በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 34ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 8 ቀን 2008
ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየአህጉረ
ስብከቱ ሓላፊዎችና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመክፈቻ ቃለ በረከት በማስተላለፍ ቀጥሏል፡፡
ቅዱስነታቸው ወደፊት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው ያሏቸውንም እንደመፍትሔ ጠቁመዋል፡፡ ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ሕሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርህ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነት ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ የምእመናን ልብ የሚያረካ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትንም በተመለከተ አባ ኃ/ማርያም መለሰ /ዶ/ር/ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ሪፖርትም በ2007 በጀት ዓመት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሊቃውንት ጉባኤን፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን፣ የበጀትና ሒሳብ መምሪያን፣ የገዳማት መምሪያን፤ የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን፣ የሰብከተ ወንጌልና የሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና የልማት ድርጅትን፣ የማኅበረ ቅዱሳንን፣ . . . ወዘተ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ ጠቅላላ የሰበካ ጉባኤው ከየአህጉረ ስብከት የቀረቡ ሪፖርቶችን በማድመጥ ላይ ይገኛል፡፡
የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም ይቀጥላል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ