2014 ኖቬምበር 14, ዓርብ

የማያለቅስ ልጅ


ፎቶ - ሐራ ተዋሕዶ

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ በተመለከተ አሠረ ሐዋርያትን የተከተለ ሆኖ እንዲጸድቅ አድርጓል፡፡ አባቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ግለሰባዊ አምባገነንነትን አልፈቀዱም፡፡ ጸሎተ ሃይማኖቱም ‹ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› በማት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ዘሐዋርያት መሆንዋን ያመለክታል፡፡ በ50/51 ዓም በኢየሩሳሌም የተሰበሰበችው ሲኖዶስም ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› አለች እንጂ  ‹እኔ› የሚል ግለሰባዊ ድምጽ አልተሰማባትም፡፡
ኢትዮጵያውያን አበው የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን የአመራር ሥርዓቶች ከግለሰብ አምባገነንነት ለማውጣት መልካም የሆነ ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ቅዳሴው በአምስት ልዑካን እንዲሆን፣ አጥቢያው በሰበካ ጉባኤ እንዲመራ፣ ገዳማት በምርፋቅ (ጉባኤ አበው) ወይም በማኅበር እንዲመሩ፣ ጵጵስናን አንድ ጳጳስ (ፓትርያርክ እንኳን ቢሆን) ብቻውን እንዳይሰጥ፣ ቢያንስ ሦስት አበው ሊኖሩ እንደሚገባ፤ አንድ አባት ብቻውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዳይለውጥ፤ አድርገው የሠሩበት አንዱ ምክንያት ግለሰባዊ አምባገነንነትን ለመቋቋም እንዲቻል ነው፡፡

ይህንን ማኅበራዊና ጉባኤያዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን አሠራርና አመራር ለማስወገድ በየዘመናቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ የዚህም ምክያቱ ግልጽ ነው፡፡ ግለሰባዊ የሆነ አመራር ለሦስት ነገሮች የተጋለጠ ነውና፡፡ የመጀመሪያው ክህደትንና ኑፋቄን ለማስገባት ይመቻል፡፡ አንዱ ወሳኝ ሌላው ‹ኦሆ በሃሊ› ስለሚሆን እርሱ ትክክል ነው ያለው ትክክል፣ ስሕተት ነው ያለው ደግሞ ስሕተት ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤያዊት በመሆንዋ አንዳንድ ግለሰቦች በየዘመናቱ ያመጡትን ክህደት በጉባኤ ተመልክታ በጉባኤ ለማውገዝ ጠቅሟታል፡፡ ደገኛ ትምርትና ድርሰት ሲገኝ ደግሞ እንዲሁ በጉባኤ ተመልክታ ለመቀበል ረድቷታል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢርን ጽፎ በጨረሰ ጊዜ ጉባ ሊቃውንቱ ተመልክተው ‹አማንኬ ዮሐንስ አፈወርቅ ወቄርሎስ አፈ በረከት ተንሥኡ በመዋዕሊነ፡፤ ኢትዮጵያ ተመሰለት በቁስጥንጥንያ፤ ወተአረየታ ላዕለ እስክንድርያ - በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋ፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፤ ከእስክንድርያም ልቃ ከፍ ከፍ ብላለች›› ብለው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ለሌሎች አካላት ቁጥጥር ስለሚመች ነው፡፡ ጌታችን አስቀድሞ ኃይለኛውን ማሠር እንዳለው መሪውን የያዘ ቤተ ክርስቲያኒቱን አን ልቡ ለመዘወር ይመቸዋል፡፡
ይኼ ነገር በዘመነ ሱስንዮስ ጊዜ ታይቷል፡፡ ሮማውያን ግብጻዊውን ጳጳስ በሮማዊ ጳጳስ በመተካት ቤተ ክርስቲያኒቱን በሮማዊ ጳጳስ ለማስመራትና ለመቆጣጠር ፈልገው ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠባይ ማኅበራዊና ጉባኤያዊ በመሆኑ ጉባኤ ሊቃውንቱ ከግብጹ ጳጳስ ጋር ሆኖ ተቃወማቸው፡፡ ጳጳሱና ሊቃውንቱም እስከ ደም ማፍሰስ ድረስ መሥዋዕት ሆኑ፡፡ ጥቅምት 19 ቀን 1621 ዓም በምዕራብ ጎጃም በምትገኘው ደብረ መዊዕ የተሰበሰቡት የቤተ ክርስቲያን ማኅበርተኞች ለዚህ ማስረጃ ናቸው፡፡ በዚህ የደብረ መዊዕ ጉባኤ እስከ 7000 የሚደርሱ ምእመናን፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ሊቃውንት ተሰባስበው ነበር፡፡ የጉባኤው መሪዎችም እነ አባ ተስፋ ኢየሱስ፣ አባ ዘጊዮርጊስ ዘዋሸራ፣ አባ እንጦንዮስ፣ አባ ግርማ ሥሉስ ዘውይት ነበሩ፡፡ የጉባኤው አፈ ጉባኤ ደግሞ አባ ግርማ ሥሉስ ነበሩ፡፡በዚህ ጉባኤ የተገኙት ሁሉ ንጉሡንና አዲሶቹን ሮማውያን የሃይማኖት መሪዎች ተቃውመው እንደ አንድ ልብ መክረው እንደ አንድ ቃል ተናግረው በተዋሕዶ ጸኑ፡፡ የንጉሥ ሱስንዮስም ጦር ጥቅምት 19 ቀን ከብቦ ፈጃቸው፡፡ 
እነዚህ ጽኑአን ጉባኤተኞች ነበሩ በኋላ ዐፄ ሱስንዮስ ሐሳባቸውን እንዲቀይሩና ‹ፋሲል ይንገሥ፣ ሃይማኖት ይመለስ› እንዲሉ ያደረጋቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ መኪና መሪውን የያዘ መኪናውን ወደ ፈለገው ሊወስደው የሚችልባት ቦታ ብትሆን ኖሮ ዘመነ ሱስንዮስን መሻገር ባልቻለች ነበር፡፡ 
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ዘመን የፈቀደለት ሁሉ ልቡ የወደደውን በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳይጭን ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ መንግሥታት ለራሳቸው የሚመቻቸው መሪ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማስቀመጥ ሞክረው ነበር፡፡ የቤተ ከርስቲያን አሠራር፣ ሕግና ሥርዓት ግን በአንድ ሰው የሚዘወር ባለመሆኑ ገመዱን ከመበጣጠስ ያለፈ ጀነሬተሩን ማቋረጥ አልተቻላቸውም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎችም በጉባኤ እንጂ በአንድ ሰው ኅሊና ብቻ የሚወሰኑ ባለመሆናቸው አስተዳደራዊ ጥቅም ከማግኘትና በደል ከማድረስ ባለፈ አጥንቷን ለመስበር ዐቅም አላገኙም፡፡ 
ይህንን ታሪካዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ሐሳብ ጠንቅቆ በመረዳት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ግለሰባዊ አምባገነንነት የሚወስደውን  መንገድ በማረም የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ክርስቶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱም የበላይ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አጽንቶታል፡፡ 
የሀገራችን ሰው ሲተርት ‹የማያለቅስ ልጅ በእናቱ ጀርባ ይሞታል› ይላል፡፡ ይራበው አይራበው፣ ይታፈን አይታፈን፣ ይመመው አይመመው፣ ይመቸው አይመቸው አይታወቅምና፡፡ ምናልባትም ዝምታው እንደ ጨዋነት ታስቦለት ዘወር ብሎ የሚያየው ላይኖርም ይችላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይና በሊቃነ ጳጳሳት መብት ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ በተነሡ ማኅበራትና ወጣቶች ላይ፣ በየገጠሩ በተሠማሩና የመከራ ገፈት በሚቀምሱ ካህናትና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን በደልና ጫና እየሰሙና እያዩ ዝም ቢሉ በእናታቸው ጀርባ ላይ ሆነው መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ለማስከበር ደግሞ አስቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶሱ መብት መከበር አለበት፡፡ ያልቆመ አንገት ራስን አይሸከምም እንዲሉ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አንድ ሆነው የቅዱስ ሲኖዶሱን መብት እንዳስጠበቁትና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ከግለሰብ አገዛዝ እንደታደጓት ሁሉ በአጠቃላይ የሰበካ ጉባኤውና በቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ የቀረቡትን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን አንድ ሆነው ለመፍታት በቀጣይ  መነሣት አለባቸው፡                                                                                                           

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...