2014 ጁላይ 9, ረቡዕ

ሐምሌ 3 ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ


                                                            በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ
 (ናታኒም ጡመራዊ መጽሔት ሐምሌ 2እንኳን  ለዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+" ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ "+

=>ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን "ዓምደ ሃይማኖት-የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ አባ ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::

+ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::




+ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

+በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን 2 አካል: ባሕርይ ነው (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት)

+ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ::

+የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

+የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

+ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ (የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን የአምላክ እናት: ዘላለማዊት ድንግል: ፍጽምት: ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

+ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

+እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሃዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን::

=>ሐምሌ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
2.ቅዱስ ክልስቲያኖስ ዘሮሜ (ታላቅ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት)
3.አባ ሉቅያስ ኤዺስ ቆዾስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

=>+"+ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ:: የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ: እስከ ዘለዓለምም ያው ነው:: ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምሕርት አትወሰዱ:: ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም:: በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና:: +"+ (ዕብ. 13:7)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...