በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ 34ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 8-10
ቀን 2008 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ ባለ 23 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ በረከት ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም የተጀመረው ጉባኤ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ሪፖርት እና የየአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች በቅደም ተከተል ቀርበዋል፡፡ በቀረቡት ሪፖርቶች መሠረትም ቃለ ጉባኤ ተነቦ በማጽደቅ ባለ 23 ነጥቦች የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአቋም መግለጫውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
1.ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ34ኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ያስተላለፉትን ቃለ ቡራኬና አባታዊ የሥራ መመሪያ ሙሉ ለሙሉ ተቀብለን ተግባራዊ ለማድረግና የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡
2.በቅዱስነታቸው ቃለ ቡራኬ ከተላለፉት መሠረታዊ መልእክቶች ውስጥ ቅዱስነታቸው ዐቢይ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይባቸው ያሳሰቧቸው፡-
አንደኛ፡-ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶ እጃችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ስብከተ ወንጌል ብንነሣ፡፡
ሁለተኛ፡-የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ሕሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርህ አስጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፤ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኩራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን በማለት የሰጡትን መመሪያ በተግባር ለመለወጥ ቃል እንገባለን፡፡
3. የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚጋፉ፣ ለቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አመራር አንታዘዝም የሚሉ፣ ቤተ ክህነት ምን አገባው፣ ሀገረ ስብከት ምን አገባው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ምን አገባው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ መዋቅራዊ ምን አድርጎልናል በሚል የማደናገሪያ ስልት መዋቅርን የሚንዱ ችግሮች በከፍተኛ ፍጥነትና ብዛት በተደራጀና በተጠና ስልት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲወያበትና መፍትሔ እንዲሰጠው ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር እንዲያስጠብቅ በከፍተኛ ስሜት እንጠይቃለን፡፡
4. በሁሉም አህጉረ ስብከት የታየው የብፁዓን አባቶች ሐዋርያዊ ጉዞ እጅግ ውጤታማ፣ ለምእመናን ጥንካሬ፣ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ እድገት አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፣ በእኛም በኩል የሚገባንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
5. በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በማደራጃ መምሪያው የተገለጹት የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ /Double Entry/ ሥርዓት የፋይናንስ ማእከላዊነትን በማረጋገጥ፣ የአገልጋዮችን የሥራ አቅም ብልጽግና በማሳደግ ብክነትነትን በማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ከብዙ ጊዜ ማሳሰቢያ በኋላ ተግባራዊ መሆኑ ጉባኤውን አስደስቷል፡፡ ይህ አሠራር በቀጣይነት በየደረጃው እስከ ታች የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ድረስ ተግባራዊ እንዲሆን ይልቁንም አሠራሩ ዘመኑ አሁን የደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ መሠረት በማድረግ በኔትዎርክ ተሳስሮ፣ በሥልጠና ተደግፎ፣ ግልጽና ተጠያቂ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ወጥና ቀጥ ያለ አመራር እንዲሰጥ እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
6. ተቋርጦ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስምሪት መጀመሩ ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ስምሪቱ በተጠናከረ መንገድ አስተማማኝ የሆነ የራሱ በጀት ተመድቦለት በሥልጠናና በተደራጀ ውጤት ተኮር በሆነ መንገድ እንዲቀጥል የበኩላችንን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
7. የታየው የገቢ እድገት ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ከበጀት እድገቱ ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ንብረት ለማፍራት የቀደሙት አባቶች ሠርተው እንዳወረሱን ሁሉ ቋሚና ዘላቂ ንብረት ለቤተ ክርስቲያን ለማፍራት በልማት ለመትጋት ቃል እንገባለን፡፡
8. ብፁዓን አባቶች ባደረጉት ጥረት ምእመናንና ካህናትን በማስተባበር የሚካሔደው የልማትና ለቤተ ክርስቲያን ንብረት የማፍራት ዘላቂ ገቢ የማስገኘት ሥራ ለሚመራው አህጉረ ስብከትም ሆነ ተቋማት ሕልውና ዋስትና ለብፁዓን አባቶች አብረዋቸው ለደከሙት የሥራ ሓላፊዎች የድካማቸው መዘክሮች ስለሆኑ ንብረቶቹ በየአህጉረ ስብከቱና በዋናው መሥሪያ ቤት ባሕር መዝገብ በአግባቡ ተቆጥረውና ተመዝግበው እንዲያዙ እንጠይቃለን ለአፈጻጸሙም የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
9. ስብከት ወንጌልን ለማስፋፋት፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በተፈለገው መጠን ለማዳረስ ብቃትና ታዛዥነት ያላቸው አገልጋዮች እጥረት ትልቅ እንቅፋት ስለሆነ የአገልጋዮችን እጥረት በተለይም በልዩ ልዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራነ ወንጌል በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
10. ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በማረሚያ ቤቶች፣ በጤና ማእከላትና በመሳሰሉት ለማዳረስ በተለይም ዘመኑ በሚፈቅደው በብዙኀን መገናኛ ወይም ሚዲያ በመታገዝ በመላው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ድምጿን በራሷ በኩል ማእከላዊነቷን ጠብቆ ለማሰማት የሚደረገውን ጥረት ከልብ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
11. ለስበከተ ወንጌል እንቅፋት የሆኑ ሕገወጥ ሰባኪያን፣ ሕገወጥ አጥማቂዎች ነን ባዮችና መዋቅር ያልጠበቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስነቅፉ እንቅስቃሴዎች ለመግታት እስካሁን ከተሠራው በይበልጥ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
12. በየጊዜውና በየዘመኑ ወቅቱ በሚፈቅደው መጠን መስመሩን ሳይለቅ ሲሻሻልና ሲዳብር የኖረው ቃለ ዓዋዲ አሁንም በይበልጥና በጥራት የሕግ ጸባይ በመያዝ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገረ መንግሥታት ተቀባነት በሚያገኝ መልኩ መሻሻሉ ሁሉም የሚጠብቀው ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለይ እስካሁን ያልተደረገው በውጭ አህጉረ ስብከት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ማእከል ባደረገ መልኩ ጊዜ ሳይሰጠው ተዘጋጅቶ እንዲሻሻል በአጽንኦት እየጠየቅን ለሚደረገው ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
13. ለማሰልጠኛዎችና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከምን ጊዜውም የተሻለ ቢሆንም በተቀናጀና ማእከላዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲደራጅ፣ በጀት ያልተመደበላቸው በጀት እንዲያገኙ፣ በበጎ አድራጊ ምእመናን የተሠሩ ሁሉ በማእከል እውቅና እየተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እንዲያገኙ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ቀመዛሙርቶቻቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
14. ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት የተሰጠው ትኩረት ልዩ ልዩ ሥልጠናና የሥርዓተ ትምህርት ከመዝሙር መጽሐፍ ጋር ተዘጋጅቶ መሰራጨቱ ወጣቶችን በወጥነት ለማስተማር በሃይማኖትና ሥነ ምግባር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጉባኤው ያመነበት ሲሆን ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመምሪያው በኩል የቀረቡ ችግሮች በተለይም ከልዩ ልዩ የወጣቶችና የጎልማሶች ማኅበራት ያለው ተጽእኖ እንዲቆም፤ የወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቆይታ የእድሜ ገደብ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡
15. በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በተመለከተ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የታየው ከመንግሥት ጋር የተቀናጀ የቅርሶች ምዝገባ፣ የቅርሶች ማስመለስ፣ የሙዚየሞች ማደራጀት፣ለቅርሶች ዋስትና ቢሆንም ሁሉንም ጥረቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርሶቿና የታሪክ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸሙ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይና ወቅታዊ መመሪያ እንዲሰጥ በታላቅ አጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
16. ወደ መናፍቃንና ወደ ኢአማኒነት ከሚፈልሰው ምእመን ቁጥር ባልተናነሰ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ለአገልጋዮች ዋስትናና ከለላ ማጣት ለቤተ ክርስቲያን የወደፊት ሕልውና ከፍተኛ ስጋት የሆነው የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና ለመቅረፍ በሥልጠና የታገዘ ሥራ፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት ላይ ያተኮረ አስተዳደርን፣ ችግሮችን በመፍታት ብቁ አገልጋዮችን ለማፍራት ያለመ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
17.በተፈጠረው የአየር ለውጥ ምክንያት በወቅቱ ለተከሰተው ድርቅ በተጎዱ አህጉረ ስብከት ለሚገኙ አድባራት፣ ገዳማትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በርካታ በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
18. በልማት፣ በአረጋውያን እንክብካቤ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን በማሳደግ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበራዊ አገልግሎትና ለወገን ደራሽነት አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ ቋሚና ዘላቂ ልማት በማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቃል እንገባለን፡፡
19. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሲኖዶሳዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት ከሲኖዶሳዊ መዋቅር የወጣ ቀኖናዊ ትውፊትን ያልጠበቀና ኢክርስቲያናዊ ኢኦርቶዶክሰዊ የሆነ ገለልተኛ ቅንጅት በመፍጠር ምእመናንን በሚያደናግሩ አካለት ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያስቀምጥለት ለተግባራዊነቱም የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
20. የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ በውጭ ያሉትን አህጉረ ስብከት የሚያጠናክር በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እየጠየቅን በዚህ ረገድ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት በሚገባ እንዲተኮርበት በታለቅ አጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
21. በአሁኑ ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም እየሰፋችና ከራሷ ምእመናን አልፎ የውጭ ሀገር ተወላጅ የሆኑ ምእመናንን ያፈራች በመሆኑ የውጭ ግንኙነት ሥራዋ ዓለማቀፋዊ ይዘቱን እንደጠበቀ እንዲስፋፋ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
22. በሊቢያ በረሃ ስለ ክርስትና ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወጣቶችን አስመልክቶ የተደረገው ሲኖዶሳዊና ቀኖናዊ ውሳኔ የተቀበልን ሲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ ሰማዕታትን የሚያስቡ፣ ከሰማዕታት ዋጋ ያገኛሉ የሚለውን በመከተል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
23. የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ የተፈጥሮ ሕግን ወሰን በማለፍ በታላላቅ ሀገሮች ተጽእኖና ድጋፍ እየተስፋፋ ያለውን የግብረ ሰዶምን እንቅስቃሴ በመቃወም ቤተ ክርስቲያን ድምጿን ለዓለም ማሰማት እንዳለባት እየጠየቅን ጥያቄውን ከዚህ በፊት ላስተጋቡ ብፁዓን አባቶች ላደረጉት ጥረት ልባዊ ድጋፋችንና አጋርነታችን በመስጠት ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ግዴታችን ስለሆነ ምእመናንን በትምህርት ወንጌል ለማነጽ ቃል እንገባለን፡፡