ዓርብ 9 ጃንዋሪ 2015

ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ



  • ሥርዐተ ቀብሩ ዛሬ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
His Grace Abune Aregawi
በተባሕትዎአቸውና በተመሰገነው ምንኵስናቸው የሚታወቁት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ፡፡ ብፁዕነታቸው ዛሬ፣ ዓርብ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ያረፉት ለተሻለ ሕክምና በገቡበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡
ብፁዕነታቸውን ለኅልፈት ያደረሳቸው፣ ከአንድ ወር በፊት ለሐዋርያዊ ተልእኮ ወደ ደቡብ ሱዳን በሔዱበት ወቅት ያጋጠማቸው ቢጫ ወባ በኩላሊታቸውና በሳምባቸው ላይ ያስከተለው ጉዳት ነው፡፡
ከጉዟቸው መልስ ‹‹እኔ ንግግሬ ከእግዚአብሔር ጋራ ነው›› በማለት ያለሕክምና ርዳታ ለኹለት ሳምንት ያኽል በተዘጋ ማረፊያቸው የቆዩት ብፁዕነታቸው፣ በብፁዓን አባቶችና በቅርብ ወዳጆቻቸው ተማኅፅኖ በዘውዲቱ ሆስፒታል እና በሳንቴ የጤና ማእከል በተደረገላቸው ከፍተኛ ክትትል የተጎዳው ኩላሊታቸው አገግሞ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በተሻለ ኹኔታ ላይ ይገኙ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ይኹንና ከዕድሜ አንጋፋነታቸው ጋራ ሕመሙ በሳምባቸው ላይ ባደረሰው ጉዳት የተፈጠረው ኢንፌክሽን ለኅልፈት እንደዳረጋቸው ተመልክቷል፡፡
በቅርበት የሚያውቋቸው ወገኖች÷ የዋልድባው መነኰስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሀብት ምክር ያላቸው፣ ታሪክ ዐዋቂና የታያቸውን በግልጽ የሚናገሩ መምህር ወመገሥጽ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
www-st-takla-org-abune-paulos-in-alex-15-july-2007-017
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በግብጽ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ሐምሌ ወር ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.፣ ሐምሌ ፰ ቀን በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም በተሠራው ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት ወቅት፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የቅዱስነታቸውን ንግግር በልሳነ ዓረቢ እየመለሱ አሰምተው ነበር፡፡
የቀደምት ቅዱሳን አበውን ትውፊት በመከተል በግብጽ ገዳማት ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያኽል በመቀመጥ ከአኃው መነኰሳት ጋራ መንፈሳቸውን ያስተባበሩት ብፁዕነታቸው፣ ልሳነ ዓረቢን አቀላጥፈው በመናገርም ይታወቃሉ፡፡ የቅድስት ሀገር ተሳላሚ ለመኾን የበቁትም በወጣትነታቸው ማለዳ ሳሉ ነበር፡፡
በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ አቡነ አረጋዊ ተብለው ጥቅምት ፲፰ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት በአራተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ነው፡፡
ብፁዕነታቸው ቀድሞ ሊቀ ሥልጣናት በተባሉበት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በበላይ ጠባቂነት ከመወሰናቸው በፊት፣ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲኹም የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን አገልግለዋል፡፡
የብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር ዛሬ፣ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለረጅም ዓመታት በአገለገሉበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በ9፡00 እንደሚፈጸም ተገልጧል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለብፁዕ አባታችን ዕረፍተ ነፍስን ይስጥልን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...