2014 ሜይ 22, ሐሙስ



ግንቦት 12 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ

                                                                                     በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ

>+"+ እንኩዋን ለዓለም ሁሉ መምሕር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅና ለኢትዮዽያውያኑ ቅዱሳን ተክለ ሃይማኖት ወክርስቶስ ሠምራ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

=>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው?

=>ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::




+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

+ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

+ከዚህች እለት በሁዋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

+ከዚህ በሁዋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኩዋን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::

=>ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
-ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
-አፈ በረከት
-አፈ መዐር (ማር)
-አፈ ሶከር (ስኩዋር)
-አፈ አፈው (ሽቱ)
-ልሳነ ወርቅ
-የዓለም ሁሉ መምሕር
-ርዕሰ ሊቃውንት
-ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
-ሐዲስ ዳንኤል
-ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
-መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
-ጥዑመ ቃል - - -

=>እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ ይክፈለን::

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56 ዓመታት በሁዋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመዋል::

=>እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

=>ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር ያድለን::

=>ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር)
2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን የተቀበለችበት)
4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
4.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
5.ቅዱስ ድሜጥሮስ

=>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...