“ይቅርታ አድርጉልን ?” :- የቤተ ክህነቱ ተቋማዊ ድቀት ምስክሮች ስልተ ነገር(በጽጌ ማርያም)
December 10, 2013 at 10:16am
በቅርቡ የበጋሻው ደሳለኝ እና የያሬድ አደመ ቀኖናዊ ያልሆነ የ“ይቅርታ አድርጉልን ?”እግረ ጉዞ ለብዙዎች የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡የ“ይቅርታ አድርጉልን ?”ሒደትም
የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንደማይሆንም በራሳቸው “ይቅርታ አድርጉልን ?”በሚሉት እና ከቤተ ክርስቲያን አውጥተው
“እምነ ጽዮን ”የስደተኞች ማኀበር በሚል በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መስመርነት በሐዋሳ ከአደራጆት ቡድናቸው ጋር
መከፋፈላቸውም ገላጭ እሆነ ነው፡፡ይህ ቀኖናዊ አግባቦችን አላሟላም የሚባለው የ“ይቅርታ አድርጉልን ?”እግረ ጉዞ ያስከተለው
መለስተኛ ውዝግብ በልጆቹ ብቻ አልተወሰነም፡፡ደዌው ተዛምቶ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችንም አምሶ
ነበር፡፡አሁንም ቢሆን ( በመሠረቱ )የጉዳዬን ማዕከላዊ ጭብጥ እና መነሻ አድበስብሶ የሚያልፍ ከመሆን የታደገው
ያገኘ አይመስልም፡፡በ“ይቅርታ አድርጉልን ?”እግረ ጉዞ ላይ የሚነሡትን ክርክሮች ወይም አሳቦች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡አንደኛው በይቅርታ በራሱ ተፈጥሯዊ ምንነትና ትርጉም ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ይቅርታ ምንድ ነው? ውግዘት ምንድ ነው? በቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣በቀኖና ድንጋጌዎችና ትውፊትስ ያለው ቦታ ምንድ ነው? የማዉገዝ ምክንያቶች ምንድ ናቸው? መናፍቃን የሚወገዙት እንዴት ነው? እንዴትስ ይመለሳሉ?የሚሉትን ጥቄዎች በመመለስ ላይ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ይህ ክርክር ዕውቀት ሰጪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በግልብ ምሁራዊነት(pseudo intellectualism)የተጣበበ መሆኑንም መደበቅ አይቻልም፡፡በዚህም ምክንያት ከስልት አኳያ ዕውቀት ሰጪነቱ ጎጂ ባይሆንም በቀጥታ“ይቅርታ አድርጉልን ?”የሚሉትን ልጆች ወይም የሐዋሳውን አፈንጋጭ ስብስብ በአድራሻ ገላጭ አይደለም፡፡ሁለተኛው በ”ይቅርታ አድርጉልን”ባዬቹ ትእምርታዊ(symbolic) ትርጉም ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ይህ ምልክታ በአብዛኛው ‹ውጫዊ› በተለይም ፖለትካዊ፣ ክልላዊነትና ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘውጌነት የሚጫነው ነው፡፡የ”ይቅርታ አድርጉልን”ን ውዝግብ ከጥቅስ እና ከቀኖና ክርክር ለጥጦ በመመልክት አገራዊ እና ምዕመን ዐቀፍ ገጽታ ለመስጠት
በመሞከር የተሻለ ነው፡፡
ሆኖም ዞሮ ዞሮ ማጠንጠኛው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አስተምህሮ አድራሽ ፈረስነት በአንድም ሆነ በሌላ ስማቸው በተደጋጋሚ በሚነሳው በጋሻው ደሳለኝ እና ያሬድ አደመ ግፋ ሲል ደግሞ የሐዋሳው አፈንጋጭ ቡድን ብቻ ስለሆኑ የክርክሩ መጨረሻ እየጠበበ ሔዶ የአንድ ቡድን አባላት ጉዳይ ይሆናል፡፡ክርክሮቹ ጠፍተው ግን በተነሳኂ ልቡና ያልተመለሱትን ልጆችን ኢ ቀኖናዊ ድርጊት ከትምህርት፣ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ከቤተ ክርስቲን ታሪክ እና ሲለጥቅም ከይቅርታ መርሕ አንጻር ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ተባይን፣ይቅር ባይንና ይቅር አባባይን በጋራ ያወግዛሉ፡፡
በሁለቱም የክርክር ዘውግ የተሰለፉ ወገኖች “የይቅርታ አድርጉልን” እግረ ጉዞ ቢቆም የክርክራቸውን አጀንዳ ዘግተው ወደ ተለመደው ኑሮ ለመመለስ ብዙ ጊዜ አይፈጅባቸው ይሆናል፡፡ግፈ ቢል ደግሞ ሌላ የያሬድ-በጋሻው እና በዙርያቸው የተሰበሰቡ ተጧሪ ‹ዘማሪያንና ሰባክያን› የሚፈጽሟቸውን ነጠላ ድርጊቶች እያነሡ በተመሳሳይ የክርክር እና የውግዘት አዙሪት ይጠመዳሉ፡፡የእነዚህ ልጆች የአስተሳሰብ ተጋሪዎችም በፊናቸው’’ ከቤተ ክርሰቲያን ይልቅ ሁሉ ለእነርሱ፤ሁሉ በእነርሱ”በሚለው ኦርቶዶክሳዊ ባልሆነው መርሕ ስር ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡አሁን የታየውም ይኸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ማኀበረ-ፖለቲካ ታሪክ እና ባህላዊ ማንነት ውስጥ ከነበራትና ከአላት ሚና አንጻር“የይቅርታ አድርጉልን”ም ሆነ ሌላ ውዝግብ ሰፊ ትኩረት ቢስብ የሚገርም አይሆንም፡፡ሆኖም ግን ትኩረቱ በተሳሳተ ዒላማ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ሁለቱም የአተያይ አቅጣጫዎች አንድም“ከይቅርታ አድርጉልን” ጀርባ ያለውን አስፈሪና አሳፋሪ የቤተ ክነቱን ውሰጣዊ እውነታ ለመጋፈጥ የሚያስችል ብቃት አጥተው የመከኑ ናቸው፡፡አንድም ግላዊ የገንዘብ፣የዝና፣የፖለቲካና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘውጌነት ወዘተ.ፍላጉት ለሟሟላት ሰልፉን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡
ለአለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት እና ከዚያም ለሚበልጡት ዘመናት ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚነሡት ውዝግቦች መሠረታዊውን ችግር እያድበሰበሱ በእንጭፍጫፊ ጉዳዩች ላይ ጉልበት የሚያስጨርሱ ናቸው፡፡የዚህ አንዱ ምክንያት ችግሩን ከምንጩ እና ከምልክቱ ለይቶ የሚመለከት፤ከዚያው በመነሳትም መሠረታዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያችል አቀራረብ መጥፋቱ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን በበላይነት ይመራታል የሚባለው ሲኖዶስም ሆነ እንቆረቆራለን የሚሉት ወገኖች በአብዛኛው እነዚህ ነገሮች አምታታው የሚመለከቱ ናቸው፡፡ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ናቸው፡፡ተቆርቋሪነትን በመግለጽ ብቻ የአደባባይ ውዳሴ ከማግበስበስ አልፈው የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ችግር በሁለንታዊ ለመረዳትም ሆነ ለመፍታት የማይችሎ ሆነው ቆይተዋል፡፡
በ”ይቅርታ አድርጉልን”እግረ ጉዞ ምሳሌነት ቁምነገሩን እንመልከተው፡፡በእኔ አስተያየት ቀኖናዊነት በጉደለው አግባብ እነዚህ ልጆች”ይቅርታ አድርጉልን”ማለታቸው የሌላ ጥልቅ በሽታ ምልክት እንጂ ራሱን የቻለ በሽታ እይደለም፡፡በቤተ ክህነቱ ሕይውት ያለው ተቋማዊ እና መንፈሳዊ ሚዛን ቢኖር ኖሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የተያዘን የሃይማኖት ጉዳይ አንዲት ዘማሪ በወኔ ተነስታ በይቅርታ ጠይቁ ለመዳኘት ባልተነሣች ነበር፡፡ልጆቹም ትናት በስብከታችው፣በመጸሐፋቸውና በመዝሙር ግጥማቸውና ዜማቸው ያጉደፉትን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ድግሞ በይቅርታ ሽፋን ዳግም ለማጉደፍና ጉዳዬን የጭቅጭቅ ጉዳይ ተደርጉ እንዲታይ ለማድረግ ባልደፈሩ ነበር፡፡ቢበዛ በአንድ የቅዱስ ሲኖዱስ ምልዐት ጉባኤ ውሳኔ ሊያበቃ የሚችልን ጉዳይ አንዲት ‹ዘማሪት› እስክትገባ መፍቀድ ትልቋን ቤተ ክርስቲያን አይመጥንም፡፡መቼ ይሆን ትልቋ ቤተ ክርስቲያናችን ከወይዛዝርት አተራማሾቿ ነጻ የምትሆነው ያስብላል፡፡
ከ”ይቅርታ አድርጉልን”ከሚለው ጥያቄ የበለጠው አሳሳቢ ሊሆን ይገባ የነበረው የቤተ ክህነቱን ሕይወት አልባ መዋቅር ታከውና በኢ ቀኖናዊ መንገድ ”ይቅርታ አድርጉልን”እና ”ይቅርታ አድርጉላቸው”ለማለት ያስቻሉትና ያነሳሱት መንፈሳዊ ፣ማኀበረ-ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውናም አስጊው ይኸው ነው፡፡
በርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ፣ማኀበራዊ/አገራዊ እና አስተዳደራዊ ሐላፊነቷን ሚዛኗን ሳትስት(ጠብቃ) እንድትጓዝ የሚያስችላት ተቋማዊ እና ሕሊናዊ ልጓም ከተሰባበረ ሰንብቷል፡፡አለ ከተባለም ያለው በቅዱሳት መጻሕፍት፣በቀናዒ ምዕመናን፣በእውነተኞቹ መናንያን እና በጥቂት አገልጋዩች ዘንድ ብቻ ነው፡፡ይህ ደግሞ ቤተ ክህነቱን ከተዘፈቀበት መንፈሳዊ እና ተቋማዊ ክስረት የማውጣት አቅምም ተልእኮም ሊሸከም የሚችል አካል አይደለም፡፡ይህ መሆኖ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አስተሳሰብ አድራሸ ፈረስ ናቸው ለሚባሉትና ”ይቅርታ አድርጉልን” ባዬች ተጋላጭነቱን አስፍቶታል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ለስሙ ቤተ ክህነት የሚባል ተቋማዊ ቅርጽ እንዳላት ከመነገሩ በቀር በሕጉና በሥርዐቱ የሚሠራ ነገር ባለመኖሩ ከሕግ አግባብ ውጪ”ይቅርታ አድርጉልን”እና ”ይቅርታ አድርጉላቸው” ተብላ መጠየቋ አያስገርምም፡፡እንደውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ሕይወት መሥራት ቀርቶ መተንፈስ ከማይችልበት ደረጃ ለመድረሱ ማሳያ ሆኑ ሊያገለግል ይችል ይሆናል፡፡ሥርዐቱ ሁሉንም ተቋማት የእርሱ ተራ ሎሌዎች እስኪሆኑ መቆጣጠር እንደሚፈልገው ሁሉ ቤተ ክህነቱን ወይ በቁም እንዲሞት ተደርጓል አለዚያም ለእንዲ ዐይነቶቹ አፈንጋጮች ከለላ በሚሆኑ ተላላኪዎች እንዲሞላ ተደርጓል፡፡
በዙዎቹን የእነዚህ ልጆች በዘማሪቷ ትከሻ ታዝለው ”ይቅርታ አድርጉልን”ማለታቸው ግራ አጋብቷል፡፡ግን ከዚህ የባሳ ስንት ነገር መፈጸሙን እያወቅን የ”ይቅርታ አድርጉልን”ጉዳይ እንደማሳያ ካልሆነ እንደ ቁልፍ ችግር ባይቀርብ በወደድኩ ነበር፡፡ልጆቹ እኮ ምስጢረ ሥላሴን” ሥላሴ አትበሉ” እያሉና ምስጢረ ሥጋዌን”…ክርሰቶስና ዲያብሎስ ቁማር ተጫወቱ…” እያሉ አላግጠው ነበር፡፡አሁን በያዙት መንገድ ከዚህ የከፋ ኑፋቄ ሊዘሩ እንደሚችሉ መጠበቅ የበለጠ ብልህነት ነው፡፡
ስለዚህ ”ይቅርታ አድርጉልን”ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ችግር አስመስሎ ማቅርብም ሆነ በዚሁ ላይ ጉልበትን መጨረስ ዒላማውን የሳተ ተኩስ ነው፡፡ከዚያ ይለቅ የኑፋቄውን መንገድ ለመረጡት ለእነዚህ ልጆችም ሆነ የእነዚሁ የኑፋቄ ሞግዚት ለሆነው ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኮር ኀይል ወደብ ሆኑ የሚያገለግለውን በቤተ ክህነቱ አመራረ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ለዘመናት የተጋገረውን የቀውስ ተራራ በድፍረት መመልከቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለአገሪቱ ይጠቅማል፡፡ራስን ከመዋሸትም ያድናል፡፡የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ችግር የመንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ድቀት ነው፡፡ይህ ካልተፈታ ግን ከቀኖና ቤተ ክርስተያን ውጭ በቀላጤ ደብዳቤ ውጉዛኑን እነ ጽጌ ስጦታውን በዐውደ ምህረታችን ልናይ እንችላለን፡፡
በርግጥ አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን ተብትበው ያሰሯትና‹ሊገድሏ›የሚተናነቋት ችግሮች የጊዜው የኑፋቄ አድራሽ ፈረስ የሆኑት ልጆች ወደ ዐውደ ምሕረቱ ከመምጣታቸው በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ከእነርሱም በኃላ ይቅጥል ይሆናል፡፡ነገር ግን እነርሱ የተጓዙባቸው የጥፋት መንገዶችና ሌሎች ከባቢያዊ ሆኔታዎች (ፖለቲካዊ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች) ችግሮቹን ለማመን በሚያስቸግር መጠንና ስፋት አባብሰዋቸዋል፡፡ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ቀንደኛ የቀውሱ አካል መሆናቸው የሚያከራክር ባይሆንም ብቸኛው ተጠያቂ ማድርግ ግን አይቻልም፡፡የይቅርታው ሒደት ኢ ቀኖናዊ ነው የሚለው ተገቢ ቢሆንም የመንፈሳዊ እና አሰተዳደራዊ ቀውሱን ተራራ እንደማይንደው ጥርጥር የለውም ፡፡ቀውሱ ከ”ይቅርታ አድርጉልን” ይጠልቃል፤ይረዝማል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ካለችበት ቀውስ አንጻር አሁን የሚያስፈልጋት ጥልቅ ራስን የምር የመፈተሸ ቁርጠኝነት ነው፡፡የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮዎች፣ትውፊትና ታሪክ የጠበቀና የሚጠብቅ የመንፈሳዊ እና ተቋማዊ ለውጥ አብዬት ሊያመጣ የሚችል ራስን የመፈተሸ ተጋድሎ ከሰሞነኛውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በእጅጉ ይጠበቃል ፡፡እርቅ የሚያስፈልገው ተጋድሎ እርሱ እንጂ ለስልት ”ይቅርታ አድርጉልን” ከሚለው የጥፋት ኀይል ጋር አይመስለኝም ፡፡ይህ የተዳፈነው የለውጥ አብዬት ከየት ይነሣል፣እነማን ያነሡታል፣እንዴትና እንደምን ተጀምሮ በምን ይጠቃለላል ይሆን የሚሎት ጥያቄዎች ቀላል መልስ የላቸውም፡፡
እንደ እኔ እስከዚያው ግን ቢያንስ ለቤተ ክህነቱ ድቀት ምስክር ይሆኑ ዘንድ የ”ይቅርታ አድርጉልን” ኀይል ባለበት ይቆይ፡፡እነዚህ ልጆች ይቅርታውን የጠየቁት ከሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ይዘውት የወጡት ጥቂት ስብስብ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መስመራዊነት ተመዝግቡ ለመንቀሳቀስ የሚያደርገው ተጨባጭ እንቅስቃሴ የ ”ይቅርታ አድርጉልን”ባዬቹን ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዘውጌነት ተጨባች ሰለሚያደርግ እና እንዳያገለግሎ ያደረጋቸውን ዕግድ በይቅርታ ለመፍታት ብቻ ነው፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ ከአካለዊ ዕገዳ እንጂ ከመንፈስ ዕገዳ አይላቀቁም፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ የልጆቹ ይቅርታ በቀጥታ ግለሰቦችን የሚመለከት ፣ግፋ ቢል ቤተ ክርስቲያኒቱን ከድቀት ሊታደጉ ከማይችሉ ኀይሎች ጋር የሚደረግ እርቅና ትእምርታዊ ትውስታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ካለው ለመረዳት ዝግጆ ነኝ፡፡ልጆቹ በዚህ በ”ይቅርታ አድርጉልን” ሒደት ውስጥ ሆነው እንኳን የሚያደርጓቸው ነገሮች ለይቅርታ የተገቡና የበቁ ናቸው ለማለት የሚያስችል አይደለም፡፡እውነተኛ ይቅረታ ለመስጠትም እንደዚያው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ይቅርታ አባባዩቹም ያሉበትን ሁኔታም መረዳት ይገባል፡፡በቅድሚያ ምንም ቢሆን ሙከራቸውን አልነቅፍም፤እንዲሳካላቸውም እመኛሉ፡፡ከዚያ ውጭ ግን እነርሱም ቢሆኑ ያለባቸው ሸክም ከባድ ነው፡፡የይቅርታ ምክንያት ለመሆን እውነተኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቢያስቸግር እንኳን ተደርጉ መቆጠርን ይጠይቃል፡፡ይህ ደግሞ በተግባር እንጂ ከአሜሪካ በመምጣት፣ልብስን በማሳመርና ጥቅስ በመጥቀስ የሚገኘ ጸጋ አይደለም፡፡
ከዚህ አንጻር ይቅር አባባዩቹ ሰለ ”ይቅርታ አድርጉልን”ባዬቹ በእውነትና ያለአድሎልዎ ሲናገሩ ተሰምተው አያውቁም፡፡ስለዚህ ከመንፈስና ከሞራል ልዕልና አኳያ ካየነው በእኛ በተራዎቹ ምዕመናን ዐይን እነርሱም ይቅርታን ለማምጣት ገና የበቁ ሆነው አይታዩም፡፡እንደዚህም ሆኑ ግን ይህ ሙከራቸው በራሱ ወደ ምንናፍቀው የቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አሐቲነት ደረጃ የሚሸጋገሩበት አጋጣሚ እንዲሆንላቸው እመኛለው፡፡
አጋጣሚዎቹ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተጥሏል/አልተጣሰም ውዝግብን ተከትሎ የተፈጠሩትን ቁስሎች እና መሰሎቻቸውን ማከም በተገባ ነበር ፡፡አሁንም መዋቅራዊ አሐቲነትን ለማምጣት እና መጥፎ ስሜቶችን ሊያስቀር የሚችል ኦርቶዶክሳዊ እርቅ በአባቶቻችን መካከል ማምጣት ያስፈልጋል፡፡አልረፈደም፡፡ድርጊቱ ግለሰባዊ መልክ ያለው ላይሆን ይችላል፡፡ነገር ግን በእርቅና በፍቅር መንፈስ ሊታከሙ የሚገባቸው ስሜቶች አሉ፡፡የቤት ሥራው የሁሉም ወገን ነው፡፡መንግስትንም ሆነ ተቀዋሚውንም ጭምር፡፡እርቅ ሕሊናና ልብ በአንድነት ቆርጠው ካልገቡበት እና እግረ ጉዞ ብቻ ከሆነ የማይደረስበት ልዕልና ነውና፡፡
ከዚህ አኳያም ሆነ አስቀድሚ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ለልጆቹ ይቅርታ መደረጉ የሚኖረው ፋይዳ ለመመዘን የሚያስቸግር መስሎ ይታያል፡፡በግሌ አጋጣሚው ሰለጉዳዩ እንድንነጋገር ከማድረግ አልፎ ቤተ ክርስቲያን ዐቀፍም ሆነ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ምክንያቱም ይቅርታው ዛሬ ባለው በቤተ ክርስቲያኒቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የሚያስከትለው ተጨባጭ ውጤት አይኖርም፡፡
ከዚህ በተረፈ እኔም ይቅርታ ቢደረግላቸው ችግር የለብኝም፡፡ከዚህ ባለፈ ግን ይቅር ተባዬቹ፣ይቅር አባባዬቹና ይቅር ባዬቹ በተመሳሳይ የመንፈስ ደረጃ ያሉ አይመስለኝም፡፡የይቅረታ ወሬውም ከሰብአዊ አዘኔታ ባሻገር የኦርቶዶክሳዊ የይቅርታ መሠረቶችን እና ፋይዳቸውን ገና አንስቶ አልጨረሰም፡፡እናም ለይቅርታ በተሻለ ደረጃ የተገቡ ያደርጋቸዋል የሚል ተስፋ የለኝም፡፡ከዚህ አኳያ ጉዳዩንም ሆነ ልጆቹን የቤተ ክህነቱ የተቋማዊ ለውጡ ድቀት ምስክሮች ወቅታዊ ስልት አድርገን ብንገነዘብ እላለሁ፡፡
ምንጭ፡- ዕንቁ መጽሔት
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ