በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የሚቀርቡ መንፈሳዊ ትምህርቶች ፤መረጃዎች እና የመሳሰሉት የሚስተናገዱበት ገጽ ነው
ሐሙስ 5 ኖቬምበር 2015
ሰኞ 2 ኖቬምበር 2015
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ: በአ/አበባ ሀ/ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ የተመደበቡትን ሓላፊነት እንዳይወጡ መደረጋቸውን ተናገሩ፤“ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ዐቢይ የሕግ ግድፈት ተፈጽሟል
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡-
- ከቅዱስ ፓትርያርኩም ኾነ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋር በመልካም የሥራ ግንኙነት ላይ ነበርኩ
- የአ/አበባ ሀ/ስብከትን ኹለት ሥራ አስኪያጆች የመለመለውና ያቀረበው አካል አይታወቅም
- ሒሳቡን እንዲያንቀሳቅሱ ሌላ ፈራሚ ሊቀ ጳጳስ የተመደቡበት ኹኔታ አሳዛኝ ክሥተት ነው
- በረዳት ሊቀ ጳጳስነት የመደበኝ ምልዓተ ጉባኤው፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ መፍትሔ ይስጠኝ
- ልዩ ደንብና መመሪያ ባልወጣበት የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት መኾኑ ክፍተት ፈጥሯል
- የፓትርያርኩ፣ የረዳት ሊቀ ጳጳሱና የሥራ አስኪያጁ ተግባርና ሓላፊነት መታወቅ አለበት
- በሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲ የሦስቱ ሓላፊዎች ሥልጣንና ተግባር ተካቶ እንዲቀርብ ተወስኗል
- ፓትርያርኩ ያለረዳት ሊቀ ጳጳሱ ምርጫ ሥራ አስኪያጆችን በመሾም የሕግ ግድፈትና ጣልቃ ገብነት የፈጸሙበትን አካሔድ በመደገፍ “ሕመም ቢኖርብኝም የሥራ ፍላጎት አለኝ” በሚል በአዲስ አበባ ለመመደብ የጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ክፉኛ ትዝብት ላይ ወድቀዋል
* * *
ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ
አዲስ አበባ፤
ጉዳዩ፡- በቅዱስ
ሲኖዶስ በተሰጠኝ የሥራ ሓላፊነት ላይ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑና ከቃለ ዐዋዲው ውጭ በደል በመፈጸሙ፤ የተፈጸመውን
የሥራና የሕግ ግድፈት በቅዱስ ሲኖዶሱ ለማሳረምና ትክክለኛ ፍትሕ እንዲሰጠኝ የቀረበ አቤቱታ ነው፤
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቼ፤
እንደሚታወቀው ኹሉ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና የበላይነት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ
ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያኗ ሕግ መሠረት የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመኾን መመደቤ
ይታወቃል፡፡እኔም በዚህ በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ታላቅ ጉባኤ እና በአባቶቼ የተሰጠኝን ሓላፊነትና አደራ ከተመደብኩበት ጊዜ አንሥቶ አቅሜ በፈቀደ መልኩ ያለውን ነባራዊ ኹኔታ በማገናዘብ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመመካከር የጠቅላይ ቤተ ክህነቱንም የሥራና የደረጃ መዋቅርን በመጠበቅ እያገለገልኩ እገኝ ነበር፤ ለዚህም እንደ ማሳያ፡-
ሀ/በሀገረ ስብከቱ የባለጉዳዮች መስተንግዶ ሥርዐት ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሁም ተጠያቂነት ያለው እንዲኾን በማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ሊጠቅም በሚችል መልኩ በማውጣት፤
ለ/የንብረትና የገንዘብ አጠባበቅ ኹኔታ በመረጃ የተደራጀ እና ዘመናዊ አሠራር እንዲኖረው በማድረግ፤
ሐ/በመንግሥት በኩል ቤተ ክርስቲያኗ ያላትን መብትና ጥቅም በመገንዘብ ከቀረጥ ነጻ በኾነ መንገድ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለሀገረ ስብከቱ የትራንስፖርት መገልገያ የሚውሉ መኪናዎች እንዲገቡ ጥረት በማድረግ፤
መ/ሀገረ
ስብከቱ የሚያከናውናቸው ሥራዎች በአጠቃላይ በተጠና ዕቅድ እንዲሠራ፤ የየክፍሎቹ ሓላፊዎች በሚለካና ሊደረስበት
በሚችል መልኩ ዕቅድ እንዲዘጋጅና የቀረበው ዕቅድም በአስተዳደር ጉባኤው ተገምግሞ ሥራ ላይ እንዲውል መመሪያ
በመስጠት ስንሠራ ቆይተናል፡፡
ከላይ ለማሳያነት የጠቀስኋቸው ተግባራት ብዙ ጠለቅ ያለ የአፈጻጸም ሒደቶች ቢኖሯቸውም አቅም በፈቀደ መልኩ ስንቀሳቀስ ቆይቼ ነበር፡፡
ኾኖም ከቅዱስ ፓትርያርኩም ኾነ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጋር በመልካም የሥራ ግንኙነት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግና መመሪያ መሠረት አባቶቼ የሰጣችኹኝን የሥራ ሓላፊነት በመወጣት ላይ ነበርኩ፡፡
ይኹንና ዐቢይ የሕግ ግድፈት በመፈጸሙ ምክንያትና ሥልጣንን አለአግባብ በመጠቀም ጣልቃ ገብነት ሥራዬን በሓላፊነት እንዳላከናውን ተደርጌአለኹ፡፡ ከዕንቅፋቶቹና ከተፈጸሙት የሕግ ስሕተቶችም መካከል፤ከላይ ለማሳያነት የጠቀስኋቸው ተግባራት ብዙ ጠለቅ ያለ የአፈጻጸም ሒደቶች ቢኖሯቸውም አቅም በፈቀደ መልኩ ስንቀሳቀስ ቆይቼ ነበር፡፡
ኾኖም ከቅዱስ ፓትርያርኩም ኾነ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጋር በመልካም የሥራ ግንኙነት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግና መመሪያ መሠረት አባቶቼ የሰጣችኹኝን የሥራ ሓላፊነት በመወጣት ላይ ነበርኩ፡፡
1/
በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50፣ የአዲስ አበባ
ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው፤ ካለ በኋላ በንኡስ ቁጥር ሦስት፣ ሀገረ ስብከቱ
የሚገኘው የሀገሪቱ ርእሰ ከተማ ላይ እንደ መኾኑ መጠን ከሌሎች አህጉረ ስብከት የሚለይባቸው ልዩ ኹኔታዎች ስላሉ
እኒኽን ኹኔታዎች ከግምት ያስገባ ለየት ያለ አደረጃጀት በቃለ ዐዋዲው እንዲኖረው እንደሚደረግ ይገልጻል፡፡
በዚህ መሠረት ልዩ መመሪያ ባልወጣበት ኹኔታ አንቀጹን በሌላ መንገድ በመተርጎምና ምክንያቱን በግልጽ ባላወቅሁት መንገድ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 53 ንኡስ ቁጥር 8ን በመተላለፍ፤
1.1) ሊቀ ጳጳሱ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልምለው ለቅዱስ ፓትርያርኩ ሳያቀርቡና በሕጉም መሠረት የጋራ ስምምነት ሳይኖረን፤
1.2) በመቀጠልም በሕጉ መሠረት የረዳት ሊቀ ጳጳሱንና የቅዱስ ፓትርያርኩን ይኹንታ መሠረት አድርጎ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማጽደቅ ሲገባው ይህ መሠረታዊ ሒደት ባልተፈጸመበት ኹኔታ፤
1.2) በመቀጠልም በሕጉ መሠረት የረዳት ሊቀ ጳጳሱንና የቅዱስ ፓትርያርኩን ይኹንታ መሠረት አድርጎ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማጽደቅ ሲገባው ይህ መሠረታዊ ሒደት ባልተፈጸመበት ኹኔታ፤
1.3)
መልማዩና አቅራቢው በውል ማን እንደኾነ ባልታወቀበትና ሕግ በማይፈቅደው መልኩ በፓትርያርኩ ቀጥተኛ የሹመት ደብዳቤ
ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ለሀገረ ስብከቱ በመመደቡ ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ
ገባ፡፡
2.
እኒህን ዋነኛ የሕግ ግድፈቶች በመዘርዘር ጉዳዩ በቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲታረም በመጀመሪያ በ11/07/2007 ዓ/ም
በመቀጠልም በ16/07/2007 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቄ ነበር፤ ነገር ግን ምላሽ አልተሰጠኝም፡፡ በተጨማሪም
ጉዳዩ በቋሚ ሲኖዶስ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲታረም በ17/7/2007 ዓ/ም አቅርቤ ነበር፡፡
3.
ያለሊቀ ጳጳሱ አቅራቢነትና መልማይነት፣ ያለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ዕውቅናና አጽዳቂነት ከሕግ ውጭ በቀጥታ
በቅዱስ ፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ የተሾሙት ሥራ አስኪያጅ፣ የቃለ ዐዋዲውን አንቀጽ 45 ንኡስ ቁጥር 7ን
በመተላለፍ፣ አሳማኝ እና ምክንያታዊ ባልኾነ መንገድ በሀገረ ስብከቱ በክፍል ዋና ሓላፊነት ተመድበው የሚሠሩትን
ሠራተኞች በ30/08/2007 ዓ/ም ያለሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ዕውቅናና ፈቃድ የተወሰኑትን ከደረጃ ዝቅ
በማድረግ፣ የቀሩትንም እዚያው ባለው የሥራ ክፍል አዘዋወሩ፡፡
ከዋና ክፍል ሓላፊዎቹ
በቀረበልኝ አቤቱታ፤ ሕጉን የጣሰና ምክንያቱ በትክክል ያልታወቀ ዝውውርና ከደረጃም ዝቅ ማድረግ በመኾኑ በተጨማሪም
ሠራተኞች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ላይ ተረጋግቶ የመሥራት መብትን የሚያሳጣ በመኾኑ ባለኝ ሥልጣንና ሓላፊነት
መሠረት በ30/08/2007 ዓ/ም ዝውውሩንና ከደረጃ ዝቅ ማድረጉን አገድኩ፡፡ ይህም በሕጉ መሠረት ተጢኖ መታየትና
መገምገም ሲኖርበት የቃለ ዐዋዲውን አንቀጽ 60 ቁጥር 2 ፊደል (ሰ)እና(ሸ) ያለአግባብ በመጥቀስና በመጠቀም
በ4/9/2007 ዓ/ም በቅዱስ ፓትርያርኩ በተፈረመ ደብዳቤ እኔ ያስተላለፍኩት ሕጋዊ እግድ ያለአግባብ ተሻረ፡፡
4.
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ24/09/2007 ዓ/ም ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተጻፈ ደብዳቤ በሥራ ገበታዬ ተገኝቼ ሥራዬን
እንድቀጥል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ እኔም በ25/09/2007 ዓ/ም ለደብዳቤው፣ በቅን ልቡና ሥራዬን እየሠራሁ መኾኑን፤
የሠራተኞችን ደመወዝ፣ የሚታወቁና አይቀሬ የኾኑትን የሀገረ ስብከቱን ዕለታዊ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችንም እየፈረምኩ
ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ በመግለጽ ሥራዬን እንደምሠራ አሳወቅሁ፤ ነገር ግን ባልተለመደ አኳኋን ገንዘብን
በሚመለከት ሌላ ሊቀ ጳጰስ እንደተመደበ ሰማኹ፤ ይህ አሳዛኝ ክሥተት ነው፡፡
ስለዚህም በረዳት ሊቀ ጳጳስነት መመደቤን በመወሰን ሥልጣኑንና ሓላፊነቱን የሰጠኝ ይህ ምልዓተ ጉባኤ እንደ መኾኑ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን በሚበጅ አካሔድ መፍትሔ ይስጠኝ ዘንድ እጠይቃለኹ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሐሙስ 29 ኦክቶበር 2015
ሰበር ዜና – አጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ ወንድሙ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ
የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ አጥማቂ ነኝ ባዩን ግርማ ወንድሙን በቁጥጥር ሥር አዋለ።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምንጮች፣ አጥማቂ ነኝ ባዩን ግርማ ዛሬ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መኾኑን ተናግረዋል።
አጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ፣ በማጥመቅ እፈውሳለኹ በሚል በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሕገ ወጥ ሀብት ሲያካብት እና በርካታ ምእመናንን ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርግ ቆይቷል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነገጋረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ አጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ ዕውቅና እና ፈቃድ በይፋ የተነፈገው ሕገ ወጥ እንደኾነ አረጋግጧል።
የፋና ምንጮች፣ አጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ በፈውስ አገልግሎት ስም የማጭበርበር ወንጀል ሳይጠረጠር እንዳልቀረ ነው የተናገሩት።
ረቡዕ 28 ኦክቶበር 2015
ሰበር ዜና – ፈቃድ የሌላቸው የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀሙ ተወሰነ፤ የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ይጀመራል
- የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈቃድ እና ዕውቅና የሌላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ በስም ተለይተው ተጠቅሰዋል
- በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የብዙኃን መገናኛ ቦርድ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው
- በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች የበለጠ ተጠናክረው አጀንዳው በልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ተወስኗል
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከማእከል የተሰጠ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ(EBS) የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ “ሃይማኖታዊ ትምህርት” የሚያስተላልፉ ፕሮግራሞች፣ የቤተ ክርስቲያንን ስም እንዳይጠቀሙ ወሰነ፡፡
ምልአተ ጉባኤው በዛሬ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ስድስተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው ያሳለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲኾን፤ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን በደብዳቤ እንዲያውቁት ይደረግ ዘንድ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
በውሳኔው÷ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞቹ፣ “ታዖሎጎስ” እና “ቃለ ዐዋዲ” በስም የተጠቀሱ ሲኾን በፕሮግራሞቹ አዘጋጅነት የሚታወቁት በተለይ የ“ታዖሎጎስ” ግንባር ቀደም ምንደኞች፣ ፕሮግራማቸው “ራሱን የቻለ የሚዲያ ተቋም” እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር ተቋማዊ ግንኙነት እንደሌላቸው በይፋ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ከዚሁ ጋር በማያያዝ፤ በሊቃውንት ጉባኤ ሳይመረመሩ እና በማእከል ሳይፈቀዱ በግለሰቦች እየተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያንን ስም ይዘው ስለሚወጡ የስብከት፣ የመዝሙር እና የመጻሕፍት ኅትመቶች እንዲኹም የአዳራሽ ጉባኤያት እና ስብሰባዎች ከተወያየ በኋላ ቀደም ሲል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማጽናት ተመሳሳይ ትእዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ “ስብከተ ወንጌል እና ሚዲያን በተመለከተ” በተራ ቁጥር ሦስት በያዘው አጀንዳ፤ ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊነቱን ጠብቆ የራስዋን ድምፅ ለዓለም የምታሰማበት እና ስብከተ ወንጌልን የምታስፋፋበት የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት እንዲጀመርም ወስኗል፡፡
ለቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ ስርጭት የሚያስፈልገውና በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አስተባባሪነት ተጠንቶ የቀረበው በጀት ባለፈው ዓመት ግንቦት በምልአተ ጉባኤው የጸደቀ ሲኾን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር እንደተመለከተው፤ በዚኽ ዓመት በጀቱ በአፋጣኝ ሥራ ላይ እንዲውል የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የፋይናንስ ምንጮቹን ወስኖ ለነገ የሚያቀርብ ሦስት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት(ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ) ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤ ተሠይሟል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ባለፈው ዓመት ግንቦት ባጸደቀው የሚዲያዎች (የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን አገልግሎት) ሥርጭት ደንብ መሠረት፤ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሚመራ የብዙኃን መገናኛ የሥራ አመራር ቦርድ የተቋቋመ ሲኾን ተግባሩን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ለ34ኛው የመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስብከተ ወንጌልን ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በአጽናፈ ዓለም ለማስፋፋት እና ለማጠናከር ስለሚያስፈልጓት ሚዲያዎች፣ በመምሪያው አስተባባሪነት በብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች የተካሔደውን ጥናት መሠረት አድርጎ መተዳደርያ ደንብ፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና የቴሌቪዥን ሥርጭት መመሪያ/ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ “የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ኹኔታ በጥልቀት ማየት” በሚል ዐቢይ አጀንዳ ሥር በፊደል ተራ ቁጥር 4/መ፣ “የተሐድሶ እንቅስቃሴን በተመለከተ”፤ የተዘጋጀው ሰነድ በተጨማሪ ማስረጃዎች ተስፋፍቶ እና ተጠናክሮ ራሱን በቻለ ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፤ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ግንባር ቀደም መሪዎች በሚሰጣቸው ተልእኮ እና ድጋፍ በቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር እና የአገልግሎት መዋቅር ውስጥ በመስረግ የኑፋቄውን አስተሳሰብ እና ድርጊት የሚያራምዱ የ66 አካላት እና ግለሰቦች የሰነድ፣ የምስል እና የድምፅ ማስረጃዎች ከኃምሳ ገጾች ማብራሪያ ጋር ተደግፎ ተዘጋጅቷል፡፡
ከቤተ ክርስቲያናችን ዐውደ ምሕረት እና የአስተዳደር መዋቅር ባሻገር፣ የኑፋቄው ግንባር ቀደም መሪዎች እና ምንደኞቻቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን(መንፈሳዊ ኮሌጆች እና የካህናት ማሠልጠኛዎች) ውስጥ በተለያየ ሽፋን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትኩረት እንዲደረግበት ምልአተ ጉባኤው ኮሚቴውን አሳስቧል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ አህጉረ ስብከት፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ሳያውቁት ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በተቋቋመው የኑፋቄው መናኸርያ “ዱባይ ሚካኤል” እና “ቤርያ ቲኦሎጂካል ኢንስቲትዩት” በሚል መሪዎቹ የመሠረቱት ሕገ ወጥ ተቋም በከፍተኛ ደረጃ ያነጋገረ ሲኾን በምልአተ ጉባኤው ጥናት ተካቶ እንዲቀርብ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ኹኔታ ጉባኤውን ያነጋገረው፣ በመንበረ ፓትርያርኩ የውጭ ጉዳይ መምሪያ በሓላፊነት የተቀመጡት መልአከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ የተባሉ ግለሰብ፣ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቁ አንጻር ያላቸው ሃይማኖታዊ አቋም እና ሥነ ምግባራዊ ኹኔታ ነበር፡፡ የግለሰቡ አመጣጥ እና አመዳደብም ከፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት እንደኾነ መጠቆሙ ደግሞ ችግሩ ከግለሰቡም በላይ ልዩ ጽ/ቤቱ እንደ መዋቅር ያለበትን አስከፊ ደረጃና አሳሳቢነቱን ለምልአተ ጉባኤው አለብቧል፡፡
ከዚኽ ውስብስብነቱና ከሚያስፈልገው ጠንካራ ቅንጅት አኳያ፤ አጀንዳው ራሱን በቻለ አስቸኳይ እና ልዩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሲወስን ጊዜው በመጪው ወርኃ ጥር ላይ ሊኾን እንደሚችል ከወዲኹ የተጠቆመ ቢኾንም በኮሚቴው ውጤታማ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚመሠረት ነው፣ በብዙኃን የምልአተ ጉባኤው ዘንድ መግባባት የተደረሰበት፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት መሠረት፤ አስቸኳይ እና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ቅዱስ ፓትርያርኩ ወይም ቋሚ ሲኖዶሱ ወይም የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በሚያደርጉት ጥሪ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሊካሔድ ይችላል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በማናቸውም ስብሰባ ላይ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ፤ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ከኾነ በሙሉ ድምፅ ያልፋል፤ በሃይማኖት እና በቀኖና ጉዳይም ድምፀ ተዓቅቦ ማድረግም አይቻልም፡፡
by ሐራ ዘተዋሕዶ
ሐሙስ 22 ኦክቶበር 2015
የ34ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአቋም መግለጫ
በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ 34ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 8-10
ቀን 2008 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ ባለ 23 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ በረከት ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም የተጀመረው ጉባኤ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ሪፖርት እና የየአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች በቅደም ተከተል ቀርበዋል፡፡ በቀረቡት ሪፖርቶች መሠረትም ቃለ ጉባኤ ተነቦ በማጽደቅ ባለ 23 ነጥቦች የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአቋም መግለጫውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
1.ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ34ኛው አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ያስተላለፉትን ቃለ ቡራኬና አባታዊ የሥራ መመሪያ ሙሉ ለሙሉ ተቀብለን ተግባራዊ ለማድረግና የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡
2.በቅዱስነታቸው ቃለ ቡራኬ ከተላለፉት መሠረታዊ መልእክቶች ውስጥ ቅዱስነታቸው ዐቢይ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይባቸው ያሳሰቧቸው፡-
አንደኛ፡-ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶ እጃችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ስብከተ ወንጌል ብንነሣ፡፡
ሁለተኛ፡-የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ሕሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርህ አስጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፤ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኩራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን በማለት የሰጡትን መመሪያ በተግባር ለመለወጥ ቃል እንገባለን፡፡
3. የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የሚጋፉ፣ ለቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አመራር አንታዘዝም የሚሉ፣ ቤተ ክህነት ምን አገባው፣ ሀገረ ስብከት ምን አገባው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ምን አገባው፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ መዋቅራዊ ምን አድርጎልናል በሚል የማደናገሪያ ስልት መዋቅርን የሚንዱ ችግሮች በከፍተኛ ፍጥነትና ብዛት በተደራጀና በተጠና ስልት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲወያበትና መፍትሔ እንዲሰጠው ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር እንዲያስጠብቅ በከፍተኛ ስሜት እንጠይቃለን፡፡
4. በሁሉም አህጉረ ስብከት የታየው የብፁዓን አባቶች ሐዋርያዊ ጉዞ እጅግ ውጤታማ፣ ለምእመናን ጥንካሬ፣ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ እድገት አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፣ በእኛም በኩል የሚገባንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
5. በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በማደራጃ መምሪያው የተገለጹት የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ /Double Entry/ ሥርዓት የፋይናንስ ማእከላዊነትን በማረጋገጥ፣ የአገልጋዮችን የሥራ አቅም ብልጽግና በማሳደግ ብክነትነትን በማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ስለሆነ ከብዙ ጊዜ ማሳሰቢያ በኋላ ተግባራዊ መሆኑ ጉባኤውን አስደስቷል፡፡ ይህ አሠራር በቀጣይነት በየደረጃው እስከ ታች የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ድረስ ተግባራዊ እንዲሆን ይልቁንም አሠራሩ ዘመኑ አሁን የደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ መሠረት በማድረግ በኔትዎርክ ተሳስሮ፣ በሥልጠና ተደግፎ፣ ግልጽና ተጠያቂ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ወጥና ቀጥ ያለ አመራር እንዲሰጥ እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
6. ተቋርጦ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስምሪት መጀመሩ ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ስምሪቱ በተጠናከረ መንገድ አስተማማኝ የሆነ የራሱ በጀት ተመድቦለት በሥልጠናና በተደራጀ ውጤት ተኮር በሆነ መንገድ እንዲቀጥል የበኩላችንን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
7. የታየው የገቢ እድገት ጉባኤውን እጅግ ያስደሰተ ሲሆን ከበጀት እድገቱ ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ንብረት ለማፍራት የቀደሙት አባቶች ሠርተው እንዳወረሱን ሁሉ ቋሚና ዘላቂ ንብረት ለቤተ ክርስቲያን ለማፍራት በልማት ለመትጋት ቃል እንገባለን፡፡
8. ብፁዓን አባቶች ባደረጉት ጥረት ምእመናንና ካህናትን በማስተባበር የሚካሔደው የልማትና ለቤተ ክርስቲያን ንብረት የማፍራት ዘላቂ ገቢ የማስገኘት ሥራ ለሚመራው አህጉረ ስብከትም ሆነ ተቋማት ሕልውና ዋስትና ለብፁዓን አባቶች አብረዋቸው ለደከሙት የሥራ ሓላፊዎች የድካማቸው መዘክሮች ስለሆኑ ንብረቶቹ በየአህጉረ ስብከቱና በዋናው መሥሪያ ቤት ባሕር መዝገብ በአግባቡ ተቆጥረውና ተመዝግበው እንዲያዙ እንጠይቃለን ለአፈጻጸሙም የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
9. ስብከት ወንጌልን ለማስፋፋት፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በተፈለገው መጠን ለማዳረስ ብቃትና ታዛዥነት ያላቸው አገልጋዮች እጥረት ትልቅ እንቅፋት ስለሆነ የአገልጋዮችን እጥረት በተለይም በልዩ ልዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራነ ወንጌል በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
10. ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከዐውደ ምሕረት ባሻገር በማረሚያ ቤቶች፣ በጤና ማእከላትና በመሳሰሉት ለማዳረስ በተለይም ዘመኑ በሚፈቅደው በብዙኀን መገናኛ ወይም ሚዲያ በመታገዝ በመላው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ድምጿን በራሷ በኩል ማእከላዊነቷን ጠብቆ ለማሰማት የሚደረገውን ጥረት ከልብ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
11. ለስበከተ ወንጌል እንቅፋት የሆኑ ሕገወጥ ሰባኪያን፣ ሕገወጥ አጥማቂዎች ነን ባዮችና መዋቅር ያልጠበቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያስነቅፉ እንቅስቃሴዎች ለመግታት እስካሁን ከተሠራው በይበልጥ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
12. በየጊዜውና በየዘመኑ ወቅቱ በሚፈቅደው መጠን መስመሩን ሳይለቅ ሲሻሻልና ሲዳብር የኖረው ቃለ ዓዋዲ አሁንም በይበልጥና በጥራት የሕግ ጸባይ በመያዝ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገረ መንግሥታት ተቀባነት በሚያገኝ መልኩ መሻሻሉ ሁሉም የሚጠብቀው ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለይ እስካሁን ያልተደረገው በውጭ አህጉረ ስብከት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ማእከል ባደረገ መልኩ ጊዜ ሳይሰጠው ተዘጋጅቶ እንዲሻሻል በአጽንኦት እየጠየቅን ለሚደረገው ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
13. ለማሰልጠኛዎችና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከምን ጊዜውም የተሻለ ቢሆንም በተቀናጀና ማእከላዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲደራጅ፣ በጀት ያልተመደበላቸው በጀት እንዲያገኙ፣ በበጎ አድራጊ ምእመናን የተሠሩ ሁሉ በማእከል እውቅና እየተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እንዲያገኙ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ቀመዛሙርቶቻቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
14. ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት የተሰጠው ትኩረት ልዩ ልዩ ሥልጠናና የሥርዓተ ትምህርት ከመዝሙር መጽሐፍ ጋር ተዘጋጅቶ መሰራጨቱ ወጣቶችን በወጥነት ለማስተማር በሃይማኖትና ሥነ ምግባር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጉባኤው ያመነበት ሲሆን ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመምሪያው በኩል የቀረቡ ችግሮች በተለይም ከልዩ ልዩ የወጣቶችና የጎልማሶች ማኅበራት ያለው ተጽእኖ እንዲቆም፤ የወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቆይታ የእድሜ ገደብ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡
15. በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በተመለከተ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የታየው ከመንግሥት ጋር የተቀናጀ የቅርሶች ምዝገባ፣ የቅርሶች ማስመለስ፣ የሙዚየሞች ማደራጀት፣ለቅርሶች ዋስትና ቢሆንም ሁሉንም ጥረቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርሶቿና የታሪክ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸሙ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይና ወቅታዊ መመሪያ እንዲሰጥ በታላቅ አጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
16. ወደ መናፍቃንና ወደ ኢአማኒነት ከሚፈልሰው ምእመን ቁጥር ባልተናነሰ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ለአገልጋዮች ዋስትናና ከለላ ማጣት ለቤተ ክርስቲያን የወደፊት ሕልውና ከፍተኛ ስጋት የሆነው የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና ለመቅረፍ በሥልጠና የታገዘ ሥራ፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት ላይ ያተኮረ አስተዳደርን፣ ችግሮችን በመፍታት ብቁ አገልጋዮችን ለማፍራት ያለመ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቅን እኛም ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
17.በተፈጠረው የአየር ለውጥ ምክንያት በወቅቱ ለተከሰተው ድርቅ በተጎዱ አህጉረ ስብከት ለሚገኙ አድባራት፣ ገዳማትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በርካታ በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
18. በልማት፣ በአረጋውያን እንክብካቤ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን በማሳደግ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበራዊ አገልግሎትና ለወገን ደራሽነት አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ ቋሚና ዘላቂ ልማት በማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቃል እንገባለን፡፡
19. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሲኖዶሳዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት ከሲኖዶሳዊ መዋቅር የወጣ ቀኖናዊ ትውፊትን ያልጠበቀና ኢክርስቲያናዊ ኢኦርቶዶክሰዊ የሆነ ገለልተኛ ቅንጅት በመፍጠር ምእመናንን በሚያደናግሩ አካለት ዙሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያስቀምጥለት ለተግባራዊነቱም የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
20. የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ በውጭ ያሉትን አህጉረ ስብከት የሚያጠናክር በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እየጠየቅን በዚህ ረገድ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት በሚገባ እንዲተኮርበት በታለቅ አጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
21. በአሁኑ ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም እየሰፋችና ከራሷ ምእመናን አልፎ የውጭ ሀገር ተወላጅ የሆኑ ምእመናንን ያፈራች በመሆኑ የውጭ ግንኙነት ሥራዋ ዓለማቀፋዊ ይዘቱን እንደጠበቀ እንዲስፋፋ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
22. በሊቢያ በረሃ ስለ ክርስትና ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወጣቶችን አስመልክቶ የተደረገው ሲኖዶሳዊና ቀኖናዊ ውሳኔ የተቀበልን ሲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ ሰማዕታትን የሚያስቡ፣ ከሰማዕታት ዋጋ ያገኛሉ የሚለውን በመከተል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
23. የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ የተፈጥሮ ሕግን ወሰን በማለፍ በታላላቅ ሀገሮች ተጽእኖና ድጋፍ እየተስፋፋ ያለውን የግብረ ሰዶምን እንቅስቃሴ በመቃወም ቤተ ክርስቲያን ድምጿን ለዓለም ማሰማት እንዳለባት እየጠየቅን ጥያቄውን ከዚህ በፊት ላስተጋቡ ብፁዓን አባቶች ላደረጉት ጥረት ልባዊ ድጋፋችንና አጋርነታችን በመስጠት ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ግዴታችን ስለሆነ ምእመናንን በትምህርት ወንጌል ለማነጽ ቃል እንገባለን፡፡
ሰኞ 19 ኦክቶበር 2015
34ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ተጀመረ
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 34ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 8 ቀን 2008
ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየአህጉረ
ስብከቱ ሓላፊዎችና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመክፈቻ ቃለ በረከት በማስተላለፍ ቀጥሏል፡፡
ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ቃለ በረከት ትናንት ቤተ ክርስቲያን
ሀብተ ወልድ እና ስመ ክርስትና ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆቿ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲናቸውን እየካዱ ወደሌላ
ጎራ የመቀላቀሉ ጉዳይ እጅግ እየናረና የምእመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ መሔዱ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የምእመናን ፍልሰት በተመለከትም መንስኤው ምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምፕ ለመግባት ለምን መረጡ? የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው ነው? የቤተ ክርስቲያንናችን ትምህርት ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት ነው? የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነው? የካህን እጥረት ስላለ ነው? ወይስ ሌሎች ከእኛ ተሽለው ስለተገኙ ነው? አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ ሊነጋገርበት ይገባል ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ወደፊት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው ያሏቸውንም እንደመፍትሔ ጠቁመዋል፡፡ ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ሕሊና እንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርህ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነት ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ፣ የምእመናን ልብ የሚያረካ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክትም በዚህ ባለንበት ዘመን ሰበካ ጉባኤን የማጠናከር እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ተልእኮ በመወጣት እድገቷንና ልማቷን በማፋጠን ተገቢ ሥራ በተገቢው ሥፍራ ሠርተን የጥንታዊትና የታሪካዊቷን ቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና በመጠበቅ ዛሬም ለሀገርና ለወገን የምትሰጠውን አገልግሎት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትንም በተመለከተ አባ ኃ/ማርያም መለሰ /ዶ/ር/ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ሪፖርትም በ2007 በጀት ዓመት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሊቃውንት ጉባኤን፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን፣ የበጀትና ሒሳብ መምሪያን፣ የገዳማት መምሪያን፤ የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን፣ የሰብከተ ወንጌልና የሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና የልማት ድርጅትን፣ የማኅበረ ቅዱሳንን፣ . . . ወዘተ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ ጠቅላላ የሰበካ ጉባኤው ከየአህጉረ ስብከት የቀረቡ ሪፖርቶችን በማድመጥ ላይ ይገኛል፡፡
የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም ይቀጥላል፡፡
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
ልጥፎች (Atom)
በአውሮጳ የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ የተውጣጡ ካህናት፡” የ...
-
June 1, 2015 ከሐራ ዘተዋሕዶ በሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ዕድገት ፊት ከተጋረጡትና አፋጣኝ እልባት ከ...
-
‹‹…ወንድማችንን እናውቃቸዋለን፤ በእውነቱ ለፌ ወለፌ የማይሉ ደረቅ ሊቅ ናቸው፤ በሃይማኖቱ ዘርፍ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንዲቱም ነጥብ እንዳትዛባ...