ማክሰኞ 5 ኖቬምበር 2013


ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በአሜሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደርጋሉ

His Holiness Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን)
  • ለ10 ዓመታት (ከ፲፱፻፸፬ – ፲፱፹፬ ዓ.ም.) በስደት፣ ለ15 ዓመታት (፲፱፹፬- ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.)  በሐዋርያዊ አገልግሎት ቆይተውበታል፡፡
  • በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ በኒውዮርክ ከተመሠረተውና የጃማይካ ተወላጆች ከሚገኙበት የኒውዮርክ ቅድስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቀጥሎ የመጀመሪያውን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በዋሽንግተን ዲሲ (መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም) አቋቁመዋል፡፡
  • ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን መዋቅርንና የሁለተኛ ሲኖዶስ  ምሥረታን በመቃወም የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቅሰቃሴመርተዋል፡፡
  • የትኛውም አካል ባላሰበበት ዘመን ስለ ዕርቀ ሰላም አሳስበዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና ሌሎች በስደት የሚገኙ አባቶችን በአትላንታ ጆርጅያ በአካል አግኝተው ከተወያዩ በኋላ ለኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ መልእክት በመላክ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር መሠረት ጥለዋል፡፡
  • ቃለ ዐዋዲው ለሰሜን አሜሪካ ሀ/ስብከት እንዲስማማ ኾኖ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በቅዱስነታቸው የሰሜን አሜሪካ ቆይታ ዘመን ነው፡፡
  • ‹‹ተዐቀቡኬ እምሐሳውያን ነብያት›› በሚል ርእስ በዋሽንግተን ዲሲ በተዘጋጀው ከፍተኛ ጉባኤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሤራ ቤተ ክርስቲያንን እያወካት መኾኑን በመግለጽ ካህናትና ምእመናን በብርቱ እንዲቋቋሙት አጠንክረው አስተምረዋል፤ በእመቤታችን ቅድስና ላይ የስሕተት ትምህርት ለማስተማር የሞከሩ ካህናትን በመምከር ከስሕተታቸው አልመለስ ያሉትን አውግዘው በመለየት ሃይማኖታዊ ቅንዐታቸውን በተግባር ገልጸዋል፡፡
  • ‹‹የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን መረከብ አንፈልግም፤ ታሪካዊ አንድነታችንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያናችን መጠበቅ አለበት›› በሚል የተነሣሣውን የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች እንቅሰቃሴ በማጠናከር የሰንበት ት/ቤቶች እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ በሀ/ስብከቱ ማኅበረ ቅዱሳን በእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር የሚያበረክተው አገልግሎት እንዲጠናከር የማይቋርጥ ምክርና አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
  • ቅዱስነታቸው በአሜሪካ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከሢመተ ፕትርክናቸው ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚያካሂዱት ነው፡፡
  • ‹‹የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና የሚያሳይ ለካህናትና ለምእመናን መንፈሳዊ ኩራት ስለኾነ በቂ የቅድሚያ ዝግጅት እየተደረገ በውጭ ሀገርም ሳይቀር ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡›› /ከመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ፴፪ው ዓመታዊ ስብሰባ የአቋም መግለጫ/
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከነገ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ ለዐሥር ቀናት የሚቆይ ሐዋርያዊ ጉብኝት በአሜሪካ ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን ይጓዛሉ፡፡
ቅዱስነታቸው ሢመተ ፕትርክናቸው ከተፈጸመበት የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያቸው በኾነው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የዋሽንግተን ዲሲ ሜሪላንድ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን የምረቃ ሥነ ሥርዐት እንደሚያከናውኑ ከልዩ ጽ/ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ የቋሚ ቅ/ሲኖዶስ አባላት የኾኑት÷ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አብረዋቸው እንደሚጓዙ ተገልጧል፡፡
በቅርቡ ፴፪ውን ዓመታዊ ስብሰባውን ያካሄደውና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት የተካተተውን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዘገባ ያዳመጠው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ በአቋም መግለጫው ተ.ቁ(3)÷ ቅዱስነታቸው በአገር ውስጥ ይኹን በውጭ የሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና የሚያሳዩ፣ ለካህናትና ለምእመናን መንፈሳዊ ኩራት›› ናቸው፡፡ በመኾኑም ‹‹የቅድሚያ ዝግጅት እየተደረገ በውጭ ሀገርም ሳይቀር ተጠናክሮ እንዲቀጥል›› አጠቃላይ ጉባኤው ድጋፉን ሰጥቷል፡፡
በሢመተ ፕትርክናቸው ወቅት የወጡ ኅትመቶች እንደሚያስረዱት፣ ቅዱስነታቸው በአሜሪካ በስደት በቆዩባቸው ዐሥር ዓመታትና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመኾን ባገለገሉባቸው ዐሥራ አምስት ዓመታት በኻያ ያህል ግዛቶች በአጠቃላይ ኻያ አምስት አብያተ ክርስቲያንን አቋቁመዋል፡፡ እኒህም ዛሬ በሦስት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ በሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ለሚመራው የአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ‹‹እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊ ፋና ወጊ ኾነውለታል፡፡›› – ‹‹ዛሬ በሦስት አህጉረ ስብከት ተከፋፍሎ የሚታየው የሰሜን አሜሪካ አገልግሎት ብቻቸውን በመኾን ምግብ አብስሎ የሚያቀርብላቸው በሌለበት ራሳቸው ቄስ፣ ራሳቸው ዲያቆን አንዳንዴም ሹፌር በመኾን ከዳር እስከ ዳር አገልግለውበታል፡፡››
በሰሜን አሜሪካ ጎልቶ የሚታየውን የገለልተኝነት መዋቅርና አስተዳደር የሚቃወሙትና በክፍለ አህጉሩ የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቀስቃሴ መሪ ናቸው የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመግለጫው ባስተላለፈው ይፋዊ ጥሪ መሠረት፣ በገለልተኛ አስተዳደራዊ መዋቅር ከሚመሩ አብያተ ክርስቲያን ወገኖች ጋራ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የሚመለሱበትንና የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚጠናከርበትን መልእክት በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እንዲያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡
ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና በስደት ከሚገኙ ሌሎች አባቶች ጋራ በፊታውራሪነት የጀመሩት የዕርቀ ሰላም ውይይት ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጠናከር በምልአተ ጉባኤው የሰፈረውን መግለጫ ተፈጻሚነት ለመርዳት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም የብዙዎች እምነትና ተስፋ ነው፡፡

ሐሙስ 31 ኦክቶበር 2013

                                                                          
Participants of the 32nd SGGA03
 

የምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት ይካሄዳል: የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ

  • ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ለሊቃውንት ጉባኤው ትእዛዝ ሰጠ
  • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
  • ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው [የአየር ሽፋኑ]ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
  • ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
Holy SynodTikmit Meeting
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ቆጠራ ለማካሄድ ከብር 29 ሚልዮን በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡን መዘገባችን የሚታወስ ሲኾን ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት የሚካሄደውን ቆጠራ ክንውን በቀጣይ የምንመለከተው ይኾናል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልኾነውን፣ በማስመሰል የሚነገረውንና የሚጻፈውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመኾኑም እውነተኛውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይኾን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሊቃውንት ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት በምልአተ ጉባኤው ላይ የተነበበውንና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጀውን የመነሻ ጽሑፍ አብራርቶ፣ አስፍቶና አምልቶ ለግንቦት፣ ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በቅርቡ በተካሄደው ፴፪ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፥ ኢትዮጵያ ከአይሁድ በፊት ጀምሮ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንታ መኖሯን፣ ክርስትናም ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስቶስ ባረገበት ዓመትና ቅዱሳን ሐዋርያት ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት በ፴፬ ዓ.ም. መኾኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት በማስረዳት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ጋራ መጠያየቃቸው ይታወሳል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት የጀመረውንና ለዐሥር ቀናት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው ባለ28 ነጥብ መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አካትቷል፡-
  • ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሞያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድ የታየው የሥራ መዋቅር ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም አይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲኾን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ ፳፻፭ ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኮሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊ እንደመኾኗ ኹሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ኾነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሞያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጎም በሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት የታደለ ሲኾን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ፳፻፮ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሄድበት ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
  • በውጭ አገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋራ ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
  • ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ኹኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመኾኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለኾነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋራ ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም. ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፡-
1.  ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ – የምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
2.  ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል – የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፣ የሕንፃዎችና ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይ ሓላፊ
3.  ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ – የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመምረጥ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
  • የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በተመለከተ ኮሌጁን ማጠናከር አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ለኮሌጁ ዋና ዲን እንዲሾም ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ለውጥ ጥናቶች የቅ/ሲኖዶሱን ሙሉ ድጋፍና ባለቤትነት አገኙ፤ በጥናቶቹ ቀጣይ አካሄድ ላይ ምልአተ ጉባኤው የአፈጻጸም አቅጣጫ ሰጥቷል፤ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ዛሬ ያበቃል፤ መግለጫም ይኖራል

Holy SynodTikmit Meeting
  • በአገልግሎት ጥራት /በሰው ተኮር ነፍስ የማዳን አገልግሎት/ ምእመናንን ማብዛትና ማጽናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከባይተዋርነትና ጠባቂነት ወደነበራት ሚና መመለስ፣ አስተምህሮዋን ከማይቃረኑ ጋራ ዓለም አቀፍ አጋርነትን በማጠናከር የሰላምና አንድነት ተምሳሌት ማድረግ፣ ለሙስና ችግሮች በንስሐ መንገድ መፍትሔ ማበጀት የቤተ ክርስቲያናችን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ማሕቀፍና ቊልፍ ጉዳዮች ኾነዋል፡፡
  • በቡድን እየተደራጁ የመንግሥትን ወቅታዊ አጀንዳዎች በአሉታዊ መንገድ የሚጠቀሙ አሉባልተኞችና ሙሰኞች እንዲሁም በቤተ ክህነቱ ቢሮክራሲ ውስጥ የተሰገሰጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ዋነኛ የለውጡ ተግዳሮቶች እንደኾኑና እንደሚኾኑ ተጠቁሟል፡፡
  • የለውጥ አመራር መዋቅሩ፣ አደረጃጀቱና ዝርዝር አሠራሩ ሕገ ወጥ ጥቅምን የሚያስቀር ተገቢ ጥቅምን የሚያጎለብት፣ ማንኛውንም ሠራተኛና አገልጋይ ለለውጡ የሚያበቃ እንጂ የማያፈናቅል መኾኑ በቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ታምኖበታል፡፡ ካህናት፣ ባለሞያ ሠራተኞች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን የለውጡ ግንባር ቀደም አራማጆች ይኾናሉ፡፡
  • ተቋማዊ ለውጡን ለመተግበር÷ ነባሩ የሰው ኃይል የሚበቃበት አዲስ የሰው ኃይል የሚወጣበት የሥራ አመራር ማሠልጠኛ አካዳሚ/የሥልጠና ማእከል/ለመገንባት ጥናቱ ተጠናቆ ዝግጅቱ ተጀምሯል፤ ማእከሉ የድኩማን/አረጋውያን መጦርያና የነዳያን መልሶ ማቋቋሚያም ያካተተ ነው፡፡
  • በአ/አበባ ሀ/ስብከት ለተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናቱ ምቹ ኹኔታ የፈጠሩትና ያስቻሉት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አለጊዜውና አላግባብ በተደረጉ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች ዝውውሮች ቢገመገሙም ከምደባቸው የመነሣታቸው ዜና ከእውነት የራቀ ነው፡፡
  • በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አዲስ የሙስና ኔትወርክ ዘርግተው ሕገ ወጥ ሲያጋብሱ በቆዩ ሦስት ሓላፊዎች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፤ ሓላፊነታቸው ለቀው ወደ አሜሪካ በሄዱት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ምትክ አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይሾማል፤ ገለልተኝነታቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸውና አገልግሎታቸው የሚጠቀስላቸው የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ቀጣዩ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚኾኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
  • የገዳማት አጠቃላይ ወቅታዊ ይዞታና ሥርዐተ ምንኵስናው የሚገኝበትን ኹኔታ ተከታትሎ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት የሚያቀርብ የሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤው ተደራጀ፤ የዴር ሡልጣን ገዳምን ውዝግብ ለመፍታት ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የሚደራደር በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሚመራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መተዳደርያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶሱ ጸድቋል፡፡ ደንቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትና ወጣቶች ጥራትና ወጥነት ባለው ሥርዐተ ትምህርት ተኮትኩተውና በሥነ ምግባር ታንጸው ተተኪዎች ለማድረግ የሚያስችል፣ ሁለገብ አገልግሎታቸውን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያንን በመከላከል ስብከተ ወንጌልን በተለያዩ መንገዶች ለማስፋፋት ሰንበት ት/ቤቶችን በይበልጥ የማደራጀት ሥራ ትኩረት ይሰጠዋል
  • ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከነበራቸው የበላይ ሓላፊነት ተነሥተው በበላይ ጠባቂነት ተወስነው ይሠራሉ፤ በኮሌጁ አስተዳደራዊና የፋይናንስ እንቅስቀሴ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን አይኖራቸውም፤ የኮሌጁ ዋና ዲን በግልጽ ማስታወቂያ በውድድር በሚካሄድ የቅጥር ሥርዐት ይመደባል፡፡
  • የካህናትና ምእመናን ምዝገባ/ቆጠራ/ ለማካሄድ የተያዘው ዕቅድ ተጨማሪ ዝርዝር ጥናት ያስፈልገዋል በሚል እንዲዘገይ ተደረገ፤ የመንግሥት ፈቃደኝነትና የበጀት አቅም እንደ ስጋት ቢጠቀስም የሊቃነ ጳጳሳት ደመወዝ በመቶ ፐርሰንት እንዲጨምር መወሰኑ አነጋጋሪ ኾኗል፡፡
About these ads

ረቡዕ 30 ኦክቶበር 2013


                                         

Ethiopian_Orhodox church bilden addis_Abeba_2

                                   የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቋመ፤ የዕጩዎችን ዝርዝር ለርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ያቀርባል

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው፣ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ዘጠነኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ የሚያስፈጽም አስመራጭ ኮሚቴ ሠየመ፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ሲኾን የትግራይ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋና ኦሮሚያ አህጉረ ስብከትን በመወከል የተመረጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት÷ ከትግራይ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ከወሎ የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ከጎንደር የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከጎጃም የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ከሸዋ የከምባታ ሐዲያ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና ከኦሮሚያ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ተሠይመዋል፡፡
ዕጩዎችን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በወጣው መስፈርት ብቻና ብቻ ለይቶ እንዲያቀርብ በምልአተ ጉባኤው ከባድ አደራ የተጣለበት አስመራጭ ኮሚቴው÷ ከመስፈርቱ ውጭ ጎጠኝነትን ጨምሮ በተለያዩ መደለያዎች ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነትን ለማግኘት ካሰፈሰፉ ቆሞሳት እንዲጠበቅ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው በመምረጫ መስፈርቱ መሠረት የዕጩዎችን ማንነት ከመለየት ባሻገር ከበጀት፣ ከመንበረ ጵጵስና እና ከጽ/ቤቶች መሟላት አኳያ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሊመደቡባቸው የሚገቡ አህጉረ ስብከትን በቅደም ተከተል በመለየት ብዛታቸውን የመወሰን ሥራም እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡
በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ በሚሰጠው ቢሮ ሥራውን የሚያከናውነው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በሥራው ወራት የፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ እንደሚያዝዘውና በተሻሻለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሕግ እንደተመለከተው ተቀባይነት ያለው የግልጽነት መርሕ በመከተልና የልዩ ልዩ ውጫዊ አካላት ጣልቃ ገብነቶችንና ተጽዕኖዎችን በመከላከል አደራውን መወጣት ይኖርበታል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጨርሶ ሪፖርቱን የሚያቀርበው ለመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሲኾን ሥርዐተ ሢመቱም የምልአተ ጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ እንደሚፈጸም ተመልክቷል፡፡
የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሌሎች መረጃዎችን ወደፊት እንደምናቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

ሰኞ 28 ኦክቶበር 2013

መጽሐፈ ቅዳሴ” ወደ ኦሮምኛ ተተረጎመ

www.youtube.com/watch?v=UYHqDqUEqoE   Cached
Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Kidase 1 of 9. Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Kidase 1 of 9. Sign in . Upload . Search . Guide Loading...

በመልካሙ ተክሌ
(አዲስ አድማስ ጥቅምት 16 2006 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን “መጽሐፈ ቅዳሴ” ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተተረጎመ፡፡ ለብዙ ዘመናት “መጽሐፈ ቅዳሴ”ን በግእዝ እና በአማርኛ ስትጠቀምበት የቆየችው ቤተክርስትያኗ፤መፅሃፉን በኦሮምኛ ማስተርጎም የጀመረችው በ1999 ዓ.ም እንደሆነ ታውቋል፡፡ የመጽሐፉ መተርጎም በኦሮሚያ ክልል ላሉ አብያተ ክርስትያናት በኦሮምኛ ለመቀደስ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ የቤተክርስትያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እያካሄደ ባለው የጥቅምት ምልዐተ ጉባዔው ትኩረት ከሰጣቸው ዋና አጀንዳዎቹ አንዱ ስብከተ ወንጌልን ማዳረስ እንደሆነ የገለፁት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የመጽሐፉ  ሕትመት እንዲቀላጠፍ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉም  ለማወቅ ተችሏል፡፡ “መጫፈ ቂዳሴ” በሚል ርዕስ የተተረጎመው የኦሮምኛ መጽሐፉ፤በቅርቡ ዝግጅቱን የተቀላቀሉትን ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ጨምሮ፣ በርካታ ጳጳሳት ተሳትፈውበታል፡፡ መጽሐፉ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተመ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከተጠናቀቀ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሊመረቅ እንደሚችል ታውቋል፡፡

ረቡዕ 23 ኦክቶበር 2013

የሃይማኖት እንከን የሌለባትና ተቆርቋሪ ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያናችን በአመራርና በአያያዝ ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ ሊገታ ይገባል – ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ

His Holiness meglecha 11
ፎቶ- ማኅበረ ቅዱሳን
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመጀመሪያው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባው ስለሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ዛሬ፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጥዋት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በቅዱስነታቸው መግለጫ መሠረት ምልአተ ጉባኤው÷ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ምእመናንን ስለ መጠበቅና ማብዛት፣ የቤተ ክርስቲያንን የትምህርት ተቋሞች በጥራትና አደረጃጀት በመለወጥ ከመማርና መሠልጠን አልፎ መከራን ለመቀበል የተዘጋጁ ላእካነ ወንጌልን አብቅቶ ስለማውጣት፣ ፍጹም የዕድገት ለውጥ ለማምጣት ስለሚያስችለው የፋይናንስና የመልካም አስተዳደር ጅምር ጥናት ሂደት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የውሳኔ አሰጣጥ የቤተ ክህነት ልዩ ልዩ ክፍሎች ሓላፊዎች፣ ካህናት፣ ሊቃውንት፣ ወጣቶችና ምእመናን ውክልናና ተሳትፎ ስለሚረጋገጥበትና የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ሰፊ ድጋፍና ተቀባይነት ስለሚያገኝበት አሠራር ይመክራል፤ ውሳኔም ያሳልፋል፡፡
‹‹የአክራሪነት፣ አሸባሪነትና ጽንፈኝነት›› ተግባራትን በማውገዝ የክርስቶስ መልእክት የኾነውን ሰላምና እኩልነት፣ መከባበርና መቻቻል፣ አብሮ መልማትና ማደግ ለሕዝቡ በየቀኑ ማስተማርና መስበክ እንደሚገባ የገለጹት ፓትርያርኩ፣ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል መደገፍና ማጎልበት አለብን፤›› ሲሉም መክረዋል፡፡
አጀንዳዎቹ÷ በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የተሰበሰበው ምልአተ ጉባኤው መንፈስ ቅዱስ በሚገልጽለት መንፈሳዊ ጥበብ እየተመራ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ፣ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የሓላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ በመወያየት ሊወስንባቸውና ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው እንደሚገባ ምልአተ ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ፓትርያርኩ፣ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ዐቢይ ጉባኤው በስብሰባው መጨረሻ የሚደርስበት ውሳኔና የሚያወጣው መመሪያ በውጤቱ÷ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፋፋ፣ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናኑን የሚያስደስት፣ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀውን የለውጥና የዕድገት ጎዳና የሚከፍት እንዲኾን በመግለጽ መግለጫቸውን ደምድመዋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባመክፈቻጋዜጣዊ መግለጫ ዐበይት የትኩረት ነጥቦች
በድንበር የለሽ ስብከተ ወንጌል በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ
  • ከትንሹ የሥልጣነ ክህነት ሹም ጀምሮ እስከ ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ድረስ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ተልእኮ በንቃት፣ በሙሉ ዕውቀት፣ በተነሣሽነት፣ በፍጹም ፈቃደኛነት እንዲነሣሣና እንዲሰለፍ የሚጠበቀውን ያህል አልተሠራም፡፡
  • ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ወልዳ፣ በሥጋ ወደሙ አሳድጋ፣ ወልደ ማርያም፣ ገብረ ሚካኤል ብላ የሠየመቻቸው ልጆቿ ከጉያዋ እየተነጠቁ ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ እርስዋ የወላድ መሐን የኾነችበት፣ ያልወለዱና ያላሳደጉ ባለብዙ ቤተሰብ የኾኑበት ክሥተት እያጋጠመ ነው፡፡
  • የቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣን ወራሾች እንደመኾናችን ቁጥር አንድ ሥራችን በድንበር ሳይገደቡ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሥሩ ያሉትን በጎች መጠበቅ ብቻ ሳይኾን ድንበር የለሽ ትምህርትና ስብከት በማካሄድ ከዛሬ ጀምሮ በየዓመቱ በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ ሊያሠራው የሚችል አሠራር መቀየስ አለበት፡፡

የትምህርት ተቋሞቻችንን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም በመለወጥ ትንሣኤዎቻቸውን ማብሠር፤
  • የምንሾማቸው ዲያቆናት፣ ቀሳውስትም ኾኑ ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይኾኑ ጌታችን እንዳደረገው የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራውን ለመቀበል የተዘጋጁ ሊኾኑ ይገባል፡፡
  • የአብነት ት/ቤቶቻችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም ተማሪውን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር ማስተካከልና ማብቃት አለብን፡፡
  • ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት እንከን ሳይኖራት፣ ሞያ ሳያንሳት፣ ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት በአያያዝና በአመራር ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት አለበት፡፡ ይህን በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል የትምህርት ቤቶቻችንን ትንሣኤ የሚያበሥር፣ ዕድገታቸውንና ጥራታቸውን የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት ዛሬ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

ስለ ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራርና መልካም አስተዳደር የተጀመረው ጥናት ሂደት
  • ምእመናን የሚፈለገውን ዐሥራት፣ በኵራትና ቀዳምያት በሕጉ መሠረት እየሰጡ አይደለም፤ የሚሰጡትም ስጦታ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛዋል፡፡ የሚፈለገውን ያህል ተደራጅተን፣ መስለን ሳይኾን ኾነን፣ በሁሉም ነገር ተዘጋጅተን ማስተማር፣ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ ቁጥጥርና አያያዝ መጠቀም አለብን፡፡
  • ከወገንተኝነትና አድሏዊነት በአግባቡ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችንን ተሰሚነት ክፉኛ እየጎዳው ነው፡፡ በመልካ አስተዳደር ዙሪያ ጉባኤው የማፍረስ ሳይኾን የመገንባት ግብ ያለው ራእይ አንግቦ ሥር ነቀል የኾነ ፍጹም የዕድገት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለውን አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አሰጣጥ የካህናትና ምእመናን ተሳትፎ ስለማረጋገጥ
  • ቅ/ሲኖዶስ በጉዳዮች ካህናትንና ምእመናንን እያሳተፈና በሐዋርያዊ ሥልጣኑ እያጸደቀ የውሳኔውን ተቀባይነትና ድጋፍ የሚያሰፋበትንና የሚያረጋግጥበትን አሠራር ይተክላል፡፡
  • የቅ/ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል ለማጎልበት መሥራት አለባቸው

ሐሙስ 17 ኦክቶበር 2013

መንበረ ፓትርያርክ

የመንበረ ፓትርያርክ 32ኛው ጉባኤ የረቡዕ ዕለት ከሰዓት ውሎ ካለፉት የተለየ ነበር፡፡ ዋና አጀንዳው ‹መቻቻልን› የተመለከተ ሲሆን አቅራቢዎቹም ከፌዴራል ጉዳዮች የተወከሉ አካላት መሆናቸውን በዕለቱ የመርሐ ግብር ዝርዝር ላይ ተገልጧል፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ይቀርብ በነበረው የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ የመብት ጥሰትና ሥልጣንን ለግል ሃይማኖት ማስፋፊያ የመጠቀም አዝማሚያዎች መኖራቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው እምነትን የመያዝ፣ የማስፋፋትና የአምልኮ ቦታ የማግኘት መብት እየተጣሰ መሆኑን የሚገልጡ ዘገባዎች ይሰሙ ነበር፡፡

በትናንትናው የከሰዓት ውሎ ስለ መቻቻል ገለጣ ከተሰጠ በኋላ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳትና የጉባኤው ተሰብሳቢዎች የየአካባቢያቸውን ችግሮች በዝርዝር ነበር ያነሷቸው፡፡ ‹‹መቻቻል እስከ ምን ድረስ ነው›› ብለው ነበር ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ የጠየቁት፡፡ ‹‹አሁን በምዕራብ ወለጋ ያለው ሁኔታ መንግሥት በአገሩ ያለ ይመስላል ወይ? ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል እንዴእንድንቻቻል አድርጉን፣ እንችላለን›› ነበር ያሉት፡፡
የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄኖክ ‹በነጆ ወረዳ በሕጋዊ መንገድ ተሠርቶ የነበረው ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ባለ ሥልጣናት ተጽዕኖ እንዲፈርስ መደረጉን፣ ለምን ታፈርሳላችሁ ብለው ድርጊቱን የተቃወሙ ስድሳ ምእመናን መታሠራቸውን›› በኀዘን ነበር የገለጡት፡፡ አያይዘውም ‹‹በባኮ ወረዳ የተመደቡ አንድ ካህን እያረሱ እያሉ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት መጡ፤ ካህኑን በሰደፍ እየደበደቡ ‹ከዚህ ሀገር ልቀቁ፣ ይህ የነፍጠኛ መኖሪያ አይደለም› እያሉ አሰቃዩዋቸው፡፡ ካህኑን ሲደበድቧቸው አንበርክከው፣ ለ15 ደቂቃ አተኩረው ፀሐይዋን እንዲያዩ እያስገደዱ ነበር፡፡ ድብደባውን ሰምተው የወጡት ባለቤታቸው በድንጋጤ ታመው ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አለፈ››
‹‹በሰንበትና በቅዱስ ሚካኤል ቀን ምእመናን ሊያስቀድሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ‹ለቅዳሴ ካህናቱ ይበቃሉ፤ እናንተ ውጡ›› እየተባሉ እንዳያስቀድሱ ይደረጋሉ፡፡ ከእኛ ቤተ ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ ሆን ተብሎ እርስ በርስ ለማጋጨት ለፕሮቴስታንቶች የጸሎት ቦታ ተሰጠ፡፡ ለምን ታጨቃጭቁናላችሁ፤ ይህ ቦታ ለእነርሱ አይሆንም ብሎ በመከራከሩ አንድ ዲያቆን ተደብድቦ ሞተ፡፡ የሕክምና ውጤቱም ሆን ተብሎ በወባ በሽታ ሞተ ተብሎ ተሠራ፡፡ ለሁለት ዓመት ያህል ተከራክረን አሁን ቦታው ለእኛ ተወሰነ፡፡
ጊምቢና መንዲ ላይ የምእመናን ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ በፖሊስ ማተባችሁን በጥሱ እየተባሉ ነው፡፡ ለምን ስንላቸው ከላይ የወረደ መመሪያ አለ ይሉናል፡፡››
ቀጥለው የሀገረ ስብከታቸውን ችግር ያቀረቡት የጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ነበሩ፡፡ ‹‹በጋሞ ጎፋ መቱ ወረዳ፣ ዋጁ ኡቆ ላይ የመስቀል ማክበሪያ ቦታችን ለሱቅ መሥሪያ ቦታ ተሰጠ፡፡ አቤት ብንል የሚሰማን በማጣታችን ዘንድሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መስቀል ሳናከብር ዋልን፡፡ ሀገሪቱ በችግር ላይ በነበረች ጊዜ እንኳን መስቀል ሳይከበር ቀርቶ አያውቅም ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ቦታ ለመንግሥት እየተሰጠ ነው፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን በቅዱስነታቸው በኩል ለክልሉ ደብዳቤ ጻፍን፡፡ ክልሉ ወሰነልን፡፡ ነገር ግን እስካሁን አልተረከብንም፡፡››
ቀጥለው ሃሳባቸውን የሰጡት የባሰ ካልመጣ በቀር ድምጻቸው ማይሰማው ብጹዕ አቡነ ያሬድ የሶማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ‹‹በሶማሌ ክልል አምስት አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ናቸው ያሉን፡፡ ምእመናኑ ብዙ ናቸው፡፡ ሲወልዱ የሚያስጠምቁበት፣ ሲያርፉ የሚቀበሩበት ቤተ ክርስቲያን እንትከል ብንል የሚሰማን አጥተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚረዱ ምእመናን በግላቸው ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ለዚህ መልሳችሁ ምንድን ነው›› ብለዋል፡፡
በገለጻው ላይ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በ4ኛው መክዘ ነው የሚለውን የተቃወሙት ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ‹‹ታሪክ ክፉም ሆነ በጎ እንደ ታሪክነቱ መተረክ አለበት፤ አቅራቢው ወንድማችን በ4ኛው መክዘ ክርስትና ገባ ያልከው ተሳስተሃል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ለማለት ‹ላይሰንስ አለህ?› አባቱን የሚኮንን ልጅ ምን ያደርጋል? ነገሥታቱን ወቀሳችሁ፣ ቤተ ክርስቲያንን ነቀፋችሁ፤ ለመሆኑ ከማን ነው ይህቺን ሀገር የተረከባችሁት? ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ጌታ ባረገ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ አለ፡፡ ይህንን ዛሬ ‹ግራጁዌት አድርገው›፤ ልዑካኑ ስትመጡ ስለምትናገሩት ነገር ዕወቁ፤››
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንድርያስም ‹‹በቤተ መንግሥት የወርቅ ዕቃ ብቻ አይኖርም፣ የእንጨትም፣ የድንጋይም ዕቃ አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሁሉም ጥሩ አይሆንም፣ መጥፎም ይኖራል፡፡ ነገር ግን እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል ብሏል፡፡ በእኔ ሀገረ ስብከት ስድስት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ ሦስቱ በአንድ አካባቢ፣ ሦስቱ በሌላ ቦታ፡፡ ይህንን ለክልሉ መንግሥት ብናሳውቅ አልረዱንም፡፡ የተበደለ ሰው ይጮኻል፤ ሲጮህ ደግሞ ፖለቲካ ነው ይባላል፡፡ ድሮ ያስቸገረን የንዋያተ ቅድሳት ዘረፋ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ወደ ማቃጠል ተዛውሯል፡፡ አንዱ ባለ ሥልጣን እንዲያውም ችግሩን ሳቀርብለት ተቆጣኝ፤ ብዙ ብናገር ነፋስ ስለሚወስደው እዚህ ላይ ይብቃ››
ከብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት ቀጥሎ የተናገሩት የወላይታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ‹‹በበዴሳ ወረዳ ያለ አንድ የሌላ እመነት ተከታይ የሆነ ዳኛ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ቄራ አንካፈልም፤ በመኪና አብረን አንሄድም› ብሎ ዐወጀ፡፡ በጋራ በመቻቻል የኖርንበትን ዕድር ሁሉ ለዩ ብሏል፡፡ ታድያ እንዴት መቻቻል ሊመጣ ይችላል፡፡››
ከጉባኤው የቀረበውን ቅሬታና ሃሳብ ያዳመጡት የፌዴራል ጉዳዮች የሥራ ኃላፊዎች የቀረቡት ቅሬታዎች በሰነድ ተደግፈው ቢደርሷቸው እነርሱም በመፍትሔው ላይ መሥራት እንደሚችሉ፤ ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤም ጉዳዩ በየደረጃው ቢቀርብለት መፍታት እንደሚችል፡፡ ቅሬታዎችን እንደዚህ ባለ መድረክ ከሚሆን በየጊዜው እየተገናኙ መፍታት ቢቻል›. የሚሉ ሃሳቦችን ሠንዝረዋል፡፡
የዘንድሮው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በአደረጃጀቱ ውበት፣ በተሳታፊዎቹ ብዛት፣ በአህጉረ ስብከቶች ቁጥር(50 ደርሰዋል)፣ በስብሰባው ቁም ነገረኛነት ካለፉት የተለየ ነበር፡፡ እነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በብርቱ እንደ ደከሙበት ያሳያል፡፡ በየዘገባዎቹ የተሰሙትን የመብት ጥሰቶች፣ ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ጫናዎች፣ የአምልኮ ቦታ እጥረቶች፣ በካህናቱ ላይ የሚፈጸሙትን ግፎችና፣ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ የመንጠቅ ርምጃዎች ግን ሊገቱ ይገባቸዋል፡፡ ከአንዳንድ ክልሎች በቀር በብዙዎቹ የዞንና የክልል ባለ ሥልጣናት ችግሩን ተረድተው ለመፍታት እንደሚጥሩ ተገልጧል፡፡ በወረዳ ደረጃ የሚገኙት ግን ሥልጣንን ተገን በማድረግ የግል እምነታቸውን እያስፋፉ መሆኑን ያሳያል፡፡ በደቡብ ጎንደርና በምሥራቅ ጎጃም የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል ርምጃዎች በጊዜው ተጣርተው መፍትሔ ካልተሰጣቸው ፍጻሜያቸው አያምርም፡፡
በየአካባቢው በሚገኙ ባለ ሥልጣናት የሚፈጸሙ ትንኮሳዎችም መቆም አለባቸው፡፡ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹አታስቆጡን› እያሉ ደጋግመው የተናገሩት ነገር የዋዛ አይደለም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት የሚፈጽሙት ገደብ አልባ ትንኮሳና ጫና ወዴት እያመራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱም አደረጃጀቷንና አሠራርዋን ይበልጥ የምትፈትሽበት፣ አሁን ለገጠማት ተግዳሮት ብቁ የሚሆን አሠራና አወቃቀር የምትይዝበት፣ ችግሮችን በስብሰባ ብቻ ሳይሆን በአካባቢያዊ ውይይት፣ በሕግ መሥመርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የምትፈታበት መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡  
ያለበለዚያ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል የተረተው ተረት መድረሱ የማይቀር ነው፡፡
በጣልያን ጊዜ ነው አሉ፡፡ ጎንደር ላይ ጣልያን በድማሚት አንዱን ተራራ ያናውጠዋል፡፡ ተራራው ‹እድም› እያለ ይፈርሳል፡፡ አንዲት የከብት እረኛ ልጅ ፈርታ ወደ እናቷ ሄደችና ‹እማዬ ኧረ ጣልያን ተራራውን እያፈረሰው ነው›› አለቻት፡፡ እናቷም ‹‹እነ ደጃዝማች እገሌ፣ እነ ፊታውራሪ እገሌ፣ እነ ራስ እገሌ እጅ አንሰጥም ብለው እየተጋደሉ ዐለፉ፡፡ ተራራውንስ ተይው ያፍርሰው፤ እርሱም መቀመጡን አብዝቶት ነበረ፡፡›› አለቻት አሉ፡፡ 

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...