ሊያዩት የሚገባ የቴሌቬዥን መርሐግብር ፡ ታህሳሥ 27 2006 ዓ.ም
- አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወይን ተክለው ለ12 ዓመታት በቦታው በመቀመጥ ሲጸልዩበት የነበሩበትና በርካታ ተዓምራትን ያከናወኑበት ቦታ ያዩበታል፡፡
- ጻድቁ አቡነ ህጻኑ ሞአ የተወለዱበትና እንደ በሬ ተጠምደው በማረስ ገድላቸውን የፈጸሙበት ታላቅ ስፍራን ይመለከቱበታል፡፡
- የቦታውን የቀደመ ታሪኩን ያውቁበታል ፤ ዛሬን ያዩበታል ፤ ነገን ያሳስብዎታል፡፡

በኢትዮጵያ በረሃዎችና አውራጃዎች
እየተዘዋወሩ በልዩ ልዩ አምልኮ የነበረውን ሕዝብ የክርስቶስ ወንጌለ መንግሥትን አስተምረውና አጥምቀው የክርስቶስን መንግሥት እንዲወርሱ
ያደረጉት ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግዚአብሔር በመራቸው
መሠረት የሐዋርያ አሠረ ፍኖት በመከተል ዘር ልዝራ ትዳር ልያዝ ሳይሉ ከአባታቸው ከጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከእግዚአኃረያ በመለየት
ታላላቅ ተዓምራትን ካከናወኑባቸው ቦታዎች ውስጥ በሰሜን ሸዋ ሀገረ
ስብከት ከደብረ ብርሃን አካባቢ የሚገኝው ወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ስፍራ አንዱ ነው፡፡ በቦታው አባታችን ወይን ተክለው ለ12 ዓመታት
በቦታው በመቀመጥ ሲጸልዩበት የነበሩ እና በርካታ ተዓምራትን ያከናወኑበት ቦታ ምድረ ከተታ በመባል የሚታወቀው የእናታቸው የእግዚአኃረያ
የትውልድ ቦታ ሲሆን የቦታው ስምም “ ወይንዬ ተክለ ሃይማኖት” ተብሎ እንዲጠራ አድርገዋል፡፡
ይህ ቦታ የሚገኝው በሰሜን ሸዋ
ሀገረ ስብከት ከደብረ ብርሃን ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በግምት
5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቀጥ ባለ ገደል ተከቦ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ጻድቁ አቡነ ህጻኑ ሞአ የተወለዱበትና እንደ በሬ ተጠምደው
በማረስ ገድላቸውን የፈጸሙበት ታላቅ ስፍራ ይገኛል፡፡ በዚሁ ስፍራ ላይ ‹‹እስትንፋስ›› የሚባል ቦታ ከመሬት ሳያቋርጥ በሚወጣው
እስትንፋስ አማካኝነት በርካቶች ከተለያዩ በሽታዎች የዳኑበትና እየዳኑ የሚገኙበት ልዩ ስፍራ ይገኛል፡፡ ይህም ቦታ በጻድቁ አቡነ
ህጻኑ ሞአ ገድል ላይ እንደሚያስረዳው ጻድቁ እንደ በሬ ተጠምደው ከሚያርሱበት ቦታ በማምለጥ ሽቅብ በመውጣት ያረፉበት ቦታ መሆኑን
ያስረዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቦታው ቀድሞ ከ100 በላይ መምህራንና ከኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ ገዳማት የመጡ አባቶች የሚያገለግሉበትና
የሚገለገሉበት ቦታ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በካህናት እጦት የተነሳ አገልግሎቱን የማይሰጥበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ፤ በአሁኑ
ሰዓት ቦታው ያለበት ደረጃ ሲታይ እንደ ቀድሞ ታሪኩ ፤ ሥራውና እንደ ታላቅነቱ ሆኖ አያገኙትም፡፡
ይህን ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ሁኔታ
ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀድሞ የነበረውን አገልግሎት ተመልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የወይንዬ ተክለ ሃይማኖትና የአቡነ ሕጻኑ
ሞአ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ዘወትር እሁድ በመላው ዓለም በEBS ቴሌቪዥን ላይ የሚተላለፈውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን
እምነት ፣ ሥርዓት እና ትውፊት ፣ ታሪክ እና ቅርስ በሚዲያ በኩል ለዓለም በማስተዋወቅ የሚታወቀው አኮቴት ዘተዋሕዶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን መርሐግብር ላይ
የቦታውን የቀድሞ ታሪክ ፤ አሁን ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይ ፕሮግራም ተሰርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ እሁድ ታህሳስ 27
2006 ዓ.ም (Sunday , January 5 2014) የሚተላፍ በመሆኑ ምዕመናን ፕሮግራሙን ማየት የሚችሉ ሁሉ በቀኑ ፕሮግራን
ይከታተሉን ዘንድ የቀደመ የገዳሙን ታሪክ እንዲያውቁ ፤ በቦታው የተከናወኑ ገቢረ ተዓምራትን እንዲመለከቱ ፤ ከአስር ዓመት በፊት
መሰረት የተጣለው እና በግንባታ ላይ የሚገኝው የወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና
በውስጡ ስለሚያስተምራቸው የአብነት ተማሪዎች እና ሌሎችን ጉዳዮች እንዲመለከቱ ሲል ሰበካ ጉባኤው በእግዚአብሔር ስም ይጋብዛል፡፡
ይህን መርሐግብር በርካታ ምእመናን
እንዲመለከቱት ለማድረግ ጽሁፉን (share and Like) የማድረግ ትብብርዎን እንጠይቃልን፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ