2014 ኦክቶበር 13, ሰኞ

‹ቀራንዮ፣ መድኃኔዓለም፣ ካህናቱ›

                                                                                  
ቅዱስ ጳውሎስ ተከስሶ በቂሣርያው ገዥ በፊስጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ አይሁድ ለብቻቸው ቀርበው በቅዱስ ጳውሎስ ላይ ይፈርድበት ዘንድ ጎትጉተውት፣ እነርሱ ማስረጃ ያሉትንም አቅርበውለት፣ ሕጋቸውንም ጠቅሰው ማሳመኛ አቅርበውለት ነበር፡፡ አሕዛባዊው ገዥ ፊስጦስ ግን እግዚአብሔርን እናውቃለንም፣ እንፈራለንም ከሚሉት አይሁድ ተሽሎ ያሉትን ከማድረግ ራሱን ከለከለ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ጉዳዩን አቀረበላቸው፡፡ ፊስጦስ አይሁድ ያቀረቡትን ስሞታ፣ ውትወታና ክስ ተቀብሎ በቅዱስ ጳውሎስ ላይ ያልፈረደበትን ምክንያት ለአግሪጳ ሲገልጥለት ‹‹ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም፣ ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፣ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም›› ብሎ መሆኑን ነግሮታል (የሐዋ.25÷16)፡፡
ይህ በሮማውያን ዘመን እጅግ የታወቀውን ራስን በእኩል ደረጃ የመከላከል መብት በተመለከተ ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ አፒያን (95-165ዓም) በጻፈው Civil War በተሰኘው መጽሐፉ (3:54) ላይ ‹‹የምክር ቤት አባሎች፣ ሕጉ የተከሰሰ ሰው የተከሰሰበትን ሰምቶ በእርሱ ላይ ከመፈረዱ በፊት መልስ የመስጠት መብት አለው ይላል›› ሲል አሥፍሮት ነበር፡፡ ፊሊክስ የጠቀሰው ይኼንን ነው፡፡ አበው በትርጓሜያቸው ‹አሕዛብ ፍርድ ይጠነቅቃሉ›› ሲሉ የመሰከሩት እንዲህ ያለው የሮማውያንን ሕግ ነው፡፡ ለዚህ ጥንቁቅ የፍርድ ሥርዓትም ሲሉ አያሌ የሮማውያንን የፍተሕና የፍርድ ሐሳቦች በቤተ ክርስቲያን የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ (በቀኖና) እንዲገቡና እንዲሠራባቸው አድርገዋል፡፡


ይህንን የምትተረጉምና የምታስተምርን ቤተ ክርስቲያን እንወክላለን የሚሉ ሰዎች ናቸው ሰሞኑን ተሰብስበው ተከሳሹ በሌለበት ፍርድ ሲሰጡ ያየናቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ተሳሳተ ተብሎ እንኳን ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአርዮስና ለንስጥሮስ፣ ለመቅዶንዮስና ለሰባልዮስ የሰጠችውን መብት ቤተ ክህነቱ ለማኅበረ ቅዱሳን ሊነፍገው አይገባም ነበር፡፡ በቀደዱላቸው ቦይ መንጎድ፣ ተጠልቷል ብለው በሚያስቡት ላይ መፍረድ ሃይማኖታቸው የሆነ፤ ፓትርያርኩን ምን ያስደስታቸዋል እንጂ የትኛው እውነት ነው ለሚለው የማይጨነቁ ሰዎች የክስ መዓታቸውን ሲያዘንቡ ማኅበሩ መልስ እንዲሰጥ ዕድል ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ ለበዓሉ የሚስማማውን ቀለም ትተው ለባለ ሥልጣኑ የሚስማማውን ቀለም መረጡ፡፡ ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ‹ካህን ከመሆን እረኛ መሆን ይሻላል› እንዳለው ከቤተ ክህነት ፊልክስ ተሽሏል፡፡
ፊሊክስ ለቅዱስ ጳውሎስ፣ ሠለስቱ ምእት ለአርዮስ፣ ማኅበረ ኤፌሶን ለንስጥሮስ የሰጡትን ዕድል ቤተ ክህነቱ ለማኅበረ ቅዱሳን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለምን?
ሰዎቹ እውነቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አንሷቸዋል ማለት ነው፡፡ የሚሉት ነገር የሆኑ አካላትን ስለማስደሰቱ እንጂ እውነት ስለመሆኑ ርግጠኞች አይደሉም፡፡ ስለዚህም ተከራካሪያቸውን ለመስማትና የእነርሱ ‹እውነት› ሲሞገት ለማየት ዐቅም ያንሳቸዋል፡፡ ወይም ደግሞ
ከክርክሩ በፊት ውሳኔውን ወስነው ጨርሰዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ለደርግ አሳልፈው የሰጡት የቤተ ክህነት ሰዎች እንዲህ ነበር ያደረጉት፡፡ ፓትርያርኩን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ውሳኔውን ወስነዋል፡፡ ነገር ግን ለውሳኔው ምክንያት መፈለግ ነበረባቸው፡፡ ስለዚህም አቡነ ቴዎፍሎስ ሠሩ ያሏቸውን ጥፋቶች ለብቻቸው ተሰብስበው፣ ‹በደላቸውን› ዘርዝረው፣ እርሳቸው መልስ ሊሰጡ በማይችሉበት ሁኔታ ለደርግ አስተላለፉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለብቻቸው መሰብሰብ የፈለጉት፣ የፓትርያርኩንም መልስ የመስጠት መብት የነፈጉበት አንዱ ምክንያት ፓትርያርኩ በሚሰጡት መልስና በሚያቀርቡት ማስረጃ እውነታቸው ነፋስ ያየው ገለባ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡ ወይም
እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ሥራ አይደለም እየሠሩ ያሉት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲበጠብጡ የኖሩት ካህናተ ደብተራ (ከቤተ ክህነት ደመወዝ እየወሰዱ ለቤተ መንግሥት ሲሠሩ የኖሩ ካህናት ነን ባዮች) ዋናው መለያቸው የሚሠሩት የራሳቸውን ሥራ አለመሆኑ ነው፡፡ የመለካዊነት ጠባይ ስላላቸው ሌሎች ተናገሩ የሚሏቸውን ይናገራሉ፣ ፈጽሙልን የሚሏቸውን ይፈጽማሉ፤ አውግዙልን የሚሏቸውን ያወግዛሉ፤ አጽድቁልን የሚሏቸውንም ያጸድቃሉ፡፡ የሚሠሩት ሥራ የላኳቸውን ሰዎች ማርካቱን እንጂ የሚያስከትለውን ነገርና የሚያስከፍለውን ዋጋ አያውቁትም፡፡ እነዚህ ነበሩ አባ በጸሎተ ሚካኤልን ያሰደዱት፣ እነዚህ ነበሩ አባ ፊልጶስን ያንከራተቱት፣ እነዚህ ነበሩ እጨጌ ዕንባቆምን ለልብነ ድንግል ከስሰው ምንም ባላጠፋው ጥፋት ‹ጉንጽ› በተባለው ዓለም በቃኝ እስር ቤት ያሳሠሩት፤ በኋላም ለሀገሪቱ ጥፋትን ያመጡት፡፡ ጥይት የመታው ሰው ተናድዶ ‹‹ምነው እንዲህ ታበላሸኝ›› ቢለው ‹‹እባክህ እኔ አይደለሁም፣ እኔ ተተኮስኩ እንጂ ተኳሹ ሌላ ነው፤ እኔ መልክተኛ ነኝ›› አለው፡፡ ‹‹ተኳሹ የት አለ?›› ቢለው ‹‹እርሱማ አይታይም ተደብቆ ነው የሚተኩሰው፤ እርሱ ስለሚደበቅኮ ነው እኔ የመጣሁት›› አለው ይባላል፡፡
ወይም እነዚህ ሰዎች ስንፍናቸውን የሚያሳይባቸውን፣ ድካማቸውን የሚገልጥባቸውን፣ ሊያጠፉት ወድደዋል፡፡ ሰውዬው ዶሮውን በጦም አርዶ ለምን አረድከው ቢባል ‹‹እሱ ነው ጠዋት እየተነሣ መንጋቱን የሚያሳብቅብኝ፣ አርፌ እንዳልተኛበት፡፡እርሱ ባይጮህ ኖሮ መንጋቱን ማን ያውቅ ነበር? ተኛህ ብሎስ ማን ይከሰኝ ነበር›› አለ አሉ፡፡ ከመንቃት ይልቅ ማንቂያውን ማጥፋት፡፡ የ13ኛው መክዘ የደቡብ ሐዋርያ አቡነ አኖሬዎስ ታላቁ በካህናተ ደብተራ ተከስሶ ወደ ንጉሥ ሰይፈ አርእድ የቀረበበት ክስ አስቂኝ ነበር፡፡ ‹‹ከንጉሡ የሚበልጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርቷል›› ነበር የተባለው፡፡ ጉዳዩን ሊያጣራ የሄደው የጉዳም አለቃ ያገኘው ቤተ ክርስቲያን ግን እንደተባለው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከክሱ ንጹሕ መሆኑ ቅጣቱን አላስቀረለትም፡፡ ከገዳሙ ወጥቶ በወለቃ በረሃ እንዲከራተት ሆኗል፡፡ ምናለ ከንጉሡ የሚበልጥ ቤተ ክርስቲያን ቢሠራ? የሚያስመሰግነው እንጂ የሚያስነቅፈው አልነበረም፡፡ ለካህናተ ደብተራ ግን ይኼ ስንፍናቸውን ይገልጠዋል፣ እንደ አውራ ዶሮውም መተኛታቸውን ያሳይባቸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል፡፡ የሚቀርቡት ክሶች ለምን ቀረቡ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በአይሁድ አደባባይ ፍርድ ሲጓደል፣ እንደ ጲላጦስ ሚስት የሚያስጠነቅቅ ያስፈልጋል፡፡ ገለልተኛ አካል አቋቁሞ የተባሉትን ያጣራ፡፡ ራሱ የማኅበሩ አመራር ለተከሰሰበት መልስ ይስጥ፡፡ አሕዛባዊው ፊሊክስ ለቅዱስ ጳውሎስ የሰጠውን መብት ሲኖዶሱ ለማኅበሩ መስጠት አለበት፡፡ ተጣርቶ በተገኘው ማስረጃና ምስክር መሠረት ውሳኔ ይሰጥ፡፡ ጥፋተኛው ይታረም፤ እውነተኛው ይገለጥ፡፡
በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ቀራንዮ መድኃኔዓለም አለቅነት ተሾመው የሄዱትን አባት ካህናቱ አስቸገሯቸው፡፡ ለጥቂት ጊዜ የተላኩበትን ሊሠሩ ሞከሩ ግን አልሆነም፡፡ በመጨረሻም ለንጉሡ እንዲቀይሯቸው አመለከቱ፡፡ ንጉሡም ምነው ምን ገጠመህ? ቢሏቸው ‹‹ካህናቱም ካህናቱ፣ ቀራንዮም ቀራንዮ፣ መድኃኔዓለምም መድኃኔዓለም›› አሉ ይባላል፡፡ ሰቃይ ተሰቃይና የመስቀያ ቦታ አንድ ሲገናኙ ያ ነው ክፉ ዘመን፡፡
ማኅበሩን እንደ ተቋም፣ እንደ ጽ/ቤትና እንደ ድርጅት ማፍረስ ቀላል ነው፤ እንደ አስተሳሰብ፣ እንደ አመለካከት፣ እንደ የአገልግሎት መሥመርና አተያይ ግን ማፍረስ አይቻልም፡፡ ዛሬ ማኅበሩን በማፍረስ የሚጀመረው አጥር ንቅነቃ ግን መጨረሻው ሲኖዶሱን በማደንበሽ እንዳይጠናቀቅ ያሰጋል፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ ነውና፡፡ 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...