ዓርብ 15 ኖቬምበር 2013

የ2005 ዓ.ም የቤተክርስቲያኒቱ ሀገራዊ ገቢ አንድ ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ተጠጋ



(አንድ አድርገን ህዳር 6 2006 ዓ.ም )፡- ዐዋጅ ነጋሪ ተብሎ ጥቅምት 2006 ዓ.ም በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ  የተዘጋጀው መጽሔት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር በሀገር ውስጥ ብቻ  የሚተዳደሩ 50 የሀገረ ስብከቶች ጠቅላላ ገቢ የሚያሳይ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡ በሰባካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የወጣው ስታስቲክሳዊ መረጃ   የእያንዳንዱን አህጉረ ስብከት የ2005 ዓ.ም የዘመኑን ገቢ ያሳያል፡፡ እንደ መረጃው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በገቢ መጠን ከሁሉም በከፍተኛ ሁኔታ ልቆ ይታያል ፡፡ ጠቅላላ ገቢውም 322,739,515 ( ሶስት መቶ ሃያ ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ አስራ አምስት) ሲሆን  ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀጥለው  
1.     አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት               322,739,515.29

2.    ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት                  46,330,546.99

3.    የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት              32,843,596.64

4.    ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት              29,805,415.24

5.    ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት                25,853,270.26

6.    ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት            21,894,699.00

7.    ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት                20,456,331.63

8.    አርሲ ሀገረ ስብከት                      19,297,272.45

9.    መቀሌ ሀገረ ስብከት                     18,352,795.05

10.  ምስቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት               17,522,762.00

11.    ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት              16,896,645.44
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ከ15 ሚሊየን ብር በላይ አመታዊ ገቢ የሰበሰቡ ሲሆኑ ፤ ከበስተመጨረሻ ከ47-50 ደረጃ ላይ የተቀመጡት ከምባታ ጠንባሮ ሀገረ ስብከት ፤ ከሚሴ ሀገረ ስብከት እና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ከ አንድ ሚሊየን ብር በታች ዓመታዊ ገቢ እንዳስገቡ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መረጃው ከገቢው የአህጉረ ስብከት 20 በመቶ እና የጠቅላ ቤተክህነት 35 በመቶ የገንዘብ መጠኑ ይጠቁማል፡፡ ይህ ሪፖርት በቤተክርስያቱ ስር የሚተዳደሩ ከሀገር ውጪ የሚገኙ ሀገረ ስከቶችን አይጨምርም፡፡ በጠቅላላው ቤተክርስቲያኒቱ በ2005 ዓ.ም የዘመኑ ገቢ ጠቅላላ 812,742,638.00 (ስምንት መቶ አስራ ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ አርባ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ 300 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ሀገራዊ ገቢ ያላት ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውስጥ ብቻ ይህን ያህል ብር ልትሰበስ ችላለች፡፡ መሰረታዊው ነገር ይህን ያህል ብር መሰብሰብ መቻሉ ሳይሆን ይህ ብር በምን አይነት የቤተክርስያኒቱን ችግር በሚቀርፉ ስራዎች መዋል አለበት? የሚለው ነጥብ ነው ፡፡  በአሁኑ ሰዓት ከ40 ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላት ቤተክርስቲያን የሚረባ ካህናትና ማሰልጠኛ ኮሌጅ የላትም ፤ በተቃራኒው ከአንድ ሚሊየን የማይዘሉት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በአዲስ አበባ  ለመላ ሀገሪቱ ላይ ላሉ የእምነት ተከታዮቻቸው ከቫቲካን በተገኝ እርዳታ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትልቅ የትምህርት ተቋም እያስገነቡ ይገኛሉ ፡፡ ይህን ዩኒቨርሲቲ ለመጨረስ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ያገኝነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ስለሆነም ትውልዱ የአባቶቹን የእምነት መስመር ተከትሎ የጠለቀ ቤተክርስቲያን እውቀት ያለው ፤ ማዕበል የማንገላታው ቀጣይ ትውልድ ለመፍጠር ቤተክርስቲያኒቱ ደረጃውን የጠበቀ የማስተማሪያ እውቀት የማስገብያ ተቋም መገንባት ይኖርባታል ፡፡ ይህ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ፤ ዛሬ በእምነት እና በእውቀት የተኮተኮቱ መምህራን ካላፈራች ነገ ምዕመኑ በተኩላ ገበያ ሰንሰለት ውስጥ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡ በንዝህላልነትና ሥራዋችን በአግባቡ ካለመሠራታቸው የተነሳ ባለፉት 20 ዓመታት ያጣቻቸውን ነፍሳት በትምህርት መመለስ ይኖርባታል፡፡ ስለዚህ የተሰበሰበው ገንዘብ ከቁጥር በላይ የሚታይ የሚጨበት ሥራ መስራት መቻል አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...