ኅዳር 25 ቀን 2007 ዓ.ም.
ባሳለፍናቸው ሳምንታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ
አስተዳደራዊ ጉባኤያትንና ውሳኔዎችን አስተላልፋለች፡፡ የመጀመሪያው ቅዱስ ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ ከሚገኙ
አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ጋር «በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደራዊ አስተሳሰብን ማበልጸግ»
በሚል መሪ ቃል ያደረጉት ጉባኤ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ በተደነገገው መሠረት የተደረጉት
ሠላሳ ሦስተኛው መደበኛ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ እና የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ናቸው፡፡
በእነዚህ ጉባኤያት በርካታ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመለከቱ ወሳኝ
ጉዳዮች ተነሥተዋል፡፡ በተለይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ ላይ ከወጡት የድምፅ
ወምስል ክሊፖች ለመረዳት እንደሚቻለው /በዚህ መምሪያው ሊመሰገን ይገባል/ ሁሉንም ጉባኤያት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ
ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኗ የዛሬ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴና የነገ ገጽታ ላይ ከፍተኛ አደጋ አምጥተዋል የሚባሉ
መሠረታዊ ጉዳዮችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ተብለው በቅዱስነታቸው ከተነሱት
ጉዳዮች አንዱና ዋናው የቤተ ክርስቲያኗ ምእመን ቁጥር መቀነስ የሚል ነው፡፡ ይህ ችግር ቤተ ክርስቲያኗም ይሁን
በሥሯ ያለ ማንኛውም አካል በግልጽ አንሥቶት የማያውቅ ከባድና ሁሉንም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ቢያንስ በመምሪያው ድረ ገጽ ከተቀመጠው የድምፅ ወምስል ሰነድ ለመረዳት እንደሚቻለው በቅዱስ ፓትርያርኩ በቀረቡት ችግሮች ላይ በጉባኤው በቂ ውይይት ተደርጎባቸዋል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከተደረገው ጉባኤ ለመረዳት እንደተቻለው ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሳቢ ነው ብለው ባነሡት በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲወያዩና የመፍትሔ ዐሳብ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት ጉባኤተኞች ውኃ የሚቋጥር ዐሳብ ሊሰጡበት አልቻሉም፡፡
የተነሣው አሳብ በእርግጥ እውነት ከኾነ የቤተ ክርስቲያኗን
አካላት በምልአት ሊያሳስብና ሊያስጨንቅ ይገባ ነበር፤ ነገር ግን ጉባኤተኞቹ ይህንን ዐቢይ ጉዳይ ትተው ሙሉ በሙሉ
ሊባል በሚችል ሁኔታ የአስተያየታቸው ትኩረት በቅዱስ ፓትርያርኩ የመግቢያ ንግግር ወደ መጨረሻ በተነሣው የማኅበራት
በተለይም ማኅበሩ እያሉ ሲያብጠለጥሉት በነበረው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ብቻ ነበር፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በማክበር በቅዱስ ሲኖዶስ ታውቆ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር ታቅፎ፣ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ ሊመሰክረው የሚችለው ለቅድስት ቤተ ክርስ ቲያን ወቅታዊነት ያለው ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ማኅበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአስተያየት ሰጪዎቹ የምቀኝነትና የጥላቻ ንግግር ማኅበሩ የበለጠ ጠንክሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ያነሧቸውን ዐበይት ችግሮች በመፍታት ሒደት አሁን ከሚያደርገው የበለጠ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያበረታታ ሳይሆን አገልግሎቱን ሽባ ለማድረግ የ«ስቅሎ፣ ስቅሎ» ዓይነት ውትወታ ነበር፡፡ ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ላይ ማተት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ዓላማው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልንወያይባቸው ይገባል ብለው ካቀረቧቸው ወቅታዊ ችግሮች ከላይ በተጠቀሰው የምእመናን ቁጥር መቀነስ ላይ መጠነኛ አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሁሉም ጉባኤያት መክፈቻ ንግግሮቻቸው ላይ ስለ ቤተ
ክርስቲያኗ ምእመናን ቁጥር መቀነስ፣ የቀነሰውም በቤተ ክርስቲያኗ ታቅፈው ሲያገለግሉና ሲገለገሉ የነበሩ ምእመናን
በልዩ ልዩ ምክንያት እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ትተው ወደ ሌሎች በመሔዳቸው እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ
ግንዛቤአቸው መረጃ አድርገው ያቀረቧቸው በ1987 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. በመንግሥት የተደረጉ ሁለት የሕዝብና
ቤት ቆጠራ ውጤቶችን ነው፡፡
በመሠረቱ እንደ ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት ከተደረገው የሕዝብና
ቤት ቆጠራ ውጤት ተነሥቶ ይህንን ማለት ሊከብድ ይችላል፡፡ እንደሚታወሰው ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው በመረጃነት
የጠቀሱትን የ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ቤተ ክርስቲያን በኦፊሴል ልትቀበለው እንደምትቸገር ገልጻ
ነበር፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗ ያቀረበቻቸው የመከራከሪያ ነጥቦች በቆጠራው ከስምንት መቶ በሚበልጡ ገዳማት፣
ከ1000 በሚበልጡ አብነት ት/ቤቶች የሚገኙ መነኮሳትን፣ መነኮሳዪያትን እንዲሁም ተማሪዎችን አላካተተም፣ በአንዳንድ
ክልሎችና ከተሞች ከተደረገው ቆጠራ የመጣው ውጤትም ተአማኒ አይደለም የሚሉ ነበሩ፡፡
በዚህም የተነሣ፤ ምንም እንኳን ባትተገብረውም፤ በወቅቱ ይህንን
ጥያቄ ለመመለስ በራሷ በጀትና መንገድ ምእመኗን እንደምትቆጥር አሳውቃ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከላይ በተጠቀሱት
ምክንያቶች የቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን ቁጥር ቀንሷል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፤ ወይም ለመናገር ጥቂት
የጥናት ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያ ርኩ በግልጽ ችግሩ እንደነበረና አሁንም ቀጥሎ የሚታይ እንደኾነ
አንሥተዋል፡፡ አያይዘውም የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ይህንን ብለን ብንወያይ ሌሎች ይሳለቁብናል ማለትን ትተው
«በሽታውን የደበቀ መድኀኒት የለውምና በግልጽ እንወያይ» ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በመሠረቱ በሁሉም ጉባኤያት እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያኗን
ደማቅ ሐዋርያዊ ጉዞ የሚገዳደሩ ጉዳዮችን በግልጽ አንሥቶ መወያየት፣ ሁሉንም የሚያስማማ ጠቃሚ የውሳኔ አሳብ
ማሳለፍ፣ ለውሳኔው ተግባራዊነት መትጋት ቤተ ክርስቲያኗን እንዲመሩ ከተቀመጡ አባቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም
ምናልባት በጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት መደረግ መጀመሩ የሚያስደስት ነው፡፡ ባሕሉ በደረጃ ወደ ሁሉም የቤተ
ክርስቲያን አካላት /ካህናት፣ ምእመናን፣ አገልጋዮች ወዘተ./ ወርዶ ተግባራዊ ሊኾን ይገባል፡፡
ይህ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ የአስተዳደር ጉባኤያት በይፋ ተገልጾ ውይይት ሲደረግበት በቤተ ክርስቲያን ልጆች አእምሮ ሊነሣ የሚችለው ጥያቄ «በእርግጥ ቀንሰናል እንዴ?» የሚል እንደሚኾን ግልጽ ነው፡፡ ይህ ጥያቄአችን አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ መልስ የሚያገኘው በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ ጥናት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ረገድ ሊካዱ የማይችሉ እውነታዎችን ማንሣት ይቻላል፡፡ ዛሬ በግልጽ ከመታወቅ አልፈው በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ከተደረገባቸውና ሊደረግባቸው ከሚገቡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮች በመነሣት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ምእመናን ከነበሩበት ቦታ እንደሌሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሁሉንም ያሳሰቡ አስተዳደራዊ ችግሮች
ካልተቀረፉ ዛሬ ጥቂት ያልናቸው ምእመናን ተበራክተው በነበሩበት ላናገኛቸው ሊሸሹ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡
የተወሰኑ ምእመናን ርቀውናል ስንል ቃሉ ሊያሳብቅ እንደሚችለው ሁሉም ቤተ ክርስቲያኗን ሙሉ በሙሉ ትተው ወደ ሌላ
እምነት ሔደዋል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም ዛሬ በልዩ ልዩ ምክንያት በነበሩበት የሌሉ ምእመናንን በሚከተሉት አራት
ክፍሎች መድበን ማየት እንችላለን፡፡
1. አገልግሎት ያቆሙ፡-
የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከነሙሉ ሙቀቱና ምልአቱ
ትውልድን ተሻግሮ ለእኛ የደረሰው፤ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ፍቅርና ትምህርት ተስበው ባላቸው ሁሉ ባገለገሉ
ምእመናን ነው፡፡ በየዘመኑ ከተጻፉ መጻሕፍት እንደምንገነዘበው እነዚህ ምእመናን በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው፣
ነፍሳቸውን ለሕልፈት በመስጠት ጭምር ቤተ ክርስቲያኗን ሲያገለግሉ ድጋፍና ኃይል የሆናቸው የአባቶች የሕይወት
ጥንካሬ፣ ለልጆቻቸው የነበራቸው ፍቅርና ክብካቤ ነበር፡፡
ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ የሚያደርግ የአበው
መልካም የሕይወት ፍሬ ዛሬ ፈጽሞ የለም ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ዛሬም ቢሆን ምንም እንኳን መጥፎው ጎልቶ እየታየ
ማንነታቸውን የከለለ ቢመስልም ስለ እውነት ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ፣ ምእመናንን በስስት
የሚመለከቱ አባቶች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም እንደሚያውቀው ዘመኑ ካባው ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት፣ ለምእመናን
ሕይወት ግድ የሌላቸው የትንቢት መፈጸሚያ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ተሹመው እዚህም እዚያም
የሚገኙበት ነው፡፡
በእነዚህ ግለሰቦች መጥፎ ሥነ ምግባር የተነሣም እንደ ቅዱስ
ፓትርያርኩ አባባል በሁሉም የአገልግሎት ትጋታቸው ከፊት ቆመው የነበሩ በርካታ ምእመናን «የመንፈስ ስብራት
እየደረሰባቸው» ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን የጸሎት ግንኙነት ሳያቆሙ በየቦታው ራሳቸውን ከአገልግሎት
አግልለዋል፡፡ የእነዚህን ምእመናን ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ለማወቅ በተለይ በአዲስ አበባና ታላላቅ ከተሞች በሚገኙ
አጥቢያዎች በሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ አባልነት ታቅፈው ሲያገለግሉ የነበሩ ምእመናን ዛሬ ያሉበትን ሁኔታ ቀረብ
ብሎ ማጥናት ይበቃል፡፡ ቤተ ክርሰቲያን በሰጠቻቸው ሥልጣን የምእመናን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይዋል
ብለው ሹማምንቱን የሞገቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቤተ ክርስቲያን ልጆች በደረሰባቸው ጫናና ግፊት ከአገልግሎት
ራሳቸውን አግልለው ታዛቢ ሆነዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ሙስና ይጥፋ፣ ብልሹ አስተዳደር ይስተካከል
ብለው የሚታገሉ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የአገልግሎት ተቋማትም የሌለ ስም እየተሰጣቸው የሚሳደዱት አገልግሎታቸውን
አቁመው ዘወር እንዲሉና ቤተ ክርስቲያኗ ያሰቡትን ለማድረግ የተመቸች ለማድረግ ነው፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ
ምናልባት ነገ ከነገ ወዲያ ወዶና ፈቅዶ ሊያገለግል ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጣ እንዳይጠፋ ያሰጋል፡፡
2. ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሔድ የታቀቡ፡-
በግል የሥራ ጫናና ድካም የተነሣ ዕለት ዕለት ወደ ቤተ
ክርስቲያን ሔደው ከአምላካቸው ጋር የማይገናኙ እንዳሉ ሁሉ፤ በቤተ ክርስቲያን በሚያዩአቸው ችግሮች በመሳቀቅ ቤት
መጸለይን እንደ አማራጭ የወሰዱ ምእመናንም በርካታ ናቸው፡፡ ምእመናን ቃሉ ይሰበክበት ዘንድ በሚገባው ቅዱስ ቦታ
ግለሰቦች ሲሰበኩበት፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ በመሠረተልን መድኀኔዓለምና እሱ በመረጣቸው ቅዱሳን ፋንታ ሹማምንቱ
ሲወደሱበትና የሌላቸው ሕይወት ሲሰበክበት ሲመለከቱ ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት መንፈሳቸው ይሰበራል፡፡ በመሆኑም
የሚበረታታ ባይኾንም የቤተ ክርስቲያናቸው ድምፅ እየናፈቃቸው፣ መዓዛ ቅዳሴውና ዕጣኑ ውል እያላቸው ወደ ቤተ
ክርስቲያን መሔድን በመሰቀቅ ቤታቸው ተወስነው የተቀመጡ ምእመናን በርካታ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
3. እምነትን ያቆሙ፡-
እምነት ቃሉን ተረድቶ በቃሉ ባለቤት አምኖ እንደቃሉ የሚኖሩት
ሕይወት ቢሆንም፤ ሰው አይተው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ፣ ሰውን ተደግፈው በቤተ ክርስቲያን የሚኖሩ ሰዎች
መኖራቸው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ያለ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ለሚኖራቸው ጥንካሬ መሠረቱ
የሚያዩአቸውና የሚደገፏቸው ሰዎች ጥንካሬ ነው፡፡ ለምእመናን ሕይወት መጠንከር ከፊታቸው ቆመው የሚሰብኳቸው ሕይወት
መጠንከርና የሚሉትን ሆነው መገኘት፣ እንዲሁም ቀድሰው የሚያቆርቧቸው፣ የሚናዝዟቸው ካህናት ጥንካሬ ወሳኝነት
አለው፡፡
በዐውደ ምሕረቱ በሕይወቱ አርአያ ሆኖ የሚታይ ሲጠፋ የምእመናን
ሕይወት አልጫ ይሆናል፡፡ አልጫነቱ ሲበዛ ደግሞ ወደ እምነት አልባነት ይለወጣል፡፡ በዚህ የተነሣ ትላንት በየትኛውም
መንገድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው የእምነትን ሕይወት ዳዴ ማለት የጀመሩ ምእመናን በትምህርት፣ በምክርና
በመልካም ሕይወት የሚያንፃቸው ሲያጡ እምነትን ወደ መተው ይሔዳሉ፡፡ በዚህም ረገድ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ይህን
ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም በዚህ ሥር ሊታቀፉ የሚችሉ ምእመናን ሊኖሩ እንደሚችሉ መካድ አይቻልም፡፡
4. እምነታቸውን የቀየሩ፡-
ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ ሒደት አማኞችን ከሚገዳደሯቸው
በርካታ ምክንያቶች የተነሣ ሙቀትና ሕይወት ከምትሆን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይተው ወደ ሌሎች ጓዳ የሚገቡ
ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ካጋጠሟት ውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ጋር
ሲነጻጸር በዚህ ርእስ ሥር ሊመደቡ የሚችሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ከላይ ካየናቸው የምእመናን ሽሽት መገለጫዎች በየትኛውም ይጠቃለሉ
ቁጥራቸው ጥቂት ይሁን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከእናታቸው ሙቀት መራቃቸው ያሳስባል፡፡ ሁላችንንም ዐቅፋ የያዘች
ቤተ ክርስቲያን «ክርስቶስ ለአንዲት ነፍስ ሲል ወደ በረሃ ወረደ» የሚለውን ንባብ አመሥጥራ የምትሰብክ ለልጆቿ
ተቆርቋሪ እናት ናትና፡፡ በመሆኑም በቅዱስ ፓትርያርኩ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ዜና ሲታወጅ ስንሰማ ሁላችንም ለምን?
እንዴት? ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ መጠየቅም ብቻ ሳይኾን ይህ የሆነበትን ምክንያት ከሥሩ ተረድተን መፍትሔውን
በመፈለግ ረገድ በያለንበት ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ለመሆኑ ጥቂትም ቢሆኑ ምእመናን ለምን ከቤተ ክርስቲያን ራቁ?
የራቁት ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ፤ ያልሸሹት በቦታቸው እንዲጸኑ ምን ይደረግ? ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን
በተለያየ ደረጃ እንዲርቁ በሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዙሪያ ያልተባለ ነገር እና ያልተሰጠ የመፍትሔ ዐሳብ የለም፡፡
የችግሩ ተጠቃሚም ኾነ የችግሩ ተጎጅ፣ ችግሩን ለመፍታት ሙሉ ሥልጣን ያለውና ዘወትር ስለ ችግሩ እያወራ ከማልቀስ
በቀር ምንም ሊፈይድ ያልቻለው፤ ሁሉም ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን ስለገጠሟት ልዩ ልዩ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ሲናገር
ይሰማል፡፡ በአጭሩ የዕውቀት ችግር የለም፡፡ የጠፋው ችግሮቹ የሚቀረፉበትን እርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት ነው፡፡
ከላይ እንደተገለጠው ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዘመን ክፉኛ እንድትፈተን ያደረጓት ምክንያቶች በርካታና የሚታወቁ ናቸው፡፡ አንድም የተባለውን ሁሉ በመድገም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ምክንያቶችን እናንሣ፡፡
ብልሹ አስተዳደር፡-
ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግቢያ ንግግሮቻቸው ለምእመናን መራቅ
በምክንያትነት ካነሧቸው ጉዳዮች ውስጥ አስተዳደራዊ ብልሹነት አንዱ ነው፡፡ እንደ ቅዱስነታቸው አገላለጽ ይህ
አስተዳደራዊ ብልሽት በምእመናን ላይ ከፍተኛ «የመንፈስ ስብራት» እያደረሰ በመሆኑ ለሽሽታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ብልሽት እየፈተናት ይገኛል ስንል ማብራሪያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ ከላይ
እንዳልነው አልሚውም አጥፊዉም ችግሩን እኩል ሲያነሣ ሲጥለው፣ ሲቋጥር ሲፈታው የሚውል ጉዳይ ነውና፡፡
ቅዱስነታቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን ክፉኛ እየተፈታተናት ያለውን
የአስተዳደር ብልሽት መገለጫዎች «ወንጌል ከሚያዝዘው የተቃረነ መሥራት፣ ጉቦ መቀበል፣ በዘር በጎጥ በመደራጀት
ሰላማዊውን ሰው መበደል፣ ያልደከሙበትን የሕዝብ ሀብት ማባከን፣ ለአገልግሎት በመትጋት ለምእመናን አርአያ አለመሆን፣
ከራስ በላይ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር አለመቆርቆር» በማለት በግልጽ አስረድተዋል፡፡ በእውነቱ ይህ ትልቅ ነገር
ነው፡፡ ምዕራባውያን የችግሩን ምንጭ ማወቅ ከሙሉ መፍትሔው ግማሹን እንደመሥራት ነው እንደሚሉት ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ
እንደተቋምና ልጆቿ በየቦታው የሚያዝኑበትን አስተዳደራዊ ችግር በግልጽ ተረድቶ መፍትሔ ያስፈልገዋል በማለት በግልጽ
ማቅረብ ይበል የሚያሰኝና በሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ሊለመድ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
እውነት ነው፤ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የኾነ አስተዳደራዊ ችግር ይታይባታል፡፡ መሪና ተመሪ በማይታወቅበት ሁኔታ፤ ሀይ ባይ የሌለ እስኪመስል ድረስ በአስተዳደር የተቀመጡ በርካታ አካላት ቅዱስነታቸው እንዳሉት ከወንጌል ፍጹም በተቃረነ ሁኔታ ጉቦ ሲቀበሉ፣ ለምን ብሎ የጠየቀን ሲያሳድዱ፣ ምእመናን እንባቸውን አብሰው ሙዳዬ ምጽዋት በሚጥሉት ሳንቲም የግል ኑሯቸውን ሲያደላድሉ ይታያል፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ በማን አለብኝነት ፀሐይ እየሞቀው በዐደባባይ፣ ስለሆነ ግድፈቱን የሚያዩ ምእመናን በእጅጉ እያዘኑ፣ የጸኑት ከቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ሳይሸሹ የሚሆነውን እያዩ ዕድሜ ለንስሐ ለሰጠ አምላክ ይጮኻሉ፡፡
በዓይናቸው የሚያዩትንና በጆሯቸው የሚሰሙትን መታገሥ ያልቻሉት
ደግሞ ዘወር ማለትን መርጠው መዳረሻቸውን የጸኑት አባቶች የሚገኙባቸውን በሩቅ ያሉ ገዳማት አድርገው ከአምላካቸው
ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቀጥለዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ በቤታቸው ተወስነው ይጸልያሉ፡፡ ማመን እንዲህ
ከኾነ ብለው ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡም እንዳሉ ሊካድ አይችልም፡፡ መማረሩና ማዘኑ ከግል
ድካማቸው ጋር ተደምሮ ከቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ወጥተው ወደ ሌሎች የሔዱም አይጠፉም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው በየደረጃው
የሚቀመጡት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚያሳዩት አስተዳደራዊ ጥሰትና ተመዝኖ መቅለል የተነሣ ነው፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህንን ጉዳይ በግልጽ አንሥተው ለውይይት ማቅረባቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹ መነገራቸው ብቻ አይበቃም፡፡ መፍትሔአቸው ላይ በፍጥነትና በትጋት አቅጣጫ ማስቀመጥና እንዲረባረቡበትም ማድረግ፣ ሰነፎችንና የሚያሰንፉትን ትቶ ጠንክረው የሚያጠነክሩትን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በተነሡትም ይሁን ባልተነሡት በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ላይ አስተዳደራዊ ቁርጠኝነት ከሌለ መቀረፍ ቀርቶ ፈቅ ሊሉ አይችሉም፡፡
ቅዱስነታቸው ካለባቸው ሓላፊነት ተነሥተው እንወያይ ብለው ቁልፍ
ችግሮችን በግልጽ ሲያስቀምጡ፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ በተመራው ጉባኤ የተሳተፉት የተወሰኑ ቡድኖች ጉዳዩን ወደዬት
አቅጣጫ ወስደው ቤተ ክርስቲያኗን በማይጠቅም ሁኔታ በማይመለከታቸው ጉዳይ ሲማስኑ እንደነበረ ተመልክተናል፡፡
በቆራጥነት ዛሬ ስላለው አስተዳደራዊ ችግር በግልጽ ሲነገር፣ መፍትሔም ያስፈልጋል ሲባል ጩኸት እንደሚበዛ፣ የሌለ
አጀንዳ ፈጥሮ የሁሉም ትኩረት ከዋናው አጀንዳ እንዲያፈነግጥ ማድረግ ሁልጊዜ የሚታይ መሆኑን ከተደረገው ውይይት
መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን ተረድቶ ወደፊት በተመሳሳይ ጉዳዮች የሚደረጉ ውይይቶች ጥናትን መሠረት ያደረጉና ሊያመጡት
የሚገባ ውጤትም ቀድሞ የተቀመጠ ሊሆን ይገባል፡፡
በአስተዳደር ረገድ የተነሣው ሌላው ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኗ
አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ አለመኾኑን ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገለጻ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር አሁን ዘመኑ
ከሚጠይቀው አንጻር ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ እውነት ነው ለሀገር የአስተዳደር ሥርዓትን እያስተማረች ሕዝብን
እያዘመነች ዛሬ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ዘመን ካመጣው አስተዳደራዊ ስልት እንኳን መማር አቅቷት የሁሉም
መሳለቂያ ሆና እናያለን፡፡ ቅዱስነታቸው እንዳሉት የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደራዊ አሠራር ማዘመን ደግሞ ከመሪዎች
የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኗ በዘመናዊ አሠራር የታገዘ ሰማያዊ አገልግሎት እንድትሰጥ የሚመኙትን
ሁሉ ያስደሰተ እንቅስቃሴ ተሰምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ዘመናዊው አሠራር ሲመጣ ጥቅማችን ይቀርብናል ባሉ አካላት
ጩኸት የጥረቱ ውጤት የት እንደደረሰ ሳንሰማ፤ በአንጻሩ እንቅስቃሴው አንዱ የማኅበረ ቅዱሳን መወንጀያ ሲኾን
እናያለን፡፡
ትምህርት፡-
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በጉያዋ አቅፋ በሙቀቷ ከምትይዝባቸው
መንገዶች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ የሰፋውና የጠለቀው ዕውቀቷ በተጉ ልጆቿ አማካይነት እየተቀዳ ለምእመናን ሲሰጥ
ቆይቷል፡፡ በትምህርት የጠገቡ ልጆቿም እናታቸውን አቅፈው በእናታቸውም ታቅፈው ኖረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተረከብናት
ቤተ ክርስቲያናችን ከገጠሟት ችግሮች አንዱ ትምህርተ ሃይማኖቷ፣ ሥርዓተ እምነቷ፣ ታሪኳና ትውፊቷ ሁሉ በአግባቡ
ከምንጩ ተቀድቶ ያለመሰጠቱ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ይህ ትምህርትን በአግባቡ የማዳረስ ችግር፤ እሱንም ተከትሎ
የምእመናን መራቅ የተከሰተው ሊቃውንት ጠፍተው አይደለም፡፡ ቅዱስነታቸው በንግግሮቻቸው እንዳሉት ሊቃውንቱን
የሚከባከብና የሚያሰማራ አስተዳደር በመጥፋቱ ነው፡፡ የአስተዳደራዊ ብልሽት መገለጫዎች ከሆኑት አንዱ በቤተ
ክርስቲያኗ ለዕውቀትና ለዐዋቂዎች የሚሰጠው ቦታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡
በየጉባኤ ቤቱ ደክመው ዕውቀትን በጠዋት የሰነቁ ሊቃውንት የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ አጥተው፣ ቃለ እግዚአብሔርን ምግብና ልብስ አድርገው በሥጋ የሚሠቃዩ በርካታ ሊቃውንት ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በአንጻሩ ዕውቀቱን አይደለም ደጃፉን የማያውቁ ዘመድ ወይም ምላስ ስላላቸው የቤተ ክርስቲያኗ ሙዳይ በሰፊው የተከፈተላቸው ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ይህ አሳዛኝ ጉዳይ
ካልተስተካከለ እንደተባለው ምእመናን መሸሻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ውሸቱንም ምኑንም ተናግረው የሚያሳምኑበት አንደበትና
ንዋይ ስለሌላቸው ተገፍተው የሚኖሩት ዕውቀት ጠገብ ሊቃውንት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ዐውደ ምሕረት መምጣት አለባቸው፡፡
ሊቃውንቱ ዝም ስላሉ ወይም እንዲሉ ስለተደረጉ ዐውደ ምሕረቱ ዕውቀት ርቦታል፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኗ
አስተዳደር በየዐውደ ምሕረቱ ስለሚሰጠው ትምህርት ይዘትና አሰጣጥ ስልት እንዲሁም የሰባክያኑ ማንነት ላይ ትኩረት
ሰጥቶ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡
ሕይወት፡-
ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን ወደው የሕይወት መሥዋ ትነት ጭምር
እየከፈሉ በዕቅፏ የቆዩት በመሪነት ከተቀመጡት አበው ሕይወት በመማር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ችግር ላይ ስትወድቅ፣
ሊቃውንቱ ሲሰደዱ ምእመናን እኛ እንቅደም እያሉ መሥዋእትነት እየከፈሉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከምንም የመጣ
አይደለም፡፡ በወቅቱ ምእመናንን ይመሩ ዘንድ በልዩ ልዩ ደረጃ የተሾሙት አባቶችና እናቶች የሕይወት መዐዛቸው
የሚስብ፣ ለልጆቻቸው የነበራቸው ፍቅር የሚይዝ ስለነበረ ነው፡፡ ዛሬ ያ ትላንት ምእመናንን እንደ መግነጢስ ዕለት
ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይስብ የነበረ የአበው የቅድስና ሕይወትና ፍቅር በብዛት አደጋ ላይ ወድቆ እናያለን፡፡
በዚህ የተነሣ ለምን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚመጡ ዕውቀቱ ያነሳቸው ምእመናን ወደ ቤቱ መጥተው የሚስባቸው
ሕይወትና ፍቅር ሲያጡ ይሸሻሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሕይወታቸው የማሰነባቸውን ሰዎች አሽቀንጥራ
ሳትጥል በዕቅፏ እንዲቆዩ የምታደርግባቸው ልዩ ልዩ ሥርዓት ያላት ስንዱ እመቤት ናት፡፡ ነገር ግን አንዳንድ
አገልጋዮች የሕይወታቸው ድቀት ከእነሱ አልፎ በሌላውም እስኪታይ ደርሶ በማይገባቸው ወንበር ላይ ተቀምጠው ሲታዩ
ምእመናን ይታወካሉ፡፡ ሲታወኩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ይሸሻሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱስነታቸው አጠንክረው እንደገለጹት በቤተ
ክርስቲያን መሪነት ያሉ ሰዎች ከምንም በላይ ሊመሯት የተሾሙባት ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የመጡባትን ነፋሳት አልፋ
እዚህ የደረሰችው በመሪዎቿ የሕይወት ቅድስናና መልካም አርአያነት መኾኑን ተረድተው ወደ ውስጣቸው ሊያዩ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ቁጥር ቀንሷል፤ አሁንም እየቀነሰ ነው፤ ፈጣን የመፍትሔ እርምጃ ካልተወሰደ ወደፊትም ተባብሶ ይቀጥላል በማለት በግልጽ መናገራቸው ነው፡፡ በጽሑፉ እንደተገለጠው እዚህ ድምዳሜ ላይ ደርሶ በግልጽ ለመናገር ጥናት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በተለይ በከተማ ባለችው ቤተ ክርሰቲያን ከሚታየውና ከሚሰማው ዘርፈ ብዙ ችግር በመነሣት በርካታ ምእመናን ምንም እንኳን ከቤተ ክርሰቲያን መራቃቸው ትክክል ነው ባይባልም፤ ላለባቸው ፈተና በምክንያትነት እያቀረቡት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
መራቃቸው ምናልባት ሙሉ በሙሉ እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላው ሔዶ
በመቀላቀል አይደለም፡፡ ከላይ እንደተገለጠውና በብዛት እንደሚታየው ቀድሞ ከነበሩበት የአገልግሎት ሕይወት በመራቅ
ወይም የዕለት ከዕለት ምልልሳቸውን በማቆም በቤታቸው መወሰን ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር
ከእምነት ውጭ ያደረጋቸው ወይም እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደረጋቸው አይጠፉም፡፡ ቅዱስነታቸውም እንዳሉት ዛሬ በቤተ
ክርሰቲያን ተንሰራፍቶ ያለው ችግር ካልተወገደ ነገ አገልግሎት እርሜ ብሎ የሚቀመጠውና ጠዋት ማታ ወደ ቤተ
ክርስቲያን የሚገሠግሠው ምእመን ቁጥር ይቀንሣል፡፡ ከዚህ ጋር ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኙነት አቁሞ እምነት አልባ
የሚሆነውና ቤተ ክርስቲያኑን ትቶ ወደ ሌላው የሚነጉደው ምእመን ቁጥር ይጨምራል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ይህንን ከትምህርቷ፣ ከሥርዓቷና ካለፈ ታሪኳ ጋር የማይሔድ ድርጊት ማስቆም አለባት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንል በየደረጃው በመሪነት ከተቀመጡት አበው ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ ማለታችን ነው፡፡ በመሪዎቹና ተመሪዎቹ፣ በአገልጋዮቹና ተገልጋዮቹ አንድነትና መፈቃቀር ዘመናትን አልፋ እዚህ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በሁሉም ላይ በሚታየው ድካም መፈተን የለባትም፡፡ በቅድሚያ ችግሩን ለመፍታት በራስ ላይ ያለን ችግር መርምሮ በማወቅ ከማስተካከል ጀምሮ በሌላውም ያለው ጉድፍ እንዲወገድ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ሁሉ መክፈል የግድ ይላል፡፡
ስለ ችግር እያወሩ እና መንጋውን በበረቱ እንዳይገባ የሚያደርግ፣
የገባውንም በሰላም እንዳይተኛ የሚያደርግ ባዕድ ጠረን ተፈጥሮ እየጨመረ መምጣቱን እያዩና እየሰሙ ለዓመታት መቀመጥ
የቤተ ክርስቲያን ባሕል አይደለም፡፡ አስቀድሞ የምእመናንን ሕይወት የሚበድል፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰማያዊ
አገልግሎት የሚገዳደር ችግር እንዳይኖር የተግባርና የእውነት ሰው ሆኖ በጸሎትም በምክክርም መታገል ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ ሁሉም በይፋ እያወራቸው ያሉትን ችግሮች መፍታት ከሚመለከተን ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ምእመናን የችግሩ
ሁሉ ተሸካሚ እንደመሆናቸው በሰበካ ጉባኤዎቻቸውና በልዩ ልዩ ስብስቦቻቸው በየአካባቢያቸው ያሉትን አስተዳደራዊና
ግለሰባዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ከቅዱስነታቸው ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗን ይመሩ ዘንድ የተቀመጡት
አበውም ስለችግሩ ከመናገር አልፈው ውጤት ያለው ሥራ መፈጸሙን በባለቤትነት መምራትና መከታተል ያስፈልጋል፡፡
ለምድራዊ ሀብታቸውና የግል ክብራቸው በመጓጓት በማን አለብኝነት ቤተ ክርስቲያኗን የሚበድሉትና የሚገዳደሩት ዕለት
ዕለት በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ሕዝቡን የሚባርከውን እግዚአብሔርን መሆኑን ተረድተው ልብ ሊገዙ ይገባቸዋል፡፡
ዓለምን የፈጠረና የሚገዛ አምላክ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ከኅዳር 1-15 ቀን 2007 ዓ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ