2015 ማርች 14, ቅዳሜ

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ 24፤44


አትምኢሜይል
መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዲ/ን ተመስገን ዘገየ
ይህ ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ለደቀመዛሙርቱ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ሲጠይቁት የተናገረው ኃይለ ቃል ነው፡፡ “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፤ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ፣ ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የዓለም ፍጻሜ ምልክቱስ ምንድን ነው?” አሉት፡፡


ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ 800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ቤተፋጌና ቢታንያም ከግርጌው የሚገኙ መንደሮች ናቸው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውም የተሰጠው በላዩ ከሚበቅሉት (ተራራውን ከሸፈኑት) የወይራ ዛፎች የተነሳ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የመላበት (በብዛት የሚገኝበት) ተራራ ማለት ነውና፡፡
የደብረ ዘይት ተራራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት እንደወጣ በ2ኛ. ሳሙ. 15፤30 “ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ” ይላል፡፡ ይህ ተራራ በሕዝቅኤል ትንቢት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደሚያርፍበት ተነግሮአል፡፡ የእግዚአብሔር ክብርም ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ፡፡ ት.ሕ11.23
ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ ዐደባባይ ደብረ ዘይት 75 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚበሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡ 
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11.1 ላይ “ወአልጺቆሙ ኢየሩሳሌም ኀበ ቤተ ፋጌ ወቢታንያ በኀበ በደብረ ዘይት ፈነወ ክልኤተ እምአርዳኢሁ ፤ወደ ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደ አሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ከደቀ መዘሙርቱ ሁለቱን ላከ” ይላል፡፡ አይሁድም ጌታን የያዙት በደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ በምትገኘው ጌቴሴማኒ ነው፡፡
አንቢቦሙ ወሰቢሖሙ ወጽኡ ወሖሩ ውስተ ደብረ ዘይት ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክሕዱኒ በዛቲ ሌሊት፣ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው፡፡ ማቴ. 26.30
ጌታችንም ሲያስተምር ውሎ ማታ ሔዶ የሚያድረው በደብረ ዘይት ተራራ ውስጥ ባለችው ኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሳዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጡ የገባውም ወደ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ማር 11.1 በዚህ ዓለም የፈጸመውን አገልግሎት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሰማይ ያረገውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ወደፊትም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ላይ መገለጫው ደብረ ዘይት እንደሆነች ተገልጿል፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ቀን ይመጣል ብዝበዛሽንም በውስጥ ይከፍላሉ፡፡ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምን ይወጉአት ዘንድ እሰበስባለሁ ከተማይቱም ትያዛለች ት. ዘካርያስ 14.1
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ በደብረ ዘይት ተራራ) ላይ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በቤተ መቅደስ ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻ ጠየቁት፡፡ እንዲህም አሉት ንገረን ይህ መቼ ይሆናል (ማር 13.3፣ማቴ 24.1-51) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ዘበሰማያት የሚለውን ጸሎት ያስተማረውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ከ62 ሀገሮች በላይ ልሳን(ቋንቋ) በሞዛይክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚዘመርበት፤ የሚሰበክበት ዕለት ስለሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል፡፡ ሰያሚውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ 24.1-36 ነው፡፡
 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ፡፡ “አማን እብለክሙ ኢይትኀደግ ዝየ እብን ዲበ እብን ዘኢይትነሠት፣ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስና ዳግም መምጣትን አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊ ንጉሥ ፊት ያለ ምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በአሕዛብ ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚህ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል” (ማቴ.24.14) በማለት በስፋት አስተምሮአቸዋል፡፡ እምበለስ አእምሩ አምሳሊሁ፣ ነገሩን በበለስ እወቁ፡፡ የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው የእስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት 11ኛ ምልክት ነው፡፡ ማቴ 24.32
ከዚህ በኋላ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር በደመና ይመጣል፡፡ “ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩላ ዐይን ወእልክቱሂ እለ ወግእዎ ይበክዩ በእንቲአሁ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር እወ አማን፣ እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል ዐይን ሁሉ ታየዋለች የወጉትም ሁሉ ያለቅሳሉ የምድር ወገኖች ሁሉ የኀዘን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፡፡” (ራእይ 1.7)
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ካስጠነቀቀበት ዐቢይ ኃይለ ቃል መካከል ስለ ሐሰተኞች መምህራን መምጣት ነበር፡፡ “እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን” የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ በማለት (በማቴ 24.5) አስጠንቅቋል፡፡ ክርስቲያኖች አሁንም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማል? በማለት እውነተኛ የወንጌል መምህራንን በመምሰል ብዙዎችን እንደሚያሳስቱ ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 7.15 ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 16.17 “ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምንቹሃለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉና” ይላል፡፡
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ “እኛስ ያለማወላወል የደጋግ አባቶችን ሃይማኖት እንይዛለን” (ሃይማኖተ አበው ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያውን እምነታችን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተከፋዮች ሆነናልና፡፡ (ዕብ 3.14) ይላል፡፡ ስለዚህ በጊዜው ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል (2ኛ ጢሞ4.2)
የዓለም መጨረሻውና የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች በማቴ 24.1 በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡

ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ምጽአቶች እንዳሉት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “….በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሥዋት ኃጢአት ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል… አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸውም ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታዩላቸዋል” (ዕብ 9.26-28 ) በማለት ተናግሮአል፡፡

የመጀመሪያው ምጽአቱ ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትህትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ በሚሞት በሚሰደድ በሚዳከም ፤በሚበረታ፤ በሚራብ፤ በሚጠማ ፤ በሚዝል በሚወድቅ በሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) እንደ አንድ ኃጥእ ሞት፣ እስኪፈረድበት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጐ መጣ፡፡

ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሸጋግረን በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ስለ እኛ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመሰቀል ሞት ታዘዘ፡፡ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ተነሳ ወደ ሰማይም በዐርባኛው ቀን አረገ በየማነ አብ ተቀመጠ፡፡ ይህ ነው የመጀመሪያው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳንና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡

ዳግማዊ ምጽአቱ፡- በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪያ ምጽአቱን) ባልተቀበሉት ላይ ሊፈርድ ዐይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል፡፡ “እግዚአብሔርስ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል (መዝ 50.3)
መጥቶም ዝም አይልም (ኤሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደልዋን፤ ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ወዮላቸሁ) እያለ ይወቅሳል ወንጌልንም ያስተምራል፡፡ ጻድቃንን “እናንተ የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ ብሎ ይጠራል ኃጥአንንም እናንተ ርጉማን ሐሩ እምኔየ፤ ከእኔ ወግዱ” ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ በፊቱ እሳት ይነዳል ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መዓት በባሕርዩ አለ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ! የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት?
ጌታችን በደብረ ዘይት ያስተማራቸው ትምህርቶች በመሠረታዊነት በ3 ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡
1. ምልክት፡- በዚያ ዘመን እንዲህ ይሆናል እያለ በፍጻሜ ዘመን የሚከሰቱትን ድርጊቶች፡፡
2. ትእዛዝ፡- በዚያ ዘመን ከጥፋት እንድን ዘንድ የሰጠን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ እያለ ፡፡

3. ማስጠንቀቂያ በፍጻሜ ዘመን እንዲህ ሁናችሁ የተገኛችሁ “ወዬላችሁ” እያለ የተናገራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ “ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” የሚለው እርጉዝ ማለት የኃጢአት ዐሳብ የጸነሱት ሲሆኑ የሚያጠቡ ያላቸው ኃጢአትን ጸንሰው በንግግር የወለዱትን ነው” 
በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ (ማቴ 24.16) በዚህ ቃል መሠረት በይሁዳ በዓለም ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ ተብሏል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ትሩፋት እየሠሩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ ይሽሹ ነው፡፡ 
ለመሆኑ ተራራ ምንድን ነው?
1. ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው “መዝ. 124.2 ይላል፡፡ በዚህ ቃል የእግዚአብሔር ረድኤት በተራራ ተመስሎ ቀርቧል፡፡ ምክንያቱም ተራራ እንደሚከልል እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይከልላልና፡፡ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡

2. ተራራ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
3. ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች “አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፣ በጽዮን በደብረ መቅደሱ ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጽዮን ላይ ” መዝ.2.6 ስለዚህ ትውልድ ድንግል ማርያምን ዓምባ መጠጊያ ያደርግ ማለት ነው፡፡
4. ተራራ የተባሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው፡፡ መዝ.86.1 መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን ፤መሠረቶቿ በቅዱሱ ተራሮች ናቸው” ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ወደ ቅዱሳን አባቶቻችን ቅረቡ በአማላጅነት ሥልጣናቸው አምናችሁ ተማጸኗቸው ሲል ነው፡፡

በሰገነት ያለውም በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ ይላል (ማቴ 24.17) ሰገነት ከፍ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቃል በሠገነት የተመሠለ በምግባር በሃይማኖት የበረታ የወጣትነት ዘመን አልፎ ከማዕከላዊነት የደረሰ ማለት ሲሆን፤ በዝቅታ የተመሠለ ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ የነፍስ ተዋርዶ ነው፡፡ 
ዴማስና ይሁዳ በሰገነት ነበሩ በኋላ ግን በዝቅታ ሥፍራ ተገኙ፡፡ መዋል በማይገባቸው ቦታ ውለው ተገኙ፡፡ በክርስትና ከፍ ከፍ ብለው በመንፈሳዊነት መጽናት አቃታቸው፡፡ እኛስ ከየትኛው ስፍራ እንሆን?
በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላ አይመለስ (ማቴ24.18) በእርሻ የተመሰለ የመነነ ወይም በምንኩስና ሕይወት ያለ ማለት ነው፡፡ በእርሻ ያለ አይመለስ ማለት በምነና በምንኩስና ያለ ይህንን ሕይወት የጀመረ አይመለስ፡፡ ስለዚህ ስደታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ አለ (ማቴ 24 .20) ክረምት የፍሬ የአጨዳ ሳይሆን የሥራ የመዝሪያ ወቅት ነው፡፡ ሰንበትም የዕረፍት ቀን ናት፤ በሠንበት ሥጋዊ ሥራ አይሠራም፡፡ አንድም በክረምት ቅጠል ካልሆነ ፍሬ አይገኝም እናንተም ሃይማኖት ይዛችሁ ምግባር ከሌላችሁ ዋጋ የላችሁም ማለቱ ነው፡፡
ሽሽት የተባለ ዕለተ ምጽአት ሲሆን በሽሽት የተመሰለው ሞት ድንገት እንደሚመጣ ዕለተ ምጽአትም በድንገት ስለሚሆን ነው፡፡ ትርጉሙ ንስሓችሁን ሳትጨርሱ የንስሐ ፍሬ ሳታፈሩ በድንገት ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ጸልዩ የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ሲኖር “ድልዋኒክሙንበሩ፤ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ማቴ 24:24 በተባለው አማናዊ ቃል መሠረት ራሱን በንስሓ አዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ 

2015 ማርች 11, ረቡዕ

እረፍቱ ለአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ


Written By Hulubante Abebe 

 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።” 
                                 
 መዝ ፴፫፡፲፭-፲፯ 
መጋቢት 5 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞች ዘንድ የፃድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል 
በዚህ እለት እምናከብረው የእረፍት መታሰቢያቸውን ሲሆን ከገድላቸውም እንዲህ ተፅፎ እናገኘዋለን 
ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ግብፅ ንሂሳ በምትባል ቦታ ከአባታቸው ስምዖን ከእናታው አቅሌስያ ነው። በአጠቃላይ የኖሩበት ዕድሜ 562 አመት ሲሆን 300 ዓመቱን በግብጽ 262 ቱን በኢትዮጵያ 100 ዓመት በዝቋላ በተጋድሎ ያሳለፉ ታላቅ አባት ናቸውኢትዮጵም የአስራት ሐገራቸው ሆና በቃልኪዳን ተሰጣቸዋለች  እናታቸው ሳትታቀፋቸው ወተት ሳይጠጡ በመንፈስ ቅዱስ አድገው በ፫ ዓመታቸው ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ እስከ ሰባቱ ሰማያት አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረበው፤ ባረከውም፤ ድንግል ማርያም ጻድቃን ሰማዕታት ወዳሉበት ተወስዶ ተባርኮ በጌታችን ቃል ተቀብሎ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳሉበት አውርዶ በዚያም አድጎ መንፈሳዊ ሥራን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተጋድሎውን ጀምሯል። በበረሃ ሲኖሩ 60 አንበሳና ነብር የተሰጣቸው ሲሆን አንበሳ እና ነምሮቹም የሚበሉትም የቅዱሱን እግር ያረፈበትን ቦታ በመላስ ነው። የአባታችን ገድል እንደሚያስረዳው እንደ ሰው ልብስ ለብሰው ሳይሆን ልብሳቸው በጸጋ የተሰጣቸው ጠጉር ነበር እሱም ልክ እንደ ልብስ ያገለግላቸው ነበር
 ከሚያስገርመው ገድላቸው ውስጥ አባታችንን ለመጠየቅ የመጡት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር መጥተው እንግዶቹን አንበሶቹ በልተው አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ መምጣታቸውን አውቆ ሲነግሯቸው ለምን ያልተፈቀደላችሁን በላችሁ ብለው የበሉትን አንበሶች የበላችሁትን አንድም ሳታስቀሩ ትፉ ብሏቸው ወደ እግዚአብሔር ጸልየው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሱ ባሉ ጊዜ የተበሉት ነፍስ ዘርተው እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባም በሰላም ወደ ባእታቸው በአባታችን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸሎት በሠላም ገብተዋል።
መጋቢት 5 በገድለ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ
ዕለቱ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ህመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግን አልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚያብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት
ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አለው፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው፤ ከመጋቢት አምስት ቀን ጀምሮ ዝክርህን ያድርጉ በአማላጅነትህም ይማጸኑ አለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዱ በእየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በዛሬዋ ቀን ሩጫውን ጨረሰ። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።
የአባቶችን የቅዱሳንን ታሪክ እንድናውቅ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከነርሱ ገድል ተምረን እኛም ወደአምላክ መንገድ እንድንቀርብብበት ነውና አምላከ ገ/መንፈስ ቅዱስ መንገዱን ያብራልን ። ገድሉንም ሰሚወች ብቻ ሳንሆን እምንማርበት ያድርግልን ።
መጋቢት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ /አባ ገብረ ሕይወት/                                     2.ቅዱስ አባ ሰረባሞን /በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ/                 3.አባ ግርማኖስ ጻድቅ /ሶርያዊ/                                                         4.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት /ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት/ 
5.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ /የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች/

                       ወስብሐት ለእግዚአብሔር

2015 ማርች 10, ማክሰኞ

እየደመሰሱ መቅዳት

ለረዥም ዓመታት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የሠራ ጋዜጠኛ ለአንድ ጥናት ወደ ጣቢያው ይሄዳል፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት እርሱ ራሱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር፡፡ ቃለ መጠይቁ የተደረገላት ሴት አሁን በሕይወት የለቺም፡፡ ለዚህ ነበር እርሷ የሰጠቺውን ቃል ፍለጋ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሄደው፡፡ ያገኘው ግን የጠበቀውን አልነበረም፡፡ የተቀዳው ቃለ መጠይቅ የለም፡፡ ምነው? አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ብዙ ካሴቶችን እየደመሰስን ቀድተንባቸዋል፡፡ በዚያ ምክንያት ያንን ቃለ መጠይቅ አሁን አታገኘውም›› አሉት፡፡ እርሱም በዚህ አዝኖ ወጣ፡፡
ለነገሩ እርሱ በካሴቱ አዘነ እንጂ ከኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫዎች አንዱ እየደመሰሱ መቅዳት ነው፡፡ የሚመጣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን፣ ዐዋቂ ወይም ታዋቂ፣ ታሪክ ጸሐፊ ወይም ዐቅድ ነዳፊ ከእርሱ በፊት ለነበረው ነገር ዋጋ ሰጥቶ፣ የየራሱን ሥራ ከመሥራትና የዘመኑን አሻራ ከማኖር ይልቅ ያለፈውን መደምሰስ ይቀናዋል፡፡ 

ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለ ቆየ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡ የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም አሣምሮ የሚጨምር ከሆነ ሀገር እያደገች፣ እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡ 
 ባቢሎን በታሪክ ቀድመው ከሠለጠኑ ሀገሮች ተርታ ነበረቺ፡፡ ነገር ግን የገዛት ሁሉ ከመሠረቷ እያፈረሰ እንደገና ሲሠራት፣ የመጣዉ ሁሉ እየደመሰሰ ሲቀዳባት ይሄው ዛሬም አላልፍላት ብሎ የጦር አውድማ ሆናለቺ፡፡ ስለ ኢራቅ ጥንታዊ ታሪክ የሚተረከውና የዛሬዋ ኢራቅ አይጣጣሙም፡፡ የመጡት ሁሉ በባቢሎን ካሴት ላይ እየደመሰሱ ሲቀዱ፣ መሠረት አልባ ጣራ ሊያቆመ ሲደክሙ፣ አሁን የመጡባት አሸባሪዎች ደግሞ ጨርሰው ታሪካዊ ቅርሶቿን በድጅኖ መናድ ጀመሩ፡፡ እየደመሰሱ መቅዳት ካንሰር መሆን ሲጀምር ይሄው ነው፡፡
ይኼ እፉኝታዊ ጠባይ ነው፡፡ እፉኝት የምትባል የእባብ ዘር አለች አሉ፡፡ አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ነው፡፡ ከወንዱ ጋር ስትገናኝ የወንዱን አባለ ዘር ትቆርጠውና ወንዱ ይሞታል፡፡ ልጆቿን በማኅፀኗ ፈልፍላ ስትወልዳቸው ደግሞ ለመውጣት ስለማይችሉ ሆዷን እየቀደዱ እናታቸውን ገድለዋት ይወጣሉ፡፡ ልጆቹ ልጅ የሚሆኑት አባትና እናታቸውን ገድለው ነው፡፡ ያለፈውን ካልደመሰሱ መኖር አይችሉም፡፡
የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡ ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡ አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡፡ 
ቅቤን ማንም አያነጥረውም፤ ባለሞያ ይጠይቃል፡፡ አንጉላውን የማስወገጃ መንገዱ ራሱ ልዩ ሞያ ጠያቂ ነው፡፡አንጉላ መስሎን ቅቤዉን ጭምር እንዳያስወግደው እንደ ዶሮ ላባ ባለ ስስ ነገር እየለዩ ማንጠርን ይጠይቃል፡፡
ታሪካችንንና ባሕላችንን፣ ወጋችንንና ልማዳችንን ስንመረምርና አንጉላውን ስንለይ፣ እንደ ቅቤ አንጣሪው በሞያ መሆን አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ሊያገኝ አይገባም፡፡ ቅቤ አንጣሪ ስሜት ውስጥ ከገባ ምች ይመታዋልና፡፡ አረሙን እንነቅላለን ብለን ስንዴውን ጨምረን እንዳንነቅለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ብለን የምንሠራቸው ሥራዎች አዙሪት ውስጥ እንዳይጥሉን ጉዳዩን የሞያና የዕውቀት ጉዳይ ማድረግ ይገባናል፡፡ ‹ዕውቀት አጠር፣ ስሜት መር› ከሆነው ጉዟችን ይልቅ ‹ዕውቀት መር፣ ስሜት አጠር› ወደሆነው ሥልጣኔ ካልወጣን በስተቀር እዚያው ጨለማው ውስጥ ስንኳትን እንኖራለን፡፡ 
ቅቤ አንጣሪ ሰው ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ያስፈልገዋል፡፡ ምች እንዳይመታው፡፡ የቅቤ ምች ያጠናግራል ይባላል፡፡ ቅቤውን በጥንቃቄ ያነጠረቺ ባለሞያ ናት ‹‹ቅቤ አንጣሪዋ እያለቺ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት› ብላ የተሳለቀቺው፡፡ ነባሩን ነገራችንን ስናነጥር ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ወሳኝ ነው፡፡ የዘመን ምች መትቶ እንዳያጠናግረን፡፡ ጎጠኛነት፣ የፖለቲካ ፍጆታ፣ የሥልጣን ፍቅርና ጊዜያዊ ጥቅም የሚባሉ ምቾች አደገኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ምቾች የመቱት ሰው ቅቤውን በሚገባ ማንጠር ቀርቶ ሌላ በሽታ በራሱ ላይ ይጨምራል፡፡ ጤነኛ የነበረው አንጣሪ ተጣሞ፣ ዓይኑ ጠፍቶ፣ ፊቱ ቆሳስሎ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱ ያለፈው ታሪኩን ሁሉ የሚያየው በማንጠሪያ ዓይኑ ሳይሆን በተጠናገረ ዓይኑ ነው፡፡ 
አሁን በደምስሶ መቅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩት ብዙዎቹ ወገኖቻችን ምች የመታቸው ናቸው፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን ምች ስለ መታው ቅቤውንና አንጉላውን መለየት አልቻሉም፡፡ አንጉላ መስሏቸው ሁሉንም ነባር ቅቤ ሊያስወግዱ የቋመጡ ናቸው፡፡ የዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡
ሰው በአንድ ቦታ ስለተሰበሰበ ብቻ ሀገር አይሆንም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እሥራኤላውያን አሜሪካና ፖላንድ መኖር ይበቃቸው ነበር፤ ለፍልስጤማውያንም ዮርዳኖስና ሊባኖስ የሚኖሩት የካምፕ ኑሮ በቂ ነበር፡፡  ሰፊ መሬት ብቻውንም ሀገርን አይመሠርትም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ሀገር ግን ከሰውም ከመሬትም በላይ ናት፡፡ ሰው በመሬቱ ላይ ሲኖር የሠራው ታሪክ፣ ያካበተው ባሕል፣ የደነገገው ወግና ሥርዓት፣ ያዳበረው ቋንቋ፣ ያመጣው ለውጥ፣ የፈጠረው ዘዴ፣ የገነባው ሥነ ልቡና፣ የተከተለው እምነት፣ የእርስ በርሱ መስተጋብር፣ ዓለምን የሚያይበት ርእዮተ ዓለም፣ ሥነ ቃሉ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም ተዋሕደው የሚፈጥሩት ነገር ነው - ሀገር፡፡ 
 
እነዚህን የተሠራንባቸውን ነገሮች ነው ማንጠር የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ እንሰብስባቸው፣ እንመዝግባቸው፣ እንለያቸው፣እንዘግባቸው፣ እንቀርሳቸው፣ እንወቃቸው፡፡ ከዚያ እናጥናቸው፣ እንመርምራቸው፡፡ በመጨረሻም እናንጥራቸው፡፡ ገመዱ ውስብስብ ነው፡፡ ለዘመናት የተፈተለና የተገመደ፡፡ ርጋታ፣ ትዕግሥትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ወስነን አይደለም ማወቅ ያለብን ዐውቀን ነው መወሰን እንጂ፡፡ አንዳንዴ መጀመሪያ እንወስናለን፣ ከዚያ እንሰይማለን፣ ቀጥለንም እንፈርጃለን፣ በመጨረሻም እንመታለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ዕውቀት፣ ጥናትና ማንጠር ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ ‹ስቅሎ ስቅሎ› ነው፡፡ ‹ትዕዛዝ ከበላይ፣ እግር ወደላይ› ይሆናል መመሪያው፡፡
 
በዚህ መንገድ ስንቱን እየደመሰስን ቀዳን፡፡ ስንቱን ነባር ዕውቀት ሳንጠቀምበት እንደ ገናሌ ወንዝ ፈስሶ ፈስሶ ቀረ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡   

የኢሬቻ በዓል በደብረ ዝቋላ እንደሚከበር የተላለፈው ዘገባ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ተወሰነ

debra zeq
  • ለአፈጻጸሙ የወረዳው እና የዞኑ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሓላፊነት ወስደዋል
  • ከመጋቢት ፭ ክብረ በዓል በፊት ማስተባበያው እንዲተላለፍ ከስምምነት ተደርሷል
  • ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ የችግሩን ቆስቋሾች ያጣራል
  • በክብረ በዓሉ ቀን የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል
* * *
  • ‹‹ለእኛ ዐዲስ ነገር ነው፤ እዚኽ ቦታ ኢሬቻ የለም፤ በአራት ወይም በስምንት ዓመት አንዴ ዝናም እምቢ እንዳይለን ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዐት ውጭ በተነገረው መልኩ የሚከበር በዓል የለም፡፡ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡››
/የአባ ገዳ ተወካዮች/
  • ‹‹ኅብረተሰቡን ከእኛ ጋራ ሊያጣሉ የሚፈልጉ ግለሰብ አመራሮች አሉ፡፡… ለተላለፈው መልእክት ሓላፊነት የሚወስድ አካል ካልተገኘ፣ የመጋቢት ፭ ክብረ በዓል ከመድረሱ በፊት በስሕተት የተላለፈ መኾኑ ይገለጽልን፡፡››
/የገዳሙ አስተዳደር/
  • ‹‹እናንተ ሰላም ፍጠሩ፤ [በክብረ በዓሉ] ከተለመደው ውጭ አንዳችም የሚደረግ አይኖርም፤ ጥበቃውም እንዲጠናከር ይደረጋል፤ የተላለፈውን ዘገባ አጣርተን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፡፡››
/የዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ሓላፊዎች/

2015 ማርች 5, ሐሙስ

በዝቋላ ገዳም ዙሪያ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ እየተዛመተ ነው


  • የሄሊኮፕተር እገዛ አልያም የውኃ ቦቴ መኪኖች ድጋፍ እየተጠየቀ ነው


በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ትላንት ጠዋት የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ አሞራ ገደልበሚባለው አቅጣጫ መዛመቱ ተገለጸ፡፡
በሰሜን በኩል ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው የገዳሙ መውጫ ትላንት ጠዋት 2፡00 የተቀሰቀሰው ቃጠሎ፣ በአዱላላ ወረዳ ሠራተኞችና በነዋሪው ሕዝብ ርብርብ ማምሻውን መጥፋቱ ከተገለጸ በኋላ ነው አሞራ ገደል በሚባለው የገዳሙ ደቡባዊ ገጽ በዛሬው ዕለት 5፡00 ላይ ዳግመኛ መቀስቀሱ የተሰማው፡፡
በገዳማውያኑ የጥሩንባ ልፈፋ በተሰባሰበው የገጠሩ ነዋሪና የወረዳው አስተዳደር ሠራተኞች እሳቱን አፈር በማልበስና በቅጠል በመተምተም  ለማጥፋት የተቻለ ቢመስልም አንድ የገዳሙ መነኰስ በስልክ እንዳስረዱት፣ ‹‹በደንብ ሳይጠፋ ቀርቶ የታፈነ ነበር፡፡ ዛሬ አሞራ ገደል ጫካ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዛፉ እርጥበት አለው፤ ጢሱ ያፍናል፡፡››  
ቃጠሎው፣ በአካባቢው ከባድ ነፋስ እየበረታ ከገደሉ ሽቅብና ወደ ጎን ወደ አዱላላ አቅጣጫ የተወሰነ የደኑን ክፍልና እዳሪ መሬት እየበላ በአስጊ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ አኹን ባለው አካሔድ ሳይገታ ወደ ምሥራቅ ከዞረና ጠበል ሜዳውን ካገኘ ወደ ደኑ በጥልቀት ስለሚገባ በእጅጉ አውዳሚ እንደሚኾን የገዳሙ መነኰስ ተናግረዋል፡፡
ከቦታው ገደላማ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንጻር የሚያፍነው ጢስና የቃጠሎው ፍጥነት የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት የገዳሙ መነኰስ፣ አመቺ የሚኾነው አስቸጋሪውን ዐቀበት በመውጣት ለሰው ኃይሉ ውኃ ማቅረብ በሚችሉ መኪኖች አልያም በአየር ርጭትበመኾኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል የሄሊኮፕተር አልያም የቦቴ መኪኖች እገዛ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲጠየቅ አመልክተዋል፡፡
የትላንቱን ቃጠሎ ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ከደብረ ዘይት ከተማ ተጉዘው ሌሊቱን ቃጠሎው በጀመረበት ስፍራው የደረሱ ምእመናንየእሳቱን መስፋፋት የሚገቱ የመከላከል ሥራዎችን ሲሠሩ አድረው መመለሳቸው ተገልጧል፡፡ የከተማው ሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን የወረዳው ማእከል አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲኹም ምእመናን÷ መሬቱን ቆፍሮ በአፈር የመከተር፣ ተቀጣጣይ ጉቶዎችንና ቁጥቋጦዎችን የመመንጠር የመከላከል ሥራ እስከ ንጋት ድረስ ሲሠራ ማደሩ ታውቋል፡፡
ዛሬ ቀትር ላይ መዛመቱ የታወቀውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከገዳማውያኑ የድረሱልን ጥሪ መተላለፉን የገለጸ አንድ ምእመን፣ በከተማው በስምንቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችና በሠርክ ጉባኤያት ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በመቅስቀስና በማስተባበር በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ለመድረስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡


zequulla
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የገዳሙ መነኰሳት እየተናገሩ ነው፡፡
ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው የጀመረው ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው በገዳሙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ነው፡፡
ይህ አቅጣጫ፣ የገዳሙ ሞፈር ቤት የሚገኝበት መውጫ መንገድ ሲኾን በአኹኑ ሰዓት በበርካታ ቦታዎች ጭስ እንደሚታይ በመነኰሳቱ ተገልጧል፡፡
የቃጠሎው መንሥኤ በውል ባይታወቅም እሳቱ በአካባቢው ባለው ከባድ የነፋስ ኃይል ወደ ገዳሙ መውጫና በገዳሙ ዙሪያ እንዳይስፋፋ ተሰግቷል፡፡
ziquwala_17የአቅራቢያው ነዋሪ ኅብረተሰብ በጥሩንባ በተላለፈው የድረሱልን ጥሪ የተሰባሰበ ሲኾን ወደ ወረዳው ጽ/ቤትም ተደውሎ የአስተዳደሩ አባሎችና የፖሊስ ኃይል በስፍራው መድረሳቸው ተገልጧል፡፡ ‹‹ቃጠሎውን በቅጠልና በአፈር ለመከላከልና መዛመቱን ለመቀነስ የነፋሱን ጋብ ማለት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፤›› አንድ የገዳሙ መነኰስ፡፡
በጥንታዊውና ታሪካዊው ገዳም ዙሪያ የእሳት ቃጠሎ ሲደርስ የአኹኑ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እንደ አርዘ ሊባኖስና የሐበሻ ጥድ ያሉት አገር በቀል ዛፎች በስፋት ወድመዋል፡፡ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ደግሞ ተኣምራዊና ግራ አጋቢ ጠባይዕ የታየበት ነበር፡፡ በምሥራቃዊ አቅጣጫ በሚገኘው የመንግሥት ደን ውስጥ ተከሥቶ በአንድ ገጽ ኃይሉ ሲቀንስ በሌላ አቅጣጫ እየተዛመተ ገዳሙን ጨርሶ ለማጥፋት በተቃረበበት ኹኔታ ከአዲስ አበባ፣ ከቢሾፍቱና ከአዳማ በተመሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና አካላት መተባበር እንዲኹም በመከላከያና በፖሊስ ኃይሎች እገዛ መገታቱ የሚታወስ ነው፡፡
በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በገዳሙ የጠበል – ሐይቅ የኢሬቻን በዓል ለማክበርና በደብረ ዝቋላ የአባ ገዳ ሐውልት ለመትከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታቀዱንና በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ መገለጹን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር በጻፈችው ደብዳቤ ተቃውሞዋን በማሰማት ላይ እንዳለች ይታወቃል፡፡DSC_0642[1]ጥንታዊውና ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በገዳሙ ደጅ ጠኚውን፣ አፈር ጠባቂውንና የአብነት ትምህርት መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ሳይጨምር እስከ 350 መነኰሳትና መነኰሳዪያት እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡

ሰበር ዜና:- በዝቋላ ገዳም ዳግም የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ


የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
abune gebre menfes kidus 004በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ደን ላይ በዛሬው እለት የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን ከገዳሙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተራራው ሥር ከወንበር ማርያም እና አዱላላ አቅጣጫ የተነሳው ቃጠሎ በገዳሙ ደን ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ ማኅበረ መነኮሳቱና ተማሪዎች፤ እንዲሁም የአካባቢው ምእመናንን ባደረጉት ርብርብ ለጊዜው አፈር በማልበስ ለማጥፋት ተችሏል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ካለው ነፋሻማና ሞቃታማ አየር ምክንያት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ገዳማውያኑ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረ ማርያም ገልጸዋል፡፡

'ዛሬ ጠዋት እየኾነ ያለው እንዲህ ነው'

2015 ማርች 4, ረቡዕ

የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለች


አትምኢሜይል
የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዘማች አዩኔ /ከሆሳዕና ማእከል/
001 hosaen mariamበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀድያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከቅዳሴ በኋላ ድንገተኛና ለጊዜው መንስኤው ባልታወቀ ሁኔታ ተቃጠለች፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወርኃዊ በዓል ለማክበር ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደተጠናቀቀ እና ቡራኬ ተቀብለው ወደየቤታቸው በተመለሱ በ20 ደቂቃ ውስጥ ካህናት እና ዲያቆናት ገና በደጀ ሰላም እያሉ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ቃጠሎው እንደጀመረም ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ በሮች ከውጭ ተቆልፈው ስለነበር ቁልፎቹን በቅርበት ለማግኘት ስላልተቻለ እሳቱን ቶሎ በቁጥጥር ለማዋል አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በውስጥ የነበሩት ንዋያተ ቅድሳት ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡

የደብሩ ካህናትና ዲያቆናት የቤተ ክርስቲያኗን በር ሰብረው በመግባት በዕለቱ ቅደሴ የተቀደሰበትን ታቦት አፈር በማልባስ ከእሳቱ ለመከላከል ተችሏል፡፡

ከተመሠረተች ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ቤተ ክርስቲያን በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ብትወድምም በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩት ታቦታት ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈዋል፡፡

ከቃጠሎው የተረፉት ታቦታት እሳቱ ከጠፋ ከሦስት ሰዓታት በኋላ በካህናት፣ በዲያቆናት እና ምዕመናን ታጅበው ለጊዜው ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ ገብተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀድያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በ1901 ዓ.ም ሲሆን፤ አካባቢው በሌሎች የእምነት ድርጅቶችና እና በ ኢ-አማንያን የተከበበ በመሆኑ ምእመናን በሃይማኖት በምግባር ጸንተው እንዲኖሩ በደብሩ በተለያዩ ጊዜያት ጉባኤ በማዘጋጀት የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየ ቦታ ነው፡፡

e

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...