ማክሰኞ 23 ሴፕቴምበር 2014

መጽሐፈ ጤፉት ለኅትመት በቃች


አትም ኢሜይል
መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም.
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
a tefut 2007 1የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡንና ሌሎችንም ታሪኮች ያያዘው መጽሐፈ ጤፉት በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት አማካይነት ከግእዝ ወደ አማርኛ ተተረጉማ ለኅትመት በቃች፡፡

መጸሐፉ በሰባት ምዕራፎች ተከፍሎ የቀረበ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ በዐፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት የነበረውን የግብጻውያንና የኢትዮጵያውያንን ግንኙነት የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ በዐፄ ዳዊት አማካይነት ቅዱስ መስቀሉ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በዐፄ ዳዊት ግዛት ስለመቀመጡ ይናገራል፡፡

ሦስተኛው ምዕራፍ ስለ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና ቅዱስ መስቀሉን ወደ መስቀለኛው የአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ ስለማስቀመጣቸው በስፋት ይገልጻል፡፡ ዐራተኛው ምዕራፍ ከቅዱስ መስቀሉና መስቀሉ ስለተቀመጠባት የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ደብር ክብር ጋር ተያይዞ በንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ የተጻፉት ደብዳቤዎችን አካትቷል፡፡

አምስተኛውና ስድስተኛው ምዕራፎች ግሸን ደብረ ከርቤ ጌታችን በተሰቀለበት በቅዱስ መስቀሉ መክበሩንና ለቦታው ስለተሰጠው ቃል ኪዳን ይዳስሳል፡፡ ሰባተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ መስቀሉ በክብር የተቀመጠበትን የግሸን ደብረ ከርቤ አምባና የአካባቢው ሹማምንት ስለተሰጣቸው ትእዛዛትና ሌሎችንም መረጃዎች ያብራራል፡፡

ሊቀ ሊቃውንት ተክለ ማርቆስ ብርሃኑ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ደብር አስተዳዳሪ ስለ መጽሐፉ መታተም ሲገልጹ “መጽሐፈ ጤፉት ለበርካታ ዓመታት የቤተክርስቲያናችንን የታሪክ፣የቀኖና፣ የሥርዐትና ሌሎችም ሰነድ ይዛ በክብር ተጠብቃ የቆየችና በየዓመቱ በውስጧ የዘችው ቃልኪዳን እየተነበበ የኖረ ሲሆን አሁን ታትሞ ለምዕመናን እንዲደርስ መደረጉ የሀገርንና የቤተክርስቲያን ታሪክ አውቀን ሥርዐቱንና ቃል ኪዳኑን ጠብቀን ለቦታው የሚገባውን ክብር እንድንሰጥ ያስችላል፡፡” ብለዋል፡፡

a tefut 2007 2መጽሐፈ ጤፉት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካይነት እንደተጻፈና በየዓመቱ፤ በተለይም በመስከረም 21 እና መጋቢት 10 ቀን የመስቀሉ አመጣጥና በግሸን ደብረ ከርቤ ስለተሰጠው ቃል ኪዳን በመተርጎም ለምእመናን ይሰማል፡፡

መጽሐፈ ጤፉትን ማግኘት የሚፈልጉ በግሸን ደብረ ከርቤና በአዲስ አበባ በ0911238610፣ 0911616880 በመደወል ማግኘት እንደሚቻል ከመጽሐፉ የኅትመት አስተባባሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...