(ክፍል አንድ) በዲያቆን ኤርምያስ ነቢዩ
መነኮሰ ማለት ከዓለም የራቀ፤ መናኝ ማለት ሲሆን
የተጀመረውም የአዳም ሰባተኛ ትውልድ በሆነ በሔኖክ ነው። ይኸውም
ይታወቅ ዘንድ የሔኖክ አባት ያሬድ ውሉደ እግዚአብሔር የተባሉት የሴት ልጆች በሰይጣን ወጥመድ ተይዘው፤
ከእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው
ከደብር ቅዱ ሲወርዱ እንደ ተነሱ በሰማ ጊዜ አስጠርቶ እንዲህ ያለውን ክፉ ሥራ እንዳይሰሩ ተቆጥቷቸው እንደ ነበር
የቤተ ክርስቲያን
መጻሕፍት ይነግሩናል። እናንተ የሴት ልጆች፤ ወዮላችሁ፤ ተው፤ የአባታችሁን
መሃላ አታፍርሱ። የ እግዚአብሔርን ት ዕዛዝ የተወ፤ ያባቱን መሐላ
ያፈረሰ፤ ከደብር ቅዱስ የወረደ፤ ከአዋልደ ቃየን ጋርም ኃጢአት የሠራ ተመልሶ ወደ ደብር ቅዱስ አይገባም ብሎ
መክሯቸው ነበር። እነርሱ ግን ምክሩን አቃልለው ከደብር ቅዱስ ወርደው ከቃየን ልጆች ጋር ዝሙት
እየፈጸሙ ይዘፍኑ ይሳለቁ ጀመር።
ሔኖክ በዚህ እያዘነ ከኖረ በኋላ ከተወለደ ጀምሮ
ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሲሆነው ከዓለም ተለይቶ በጾም ጸሎት ጸንቶ ወደ አንጻረ ገነት ሄዶ በግብረ ምንኩስና ኖሯል። በዚያም ለስድስት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ብሔረ
ሕያዋን አርጓል። ዘፍ 5፤24 ዕብ 11፤5። ኤልያስም ሔኖክን አብነት አድርጎ በጾም በትኅርምትና በድንግልና ከኖረ በኋላ
በሠረገላ እሳት ወደ ሰማይ አርጓል። 2ኛ ነገ 2፤11 በዚህም መዓስባንና ደናግላን በሥር ዓተ ምንኩስና ጸንተው ንጹሐን የመንፈስ
ቅዱስ አርጋብ ሆነው ወደ መንግሥተ ሰማይ ማረጋቸው ከሔኖክና ከኤልያስ ምሳሌነት እንረዳለን። ሔኖክና ኤልያስ መነኮስ ማለት ከዓለም
የራቀ በመሆኑ ከዓለም ርቀው የሰሩት የብቸኝነት ሥራቸው መነኮሳት ያሰኛቸዋል።
በተጨማሪም የእግዚአብሔር አገልጋይ (ካህን) ሆኖ
ጠጉሩን ሳይላጭ ፤ ጥፍሩን ሳይቆረጥ፤ ጠጅ ሳይጠጣ፤ በስንዴና በወይን እያስታኮተ የኖረው ርዕሰ ባህታዊ መልከ ጼዴቅም ለመነኮሳት
አብነታቸው ነው። ዘፍ 14፤ 8-23 ዕብ 7፤1-5። ለመዓስባን ሥርዓተ
ምንኩስናን የጀመረላቸው ሔኖክ ለደናግላን ደግሞ ኤልያስ ነው። ይኸውም
ለአዲስ ኪዳን ምንኩስና መሰረት ነው ማለታችን ነው። ጌታችን ሐዋርያትንና
አርድዕትን የመረጠው ከመዓስባንም ከደናግላንም ነው። ለሁሉም እክል
ሥልጣን በመስጠትም ተካክለው መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ አድርጓል።
ዮሐንስ መጥምቅም ሔኖክንና ኤልያስን አብነት በማድረግ በገዳም ተወስኖ የግመል ጸጉር ለብሶ፤ ወገቡን በጠፍር መታጠቂያ
ታጥቆ፤ የማርና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ በግብረ ምንኩስና ጸንቶ ኖሯል።
ማቴ 3፤4 ሉቃ 1፤15
መናፍቃን እንደሚሉት
ምንኩስና “ሰው ሰራሽ ጽድቅ” ሳይሆን የ እግዚአብሔር ሰዎች ገንዘብ ያደረጉት
የ እግዚአብሔር ጸጋ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ቤቱን፤ ወንድሙንና እህቱን፤ አባቱንና እናቱን፤ ሚስቱንና ልጆቹን እርሻውንም ሁሉ ትቶ በስሜ አምኖ የተከተለኝ መቶ እጥፍ ይቀበላል።
የዘለዓለም ድኅነትም ያገኛል ብሎ ስለ መ ዓረገ ምንኩስና ደገኛነት የተናገረውን ቃል በመዝለል “ምንኩስና ከአምላክ ሕግ የተለየ
ከንቱ ሰው ሰራሽ ጽድቅ ነው እያሉ መሣለቅ ከወንጌል ጎዳና መውጣትን ያመለክታል። ማቴ 19፤29
ቀጥሎም በሉቃስ ወንጌል “አንድ ሰው አቤቱ ልከተልህ
እወዳለሁ” ነገር ግን አስቀድሜ የቤቴን ሰዎች እሠራ ዘንድ ፍቀድልኝ ቢለው፦ “ማንም በእጅ ዕርፍን ይዞ እያረሰ ወደ ኋላው የሚመለከት
ለ እግዚአብሔር መንግስት የተዘጋጀ አይደለም” ብሎ የመለሰለት ቃል የምንኩስናን ሥር ዓት ለመሥራት መሆኑ የሚታበል አይደለም። ሉቃ
9፤28
የሰው ሃብቱ ልዩ ልዩ ስለሆነ የተቻለው በድንግልና
መንኩሶ እንደ ኤልያስ እግዚአብሔርን ያገለግላል። ያልተቻለው ደግሞ
እንደ ሔኖክ ቤት ሠርቶ ሚስት አግብቶ ሕጻናትን ወልዶ ቀጥቶ አሳድጎ በዚህ ዓለም ከኖረ በኋላ ይመነኩሳል። ይህም ሐዋርያትን አብነት አድርጎ ቤቱን፤ ንብረቱን፤ ሚስቱንና ልጆቹን ትቶ
የምናኔን ሥራ ይሠራል ማለት ነው። በዚህ ዓለም እየኖሩ እግዚአብሄርን
ከምንም በላይ ደስ ያሰኙ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ልብ ሳይከፈል በመላ
ኃይል እግዚአብሄርን ለማገልገል ምንኩስና መልካም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ
“እኔ ኃዘን እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው በሚያስደስተው
ገንዘብ እግዚአብንሔርን ያስበዋልና። ሚስት ያገባ ግን ሚስቱን በሚያስደስታት
ገንዘብ የዚህን ዓለም ንብረት ያስባል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የ እግዚአብሔርና የሰው ፈቃድ ይለያያል። ያለው ለዚህ ነው።
1ኛ ቆሮ 7፤32-34
ከዚህ በላይ ስለ ምንኩስና መዘርዘራችን የ እግዚአብሔር
ጸጋ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ጥንት አዳምና ሔዋን ወንድና ሴት ሆነው መፈጠራቸውን ፤ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ “ወንድ አባቱንና እናቱንትቶ ከሚስቱ ጋር ይከተላል፤ ባልና
ሚስት አንድ አካል ይሆናሉ። እንዲህም ከሆነ አንድ አካል እንጂ ሁለት
አካል አይባሉም። እግዚአብሄር አንድ ያደረጋቸውን ሰው አይለያቸውም። ከዚህስ አስቀድሞ በኦሪት የተጻፈውን አልተመለከታችሁምን?” ብሎ ማስተማሩን
በመዘንጋት አይደለም። ዘፍ 3፤24 ማቴ 19፤4-6
ይቆየን...........
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ