2015 ኖቬምበር 29, እሑድ

“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጽሑፍ ቅርስ ላይ ከአለኝ ትዝብት”


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን

ኒው ዮርክ ከተማ

(የተራድኦ ድግስ ምሽት፥ ኅዳር  ቀን ፳፻፯ . = November 14, 2015) 


ጌታቸው ኃይሌ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንድታገለግሉ የተመረጣችሁ የተከበራችሁ ካህናትናዲያቆኖት፥ የመድኃኔ ዓለም አባላት እንድትሆኑ የሐዋርያትን ጥሪ ያከበራችሁየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እኅቶቼና ወንድሞቼ፥ በዚህ የበጎአድራጎት ምሽት ላይ ተገኝቼ ለሥጋ ጣፋጩን የኢትዮጵያ ምግብ በስመጥር ጠጅአያወራረድኩ እንድመገብና ስለመንፈስ አርኪው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ያሉኝን አንዳንድ ትዝብቶች እንዳጫውታችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የትልቅ ታሪክ ችቦ ተሸካሞችነን። ችቦውን መሸከም መስቀለ ሞቱን የመሸከም ያህል ይከብዳል፤ ግን የኩሩውማንነት መታወቂያችን ስለሆነ ከባዱን ሸክም በደስታና በጸጋ እንሸከመዋለን።ስለችቦውና ስለ አቀጣጣዮቹ ተናገር ስላሉኝ ተደስቻለሁ። ቅዱስ ዳዊት “ተፈሣሕኩእስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር” (ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ስላሉኝተደስቻለሁባለው አነጋገር ስለተጠቀምኩ መንፈሱ እንደማይወቅሰኝ እለምነዋለሁ።

ትልቁን ታሪካችንን በመመዝገብ የትልቅ ሕዝብ ቀጣዮች መሆናችንን የነገሩን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ናቸው። ባለውለታዎች ስለሆኑ፥  እናመስግናቸው፤ ቅዱሳንስለሆኑ፥  እንዲጸልዩልን እንለምናቸው።
“ሊቃውንት አባቶቻችን ምን ምን መዘገቡልን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናቱእንደቀጠለ ነው። በዚህ ጥናት ላይ የምዕራባውያን ምሁራን ተሳትፎ ከፍ ያለ ቦታይዟል፤ አድናቆትም አለኝ። የምዕራባውያን ምሁራን በምርምራቸው የሚያደርጉትንስሕተት ሁሉ ከክፋታቸው እንደመነጨ አድርጌ አላየውም። ለምሳሌ በኪዳነ ወልድክፍሌ ስም የሚታወቀውን መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስየሚመጥን የግዕዝ መዝገበ ቃላት በኢትዮጵያ አልተጻፈም። የዚህ ድንቅ መጽሐፍመሠረት ጀርመናዊው ዲልማን በላቲን ቋንቋ ያዘጋጀው የግዕዝ መዝገበ ቃላት ነው።እኔም ማስረጂያ ይዤ እንዲያርሙ የምጠይቃቸውን እርማት፥ በማልቀበለውምክንያት እምቢ ያሉበትን ጊዜ አላጋጠመኝም።

የምዕራባውያን ምሁራን የግዕዝን ምንጮች ከሚመረምሩበት ምክንያት አንዱ፥በዓለም ላይ የጠፉ የጥንት የክርስትና ሃይማኖት ምንጮች ኢትዮጵያ ገዳማት ውስጥይገኙ እንደሆነ ለማወቅ ነው። ክርስትና የዛሬውን መልክ እስኪይዝ ብዙ እንቅፋቶችንአልፏል። እንቅፋቶቹን ከፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ ብዙ የክርስትናን ታሪክ ዘጋቢዎችመነሣት ነው። እዚህ ላይ በእኛ ዘንድ የተፈጸመውንና የታመነውን የሥራውን ዜናበሥርዐት ሊጽፉ የጀመሩ ብዙዎች ናቸው ያለውን የቅዱስ ሉቃስን ምስክርነትመጥቀስ ይቻላል። የጥንቶቹ ሊቃውንት ከውዝግብ ለመውጣት ሲሉ ጥቂቶቹንመጻሕፍት መርጠው የቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መጻሕፍት አድርገው አወዛጋቢ ነገርያለባቸውን ሌሎቹን ኮነኗቸው፤ አጠፏቸውም። ዛሬ የሃይማኖት ተመራማሪዎችእነዚህ የተኮነኑ መጻሕፍትና በሌላ ምክንያት የጠፉ ስለክርስትና ታሪክ የሚነግሩን ነገርይኖራል በማለት ይፈልጓቸዋል።

በመጠኑም ቢሆን ተገኝተዋል። በጣም የታወቁትን ልተውና አንድ አሜሪካዊ ተማሪበቅርብ ቀን ስላገኘው የጥንታዊ ድርሰት ብጣሽ (fragment) ልናገር። ሙሴናየፈርዖን ጠንቋዮች ታምራት በመሥራት ይወዳደሩ እንደነበረ እናስታውሳለን። አንድያልታወቀ ደራሲው ስለፈርዖን ጠንቋዮች የደረሰው ጥንታዊ ድርሰት ኖሯል። መኖሩየታወቀው የድርሰቱ አንድ ብጣሽ በግሪክኛው ተገኝቶ ነው። ይህ ተማሪ ያገኘውየግዕዝ ብጣሽ ብራና ግሪክኛው ውስጥ ያለውን የሚመሰክርና የጐደለውን የሚያሟላነው። ተማሪው ከማግኘቱ በፊት እንዲህ ያለ ድርሰት በግዕዝ መኖሩን ማንምአያውቅም ነበር። ይቺ ብጣሽ የብራና ጽሑፍ መገኘት ያደረገው አስተዋጽኦ በብጣሹመጠን የሚገመት አይደለም።

በግሌ ወደ አጋጠሙኝ ሁለት ጉዳዮች ልሻገር። አባ ባሕርይ መዝሙረ ክርስቶስንሲደርሱ ከጠቀሟቸው ብዙ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ከሊላ ወድምና የሚባለውመጽሐፍ እንደሆነ ነግረውናል። እኔም ድርሰቶቻቸውን ስተች አንሥቼዋለሁ።መጽሐፉ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጒሞ ሳለ በግዕዝ ስላልተገኘ፥ ሊቃውንቱየመነኵሴውን ቃል መጠራጠር ጀምረው ነበር። ግን መጽሐፉ ራሱ ባይገኝም፥ የሐይቅገዳም መጽሐፉ እንደነበረው ማስረጃ አግኝቻለሁ፤ መዝገባቸው ከመዘገባቸውመጻሕፍት አንዱ ከሊላ ወድምና ነበረ። መጽሐፉን አይተውት ይሁን ወይም ስሙንከመዝገብ ላይ አግኝተውት ይሁን ባይታወቅም፥ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃንከአዘጋጁት የመጻሕፍት መዝገብ ውስጥ አግብተውታል።


ሁለተኛው፥ ዮሴፍ ወአስኔት የሚባለውን መጽሐፍ የሚመለከት ነው። ይህምመጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጕሞ ሲገኝ በግዕዝ አልተገኘም። ግን አባ ጊዮርጊስዘጋስጫ መጽሐፈ ምስጢር በሚባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እመቤታችንን ንህብዘአስኔት (የአስኔት ንብብለዋታል። አስኔት ንብ እንደነበራት የሚነግረን ምንጭዮሴፍ ወአስኔት ብቻ ስለሆነ ደራሲው አባ ጊዮርጊስ መጽሐፉ እንደነበራቸው--ኢትዮጵያ እንደነበራት--ታምኖበታል። እዚህም ላይ ትንሽ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ።

ከእኛ ሊቃውንትም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴና ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃንምን ምን መጻሕፍት እንዳሉን በዝርዝር ጽፈዋል። ግን በቂ አይደለም። ምርምሩይቀጥላል። ምኞቴ በዚህ በተቀደሰ ተግባር ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እንዲሰማሩነው። አባቶቻችንን የማደንቀው ለግዕዝ ያንን ሁሉ የሃይማኖት መጽሐፍ የመቀበያችሎታ ማስታጠቃቸው ነው። ይህ የሚያመለክተው ግዕዝ ከአክሱም ዘመነ መንግሥትበፊት ዳብሮ እንደነበረ ነው። ለምሳሌ ግዕዝ ተቆጣ ለማለት ከአራት የማያንሱቃላት እንዳሉት በአጋጣሚ አይቻለሁ፤ መአከ (ተምእከ) መጐጸ(አመጐጸ) ተምዐ (ተምዕዐ) ተቈጥዐ

አማርኛ የሌለው አንዳንድ ቃላትም አጋጥመውኛል፤ ለምሳሌ፥ ሕልበት(nostril)ምንሀብ (factory). አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሕልበት መተርጐሚያ አማርኛቢያጡ፥ የአፍንጫ ጉንጭ አሉት።

የግዕዝን ችሎታ ብናውቅ ኖሮ፥ bank የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አማርኛ ውስጥአይገባም ነበር። ባንክ በመሠረቱ የገንዘብ መለዋወጫ ጠረጴዛ (bench)ነው።የሉቃስን ወንጌል ስናነብ ምዕራፍ ፲፱ ላይ ጌታችን የሰጠን አንድ ምሳሌ እናገኛለን።እንደምሳሌው፥ አንድ ጌታ ከአሽከሮቹ ለዓሥሩ ነግደው እንዲያተርፉለት ዓሥርምናናት ከፋፍሎ ሰጥቷቸው ነበር። በመጨረሻ ሁሉም ገንዘቡን ከነትርፉ ለጌታቸውሲያስረክቡ፥ አንዱ ብቻ የወሰደውን ሳይነግድበት ሳያተርፍበት እንዳለ ከትቶ እንዳለለጌታው መልሶ ሰጠው። ጌታው አዝኖና ተቆጥቶ እንዲህ አለው፤

“ወለምንት ኢያግባእከ ወርቅየ ውስተ ማእድ”
([ላለመነገድህ ምክንያት ካለህ] ታዲያ ገንዘቤን ለምን ከማእድ አላስገባህም?”
ምንጩ ግሪክኛው የሚለውም “ትራፔዛ” (ጠረጴዛነው። ታዲያ የአማርኛው ትርጕምከላይ እንዳመለከትኩት መሆን ሲገባው፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ትርጉም “ባንክ”፥የኦርቶዶክሶቹ “ለዋጮች” ይላል። ግን ቀደም ብሎ “ማእድ” እንዳለ ከግዕዝ ወደአማርኛ ቢተላለፍ ኖሮ “ባንክ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ምንም ሳይጕድልብንልናስቀረው እንችል ነበር።

የዮሐንስ ወንጌልን ሳነብና  ምዕ 19 . 24 ላይ ስደርስ ደግሞ፥ ስለ ግዕዝ የቃላትብልጽግናና ስለአባቶች ጥንቃቄ የገረመኝና እኛን ልጆቻቸውን የሚወቅስ ነገርአጋጠመኝ፤ ጥቅሱን እንዳለ ልጥቀሰው፤
 
ወሐራሰ ሶበ ሰቀልዎ ለኢየሱስ ነሥኡ አልባሲሁ ወረሰይዎ አርባዕተ ክፍለ ለአሐዱሐራ ክፍለ። ወክዳኖሂ እልታኀ ዘአልቦ ርፍአት ዘእምላዕሉ እኑም ኵለንታሁ።ወተባሀሉ በበይናቲሆሙ ኢንግምድ ወኢንስጥጥ አላ ንትፋሰስ ለዘረከቦ ይርከቦ። ከመይብጻሕ ቃለ መጽሐፍ ዘይቤ። ተካፈሉ አልባስየ ለርእሶሙ ወተዓፀው ዲበ ዐራዝየ።

ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፥ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ አራት ቦታ ከፈሉት። መርፌ ስላልነካው ከላይ እስከታች አንድ ወጥ ሆኖ ስለተሠራው ስለ ፈርጅ ቀሚሱ ግን እርስ በርሳቸው (እንዲህ) ተባባሉ፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰው ይድረሰው እንጂ አንቅደደው”። ይህም፥ “ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉት፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።)
እንግሊዝኛውም እንደ አማርኛው ከሁለቱም ቦታ “ዕጣ ተጣጣሉ”(cast lotsነውየሚለው።
. . . So they said to one another, Let us not tear it, but cast lots for it to see who will get it. This was to fulfill what the scripture says, They divided my clothes among themselves, and for my clothing they cast lots.

በግዕዝ ግን አነጋገሩ የተገለጠው በሁለት የተለያዩ ሐረጎች መሆኑን ልብ እንበል፤ ተፋሰሱ  ተዐፀዉ ለምን እንዲህ ሆነ ብየ የግሪኩን ምንጭ ባየው፥ እውነትምሁለቱ ሐረጎች በግሪክኛውም የተለያዩ ናቸው፡ lachomen እና ebalon kleeron


* * * * * * * *
ባሁኑ ሰዓት ጥሪየ አድርጌ የያዝኩት አባቶቻችን ከውጪው ዓለም ምን ተረጐሙልን፥እነሱስ በተረጐሙት ላይ ምን አከሉበት የሚሉትን ሁለቱን ጥያቄዎች መመለስን ነው።አምሳያቸው እውጪ አገር ካለ ከውጪ የተተረጎሙ ናቸው ማለት አያስቸግርም።ደንቃራ የሆነብኝ አንዳንዶቹን የግዕዝ መጻሕፍት ከምዕራቡ ዓለምና ከመካከለኛውምሥራቅ ጠፍተው ነው እንጂ፣ ትርጕም ናቸው የሚለው አነጋገር ነው። እርግጥከሌላው ዘንድ ጠፍተው እኛ ዘንድ የተገኙ አሉ። ይኸም ቢሆን አባቶቻችንና ቤተክርስቲያናችንን የሚያስመሰግን ነው።

ቢሆንም እኛ ተቀባዮች ብቻ ባንሆን እንመርጣለን፤ ለነገሩ ተቀባዮች ብቻምአይደለንም። ይኸንንም ለማሳየት ለዛሬው ንግግሬ ሁላችሁም በምታውቁትበመጽሐፈ ቅዳሴያችን ላይ አተኩራለሁ። 

የዶክተር ገብረ ጻድቅ ደገፉና የኔ መምህር ቄስ ማርቆስ ዳውድ የመጽሐፈ ቅዳሴውንእንግሊዝኛ ሲያሳትሙ፥ እመቅድሙ ውስጥ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤
 
It is said by the Ethiopian Church authorities that they received their liturgy of fourteen Anaphoras from the Church of Egypt. The Church of Egypt confirms this but has, unfortunately, lost most of the fourteen.
 
(በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣኖች ዘንድ ዓሥራ አራቱን የቅዳሴ መጻሕፍታቸውን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን እንደወሰዱ ይነገራል። የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይኸንን ታረጋግጣለች። ግን መጥፎ ዕድል ሆኖ ከዓሥራ አራቶቹ አብዛኛዎቹ ጠፍተውባታል።
 የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የጠፉባት የቅዳሴ መጻሕፍት ቍጥር የሚታወቀው ኢትዮጵያውስጥ ባሉት መጻሕፍት ቍጥር መሆኑ ነው። እንዲህ ከሆነ፥ ከዓሥራ አራት ሊበልጡነው። ምክንያቱም ቄሱ አልሰሙም እንጂ፥ ቅዳሴዎቹ ወደኻያ ይጠጋሉ። መምህሬ ቄስማርቆስ ዳውድ ይህን መቅድም ሲጽፉና ትርጕሙን ሲያሳትሙ እያወቁ ሁለት በደልፈጽመዋል፤ (1) “የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይኸንን ታረጋግጣለች” ያሉት ማስረጃሳይኖራቸው ነው። (2) መጽሐፈ ቅዳሴውን የተረጐመላቸው አብሮ አደግ ወዳጄናጓደኛየ ዶክተር ገብረ ጻድቅ ደገፉ ነው። ግን እኝህ መንፈሳዊ አባትና መምህር ይኸንንሐቅ ጨቁነውታል፤ የገብረ ጻድቅን ስም ለምስጋና እንኳን አላነሡትም።

ከታተመው መጽሐፈ ቅዳሴ ውስጥ ያሉት የቅዳሴ ጸሎቶች (አኰቴተ ቍርባንዓሥራአራት የሆኑት ለኅትመት የተመረጠው የብራና ቅጂ ውስጥ ያሉት ዓሥራ አራትስለነበሩ ነው። ካህናቱ እንደምታስታውሱት፥ ቅዳሴ ጎርጎርዮስ (ነአኵቶ ለገባሬሠናያት--ነአኵተከ እግዚኦን አይደለምየሚያነሣው ሊቀ ጳጳሱን አባ ዮሐንስን(፲፮ኛው 1676-1718) እና ጳጳሱን አባ ሲኖዳን (1671-1693) ነው። የእትሙምንጭ የተቀዳው በነሱ ዘመን 1676 እና 1693 መካከል በነበረው ዘመን ነውማለት ነው።

ያደረግሁት ምርምር ጥሩ ዕድል ሆኖ ከዓሥራ አራቶቹ አብዛኛዎቹ ከግብፅ ቤተክርስቲያን የመጡ ሳይሆኑ፥ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰቶች መሆናቸውንአረጋግጦልኛል። አባ ጊዮርጊስ በአፄ ዳዊትና በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን የኖሩ ብዙመጻሕፍት የደረሱ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ናቸው። ከድርሰቶቻቸው ውስጥኆኅተ ብርሃን፣ አርጋኖነ ውዳሴ (= አርጋኖነ ድንግል) ውዳሴ መስቀል፤ መጽሐፈብርሃን፣ ጸሎተ ፈትቶ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምስጢር የሚባሉ መጻሕፍትይገኛሉ።

ደራሲያቸው ያልተረጋገጠውን አኰቴተ ቁርባኖች የመረመርኩትና የጥናቴን ውጤትለኅትመት የላክሁት እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉበትን ስልት መሣሪያ በማድረግ ነው።ምርምሬን የጀመርኩት ውበቱን ምዕራባውያን በመሰከሩለት ድርሰታቸው አርጋኖነውዳሴ ነው። ግን መጀመሪያ አርጋኖነ ውዳሴ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንጂ፥እንደሚታመንበት የአርመናዊው ጊዮርጊስ (Giorgis the Armenian)እንዳይደለ ማስመስከር ነበረብኝ። ያስመሰከርኩበት ጥናት የምዕራባውያን ሊቃውንትቀንድ የሆነ ሊቅ፥ The erroneous dating of the Arganonä Wəddase . . . as well as its false attribution to un unknown Giorgis the Armenian have been conclusively refuted ሲል ፍርዱን መዝግቧል።

ይኸ በራሱ አንድ አስደሳች የድካም ውጤት ነው። እርግጥ በኛ ዘንድ አርጋኖነ ውዳሴየአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆኑን የሚጠራጠር የለም። ግን የኢትዮጵያ ታሪክ በምዕራቡዓለም በሰፊው ስለሚጻፍ፥ ልጆቻችንም እነሱ ዘንድ ስለሚማሩ፥ ታሪካችንንበተገኘበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ማስተካከል ግዴታችን ነው። ከቅዳሴዎቹ አብዛኞቹ የአባጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆናቸውን ለማሳየት የምጥረውም ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን የመጡናቸው ተብሎ በሀገራችን ሳይቀር ተቀባይነት ያገኘውን የተሳሳተ እምነት ለማስቀረትነው። አርጋኖነ ውዳሴ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆኑ ከተረጋገጠ የአጻጻፋቸው ስልትምን እንደሚመስል ላሳይ። በድርሰቶቻቸው ላይ ሁሉ በተለይ ከዚህ በታች ያሉትባሕርዮች ጎልተው ይታያሉ፤
1. ይዞታቸው እንደ መጽሐፈ ምስጢር ነገረ መለኮት ማስተማሪያ ናቸው፤
2. በጀመሩበት ቃል ብዙ አረፍተ ነገሮች ያከታትሉበታል፤
3. በአረፍተ ነገሩ መጀመሪያ ሐረግ ላይ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛው ሐረግያጠነክሩታ፤
4. በአረፍተ ነገሩ መጀመሪያ ሐረግ ላይ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛው ሐረግያፈርሱታል፤
5. አረፍተ ነገሮቹ ቤት የሚመቱ የማይመቱም ቅኔዎች ናቸው፤
6. ካለው ግስ ላይ አዳዲስ ቃላት ይፈጥራሉ፤
7. ለኛ ባልታወቁ የውጪ ቃላት ይጠቀማሉ፤

እነዚህ የአጻጻፍ ባሕርዮች በብዙዎቹ ቅዳሴዎች ላይ ይታያሉ።
ቅዳሴ በመሠረቱ ከጸሎተ ሃይማኖት አልፎ ነገረ መለኮት መተቻ አይደለም። ብዙዎቹቅዳሴዎቻችን ግን እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰቶች እንደ መጽሐፈ ምስጢር እናእንደ ፍካሬ መለኮት መለኮትን በሰፊው ይተቻሉ። ሁሉንም የአባ ጊዮርጊስን የአጻጻፍባሕርዮች ለማሳየት ከሁሉም ምሳሌ መስጠት መጽሐፈ ቅዳሴውን መገልበጥይሆናል። ግዕዝ የማያውቀውንም ያሰለቸዋል። ሆኖም ከዚህ በታች ያሉትን ብቻእንመልከት፤

ከአርጋኖነ ውዳሴ ለምሳሌ
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እሙስና፡ (ከብልሸት መሸሻ አንቺን አገኘሁ ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምአፈ፡ አናብስት፡ (ከአንበሶች አፍ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምአፈ፡ ተኵላተ፡ ዐረብ፡ (ከዐረብ ተኵላ አፍ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምቃለ፡ ዘይጽዕል፡ (ከተሳዳቢ ቃል መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምእደ፡ ኵሎሙ፡ ጸላእትየ፡ (ከጠላቶቼ ሁሉ እጅ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)

(1) ከቅዳሴ ማርያም፤

አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ክበብ . . . አላ መንክር. . .  (መለኮቱ ክበብ የለውም . . . አስደናቂ እንጂ . . .።)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ግድም ወኑኅ . . . አላ ምሉእ . . . (መለኮቱ አግድሞሽና ርዝመት የለውም . . . በሁሉም ዘንድ የሞላ ነው እንጂ . . .)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ምስፋሕ . . . አላ ውስተ ኵሉ . . (መለኮቱ መስፋፊያ ቦታ የለውም . . ግዛቱ በሀገሮች ሁሉ ነው እንጂ . . .)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ዘበላዕሉ ጠፈር . . . አላ ጠፈር ውእቱ . . . (መለኮት በላዩ ጠፈር የለበትም . . . እሱ እራሱ ጠፈር ነው ኢንጂ . . .)

ይህ ጥቅስ (1)ነገረ መለኮት ነው፤ (2) አረፍተ ነገር በጀመረበት ቃል (አኮአረፍተነገር ይደጋግማል፤ (3) በመጀመሪያው ሐረግ ውስጥ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛውሐረግ ያፈርሰዋል (አላ)

(2) ከቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤

አልብከ ጽንፍ ወአልብከ ማኅለቅት፤ (ዳርቻ የለህም፥ መጨረሻም የለህም፤)
አልቦ ዘረከቦ ወአልቦ ዘይረክበከ፤ . . . (ያገኘው የለም፥ የሚያገኝህም የለም . . .፤)
አልብከ ጥንት . . . (መጀመሪያ [origin] የለህም. . .፤)
ፈጠርከ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትትቀነይ፤ (ሳትገዛ ሁሉን ፈጠርክ፤)
ትጸውር፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትደክም፤ (ሳትደክም ሁሉን ትሸከማለህ፤)
ትሴሲ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢታሐጽጽ፤ (ሳታጓድል ሁሉን ትመግባለህ፤)
ትሔሊ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢታረምም። (ዝም ሳትል ለሁሉ ታስባለህ፤)
ትሁብ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትቀብል  (ሳትጐድል ለሁሉ ትሰጣለህ፤)
ታረዊ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትነጽፍ፤ (ሳትጠግ ሁሉን ታጠጣለህ፤) 8

ትዜከር፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትረስዕ። (ሳትረሳ ሁሉን ታስታውሳለህ፤)
ተዐቅብ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትነውም፤ (ሳትተኛ ሁሉን ትጠብቃለህ፤)
ትሰምዕ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትጸመም፤ (እምቢ ሳትል ሁሉን ትሰማለህ፤)
ተኀድግ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትነሥእ። (ሳትወስድ ለሁሉ ትተዋለህ።)
በተለይ እነዚህን ቀጥሎ የጠቀስኳቸውን ሁለት ጥቅሶች ብናስተያያቸው ሁሉምከአንድ ሰው አእምሮ የወጡ ከመሆናቸው ላይ እንደርሳለን፤

(ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤
ነሥአ፡ ኅብስተ፡ በእደዊሁ፡ ቅዱሳት፡ ወብፁዓት፡ ሕፄሃ፡ ለመርዓትከ፡ ወኅዳጋቲሃ፡ለእንተ፡ ኀደጋ፡ ምኵራብ።
(በቅዱሳትና ብፁዓት እጆቹ ኅብስት አነሣ። [ኅብስቱ] ለሙሽራህ [ለምእመናንህ/ለቤተ ክርስቲያንህ] ማጫ፥ ለፈታሃት ለምኵራብ መፋቻ ሆኗል።)

(ከውዳሴ መስቀል፤
መስቀል፡ ዘኮነ፡ ሕፄሃ፡ ለመርዓትከ፡ ወኅዳጋቲሃ፡ ለእንተ፡ ደኃርካ፡ በምኵራብ።
(መስቀል የሙሽራህ [የቤተ ክርስቲያንህ] ማጫ በምኵራብ ለፈታሃት [ለሕዝበ አይሁድ] መፍቻ ሆኗል።)

(ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ አብ፡ ቅዱስ።
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ ወልድ፡ ቅዱስ።
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ።

(ከመጽሐፈ ምስጢር፤
ኅሩም፡ አብ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በህላዌሁ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በራእየ፡ ትንቢት፡ለነቢያቲሁ።
ኅሩም፡ ወልድ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በመለኮቱ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በትስብእቱ።
ኅሩም፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በካልእ፡ ግርማሁ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በንጻሬ፡ዘይትፈቀድ፡ በዘይረድኦሙ፡ ለቅዱሳን።

እነዚህ  (እና  (የተጠቀሱ ኀይለ ቃሎች ከአንድ ሰው እንጂ ከተለያዩ ሰዎችአእምሮ የወጡ አይደሉም።

(3) ከአትናቴዎስ ቅዳሴ፤

ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ክቡር፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ንጉሥ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ንጉሥ ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ባዕል፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ሀብታም ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ልቡስ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ብርሃን የለበሰ ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ መላኪ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ገዢ ሆኖ ሳለ . . . )
ኦአዳም፡ ምንተኑ፡ ረሰይናክ፡ . . . (አዳም ሆይ ምን አደረግንህ . . .?)
ኦአዳም፡ ምንተኑ፡ ረሰይናክ፡ . . . (አዳም ሆይ ምን አደረግንህ . . .?)
ኦሔዋን፡ ምንተኑ፡ ረሰይናኪ፡. . . (ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ . . .?)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ እስመ፡ አኮ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ ልንነቅፋችሁ አይቻልም. . .)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ አንትሙሰ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ . . .)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ አንትሙሰ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ . . .)
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ቀዳማዊት፡ ይእቲ፡ ወአኮ፡ ደኃራዊት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ደኃራዊት፡ ይእቲ፡ እንተ፡ ትሰፍን፡ ለዓለም።. . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ለአብርሃም፡ ተከሥተት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ለሙሴ፡ በደብረ፡ ሲና፡ ተከሥተት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ በነቢያት፡ ተዐውቀት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ቅድስቱ፡ ለአብ፡ ቡርክቱ፡ ለወልድ፡ ልዕልቱ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ።
ኦ፡ ባዕዳት፡ ዕለታት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ተአመርክን፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ብሊት፡ ተፀርዐት፡ ወሐዳስ፡ ጸንዐት።
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ሙቁሓን፡ ተፈትሑ፡ ወአግብርት፡ ግዕዙ።
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ምዝቡር፡ ተሐንጸ፡ ወሰይጣን፡ ተኀጕለ።

(4) ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፤

አልቦ፡ ጥንት፡ ለህላዌሁ፤ (አነዋወሩ መጀመሪያ የለውም፤)
ወአልቦ፡ ማኅለቅት፡ ለክዋኔሁ፤ (አኳኋኑም መጨረሻ የለውም፤)
አልቦ፡ ኍልቍ፡ ለመዋዕሊሁ፤ (ዘመኑ ቍጥር የለውም፤)

ወአልቦ፡ ሐሳብ፡ ለዓመታቲሁ። (ዓመቶቹም ልክ ቍጥር የለውም፤)
ወአልቦ፡ ርስዓን፡ ለውርዛዌሁ፤ (ጕልምስናውም እርጅና የለውም፤)
ወአልቦ፡ ድካም፡ ለጽንዐ፡ ኃይሉ፤ (የኀይሉ ጥንካሬ ድካም የለውም፤)
ወአልቦ፡ ሙስና፡ ለመልክኡ፤ (መልኩም ብልሹነት የለውም፤)
ወአልቦ፡ ጽልመት፡ ለብርሃነ፡ ገጹ። (የፊቱም ብርሃን ጨለማ የለውም፤)
አልቦ፡ ድንጋግ፡ ለባሕረ፡ ጥበቡ፤ (የጥበብ ባሕሩ ዳርቻ የለውም፤)
ወአልቦ፡ መስፈርት፡ ለሣህለ፡ ትእዛዙ፤ (የትእዛዙም ምህረት ልክ የለውም፤)
አልቦ፡ ዐቅም፡ ለስፍሐ፡ መንግሥቱ፤ (የመንግሥቱ ስፋት መጠን የለውም፤)
ወአልቦ፡ ወሰን፡ ለራኅበ፡ ምኵናኑ። (የግዛቱም ስፋት ወሰን የለውም፤)

ከዚያ ይህ ይቀጥላል፤
ሥውር፡ ውእቱ፡ (ሥውር ነው)
ወምጡቅ፡ ውእቱ፡ (ምጡቅ ነው)
ነዋኅ፡ ውእቱ፡ (ረጂም ነው)
ቀላይ፡ ውእቱ፡ (ጥልቅ ባሕር ነው)
ልዑል፡ ውእቱ፡ (ልዑል ነው)
ወእሙቅ፡ ውእቱ፡ (ጥልቅ ነው)
ጽኑዕ፡ ውእቱ፡ (ጠንካራ ነው)
መዋዒ፡ ውእቱ፡ (አሸናፊ ነው)
ጠቢብ፡ ውእቱ፡ (ጥበበኛ ነው)
ማእምር፡ ውእቱ፡ (ዐዋቂ ነው)
ኃያል፡ ውእቱ፡ (ኀይለኛ ነው)
ተባዕ፡ ውእቱ፡ (ጀግና ነው)
ክቡር፡ ውእቱ፡ (ክቡር ነው)
ከሀሊ፡ ውእቱ፡ (ቻይ ነው)
ዋሕድ፡ ውእቱ፡ (አንድዬ ነው)
ወብሑት፡ ውእቱ፡ (ብቸኛ ነው)
መንክር፡ ውእቱ፡ (አስደናቂ ነው)
ከዚህ በታች ያለውን በማነጻጸ የእግዚአብሔርን አገላለጽ እንመልከት፤
ኄር፡ ዘእንበለ፡ እከይ፤ (ክፋት የለለበት ደግ፤) 11

ወየዋህ፡ ዘእንበለ፡ በቀል፤ (በቀል የሌለበት የዋህ፤)
ወዕጉሥ፡ ዘንበለ፡ መዓት፤ (ቁጣ የሌለበት ታጋሽ፤)
ጻድቅ፡ ዘእንበለ፡ ኃጢአት፤ (ኀጢአት የሌለበት ጻድቅ፤)
ወንጽሕ፡ ዘእንበለ፡ ርስሐት፤ (እድፍ የሌለበት ንጹሕ፤)
ወራትዕ፡ ዘእንበለ፡ ጥውየት፤ (ጠማማነት የሌለበት ቅን፤)
ወሃቢ፡ ዘእንበለ፡ ክልአት፤ (ንፍገት የሌለበት ሰጪ፤)
ወጸጋዊ፡ ዘእንበለ፡ ደንፅዎ፤ (ስስት የሌለበር ለጋሽ፤)
ሠራዬ፡ ኃጢአት፡ ዘእንበለ፡ በቀል፡ ወቂም፤ (በቀልና ቂም የሌለበት ኀጢአት ይቅር ባይ፤)
መጽያሕት፡ ዘእንበለ፡ ማዕቀፍ፤(እንቅፋት የሌለበት ጥርጊያ ጎዳና፤)
ወዐሠር፡ ንጹሕ፡ ዘእንበለ፡ አሥዋክ። (እሾኽ የሌለበት ንጹሕ ፈለግ፤)

ቅዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ለመሆናቸው ምንምጥርጥር የለውም። ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግና ቅዳሴ ቄርሎስም የሳቸው ሳይሆኑአይቀሩም።

ሌላው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሥራ መታወቂያ ካለው ግስ ላይ አዳዲስ ቃላትይፈጥራሉ። በቅዳሴ ማርያም ውስጥ የሚገኙ ቃላት “አማዕበለ” (ማዕበል አነቃነቀ)“መስግዲ” (አሰግድ) “መትሐቲ” (ዝቅ አርጌ) “መቅንዪ” (አስገዥየአባ ጊዮርጊስፍጥረቶች ናቸው።

ለኛ ባልታወቁ የውጪ ቃላት ይጠቀማሉ ብያለሁ። በሥነ ጽሑፍ ውስጥ ፒላስ”(ድንኳንየሚለው ቃል የተገኘው ሦስት ቦታ ብቻ ነው፤ 1. በመጽሐፈ ምስጢር፤ 2.በአርጋኖነ ውዳሴ፤ 3. በቅዳሴ ቄርሎስ፤

 
ሜሎስ (እሳታዊየሚለው ቃል የተገኘው ሦስት ቦታ ብቻ ነው፤ 1. በመጽሐፈምስጢር፤ 2. በቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ፤ (3) በቅዳሴ ቄርሎስ፤

እመቤታችን ታቦት ዘዶርታቦተ ዶር የተባለችው 1. ቅዳሴ ማርያም 2.በመጽሐፈ ምስጢር ውስጥ ብቻ ነው።

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ቅርሳችን ተዝረክርኳል። እስካሁን የደረሱለት ምዕራባውያን ብቻናቸው። የኛ ዝምታና ቍጭትአልባነት ባለማወቅና አስታዋሽ በማጣት ይመስለኛል።ቢያውቅና አስታዋሽ ቢያገኝ ቍጥሩ ከአምሳ ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ የማንነቱመታወቂያ ቅርሱ ሲወድም ዝም ብሎ አያይም። ሳንውል ሳናድር የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ቅርስ ድርጅት ማቋቋም አለብን። ድርጅቱ መጻሕፍቱ የሚጠበቁበትን ዘዴይፈልጋል፤ ለሚመረምሯቸው ተማሪዎች የገንዘብ እርዳታ ይሰጣል።

ስላዳመጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...