ቅዳሜ 28 ጁን 2014

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም


 እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ
                                                                             
                 በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ
(ናታኒም ጡመራዊ መጽሔት ሰኔ 21 ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ: ፊልዽስዩስ በምትባል ሃገር በዼጥሮስ እጅ የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን አነጸ ብለን ነበር:: በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ መላዕክትን: ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዟት ወረደ::

+ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ:-
-አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ ሥርዓተ ቤተ ክርረስቲያንን አሳየ::
-ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው:: ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት (ፓትርያርክ) ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት "አክዮስ" እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ:: አክዮስ ማለት በግዕዙ "ይደልዎ": በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል: ያሥምርለት" እንደ ማለት ነው::

+ጌታችን ይሕን ከከወነ በሁዋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ:: አማናዊት ማሕደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ: ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ: ቅዱስ እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ: ሐዋርያት ድንግልን ከበው: መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ::



+በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይችል ደስታ ተደረገ:: ከቅዳሴ በሁዋላ ጌታችን ሐዋርያትን አዘዛቸው:: "ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም አብያተ ክርስቲያናትን እነጹ:: ይህችን ዕለት የሚያከብራትን አከብረዋለሁ::" ብሏቸው ከድንግል እናቱ ከመላዕክቱ ጋር ዐረገ::

=>በሌላ በኩል ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህ ቀን (ሰኔ 21) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ ላይ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች:: ጌታችንም "ስምሽን የጠራውን: በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ" ብሏታል::

=>የድንግል እመቤታችን ልመናዋ ክብሯ: ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን::

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል::

+ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሸሹ" ብሎ መከራቸው:: ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በሁዋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

+እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች::

+ሐዋርያው "ምነው ልጄ ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ:: የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል የገደልኩሽ እኔ: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው:: እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች:: ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

=>ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
8.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)
9.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
4.አባ አሮን ሶርያዊ
5.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

=>"ስለ ጽዮን ዝም አልልም... አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ:: የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ:: በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ::" (ኢሳ. 62:1-3)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...