ ጨርቅ አዲስ እንደሆነ ሁሉ  አሮጌ ደግሞ ይሆናል ። ሁለቱ ነገሮች በሰው ሕይወት ላይ ይፈራረቃል ። ክፋትና በጎነት ፤ ኃጢአትና ጽድቅ ፤ ቂመኛነት እና ይቅርባይነት ፤ ለጋስነት እና ንፉግነት  በአጠቃላይ የሥጋና የመንፈስ  ፈቃዳት በሰው  ልጆች ሕይወት ላይ ይሟገታሉ ። በአንጻሩ የመንፈስ ፈቃዳትን ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ እና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆን አዲስ ሕይወት ያስፈልጋል ። ይህውም በጥምቀት  የሚገኘው በጥምቀት ነው። “ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአበሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?........... የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፡ ያውም እናንተ ናችሁ። 
1.ቆሮ .3፤16
አዲስ ሕይወት ያልው ሰው አዲስ መንፈስ፤ አዲስ ልብም ይኖረዋል ። ለበጎ ሥራ የሚነሳሳ የይቅርታ ፤’ የሰላም’፤ የፍቅር ልብ የሚኖረው አዲስ ሕይወት ሲኖረን ነው ። ያን ጊዜ “ የድንጋዩንም ልብ  ከሥጋችሁ አወጣለሁ »  ተብሎ እንደተጻፈው  ክፉ ሐሳብ እና ተግባር ሁሉ ከሰው ይወገዳል ። የድንጋይ ልብ ያለው ሰው ጨካኝ  የማይጸጸት ለሰው የማይራራ ይሆናል። አሁን በዘመናችን የምናየውና የምንሰማው ይህንኑ ነው። ‘’ የሥጋንም  ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ ......... መልካም ያይደለውን ሥራችሁን  ታስባላችሁ ስለ በደላችሁና ስለ ርኩሰታችሁም ራሳችሁንም ትጸየፋላችሁ። ሕዝ.36 ፤ 32  በምድር ላይ ያለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔ ፍጥረት እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም ። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የሚቻለው በጥምቀት ነው ።” አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፍስ  ተቀበላችሁ እንጂ  እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና  የእግዚአብሔር ልጆች  መሆናችንን  ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ .8 ፤ 15  ልጆች ሲያጠፉ  ወይኔ! አባቴ ፤ እናቴ ይቆጡኛል  ይፈራል እንጂ ሌላ ሰው አይፈራም  አባትም ከሌሎቹ ልጆች ለይቶ ልጁን ይቆጣጠራል  የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟላለታል።  እግዚአብሔርም ለኛ ለልጆችሁ እንዲሁ ነው ።  አሁን እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎችም ሆይ ! በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል  እስኪ ፍረዱ ፡ ለወይኔ ያላደረኩለት ከዚኦህ ሌላ አደረግለት ዘንድ የሚገባኝ መንድንው?   ኢሳ፤ 5 ፤ 3  የሚሰጠንም ፀጋ ከልጅነታችን አንፃር ነው ብዙ ነገር ስለተደረገልን ብዙ ነገር ደግሞ ይጠበቅብናል ።
በአጠቃላይ  ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የጥምቀት በዓል ሲከበር ብቻ የሚታወሱ አይደሉም ነገር ግን በየዓመቱ በዓልትን ስናከብር መሠረታዊ የሆኑ የድኅንት መንገዶችን ማክበር  ትኩረት ሰጥቶ ማስታወስ  ይገባል ። ይልቁንም በዓላትን በስደት ሀገር ሆኖ ሲከበር ደግሞ ሥርዓተ ሃይማኖቱን ጠብቆ በጎ የሆነውን ባህላችንንና አለባበሳችን ሳይቀር ሳንተው ያለንበትን ሀገር ሀገራችን አድርገን ማክበር ይገባል።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን !
                              
                                       ከሰሜን አውሮፓ  ፊንላንድ
            

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...