2015 ማርች 10, ማክሰኞ

እየደመሰሱ መቅዳት

ለረዥም ዓመታት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የሠራ ጋዜጠኛ ለአንድ ጥናት ወደ ጣቢያው ይሄዳል፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት እርሱ ራሱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር፡፡ ቃለ መጠይቁ የተደረገላት ሴት አሁን በሕይወት የለቺም፡፡ ለዚህ ነበር እርሷ የሰጠቺውን ቃል ፍለጋ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሄደው፡፡ ያገኘው ግን የጠበቀውን አልነበረም፡፡ የተቀዳው ቃለ መጠይቅ የለም፡፡ ምነው? አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ብዙ ካሴቶችን እየደመሰስን ቀድተንባቸዋል፡፡ በዚያ ምክንያት ያንን ቃለ መጠይቅ አሁን አታገኘውም›› አሉት፡፡ እርሱም በዚህ አዝኖ ወጣ፡፡
ለነገሩ እርሱ በካሴቱ አዘነ እንጂ ከኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫዎች አንዱ እየደመሰሱ መቅዳት ነው፡፡ የሚመጣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን፣ ዐዋቂ ወይም ታዋቂ፣ ታሪክ ጸሐፊ ወይም ዐቅድ ነዳፊ ከእርሱ በፊት ለነበረው ነገር ዋጋ ሰጥቶ፣ የየራሱን ሥራ ከመሥራትና የዘመኑን አሻራ ከማኖር ይልቅ ያለፈውን መደምሰስ ይቀናዋል፡፡ 

ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለ ቆየ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡ የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም አሣምሮ የሚጨምር ከሆነ ሀገር እያደገች፣ እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡ 
 ባቢሎን በታሪክ ቀድመው ከሠለጠኑ ሀገሮች ተርታ ነበረቺ፡፡ ነገር ግን የገዛት ሁሉ ከመሠረቷ እያፈረሰ እንደገና ሲሠራት፣ የመጣዉ ሁሉ እየደመሰሰ ሲቀዳባት ይሄው ዛሬም አላልፍላት ብሎ የጦር አውድማ ሆናለቺ፡፡ ስለ ኢራቅ ጥንታዊ ታሪክ የሚተረከውና የዛሬዋ ኢራቅ አይጣጣሙም፡፡ የመጡት ሁሉ በባቢሎን ካሴት ላይ እየደመሰሱ ሲቀዱ፣ መሠረት አልባ ጣራ ሊያቆመ ሲደክሙ፣ አሁን የመጡባት አሸባሪዎች ደግሞ ጨርሰው ታሪካዊ ቅርሶቿን በድጅኖ መናድ ጀመሩ፡፡ እየደመሰሱ መቅዳት ካንሰር መሆን ሲጀምር ይሄው ነው፡፡
ይኼ እፉኝታዊ ጠባይ ነው፡፡ እፉኝት የምትባል የእባብ ዘር አለች አሉ፡፡ አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ነው፡፡ ከወንዱ ጋር ስትገናኝ የወንዱን አባለ ዘር ትቆርጠውና ወንዱ ይሞታል፡፡ ልጆቿን በማኅፀኗ ፈልፍላ ስትወልዳቸው ደግሞ ለመውጣት ስለማይችሉ ሆዷን እየቀደዱ እናታቸውን ገድለዋት ይወጣሉ፡፡ ልጆቹ ልጅ የሚሆኑት አባትና እናታቸውን ገድለው ነው፡፡ ያለፈውን ካልደመሰሱ መኖር አይችሉም፡፡
የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡ ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡ አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡፡ 
ቅቤን ማንም አያነጥረውም፤ ባለሞያ ይጠይቃል፡፡ አንጉላውን የማስወገጃ መንገዱ ራሱ ልዩ ሞያ ጠያቂ ነው፡፡አንጉላ መስሎን ቅቤዉን ጭምር እንዳያስወግደው እንደ ዶሮ ላባ ባለ ስስ ነገር እየለዩ ማንጠርን ይጠይቃል፡፡
ታሪካችንንና ባሕላችንን፣ ወጋችንንና ልማዳችንን ስንመረምርና አንጉላውን ስንለይ፣ እንደ ቅቤ አንጣሪው በሞያ መሆን አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ሊያገኝ አይገባም፡፡ ቅቤ አንጣሪ ስሜት ውስጥ ከገባ ምች ይመታዋልና፡፡ አረሙን እንነቅላለን ብለን ስንዴውን ጨምረን እንዳንነቅለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ብለን የምንሠራቸው ሥራዎች አዙሪት ውስጥ እንዳይጥሉን ጉዳዩን የሞያና የዕውቀት ጉዳይ ማድረግ ይገባናል፡፡ ‹ዕውቀት አጠር፣ ስሜት መር› ከሆነው ጉዟችን ይልቅ ‹ዕውቀት መር፣ ስሜት አጠር› ወደሆነው ሥልጣኔ ካልወጣን በስተቀር እዚያው ጨለማው ውስጥ ስንኳትን እንኖራለን፡፡ 
ቅቤ አንጣሪ ሰው ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ያስፈልገዋል፡፡ ምች እንዳይመታው፡፡ የቅቤ ምች ያጠናግራል ይባላል፡፡ ቅቤውን በጥንቃቄ ያነጠረቺ ባለሞያ ናት ‹‹ቅቤ አንጣሪዋ እያለቺ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት› ብላ የተሳለቀቺው፡፡ ነባሩን ነገራችንን ስናነጥር ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ወሳኝ ነው፡፡ የዘመን ምች መትቶ እንዳያጠናግረን፡፡ ጎጠኛነት፣ የፖለቲካ ፍጆታ፣ የሥልጣን ፍቅርና ጊዜያዊ ጥቅም የሚባሉ ምቾች አደገኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ምቾች የመቱት ሰው ቅቤውን በሚገባ ማንጠር ቀርቶ ሌላ በሽታ በራሱ ላይ ይጨምራል፡፡ ጤነኛ የነበረው አንጣሪ ተጣሞ፣ ዓይኑ ጠፍቶ፣ ፊቱ ቆሳስሎ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱ ያለፈው ታሪኩን ሁሉ የሚያየው በማንጠሪያ ዓይኑ ሳይሆን በተጠናገረ ዓይኑ ነው፡፡ 
አሁን በደምስሶ መቅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩት ብዙዎቹ ወገኖቻችን ምች የመታቸው ናቸው፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን ምች ስለ መታው ቅቤውንና አንጉላውን መለየት አልቻሉም፡፡ አንጉላ መስሏቸው ሁሉንም ነባር ቅቤ ሊያስወግዱ የቋመጡ ናቸው፡፡ የዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡
ሰው በአንድ ቦታ ስለተሰበሰበ ብቻ ሀገር አይሆንም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እሥራኤላውያን አሜሪካና ፖላንድ መኖር ይበቃቸው ነበር፤ ለፍልስጤማውያንም ዮርዳኖስና ሊባኖስ የሚኖሩት የካምፕ ኑሮ በቂ ነበር፡፡  ሰፊ መሬት ብቻውንም ሀገርን አይመሠርትም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ሀገር ግን ከሰውም ከመሬትም በላይ ናት፡፡ ሰው በመሬቱ ላይ ሲኖር የሠራው ታሪክ፣ ያካበተው ባሕል፣ የደነገገው ወግና ሥርዓት፣ ያዳበረው ቋንቋ፣ ያመጣው ለውጥ፣ የፈጠረው ዘዴ፣ የገነባው ሥነ ልቡና፣ የተከተለው እምነት፣ የእርስ በርሱ መስተጋብር፣ ዓለምን የሚያይበት ርእዮተ ዓለም፣ ሥነ ቃሉ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም ተዋሕደው የሚፈጥሩት ነገር ነው - ሀገር፡፡ 
 
እነዚህን የተሠራንባቸውን ነገሮች ነው ማንጠር የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ እንሰብስባቸው፣ እንመዝግባቸው፣ እንለያቸው፣እንዘግባቸው፣ እንቀርሳቸው፣ እንወቃቸው፡፡ ከዚያ እናጥናቸው፣ እንመርምራቸው፡፡ በመጨረሻም እናንጥራቸው፡፡ ገመዱ ውስብስብ ነው፡፡ ለዘመናት የተፈተለና የተገመደ፡፡ ርጋታ፣ ትዕግሥትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ወስነን አይደለም ማወቅ ያለብን ዐውቀን ነው መወሰን እንጂ፡፡ አንዳንዴ መጀመሪያ እንወስናለን፣ ከዚያ እንሰይማለን፣ ቀጥለንም እንፈርጃለን፣ በመጨረሻም እንመታለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ዕውቀት፣ ጥናትና ማንጠር ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ ‹ስቅሎ ስቅሎ› ነው፡፡ ‹ትዕዛዝ ከበላይ፣ እግር ወደላይ› ይሆናል መመሪያው፡፡
 
በዚህ መንገድ ስንቱን እየደመሰስን ቀዳን፡፡ ስንቱን ነባር ዕውቀት ሳንጠቀምበት እንደ ገናሌ ወንዝ ፈስሶ ፈስሶ ቀረ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡   

የኢሬቻ በዓል በደብረ ዝቋላ እንደሚከበር የተላለፈው ዘገባ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ተወሰነ

debra zeq
  • ለአፈጻጸሙ የወረዳው እና የዞኑ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሓላፊነት ወስደዋል
  • ከመጋቢት ፭ ክብረ በዓል በፊት ማስተባበያው እንዲተላለፍ ከስምምነት ተደርሷል
  • ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ የችግሩን ቆስቋሾች ያጣራል
  • በክብረ በዓሉ ቀን የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል
* * *
  • ‹‹ለእኛ ዐዲስ ነገር ነው፤ እዚኽ ቦታ ኢሬቻ የለም፤ በአራት ወይም በስምንት ዓመት አንዴ ዝናም እምቢ እንዳይለን ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዐት ውጭ በተነገረው መልኩ የሚከበር በዓል የለም፡፡ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡››
/የአባ ገዳ ተወካዮች/
  • ‹‹ኅብረተሰቡን ከእኛ ጋራ ሊያጣሉ የሚፈልጉ ግለሰብ አመራሮች አሉ፡፡… ለተላለፈው መልእክት ሓላፊነት የሚወስድ አካል ካልተገኘ፣ የመጋቢት ፭ ክብረ በዓል ከመድረሱ በፊት በስሕተት የተላለፈ መኾኑ ይገለጽልን፡፡››
/የገዳሙ አስተዳደር/
  • ‹‹እናንተ ሰላም ፍጠሩ፤ [በክብረ በዓሉ] ከተለመደው ውጭ አንዳችም የሚደረግ አይኖርም፤ ጥበቃውም እንዲጠናከር ይደረጋል፤ የተላለፈውን ዘገባ አጣርተን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፡፡››
/የዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ሓላፊዎች/

2015 ማርች 5, ሐሙስ

በዝቋላ ገዳም ዙሪያ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ እየተዛመተ ነው


  • የሄሊኮፕተር እገዛ አልያም የውኃ ቦቴ መኪኖች ድጋፍ እየተጠየቀ ነው


በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ትላንት ጠዋት የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ አሞራ ገደልበሚባለው አቅጣጫ መዛመቱ ተገለጸ፡፡
በሰሜን በኩል ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው የገዳሙ መውጫ ትላንት ጠዋት 2፡00 የተቀሰቀሰው ቃጠሎ፣ በአዱላላ ወረዳ ሠራተኞችና በነዋሪው ሕዝብ ርብርብ ማምሻውን መጥፋቱ ከተገለጸ በኋላ ነው አሞራ ገደል በሚባለው የገዳሙ ደቡባዊ ገጽ በዛሬው ዕለት 5፡00 ላይ ዳግመኛ መቀስቀሱ የተሰማው፡፡
በገዳማውያኑ የጥሩንባ ልፈፋ በተሰባሰበው የገጠሩ ነዋሪና የወረዳው አስተዳደር ሠራተኞች እሳቱን አፈር በማልበስና በቅጠል በመተምተም  ለማጥፋት የተቻለ ቢመስልም አንድ የገዳሙ መነኰስ በስልክ እንዳስረዱት፣ ‹‹በደንብ ሳይጠፋ ቀርቶ የታፈነ ነበር፡፡ ዛሬ አሞራ ገደል ጫካ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዛፉ እርጥበት አለው፤ ጢሱ ያፍናል፡፡››  
ቃጠሎው፣ በአካባቢው ከባድ ነፋስ እየበረታ ከገደሉ ሽቅብና ወደ ጎን ወደ አዱላላ አቅጣጫ የተወሰነ የደኑን ክፍልና እዳሪ መሬት እየበላ በአስጊ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ አኹን ባለው አካሔድ ሳይገታ ወደ ምሥራቅ ከዞረና ጠበል ሜዳውን ካገኘ ወደ ደኑ በጥልቀት ስለሚገባ በእጅጉ አውዳሚ እንደሚኾን የገዳሙ መነኰስ ተናግረዋል፡፡
ከቦታው ገደላማ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንጻር የሚያፍነው ጢስና የቃጠሎው ፍጥነት የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት የገዳሙ መነኰስ፣ አመቺ የሚኾነው አስቸጋሪውን ዐቀበት በመውጣት ለሰው ኃይሉ ውኃ ማቅረብ በሚችሉ መኪኖች አልያም በአየር ርጭትበመኾኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል የሄሊኮፕተር አልያም የቦቴ መኪኖች እገዛ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲጠየቅ አመልክተዋል፡፡
የትላንቱን ቃጠሎ ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ከደብረ ዘይት ከተማ ተጉዘው ሌሊቱን ቃጠሎው በጀመረበት ስፍራው የደረሱ ምእመናንየእሳቱን መስፋፋት የሚገቱ የመከላከል ሥራዎችን ሲሠሩ አድረው መመለሳቸው ተገልጧል፡፡ የከተማው ሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን የወረዳው ማእከል አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲኹም ምእመናን÷ መሬቱን ቆፍሮ በአፈር የመከተር፣ ተቀጣጣይ ጉቶዎችንና ቁጥቋጦዎችን የመመንጠር የመከላከል ሥራ እስከ ንጋት ድረስ ሲሠራ ማደሩ ታውቋል፡፡
ዛሬ ቀትር ላይ መዛመቱ የታወቀውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከገዳማውያኑ የድረሱልን ጥሪ መተላለፉን የገለጸ አንድ ምእመን፣ በከተማው በስምንቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችና በሠርክ ጉባኤያት ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በመቅስቀስና በማስተባበር በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ለመድረስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡


zequulla
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የገዳሙ መነኰሳት እየተናገሩ ነው፡፡
ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው የጀመረው ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው በገዳሙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ነው፡፡
ይህ አቅጣጫ፣ የገዳሙ ሞፈር ቤት የሚገኝበት መውጫ መንገድ ሲኾን በአኹኑ ሰዓት በበርካታ ቦታዎች ጭስ እንደሚታይ በመነኰሳቱ ተገልጧል፡፡
የቃጠሎው መንሥኤ በውል ባይታወቅም እሳቱ በአካባቢው ባለው ከባድ የነፋስ ኃይል ወደ ገዳሙ መውጫና በገዳሙ ዙሪያ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል፡፡
ziquwala_17የአቅራቢያው ነዋሪ ኅብረተሰብ በጥሩንባ በተላለፈው የድረሱልን ጥሪ የተሰባሰበ ሲኾን ወደ ወረዳው ጽ/ቤትም ተደውሎ የአስተዳደሩ አባሎችና የፖሊስ ኃይል በስፍራው መድረሳቸው ተገልጧል፡፡ ‹‹ቃጠሎውን በቅጠልና በአፈር ለመከላከልና መዛመቱን ለመቀነስ የነፋሱን ጋብ ማለት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፤›› አንድ የገዳሙ መነኰስ፡፡
በጥንታዊውና ታሪካዊው ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ ሲደርስ የአኹኑ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እንደ አርዘ ሊባኖስና የሐበሻ ጥድ ያሉት አገር በቀል ዛፎች በስፋት ወድመዋል፡፡ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ደግሞ ተኣምራዊና ግራ አጋቢ ጠባይዕ የታየበት ነበር፡፡ በምሥራቃዊ አቅጣጫ በሚገኘው የመንግሥት ደን ውስጥ ተከሥቶ በአንድ ገጽ ኃይሉ ሲቀንስ በሌላ አቅጣጫ እየተዛመተ ገዳሙን ጨርሶ ለማጥፋት በተቃረበበት ኹኔታ ከአዲስ አበባ፣ ከቢሾፍቱና ከአዳማ በተመሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና አካላት መተባበር እንዲኹም በመከላከያና በፖሊስ ኃይሎች እገዛ መገታቱ የሚታወስ ነው፡፡
በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በገዳሙ የጠበል – ሐይቅ የኢሬቻን በዓል ለማክበርና በደብረ ዝቋላ የአባ ገዳ ሐውልት ለመትከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታቀዱንና በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ መገለጹን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር በጻፈችው ደብዳቤ ተቃውሞዋን በማሰማት ላይ እንዳለች ይታወቃል፡፡DSC_0642[1]ጥንታዊውና ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በገዳሙ ደጅ ጠኚውን፣ አፈር ጠባቂውንና የአብነት ትምህርት መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ሳይጨምር እስከ 350 መነኰሳትና መነኰሳዪያት እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡

ሰበር ዜና:- በዝቋላ ገዳም ዳግም የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ


የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
abune gebre menfes kidus 004በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ደን ላይ በዛሬው እለት የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን ከገዳሙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተራራው ሥር ከወንበር ማርያም እና አዱላላ አቅጣጫ የተነሳው ቃጠሎ በገዳሙ ደን ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ ማኅበረ መነኮሳቱና ተማሪዎች፤ እንዲሁም የአካባቢው ምእመናንን ባደረጉት ርብርብ ለጊዜው አፈር በማልበስ ለማጥፋት ተችሏል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ካለው ነፋሻማና ሞቃታማ አየር ምክንያት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ገዳማውያኑ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረ ማርያም ገልጸዋል፡፡

'ዛሬ ጠዋት እየኾነ ያለው እንዲህ ነው'

2015 ማርች 4, ረቡዕ

የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለች


አትምኢሜይል
የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዘማች አዩኔ /ከሆሳዕና ማእከል/
001 hosaen mariamበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀድያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከቅዳሴ በኋላ ድንገተኛና ለጊዜው መንስኤው ባልታወቀ ሁኔታ ተቃጠለች፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወርኃዊ በዓል ለማክበር ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደተጠናቀቀ እና ቡራኬ ተቀብለው ወደየቤታቸው በተመለሱ በ20 ደቂቃ ውስጥ ካህናት እና ዲያቆናት ገና በደጀ ሰላም እያሉ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ቃጠሎው እንደጀመረም ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ በሮች ከውጭ ተቆልፈው ስለነበር ቁልፎቹን በቅርበት ለማግኘት ስላልተቻለ እሳቱን ቶሎ በቁጥጥር ለማዋል አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በውስጥ የነበሩት ንዋያተ ቅድሳት ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡

የደብሩ ካህናትና ዲያቆናት የቤተ ክርስቲያኗን በር ሰብረው በመግባት በዕለቱ ቅደሴ የተቀደሰበትን ታቦት አፈር በማልባስ ከእሳቱ ለመከላከል ተችሏል፡፡

ከተመሠረተች ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ቤተ ክርስቲያን በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ብትወድምም በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩት ታቦታት ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈዋል፡፡

ከቃጠሎው የተረፉት ታቦታት እሳቱ ከጠፋ ከሦስት ሰዓታት በኋላ በካህናት፣ በዲያቆናት እና ምዕመናን ታጅበው ለጊዜው ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ ገብተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀድያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በ1901 ዓ.ም ሲሆን፤ አካባቢው በሌሎች የእምነት ድርጅቶችና እና በ ኢ-አማንያን የተከበበ በመሆኑ ምእመናን በሃይማኖት በምግባር ጸንተው እንዲኖሩ በደብሩ በተለያዩ ጊዜያት ጉባኤ በማዘጋጀት የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየ ቦታ ነው፡፡

e

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...