- ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
- ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡
- አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡
- አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት፡፡
- አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
* * *
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በአንገታቸው ላይ ክር ያስራሉ፤ ለሕፃኖቻቸውም ክርስትና ሲነሡ ክር ያስሩላቸዋል፡፡ በሕፃናቱም ኾነ በዐዋቂዎቹ ክርስቲያኖች አንገት ላይ የሚታሰረው ክር በግዕዝ ማዕተብ በአማርኛ ማተብ ይባላል፡፡ ቃሉ ወጣው ዐተበ ካለው ግዕዛዊ ግስ ነው፡፡ ዐተበ ፍቺው አመለከተ፣ ባረከ ማለት ነው፤ ማዕተብ ፍቺው ከዚኽ ይወጣል፡፡ ምልክት ማለት ነው፡፡ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የክር ማተብ ለሃይማኖት ምልክትነት ወይም መታወቂያ ከመኾኑ በፊት፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃይማኖት አባቶች ከጣዖት አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበራቸው፡፡ ስለ ታላቁ የሃይማኖት አባት ስለ ጻድቁ አብርሃም የሃይማኖት ማኅተም(ምልክት) ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የኾነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፡፡›› (ሮሜ ፪÷፲፩፤ ዘፍጥ.፲፯÷፱ – ፲፬)
በሥርዐተ ኦሪት ብኵርና ከጥንት ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ ኾኖ ስለሚቆጠር ብኵርና ላለው ኹሉ የአባት በረከት ከሌሎች ይልቅ በይበልጥ ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ኾኖ ስለሚሰጠው ብኵርና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፡፡ ብኵርና ማቃለል ዋጋ የሌለው ጸጸትን ያስከትል ነበር፡፡ ብኵርና ለዘመነ ሐዲስ ክርስትና ምሳሌ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ክርስትናውን ንቆ አቃሎ ዓለምን መስሎ የሚኖር ሰው፣ ለጊዜያዊ መብል ፍለጋ ብኵርናውን በሸጠው በያዕቆብ ወንድም ዔሳው ተመስሏል፤ ‹‹. . .ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚኽ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደተጣለ ታውቃላችኹና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና፡፡›› (ዕብ.፲፪÷፲፮፤ ዘፍጥ. ፳፭÷፳፱ – ፴፬፤ ፳፯÷፴ – ፵)
ብኵርና ለክርስትና ምሳሌ መኾኑ ከላይ ተገልጧል፡፡ ትዕማር ከይሁዳ መንትያ ልጆችን ፀንሳ በምትወልድበት ጊዜ በኵሩ እጆቹን ሲያወጣ አዋላጅቱ ቀይ ፈትል ለምልክት አስራበታለች፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ድርጊት በሐዲስ ኪዳን ሲተረጎም ከትዕማር የተወለደው በኵሩ ዛራ ለክርስቲያን ምሳሌ ሲኾን ቀዩ ፈትል ለክርስትናው ምልክት፤ ለማዕተብ ምሳሌ ኾኗል፡፡
አዋላጅቱ ለአጥማቂው ቄስ ምሳሌ ናት፡፡ ትዕማር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ስትኾን በኋላ የመጣው ፋሬስ በኵሩን ጥሶ ቀድሞ መወለዱና ከቀይ ፈትል አልባ መኾኑ በምሳሌያዊ ትንቢትነት፣ ከቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከተወለዱ በኋላ ክርስትናቸውንና ጥምቀታቸውን ክደው የእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ተቃዋሚዎች በመኾን ፊት ከተፈጠረ ጆሮ እንደ ቀንድ ብቅ ያሉ የመናፍቃንና የኢጥሙቃን (ኢአማንያን) ምሳሌ እንደኾኑ ያስረዳል፡፡ (ማቴ.፩÷፫፤ ዘፍጥ.፴፰÷ ፳፮ – ፴)
በዛራ ልማድ ጌታችን ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር አስራዋለች፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ለኖሎት ተገልጦ ምልክቱን እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፡- ‹‹ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲኹ፤ ምልክቱ ይህ ነው፡፡ ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ ታገኙታላችኹ፡፡›› (ሉቃ.፪÷፲፪) እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር እንዳሰረችው ‹‹ወወለደት ወልደ ዘበኵራ ወአሰርቶ መንኮብያቲኹ፤ የበኵር ልጅዋን ወለደች፤ አውራ ጣቱን አሰረችው፡፡›› ( ሉቃ.፪÷፯፤ የግእዝና አማርኛ ነጠላ ትርጉም አማርኛ ሒዲስ ኪዳን ይመልከቱ)
ድንግል እመቤታችን አውራ ጣት ማሰሯ ለክርስቲያኖች ማዕተብ ማሰር አብነት ኾኗል፡፡ ጣቱን ማሰሯ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይኸውም፡- ፩ኛ/ሕፃን ስለኾነ እንዲያጸናው፤ ፪ኛ/ጣቱን ባይታሰር ምትሀት ነው፤ ሰው አልኾነም ለሚሉ መናፍቃን ለክሕደታቸው ምክንያት ባገኙ ነበርና ምክንያት ለማሳጣት፤ ፫ኛ/ቀደም ብለን እንደገለጽነው ልማዳችንን አስቀረብን እንዳይሉ በዛራ ልማድ፤ ፬ኛ/ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ ከመስቀል አውርደው እንዲኽ አድርገው ይገንዙሃል ለሰው ቤዛ ለመኾን ልትታሰር መጣኽን፣ ስትል ነው በማለት መምህራነ ቤተ ክርስቲያን በአንድምታ ትርጓሜያቸው ያትታሉ፡፡
* * *
በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ክርስቲያን የኾነ ኹሉ ማተብ የማሰር ልምድ የጀመረው በሃይማኖተ አበው በድርሳነ ያዕቆብ እንደተገለጸው፣ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአምስተኛው ምእት ዓመት ያስተምር በነበረው በሊቀ ጳጳሱ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ዘመነ ስብከት ነበር፡፡ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡ መምህሩ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሲመሰክር በመለካውያን (ልዮናውያንና ንስጥሮሳውያን) ግፊትና ተቃውሞ መከራ ሲቀበል ጽሕሙ ተነጭቶ ጥርሶቹ ረግፈው ስለነበር የተነጨ ጽሕሙን የረገፉ ጥርሶቹን በመሐረም ቋጥሮ ‹‹ዝንቱ ፍሬ ሃይማኖቱ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የምናቀርብለት የሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› በማለት ለእስክንድርያ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ እጅ ልኮላታል፡፡ እርሱም ስለ ሃይማኖት በደሴተ ጋግራ ታስሮ ሰማዕት ኾኗል፡፡
ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ያዕቆብ አልባሌ መስሎ በሶርያ ብቻ ሳይኾን በእስክንድርያ የሴት ቀሚስ ሳይቀር ለብሶ ሲያስተምር ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ቢጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው ጀመር፡፡ ሌሊት ሌሊት ሲያስተምርና ሲጸልይ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሶቹ እንደ ፋና ያበሩለት ነበር፡፡ ይህም በተኣምራት የተፈጸመ ነው፡፡
ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
ቆይቶ ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ፣ ኢአማንያን አምነው ሲጠመቁ ቀይ፣ ነጭና ሰማያዊ ፈትሎች በአንድ ላይ ተገምደው መታሰር ጀመረ፤ ትርጓሜውም የሦስቱ አንድ ላይ መገመድ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት የሚያመለክት ምሳሌ ነው፡፡ ይኽንንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲያስረዱ፡- ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይለ ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን፤ ሥላሴ ለክርስቲያን ኹሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው፤ ብለዋል፡፡
ቀለሞቹ ደግሞ ቀይ፡- ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ አድኖናል፤ ስለ ስሙም በሰማዕትነት ደማችንን ማፍሰስ ይገባናል የማለት፤ ነጩ፡- የጥምቀት በጥምቀትም የሚገኝ ስርየተ ኃጢአት፤ ሰማያዊ፡- በጸጋ ልጅነት አግኝቻለኹ፤ ሰማያዊ አባት አለኝ፤ ሰማያዊ ርስት መንግሥተ ሰማይ ይቆየኛል፤ ስለዚኽም በሰማያዊ ግብር ጸንቼ መኖር በሰማያዊት ሕግ ሕገ ክርስቶስ ወንጌል ተመርቼ መኖር ይገባኛል እንደማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ክርስትና የገባው በዘመነ ሐዋርያት በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይኹንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ጋራ የዕኩልነት ማዕርግ ያገኘችው በአራተኛው ምእት ዓመት በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደኾነ ተረጋግጧል፡፡ በዚኽ ዘመን አቡነ ሰላማ ሕዝቡን አጥምቀው ወደ ክርስትና ሲመልሱ ለክርስትናቸው ምልክት ከግንባራቸው ላይ እየበጡ መስቀለኛ ምልክት ያደርጉላቸው እንደነበር ይተረካል፡፡
ከአቡነ ሰላማ የጀመረው ማዕተብ የማሰር ትውፊት በዘጠኙ ቅዱሳን ዘመንም እየተስፋፋ ሔዶ በቤተ ክርስቲያን ክርስትና ለሚነሡ ኹሉ ሥርዐተ እምነታችን ኾኖ ቆይቷል፡፡ እስከ አኹንም በተለይ በሰሜናውያን ዘንድ በመበጣትም ኾነ በንቅሳት ለክርስትናቸው ምልክት መስቀል ከግንባራቸው ማድረግ የጸና ልምድ ኾኖ ይታያል፡፡
* * *
ማዕተብ ያላሰረ ኦርቶዶክሳዊ የአባቶቹን የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም ክርስቲያን ያልኾነውን ማተብ የለሽ፣ ያልተጠመቀ፣ አረሚ ይሉታል፡፡ ክርስቲያን በማተቡ መነኵሴ በቆቡ እንዲታወቅ ማተብ አልባ መኾን ደግሞ ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማተቡ ክርስትናውን ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡በተለመደው አነጋገር÷ እገሌ ማተብ አለው፤ ባለማተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን ነው፤ እውነተኛ ሐቀኛ ነው የማለትን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ባለማተቢቱ ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማለት ፍች አለው፡፡ በዚኽ ምክንያት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የማተብ ትርጉም ከፍተኛ ቁምነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡
አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡ ለደብዳቤ፣ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ ይሠራበታል፡፡
በዚኹ አንፃር የክርስቲያን ማዕተቡም ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በቅድሚያ፣ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን፣ ክርስትናኽን ካድ ማተብኽን በጥስ የሚል ዐላዊ ቢመጣና ያን ምልክት አይቶ ቢሠዋው የሰማዕትነት ክብር ያገኘበታል፡፡ ያም ባይኾን በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡
ኹለተኛው፣ ያለጥርጥር ክርስቲያን መኾኑ ታውቆለት ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም፡፡ ሦስተኛ፣ ከማይታወቅበት አገር እንደወጣ በበሽታም ይኹን በአደጋ ሕይወቱ ቢያልፍ በማተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዐት ተፈጽሞለት በቤተ ክርስቲያን ሊቀበር ይችላል፡፡
አራተኛ፣ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውኃ ዋና ወይም በበረሓ ጎዳና በውኃ የሚኖሩ ወይም በበረሓ ያሉ አጋንንት በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህም በየጠበሉ ስፍራ በተኣምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት፡፡ እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው በልባችን ብቻ ሳይኾን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው ሰብአዊ ተፈጥሯችን ኹሉ መኾን ይገባዋል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና ፈጣሪ ስለኾነ ነው፡፡ ‹‹ስለዚኽ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለኹ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለኹ፡፡›› (ማቴ.፲÷፴፪÷፴፫)
በዚኽ ቃለ ወንጌል መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መኾናችንን የምንገልጸው በልባችን ብቻ ሳይኾን በቃላችንና በሥራችንም ጭምር ነው፡፡ በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር እንመሰክራለን፡፡ የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን፤ አናፍርበትም!! የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም ዓርማ በማተባችን እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፮÷፲፫፤ ኢዩኤ. ፪÷፴፪፤ ሮሜ ፮÷፩-፭፤ ማቴ.፭÷፲፩-፲፪፤ ፩ኛጴጥ.፫÷፳፩-፳፪፤ ፬÷፲፪-፲፮)
ከወንጌል የተለየች ትምህርት እንዳንቀበል ሐዋርያት አስጠንቅቀውናል፡፡ መላእክት በራእይ ገልጸውልናል፤ ከእግዚአብሔር አግኝቻለኹ ብለው የሚመጡትን መናፍስት እንድንመረምራቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዘናል፡፡ ማተብ የማሰር የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊታችንን የሚቃወሙ በክርስቶስና ሞትና ትንሣኤ የማያምኑ ተረፈ አይሁድ ስለኾኑ ተቃውሞውን ዋጋ ሳንሰጠው ማተባችንን እናጠብቃለን፡፡ ‹እንደ ውሻ በአንገታችኹ ገመድ አስራችኹ› ተብለን በመነቀፋችንም እንደሰትበታለን እንጂ አንሠቀቅም፡፡ ውሻ ለጌታው ታማኝ ነው፡፡ ሌሎች የተለከፉ ያበዱ ዘላን ውሾች እንዳይለክፉትና ከሞት እንዳያደርሱት ወይም ወንበዴዎች በሥጋ መርዝ ቀብተው ለሥጋው ሲሣሣ እንዳይገድሉት ትንሽ ጎጆ ሠርቶለት ቢያስረው ለውሻው ሕይወት አስፈላጊ እንደኾነ በኹሉም የታወቀ ነው፡፡
በዚኹ አንፃር ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡ በድርሳነ ሰንበት ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የውሻን ታማኝነት ለክርስቲያን ታማኝነት ምሳሌ አድርጎ ገልጾታል – ‹‹ከልብሰ የአምር እግዚኡ፤ ውሻ ጌታውን ያውቃል››፡፡ ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል በውሻ የተመሰለችውን ከነናዊቷን ሴት ስለ ታማኝነቷ አድንቋታል፤ ልጅዋንም ፈውሶላታል፡፡(ማቴ.፲፭÷፳፩-፳፰)
ማዕተብን ከሚቃወሙ አንዳንዶች ‹‹ጽዳት ያጎድላል›› በማለት ያመካኛሉ፡፡ በርግጥ የጠንቋይ ክታብ የቃልቻ ግሣንግሥ መሰብሰቢያ ካደረጉት የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሳይኾን የሚያጎድለው የነፍስንም ጽዳት የሚያጎድል መኾኑ ዕውቅ ነው፡፡ ማተብ እና መስቀሉ ግን ጽዳት ያጎደለበት ጊዜ ስለሌለ ሰበብ አያዋጣም፡፡ ስለዚኽ የክርስትናችንን ዓርማ የነፍሳችንን ሰንደቅ ዓላማ በነፃነት ስናውለበልብ ለመኖር ያብቃን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- መለከት መጽሔት፤ ፩ኛ ዓመት ቁጥር ፮፤ ሚያዝያ ፲፱፻፹፭ ዓ.ም.
About these ads
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ