2014 ጁላይ 24, ሐሙስ

ሐምሌ 17 ነቢዩ ቅዱስ ዮናስ

በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ 
(ናታኒም ጡመራዊ መጽሔት ሐምሌ 17)"+እን  ለነቢዩ ቅዱስ ዮናስ እና ለእናታችን ቅድስት አፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+" ቅዱስ ዮናስ ነቢይ "+

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ ቅዱስ ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) አብድዩና ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል:: ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ በሐዲስ ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+" ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት "+

=>እናታችን ቅድስት አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ: ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው:: "አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው ጌታ ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

2014 ጁላይ 22, ማክሰኞ

ሐምሌ 15 ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ


በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ 
(ናታኒም ጡመራዊ መጽሔት ሐምሌ 15)"+ እንን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "+

=>እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

+ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ዽዽስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

2014 ጁላይ 16, ረቡዕ

ዐይናማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ

እምየዋ! እምየ አድማሱ ጀምበሬ። ምነው በዕድሜ ደርሰን ዐይንዎን አይተን ድምፅዎን ሰምተን በነበር። ዛሬማ ቸልታችንን ዕድሜ ይንሳው እና ኹሉን ነገር ችላ ብለን ለነአባ እንቶኔ ስለተውነው፤ እንደናንተ ያሉቱን ሊቃውንት አሟጥጠን ጨርሰን፤ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኝ እና ግራቸውን በማይለዩ ገላግልት እየተወከለች የነውር ማዕድ ትፈተፍት ይዛለች።

ለመልአከ ብረሃን አድማሱ ጀምበሬ መወድስ
እንትኰ በለሰ እመ-በላዕክሙ ወተጋባእክሙ ደርገ ኀበ-ሀለወ ገደላ
አንስርተ-ዲዮስቆሮስ ሊቅ ሊቃውንተ-ጎንደር ገሊላ
እሞትክሙ ሞተ ዘኢዩኤል ወእምየብሰት እስከ-ፍጻሜነ ዜናክሙ ሰግላ
በሊዐ-እክለ-ባዕድ እስመ ውእቱ
ዘበርእሰ-ነቢይ አብቈለ አፈ-አንበሳ-ሐቅል አሜከላ
ማዕዳኒ እንዘ-ነውር በትፍዐ-ጽልዕ መሐላ

2014 ጁላይ 15, ማክሰኞ

በዓለ ሥላሴ

     
ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም.                                                        መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ወበዛቲ ዕለት ቦኡ ሥሉስ ቅዱስ ውስተ ቤተ አብርሃም ወተሴሰዩ ዘአቅረቦ ሎሙ፡፡ በከመ መጽሐፍ ውስተ ኦሪት ወአብሠርዎ ልደቶ ለይስሐቅ ወባረክዎ፡፡ በዚችም ቀን ልዩ የሆኑ ሦስቱ አካላት /ቅድስት ሥላሴ/ በኦሪት መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ወደ አብርሃም ቤት ገቡ ያቀረበላቸውንም ተመገቡ፡፡ የይስሐቅንም ልደት አበሠሩት ባረኩት አከበሩትም፡፡
መጽሐፈ ስንክሳር ዘሐምሌ ሰባት
trinity 2
ሥላሴ ማለት በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት አንድ አምላክ በሦስት አካላት እንዳለ ለአበው ለነቢያትና ለሐዋርያት መገለጡን አምነን የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ሥላሴ ማለት የግእዝ ቃል ሲሆን ሦስት፤ ሦስትነት ማለት ነው፡፡

የአንድ አምላክ በሦስትነት መገለጥን ለመረዳት በኦሪት ዘፍጥረት 1፡26 ላይ በተገለጠው መሠረት “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌችን እንፍጠር” ይላል ይህ አገላለጽ “እግዚአብሔርም አለ” ሲል አንድነትን (አንድነታቸውን) “እንፍጠር” ሲል ከአንድ በላይ (ሦስትነትን) መሆንን ያስረዳል፡፡

ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

ፈቃደ እግዚአብሔር ምንድነው? እንዴት ማውቅ ይቻላል ?
                                    ወለተ ማርያም /ከሮቤ ባሌ ጎባ
በ ኢሜል lemabesufekade@gmail.com የተላከ
  

ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላልየሚለው የሰው ሁሉ ጥያቄ ነው። ብዙዎቻችን መመዘኛችን ሥጋዊ በመሆኑ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ፥ ለመቀበልም እንቸገራለን። የሚነገረው ሁሉ ለኅሊናችን መልስ ስለማይሆን አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም እንላለን። ለምሳሌ፦ ከአይሁድ የተላኩ ካህናትና ሌዋውያን፦ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን፦ «እንኪያስ አንተ ማነህ? አንተ ኤልያስ ነህንባሉት ጊዜ፦ «አይደለሁም » ብሏቸዋል። ዮሐ ፩፥፳፩። ነቢዩ ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ቢያርግም በስሙ የተነገረ « እነሆ፥ ታላቋና የምታስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ቴስብያዊው ኤልያስን እልክላችኋለሁ።» የሚል ትንቢት አለ። ሚል ፬፥፭። ይኽንን ይዘው ነው፥ «ኤልያስ ነህንያሉት። ዮሐንስ «አዎን ነኝ፤» ማለት ይችል ነበር። ምክንያቱም ጌታችን «ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።» በማለት እንደመሰከረለት በሁሉ ኤልያስን ይመስለዋልና። ማቴ ፲፩፥፲፬። ነቢዩ ኤልያስ፦ ፀጉራም ፥ጸዋሚ ፥ተሐራሚ፥ ዝጉሐዊ፥ ባሕታዊ ድንግላዊ ነው። ቅዱስ ዮሐንስም ልብሱ የግመል ፀጉር ሆኖ፦ ጸዋሚ ተሐራሚ ዝጉሐዊ ፥ባሕታዊ ድንግላዊ ነው። ይሁን እንጂ «አይደለሁም፤» ያለው፦ «ነኝ፤» የሚለው እውነት ለአይሁድ ለኅሊናቸው መልስ ስለማይሆን ነው። ለእኛም ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር የሚነገረው እውነት ሁሉ ለኅሊናችን መልስ አይደለም። 
ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ በሕግ በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልጋል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ወደ እር ቅረቡ

2014 ጁላይ 11, ዓርብ

በዓለ ዕረፍቶሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በታናሽ ኤስያ እየዞረ በቃሉ እያስተማረ በመልእክትም እየጻፈ ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ በመከራም እንዲታገሱ እየመከረ ካጽናናቸው በኋላ በሮሜ ለክርስቶስ መስክሮ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ዘመኑ ሲደርስ በ67 ዓ.ም ወደ ሮሜ ገብቶ ያስተምር ጀመር፡፡

ኔሮን ቄሳርም በዚያ ዘመን በክርስቲያን ላይ የሚቃጠለው የቁጣ እሳት ገና አልበረደለትም ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ አሰረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በምሴተ ሐሙስ ጌታው በተያዘ ጊዜ ስለ ደረሰበት ፈተና ጌታዉን አላውቀዉም ብሎ መካዱ ብቻ ትዝ እያለው ያዝን ነበር እንጂበመታሰሩ አላዘነም ነበር፡፡…

ኔሮን ቄሳርም ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ ካሰረው በኋላ ወደ አካይያ ዘምቶ ነበርና በዘመቻው ድል አድርጎና ደስ ብሎት ወደ ሮሜ ሲመለስ አረማውያን የሆኑ መኳንንቱን ደስ ለማሰኘትና አማልክቱን ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ሁሉ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስም ሞት በመስቀል እንዲሆን ታዘዘ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን ወአመሰ ልሕቅ ባዕድ ያቀንተከ ሐቄከ ወይወስደከ ሀበ ኢፈቀድከ ብሎ የነገረው ቃል ትዝ አለውና አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡

2014 ጁላይ 10, ሐሙስ

ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላል ?




   ብዙ ጊዜ ከተለያዩ ችግሮች የተነሳ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሄ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ገዳማት በመሄድ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ እፈልጋለሁ  ለመሆኑ ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማውቅ ይቻላል ? ፈቃደ እግዚአብሔር ሲባልስ ምን ማለታችን  ነው?ሁሉም ሰው ማወቅ ይችላል?                                                   ወለተ ማርያም / ከሮቤ ባሌ ጎባ/
እህታችንን ይህንን የብዙዎችን ጥያቄ በመጠየቋ እናመሰግናል  መልሱን ይጠብቁ
 ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ካላችሁ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን  እንገልጣለን  ላኩልን;;


   ኢሜል. lemabesufekad@gmail.com    



                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...