ሐሙስ 24 ጁላይ 2014

ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?




ባለፈው ጽሁፋችን ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዳናውቅ ያደረጉንን ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ለማየት ሞክረናል ከዚህ ቀጥለን ደግሞ ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ እንድንችል ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን፡፡
1.   በሃይማኖት  ትምህርት መብሰል
የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠውን የማሰብ የማገናዘብ ፀጋውን በእውቀት የማዳበር  የማስፋፋት የማጣጣም ሓላፊነት አለበት  ይህ ካልሆነ በሁሉ ነገር ጥሬ ይሆንና  በነፍሱ እና በሥጋውም ሲቸገር ይኖራል እንኳዋን ከእግዚአብሔር ጋር ይቅርና ከሰው ጋርም መኖር ይቸገራል፡፡ በሃይማኖት ትምህርት የበሰለ ሰው ደግሞ እግዚአብሔር የሚወደውን  ሁሉ ለመረዳት አቅም ይኖረዋል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዴት እንደሚገለጥ  መረዳት ይችላል ::  ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች  ምሳ 2፤ 10  የብዙ ሰው ችግር  ሆኖ የሚታየው በአብዛኛው የሃይማኖት ትምህርት እውቀት ማጣት ነው ፡፡ እንደሚታወቀው  ሕዝበ ክርስቲያኑ መሠረታዊ  የሃይማኖት ትምህርትን  እንደ አስኮላው ትምህርት በየአጥቢያቸው መርሃግብር  ወጥቶ መማር እስካሁን አልተለመደም ይሁን እንጂ አሁን ዘመኑ የግድ ይህንን ማድረግ እንደሚገባ  ያስገድዳል፡፡ ሁሉም ሰው ስለሃማኖቱ ጠንቅቆ ማውቅ ሲችል ነው እግዚብሔር የሚወደውን ማውቅና ማሳወቅ የሚችለው ይህ ካልሆነ ግን  ወደ ስህተት መንገድ ተያይዞ መጥፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ለዚህ ነው ነቢዩ ፤ ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአልአንተም እውቀትን ጠልተሃልና…. በማለት የተናገረው፡፡ ሆሴ 4፤ 6
ይህ ዘመናችን እጅግ በጣም የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ ተአምራት ሚመስሉ ግን ያልሆኑ እውነት  የሚመስሉ ሐሰት የሆኑ  በሃይማኖት ትምህርት በስለናል አውቀናል የሚሉትን እንኳን ሳይቀር የማረኩ ነገሮች የሚታዩበት ዘመን ነው  እንዲህ ያለውን ዘመን ደግሞ በሃማኖት ትምህርት የበሰለ ሰው ካልሆነ በስተቀር ሊቋቋመው አይችልም :: ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ  እንደተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፡፡ ተብሎ እንደተጻፋ ቆላስይስ 2፤7
2.ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ማማከር
    ሌላው እጅግ በጣም ሊተኮርበት የሚገባ  ነገር ግን እስካሁን በአብዛኛው ኢየተዘነጋ የመጣው ነገር  በቤተ ክርስቲያን  የሚታወቁ  ሊቃውንትን የማማከር ተግባር ሊተኮርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም  ብዙ ጊዜ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በዘፈቀደ ሲመሩት ይስተዋላል ወደ ተለያዩ ገዳማትም ሲገጓዙ ከጉዞው በፊት  ማማከርን መልመድ ያስፈልጋል፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ፤ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ ፡፡ ኢዮ 8፤8 በማለት የተናገረው ለዚሁ ነው፡፡ አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል ሽማግሌዎችን ጠይቅ  ይነግሩህማል ዘዳ 32፤7
አንድ በሓላፊነት ላይ ያለ ሰው የሚሰራው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የግድ አማካሪ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወቱም ውጤታማ ሊሆን የሚፈልግ ሰውም አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ከፉ ምክርም እንዳለ መጠንቀቅ  እንደሚገባ መዘንጋት የለበትም እውነተኞቹ  የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ብዙ ጊዜ በየ ካፍቴርያውና በመሳሉት ቦታም ስለማይገኙ ምእመናን መቀላሉ ስለማያገኗቸው ለክፉ መካሪዎች እንዳይጋለጡ  መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡
3.ከኃጢአት መንጻት     
ኃጢአት ሰው መልካም ሆነውን ነገር ተግባራዊ እንዳያደርግ የሚያደርግ የሰው ልጆች የመንፈሳዊ ሕይወት ማነቆ ነው፡፡ የሚጠጋውም ርኩስ መንፈስ ብቻ ነው ከዚህ የተነሳ መንፈሳዊ ነገር ማሰብም ሆነ መሥራት አይችልም ፡፡መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፡ ዘፍ 4፤7  /  ሰው በኃጢአት በኖረ ቁጥር መልካም አስተሳሰቡ ቀናነቱ ሌሎችም መንፈሳዊ ተግባራትና ሐሳብ እየመነመኑ ይሄዳሉ ብሎም ይጠፋሉ ለዚህ ሁሉ መነሻው ኃጢአት ነው፡፡የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፡ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም፡ኢዮ 18፤5 / ተብሎ እንደተጻፈው ፡፡ ስለዚህ ሰው ከኃጢአት ሳይነጻ ፈቃደ እግዚብሔርን ማውቅ መረዳት አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በሰው በጎ ሥራ ከተደሰተ ለሰው ሁሉ የሚያስፈልገውን የሚያውቅ አምላክ ነውና በጊዜውና በሰዓቱ ሁሉንም ያከናውናል፡፡ እግዚአብሔር የሚያደርገው ሁሉ በጎ ነውና፡፡



 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...