የምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት ይካሄዳል: የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ
- ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ለሊቃውንት ጉባኤው ትእዛዝ ሰጠ
- የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
- ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው [የአየር ሽፋኑ]ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
- ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ቆጠራ ለማካሄድ ከብር 29 ሚልዮን በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡን መዘገባችን የሚታወስ ሲኾን ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት የሚካሄደውን ቆጠራ ክንውን በቀጣይ የምንመለከተው ይኾናል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልኾነውን፣ በማስመሰል የሚነገረውንና የሚጻፈውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመኾኑም እውነተኛውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይኾን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሊቃውንት ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት በምልአተ ጉባኤው ላይ የተነበበውንና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጀውን የመነሻ ጽሑፍ አብራርቶ፣ አስፍቶና አምልቶ ለግንቦት፣ ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በቅርቡ በተካሄደው ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፥ ኢትዮጵያ ከአይሁድ በፊት ጀምሮ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንታ መኖሯን፣ ክርስትናም ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስቶስ ባረገበት ዓመትና ቅዱሳን ሐዋርያት ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት በ፴፬ ዓ.ም. መኾኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት በማስረዳት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ጋራ መጠያየቃቸው ይታወሳል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት የጀመረውንና ለዐሥር ቀናት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው ባለ28 ነጥብ መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አካትቷል፡-
- ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሞያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድ የታየው የሥራ መዋቅር ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም አይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
- ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲኾን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ ፳፻፭ ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኮሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊ እንደመኾኗ ኹሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ኾነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሞያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጎም በሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት የታደለ ሲኾን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ፳፻፮ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሄድበት ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
- በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
- በውጭ አገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋራ ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
- ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ኹኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመኾኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለኾነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋራ ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም. ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፡-
2. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል – የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፣ የሕንፃዎችና ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይ ሓላፊ
3. ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ – የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመምረጥ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በተመለከተ ኮሌጁን ማጠናከር አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ለኮሌጁ ዋና ዲን እንዲሾም ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡