- በኢትዮጵያ እመቤታችንን መውደድ በልማድ እንደ ተረት በማይታይ ዓይነት ኹኔታ ተስፋፍቶ የኖረ አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም ቢኾኑ እንዳላቸው የእምነት መጠን በእመቤታችን ስም ጸሎት ጸልየው፣ ስእለት ተስለው፣ ምጽዋት አድርገው፣ ዝክርዋን ዘክረው፣ ስምዋን ጠርተው፣ በአማላጅነትዋ ተማፅነው ዐሳባቸው እየተፈጸመላቸው፣ የጎደለው እየሞላላቸው፣ የጠመመው እየተቃናላቸው፣ ድውያን ፈውስ በማግኘት፣ ሠራተኞች ለሥራቸው የተቃና መንገድ በማግኘት፣ መምህራን በሚያስተምሩበት፣ ቅዱሳን ገድላቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜና ምክንያት ኹሉ የእመቤታችንን ረድኤት እያገኙ ስለሔዱና ዛሬም ያው ያልተቋረጠ ስለኾነ ነው፡፡
- ከቀደሙ ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ
ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደነበረ ተነግሯል፡፡ (መጽ.
መሳ.፲፩፥፵፡፡) እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፥ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን፥
የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡
* * *
- ‹‹ተንሥአ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፡፡›› ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ
ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት፡፡›› (መዝ.፻፴፩፥፰)
- ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎት ኰኵሕ ቅሩበ
ጥቅም፡፡›› ‹‹አቅራቢያዬ መልካማ ርግቤ ተነሽ ነዪ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው
ጥላ፡፡›› (መኃ.፪፥፲-፲፬)
በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ የሚታየው በብዛት ልጆች ተሳትፎ የሚያደርጉበት የፍልሰታ ጾምና በዓል ነው፡፡ ፍልሰታ የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው፡፡
ታሪኩ እንደሚገልጸው፣ እመቤታችን ካረፈች በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኀዘን ላይ እንዳሉ ለጊዜው በኢየሩሳሌም ያልተገኘውና በሀገረ ስብከቱ የነበረው ቅዱስ ቆማስ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ቅዱሳን መላእክት ሥጋዋን ወደ ገነት ሲያፈልሱ አይቶና ደርሶ ነገሩንም ከመላእክት ተረድቶ ለወንድሞቹ ለሐዋርያት ነግሯቸው ነበር፡፡
ሐዋርያትም ከእመቤታችን በመለያየታቸው እያዘኑ ምስጢሩን ለማወቅ ይጓጉ ስለነበር ጌታ ተገልጾላቸው፤ ‹‹እናቴን አሳያችኋለሁ፤›› የሚል ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህ ተስፋ ላይ ሳሉም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣ ‹‹ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረን በጾም እመቤታችንን እንዲያሳየን ፈጣሪያችንን እንጠይቀው፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ዐሳቡን ተቀብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ኹለት ሱባዔ ከጾሙ በኋላ ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታ መላውን ሐዋርያት ወደ ገነት አውጥቶ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር እመቤታችንን ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ አንሥቶ ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን አሳይቶ ለዓለም ይህንኑ እንዲያስተምሩ አዘዛቸው ይላል፡፡
መሠረቱ ግን ቀደም ሲል የገለጥነው በመዝሙር ፻፴፩፥፰ ላይ፤ ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤›› የሚለው ነውና እንግዳ ነገር ሊኾን አይችልም፡፡ በዚኹ መሠረት ኢትዮጵያ ይህን ጽሑፍ ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ‹‹ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ኹሉ ክብርዋ ነው፤ በወርቀ ዘቦ ልብስ ተሸልማለች፤ በኋላዋም ለንጉሥ ደናግልን ይወስዳሉ፤ ባልንጀሮችዋንም ይወስዱልኻል፡፡ በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤ ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው፥ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ያመጡልሻል፤›› ተብሎ በተነገረው የነቢያት ቃል መሠረት ልጆችም ወላጆችም በመተባበር የእመቤታችንን የፍልሰታ ጾምና በዓል ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡
ከቀደሙ ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደነበረ ተነግሯል፡፡ (መጽ. መሳ.፲፩፥፵፡፡) እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፥ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን፥ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡
የጾመ ፍልሰታን መታሰቢያ ለመፈጸም ልጆችም ወላጆችም ይተባበራሉ፤ ጾሙ በፍትሕ ነገሥት በአንቀጽ ፲፭ ከተዘረዘሩት አጽዋም አንዱ ነው፡፡ ጾሙ ከፍቅር ጋራ የሚፈጸም ስለሆነ ልጆችም ወላጆችም የሚጾሙት በጉጉት ነው፡፡ ወላጆችም ከባድ ምክንያት ካላጋጠማቸው በስተቀር ከአልጋው ወርደው፣ ከመሬት ላይ ተኝተው ወይም ከቤታቸው ወጥተው በቤተ እግዚአብሔር ዙሪያ ማረፊያ አሰናድተው ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ድረስ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም በመስማት፣ በምጽዋት፣ ቅዳሴ በማስቀደስ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ይጾሙታል፡፡
ልጆችም ረኀብ ሳይሰማቸው፣ ውኃ ጥም ሳያሸንፋቸው ከሰባት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ሕፃናት እየጾሙ ይቆርባሉ፤ በመጨረሻም ነሐሴ ፲፮ ቀን ወላጆች በዓሉን በሥነ ሥርዓት ሲያከብሩ ልጆችም በልዩ ሥነ ሥርዓት ያከብሩታል፡፡
‹‹አሸንዳ›› የሚባል ሣር ዓይነት ቅጠል አለ፤ ኹኔታው ቀጭን ቢኾንም ቁመቱ ረዘም ያለ ኾኖ ቅርፁ ፊላ ዓይነት ነው፤ ሲነቅሉት ሥሩ ነጭ ነው፡፡ ዛጎል ይመስላል፡፡ በልዩ አሠራር ሠርተው በቀሚሳቸው ላይ ይታጠቁታል፤ እንደ ዘርፍ ኾኖ ወደ ታች ይወርዳል፤ በሚጫወቱበት ጊዜ ዙሪያውን ሲነሣ ክንፍ ይመስላል፡፡ በዚኽ ዓይነት ሥርዓት በዓሉን ሲያከብሩ ይውላሉ፤ በተለይ በገጠር ላሉ ሴቶች ሕፃናት ቆነጃጅት ልዩ በዓላቸው ነው፡፡
አሸንዳ ከሚባለው ሣር ዓይነት ቅጠል በልዩ አሠራር ሠርተው የሚታጠቁትና ሲጫወቱ ዙሪያውን የመነሣቱ ኹኔታም መላእክት እመቤታችንን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው እያመሰገኑ ማሳረጋቸውን ያሳስባል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕራፍ ፮ ላይ ባየው ራእይ÷ ሱራፊ መልአክ በኹለት ክንፍ ፊቱን፣ በኹለት ክንፍ እግሩን ሲሸፍን፣ ኹለት ክንፉን በግራ በቀኝ ዘርግቶ ረብቦ ይታያል የሚለውን ያመለክታል፤ በዓሉንም የአሸንድዬ በዓል ይሉታል፡፡ በእውነት፤ ‹‹ደናግልን ለንጉሥ በኋላዋ ይወስዳሉ፤›› ሲል ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ቃል ልጆች በእመቤታችን ፍቅር እየተኮተኮቱ አድገው ለእግዚአብሔር ቤተሰብ መኾናቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ ሥርዓት ያደጉ ልጆችን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ከእመቤታችን ፍቅር የሚለያቸው የለም፡፡
በኢትዮጵያ እመቤታችንን መውደድ በልማድ እንደ ተረት በማይታይ ዓይነት ኹኔታ ተስፋፍቶ የኖረ አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም ቢኾኑ እንዳላቸው የእምነት መጠን በእመቤታችን ስም ጸሎት ጸልየው፣ ስእለት ተስለው፣ ምጽዋት አድርገው፣ ዝክርዋን ዘክረው፣ ስምዋን ጠርተው፣ በአማላጅነትዋ ተማፅነው ዐሳባቸው እየተፈጸመላቸው፣ የጎደለው እየሞላላቸው፣ የጠመመው እየተቃናላቸው፣ ድውያን ፈውስ በማግኘት፣ ሠራተኞች ለሥራቸው የተቃና መንገድ በማግኘት፣ መምህራን በሚያስተምሩበት፣ ቅዱሳን ገድላቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜና ምክንያት ኹሉ የእመቤታችንን ረድኤት እያገኙ ስለሔዱና ዛሬም ያው ያልተቋረጠ ስለኾነ ነው፡፡
በረድኤት ከሚያገኙት ተስፋ ሌላ በራሳቸውም ኾነ በሌላ ሰው በኩል በራእይ፣ በሕልም፣ በገሃድ እየተገለጸች የምታደርግላቸው ማጽናናት ልባቸውን የፍቅርዋ ምርኮኛ፣ የረድኤትዋ እስረኛ አድርጎት ይኖራል፡፡ ይህም ለአባቶቻችን ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ስለ እውነት ምስክርነት ሲባል ይህ ለኹላችንም እንኳ የደረሰ ተስፋ መኾኑን ላረጋግጥላችኹ እወዳለኹ፡፡ ስለዚህ ነው ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች ለእመቤታችን በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ቀን የሚያደርጉትን ጾምና በዓል የበለጠ ያደርገዋል ያልኹት፡፡
በዮሐንስ ራእይ ምዕ. ፲፱ ፥ ፯-፰ ላይ፤ ‹‹የበጉ ሠርግ ደርሷልና ደስ ይበለን፤ ሴቲቱም ተዘጋጅታለች፤ እንድትለብስም ንጹሕ የብርሃን ልብስ ተሰጣት፤ ይኸውም ልብስ የቅዱሳን ክብር ነው፡፡ መጽሐፍ ወደ በጉ ሠርግ የተጠሩ ብፁዓን ናቸው፤ ይህ የእውነት ቃል የእግዚአብሔር ነውና አለኝ፤›› የሚል ተጽፏል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ በላከው መልእክቱ ምዕ. ፬ ፥ ፲፯ ላይ፤ ‹‹ጌታን ለመቀበል በደመና ወደ አየር እንነጠቃለን፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከጌታ ጋራ ለዘለዓለም እንኖራለን፤›› በማለት የገለጠው ተስፋ ለቅዱሳን በመታደሉ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ.፳ ፥ ፱-፲፪ የገለጠው የሰው ኹሉ ትንሣኤ ከመድረሱ አስቀድሞ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቅድስናን ክብር እንድትጎናጸፍ ልጅዋ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፈቀደ በእናትነትዋ በመንፈስ ቅዱስ መቀደስን በቅድሚያ እንዳገኘች፤ ዛሬም÷ ኋላም ሞቶ ተነሥቶ በዐዲስ ሕይወት ከጌታ ጋራ መኖርን አግኝታለችና ይህን የሚያምን ልብ ሕያውነትዋን፣ በሕይወት መኖርዋን አምኖ፤ ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኘሽ እናታችን፣ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ከልጅሽ ለምኚልኝ፤ አማልጂኝ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መንበር ፊት በምታቀርቢው ጸሎትሽ፣ አማላጅነትሽ አስቢኝ፤›› እያለ ሊጸልይ ይገባዋል፡፡
ምንጭ፡- ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፤ ፲፱፻፸፱ ዓ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ