ታኅሣሥ 13 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን 7ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ታኅሣሥ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. አካሔደ፡፡
መነሻውን አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ማእከል ያድረገው ጉዞ ከለሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ከ80 በላይ በሚሆኑ አንደኛ ደረጃ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች ከ5000 በላይ ምእመናንን በመያዝ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
መርሐ
ግብሩ በገዳሙ አባቶች በጸሎተ ወንጌል ከረፋዱ 4፡30 ተጀምሯል፡፡ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የገዳሙ 12ቱ ንቡራነ እድ፤ እንዲሁም
የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት “ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች” መዝ. 11፡7 የሚለውን ጥቅስ መነሻ
በማድረግ የተዘጋጀው 7ኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በመዝሙራቱ፤ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ሲቀርብ
ውሏል፡፡
በዚህም መሠረት በጠዋቱ መርሐ ግብር ክፍል አንድ የወንጌል
ትምህርት የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ ሰባኬ ወንጌል በሆኑት በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ “በቅንነት የሚሄድ
ይድናል” ምሳ.28፡18 በሚል ርእስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም ገዳማዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም
የጎርፍ አደጋ፤ የብዝኅ ሕይወት መመናመን፤ የሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ሌሎችም ችግሮች እየተፈታተኑት ይገኛል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በገዳሙና በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ
ሥራ ተገብቷል፡፡ ፕሮጀክቱን አስመልከቶ የተዋቀረው ኮሚቴ ተወካይ በዲያቆን ቱሉ ስለ ጥናቱ ገለጻ ተደርጓል፡፡
በቀረበው ጥናትም የገዳሙ የወደፊት አቅጣጫና ዕጣ ፈንታ ያሳሰባቸው የገዳሙ አባቶች በ2003 ዓ.ም. ለማኅበረ ቅዱሳን በደብዳቤ በማሳወቃቸው ጥናቱን ለማጥናት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
የተቀረጹት 11 ፕሮጀክቶች በሦስት ዙር በመክፈል እጅግ
አንገብጋቢ የሆኑትን፣ የመጸዳጃና የአካባቢ ንጽሕና፤ የመሬት መንሸራተርትና የጎርፍ አደጋ፤ የመነኮሳት በዓት ችግር፤
የአብነት ትምህርት ቤት አደጋ ላይ መሆኑ፤ መቃብር ቦታ ችግር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ የጠቀሱት ዲያቆን ቱሉ
በሁለተኛው ዙር የአብነት ትምህርት ቤትና የሥልጠና ማእከል ግንባታ፤ መኪና ማቆሚ ቦታ ዝግጅት፤ መቃብር ሥፍራ
ዝገጅት ፕሮጀክች እንዲሁም በሦስተኛው ዙር የጤና ጣቢያ ግንባታ፤ የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፤ የአስኳላ ትምህርት ቤት
ግንባታ ፕሮጀክቶች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡
በቅድሚያ ሊሰሩ ከታቀዱት ውስጥ 24 ክፍል ያለው መጸዳጃ
ቤት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት መጀመሩን፤ 8 ክፍሎችን የያዘ የገላ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤት መጠናቀቁን፤
የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት /ቤዝመንት/ እየገፋ ያለውን ጎርፍ ለመከላከል 100 ሜትር ርዝመት እና 10 ሜትር
ቁመት ያለው የጎርፍ መከለያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ፤ በቅርቡም 2500 ሰው ማስተናገድ የሚችል የእንግዳ
ማረፊያና ሁለገብ አዳራሽ ለመሥራት ዲዛይኑ አልቆ ቦታው በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
ከሰዓት በኋላ የተካሔደውን መርሐ ግብር በማኅበረ ሰላም መዘምራንና በሊቀ ዲያቆን ምንዳዬ ብርሃኑ ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ ተጀምሯል፡፡
ሁለተኛው የወንጌል ትምህርት በደብረ ገነት ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሐዲሳትና የፍትሐ ነገሥት ጉባኤ ቤት መምህር በሆኑት መምህር ወልደ ትንሣኤ “ቸልተንነት” በሚል ርእስትምህርት ተሰጥቷል፡
ብፁዕ
አቡነ ቀውስጦስ የሰላሌና ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ዛሬ ባየሁት ነገር በጣም
ተደስቻለሁ፤ በእንደዚህ ያለ ሰፊ ጉባኤ ተገኝቼ አላውቅም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ `በጉባኤ መካከል እያለን
ብቻችንን የቆምን ይመስለናል` ይላል፡፡ እኔም ምንድነው ነገሩ፤ የት ነው ያለሁት እስክል ድረስ በመንፈሳዊ ተመስጦ
ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ታላቅ ገዳም ይህንን ታላቅ ጉባኤ በማድረጉ ምእመናን እምነታችሁን በሥራ
እየተረጎማችሁት መሆኑን ያየሁበት ነው. . . ክርስቲያናዊ ሥራ እየሠራ ያለ ክርስቲያን መሥጋት የለበትም፡፡
ፈቃዱን እየፈጸሙ የሚያገለግሉ ሁሉ ነፍሳቸው በአደራ ጠባቂው በእግዚአብሔር እጅ ላይ ነው፡፡ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር
አደራ ሰጥታችሁ ክርስቲናዊ አገልግሎታችሁን እስከ መጨረሻው ድረስ እንድትፈጽሙ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ልጅ አባቱ
አይዞህ ካለው ካሰበው ሁሉ ነገር ላይ መድረስ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ የሚጓዝ ብፁዕ ነው እንዳለው
ቅዱስ ዳዊት የምንመካውም ኃይላችንም እግዚአብሔር ስለሆነ በርትታችሁ አገልግሎታችሁን ፈጽሙ” ብለዋል፡፡
|
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ