ቅዳሜ 6 ሴፕቴምበር 2014

አዲሱ ዓመት - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ፩)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 የምወዳችኁ ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የደስታ የሰላምና የጤና እንዲኾንላችኁ ትሻላችሁን? እንኪያስ ገና ከዥመሩ በስካር፣ በዘፈን፣ በገቢረ ኀጢአት ለማሳለፍ አታቅዱ፡፡ የአዲሱ ዓመት የመዠመሪያውን ዕለት ብቻ ሳይኾን እያንዳንዱን ቀን በገቢረ ኀጢአት አትዠምሩት፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ፣ ምግባር ትሩፋት በመሥራት አሐዱ በሉ እንጂ፡፡ ዕለታት ክፉዎች ወይም ጥሩዎች የሚኾኑት በተፈጥሮአቸው እንደዚያ ኾነው አይደለም፡፡ ዕለቱን ክፉ ወይም ደግ እንዲኾን የምናደርገው እኛው ነን፡፡ የአምናው ማግሰኞ ከዘንድሮ ማግሰኞ የተለየ አይደለም፡፡ የተለየ የሚያደርገው የእኛ ብርታት ወይም ስንፍና ብቻ ነው፡፡
የጽድቅን ሥራ የምንሠራበት ከኾነ አዲሱ ቀን ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመት ለእኛ መልካም ነው፡፡ ኀጢአት የምንሠራበት ከኾነ ግን ቀኑ ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመትም ክፉና መከራ የመላበት ይኾንብናል፡፡ አዲሱን ዓመት በበጐ ሥራ የምንዠምረው ከኾነ በዓመቱ በምናደርገው ማንኛውም ክንውን ላይ በጐ ተጽዕኖ ያሳድርብናል፡፡ በትግሃ ሌሊት፣ በቀዊም፣ በጾም በጸሎት እንድንበረታ ስንቅ ይኾነናል፡፡ በስካር፣ በዘፈን፣ በኀዘን የምንዠምረው ከኾነ ግን ዓመቱ ሙሉ እንዲኽ የተጐሳቈለ ዓመትን እናሳልፋለን፡፡ ሕይወታችንን በከንቱ እንገፋለን፡፡ ዲያብሎስም ይኽን ጥንቅቅ አድረጐ ስለሚያውቅ ዓመቱን በገቢረ ኀጢአት እንድንዠምረው እየቀሰቀሰ ነው፡፡ ፈቃዳችንን አጥፍቶ፣ ዓይነ ልቡናችንን አሳውሮ በዘፈን፣ በስካር፣ በዋይታ እንድንዠምረው በተለያየ መንገድ እየለፈፈ ነው፡፡
 ሰነፍ ሰው “ቀኑ ክፉ ወይም መልካም የሚኾነው በእኔ ምክንያት አይደለም” ብሎ ያምናል፡፡ እንዲኽ በማመኑም ክፉ ነው ብሎ በሚያስበው ቀን ገቢረ ጽድቅ መሥራት እንደሚቻል አያስብም፡፡ ቢያደርግም ትርጕም እንደሌለው አድርጐ ይቈጥሯል፡፡ የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በተመቻቸለት ቀንም ልል ዘሊል ከመኾኑ የተነሣ ምግባር ትሩፋት ለመሥራት አይሽቀዳደምም፡፡ ስንፍናው ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት አይረዳም፡፡ ድኅነቱን ሳይፈጽም ዕድሜውን ኹሉ በከንቱ ይገፋል፡፡ እንዲኽ ያለ የሥጋም የነፍስም ጕዳት እንደሚያገኘው ዲያብሎስ ዓይነ ልቡናውን ስለሚያሳውርበት ከአጋንንት ወጥመድ ለመሸሽ ዓቅምን ያጣል፡፡
 ዲያብሎስም ዕለት ዕለት ይኽን እንዳንገነዘብ በተለያየ ማጥመጃ መንገዶች እኛን ለመጣል ይሯሯጣል፡፡ አንዱ መንገድም ስለ ክርስትና ሕይወታችን ግድ እንዳይኖረን ማድረግ ነው፡፡ በዚኽም ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችንን ያሳጣናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በገቢር እንድንሰድብ ያደርገናል፡፡ ነፍሳችንን በቆሸሸ ስፍራ ተወሽቃ እንድትቀር ያደርጋታል፡፡
 የምወዳችኁ ልጆቼ! እኛ ግን ይኽን ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ከኀጢአት በቀር ክፉ ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ከምግባር ከትሩፋት በቀርም መልካም ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዚኽም ዘወትር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን ልንኖር እንዲገባን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡ መጠጥ ደስታን አያመጣም፤ ደስታን የሚያመጣው ጸሎት ነው፡፡ ደስታን የምናገነኘው ቃለ እግዚአብሔርን ከመስማት እንጂ ከስካር አይደለም፡፡ ስካር የነፍስ መታወክን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ተመስጦን ያመጣል፡፡ ስካር ሁካታን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ሁካታን ያርቃል፡፡ ስካር ዓይነ ልቡና እንዲጨልም ያደርጋል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን የጨለመው ዓይነ ልቡናችን ብሩህ እንዲኾን ያደርጋል፡፡ ስካር የኀጢአት ጓዝ ይዞ ይመጣል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን አዲስ የሚመጡትን ብቻ ሳይኾን የነበሩትንም ያስወግዳል፡፡
 ልጆቼ! የዚኽን ዓለም ደስታ ንቆ ሰማያዊ ደስታን እንደመሻት ያለ ጥበብ ምንም የለም ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ገንዘብ የምናደርግ ከኾነ፣ ለሰማያዊ ሕይታችን ቅድሚያን የምንሰጥ ከኾነ የዚኽ ዓለም ዝባዝንኬ ቢቀርም አይከፋንም፡፡ አንድ ሰው ባለጸጋ ስለኾነ ቅናት አይይዘንም፡፡ ምንም ምድራዊ ሀብት ባይኖረንም ድኾች እንደኾንን አናስብም፡፡ ባለ ጸጋውን ክርስቶስ የያዘ ሰውስ እንዴት ድኻ ይባላል? በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በዓል ማድረግ ማለትም ይኸው ነው፡፡
 እግዚአብሔር የሚወዳችኁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! አንድ ክርስቲያን በዓልን ሲያከብር ሳምንትን ወይም ወርን ወይም ዓመትን ጠብቆ መኾን የለበትም፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር እንደሚስማማ አድርጐ ዕለት ዕለት በዓል ሊያደርግ ይገቧል እንጂ፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር የሚስማማ በዓል ማለትስ ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምን እንደሚለን አብረን እናድምጠው፡- “በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” /1ኛ ቆሮ.5፡8/፡፡ ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ዕለት ዕለት በዓልን ያከብራል፡፡ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተጠበቀለት ነው፡፡ ከሰማያዊው ማዕድና መጠጥ ተካፍሎ ሐሴት ያደርጋል፡፡ በዚኽ ምድር ላይ የሚደረጉ ጊዜያዊ ክንውኖች ስለቀረበት የኾነ ነገር እንደቀረበት አያስብም፤ ርሱ ያገኘው ከዚኽ በእጅጉ የሚልቅ ነውና፡፡ ነፍሱን ከሚያቆሽሹ ገቢረ ኀጢአቶች ራሱን ይጠብቃል፡፡
  በገቢረ ኀጢአት ተሰማርተን ሳለ ሺሕ ጊዜ በዓላትን ብናከብር ግን እንዳከበርን ልንቈጥረው አይገባንም፡፡ ያከበርነው የበዓል ቀን (በዓል ማለት ደስታ ማለት ነው) ሳይኾን የኀዘን ቀን ነውና፡፡ ነፍሴ በኀጢአት ቀንበር ተይዛ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሳለች የደስታን ቀን ባከብር ለእኔ ምን ጥቅም ያመጣልኛል?
 እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የምትወዱት ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የእውነት አዲስ ዓመት እንዲኾንላችኁ ካሻችኁ ነፍሳችኁን ከኀጢአት ቀንበር አላቋት እንጂ ድጋሜ በኀጢአት ሸክም አትጫኗት፡፡ አሮጌው ዓመት እንዳለቀ ስታዩ እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ወደሌላ ዘመን አሸጋግሯቸዋልና እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ልቡናችኁንም ውቀሱት፡፡ በዕሜአችኁ ስንት ጊዜ እያለፈ እንደኾነ እያሰባችኁም ራሳችኁን እንዲኽ ብላችኁ ጠይቁት፡- “ቀናት እየሮጡ ነው፡፡ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው፡፡ የዕድሜዬ መንገድም እየተጋመሰ ነው፡፡ ታድያ ምን በጐ ምግባር ያዝኩ? ከዚኽ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው፡፡ ታድያ ምን የጽድቅ ሥራ ሠራኹ? በዚኽ ዕድሜዬ መሥራት የነበረብኝ ምግባር ትሩፋት ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ አልችልም፡፡ ታድያ ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ የማልችላቸውም የጽድቅ ሥራዎች (ፆም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ አገልግሎት፣… ዕድሜ ሲገፋ ይከብዳሉና) እንዳቅሜ እያደረግኩ ነውን?”
ተወዳጆች ሆይ! አዲስ ዓመት ሲመጣ እነዚኽን ነገሮች በጥንቃቄ ልናስብባቸው ይገባናል፡፡ ይኽን እያደረግንም ስለቀጣዩ ዓመት እናስብ፡፡ ይኽን የምናደርግ ከኾነ “ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፤ ዓመቶቻቸውም በችኰላ” አይባልብንም /መዝ.78፡3/፡፡ ዕለት ዕለት በዓልን እናድርግ ብዬ የገለጥኩላችኹም ይኸው ነው፡፡ የእኛ በዓል ዘወትር መኾን ይገባዋል፡፡ የክርስቲያኖች በዓል በዓመታትና በቀናት ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በሳምንት፣ በወር፣ በዓመት የሚከበሩ በዓላት እንዲኖሩ ማድረጓ ዘወትር ከዚኹ ልንርቅ እንደማይገባ ማሳሰቧ እንጂ ሌላ አይደለምና፡፡ ይኽን በዓል በየዕለቱ ማድረግም ለኹሉም ይቻላል፤ ለድኻውም ለባለጸጋውም ይቻላል፡፡ በዓልን ለማድረግ (የጽድቅ ሥራን ሠርቶ ሐሴት ለማድረግ) የሚያስፈልገው ቅን ልቡና እንጂ ገንዘብ አይደለምና፡፡ ወዳጄ ሆይ! ገንዘብ የለኽምን? ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርግ፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምታደርግ ከኾነ ገንዘብ ካላቸው በላይ ባለጠጋ ነኽ፡፡ “እንዴት?” ትለኝ ይኾናል፡፡ እኔም እንዲኽ ብዬ እመልስልሃለኹ፡- የእነዚያ (የባለጠጐቹ) ገንዘብ ያልቃል፡፡ ያንተ ግን ብል አይበላውም፡፡ ጊዜ አይለውጠዉም፡፡ አያልቅም፡፡ ወደ ሰማያት፣ ወደ ሰማየ ሰማያት፣ ወደ ምድር፣ ወደ አየራት፣ ወደ እንስሳቱ ዓይነት፣ ብዙ የብዙ ብዙ ወደሚኾኑት ዕፅዋት፣ ወደ ደቂቀ አዳም በጠቅላላው፣ ወደ መላዕክት፣ ወደ መላዕክት አለቆች፣ ወደ ኀይላት ተመልከት፡፡ እነዚኽ ኹሉ የአምላክኽ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ የእነዚኽን አምላክና መጋቢ ባርያ መኾን ድኻ መኾን አይደለምና ድኻ አይደለኽም ብዬ እነግርኻለኹ፡፡
 ተወዳጆች ሆይ! ቀናትን ቈጥሮ በዓል ማድረግ የክርስቲያን ግብር አይደለም፤ የአሕዛብ ግብር እንጂ፡፡ እንዴት? የክርስቲያኖች ተፈጥሮ በቀንና በወር የተገደበ አይደለምና፡፡ አገራችን ሰማይ ነው፡፡ ግብራችን ሰማያዊ ነው፡፡ ኅብረታችንም ከሰማያውያን መላዕክት ጋር ነው፡፡ በዚያ መዓልት ለሌሊት ስፍራውን አይለቅም፡፡ ሌሊትም በተራው ለመዓልት አይለቅም፡፡ እዚያ ኹሌ መዓልት ነው፡፡ እዚያ ኹል ጊዜ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚኽ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ” እንደተባልን ኹል ጊዜ ማሰብ ያለብን ይኽንን ነው /ቈላስ.3፡1/፡፡ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችን ከዚኽ ምድራዊ አቈጣጠር በላይ ነው፡፡ በንጽሕና በቅድስና እየኖርን ዘወትር በዓልን የምናከብር ከኾነም የዚኹ ዓለም ሌሊት ለእኛ ሌሊት አይደለም፤ መዓልት ነው እንጂ፡፡ ዘመናችንን በሙሉ በገቢረ ኀጢአት፣ በስካር፣ በዘፈን የምናሳልፈው ከኾነ ግን መዓልቱ ለእኛ መዓልት አይደለም፤ ሌሊት ነው እንጂ፡፡ ፀሐይዋ ብትወጣም ልቡናችን ገና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖራልና ቀን እንደወጣ አይቈጠርም፡፡
ይቀጥላል…

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...