በደመላሽ ኃይለ ማርያም
የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ፍሬ
ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ለታክሲ ሹፌሮች፣ ተራ አስከባሪዎችና ረዳቶቻቸው አገልግሎት እንዲሰጥ የመሠረተውን
ጉባኤ 8ኛ ዓመት አስመልክቶ ታኅሣሥ 25 እና 26 ቀን 2007 ዓ.ም. “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ
በርሳችን እንተያይ” በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ መሪ ቃል በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አባላቱና በርካታ ምዕመናን
በተገኙበት ተከበረ፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብሩ አስተዳዳሪ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ የታክሲ አገልግሎት ሥራን በሚመለከት ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር አያይዘው “ኖላዊ” በሚል ርዕስ በተጋባዥ መምህራን ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡
የታክሲ ሹፌሮች፣ ረዳቶቻቸው እና ተራ አስከባሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን በጎ ያልሆነ ግንኙነት ለማሻሻል እና በክርስትና ሕይወታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍራት እንዲቻል፤ እንዲሁም በእነሱ ቸልተኝነት እና ጥድፊያ በመኪና አደጋ እየጠፋ ያለውን የሰውን ሕይወት ለመቀነስ ታስቦ ጉባኤው መመስረቱን የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ ዲያቆን ያሬድ ያስረዳል፡፡
ዲያቆን ያሬድ አክሎም “የአባላቱን ቁጥር ከዚህ የበለጠ በማሳደግና በጉባኤው ውስጥ በማካተት ትምህርተ ሃይማኖት እንዲማሩ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት እንዲያውቁ፤ በሥነ ምግባር የታነጹና ሥርዓት አክባሪዎች ሆነው ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ከፈጣሪ ጋር እንጥራለን” ብሏል፡፡
ከተጋባዥ እንግዶች መካከልም የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ድንገተኛ፤ ለንስሐ እና ለኑዛዜ የማያበቃውን በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት ለመከላከል ምእመናን እና የታክሲ ሹፌሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጪው ዓመት ሃምሳኛ ዓመቱን የሚያከብረው ይህ የፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት እየሠራ ያለው ሥራ እጅግ በጣም ሊበረታታ የሚገባውና በሌሎችም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊለመድና ሊሰራበት እንደሚገባ ጉባኤውን የተከታተሉ ምእመናን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ