ዓርብ 24 ጃንዋሪ 2014

ፓትርያርኩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሙስና ላይ እንዲዘምቱ አዘዙ


  • በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
  • ሰንበት ት/ቤቶቹ የአማሳኝ አስተዳዳሪዎችን ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፴፩፤ ቅዳሜ ጥር ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
His Holiness Patriartch Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተንሰራፋውና ለዕድገቷ መሰናክል ኾኖ በተደነቀረው ሙስናና ሸፍጥ ላይ በተጠናከረ ኃይል በመዝመት የተጀመረውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ከዳር እንዲያደርሱ አዘዙ፡፡
Dn Yonas Isayas of A.A.D SSD Unity reading the position paper
የአ/አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር ተወካይ ዲያቆን ዮናስ ኢሳይያስ ለፓትርያርኩ የፁረ ሙስና እንቅስቃሴ፣ ለአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ተግባራዊነት የሰንበት ት/ቤቶቹን የድጋፍ መግለጫ ሲያሰማ
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ቅዱስነትዎ በይፋ የገለጹትንና እንዲስተካከል አበክረው ማሳሰቢያ የሰጡበትን የቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማረም በሚደረገው ጥረት ኹሉ በግንባር ቀደምነት መሰለፍ የእኛም የወላጆቻችንም ጽኑ አቋም እንደኾነና በታዘዝንበት መሥመር ኹሉ ለመሰለፍ ዝግጁዎች መኾናችንን ለቅዱስነትዎ በላቀ አክብሮትና ትሕትና ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

አቡነ ማትያስ ትእዛዙን የሰጡት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በሥር ነቀል እርማት ለማስተካከል ያስተላለፉትን መግለጫ ለመደገፍና የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያዘጋጀው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ተግባራዊ እንዲኾን ለመጠየቅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለተሰበሰቡት በሺሕ ለሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰጡት መመሪያ፣ ቃለ ምዕዳንና የበዓለ ጥምቀት ቡራኬ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 160 ገዳማትና አድባራት የተሰበሰቡት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አማካይነት ባወጡት መግለጫ፣ ፓትርያርኩ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በማውገዝ ለማስተካከል አበክረው ሥራ በመጀመራቸው ምስጋናቸው አቅርበዋል፡፡ ብዙኃን የሰንበት ት/ቤት አባላት አይነኬ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያስተቻት የቆየውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር እስከ እስር ደርሰው ሲታገሉት እንደቆዩም ተናግረዋል፡፡
የሙስናና ብልሹ አስተዳደር ተጠቂ እየኾኑ በማደጋቸው አስከፊነቱን በሚገባ እንደሚያውቁ በመግለጫቸው ያተቱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ፣ ፓትርያርኩ በየጊዜው ያስተላለፏቸውን መመሪያዎች በመከታተልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትና በየክፍለ ከተማቸው በመወያየት ችግሩ ከመሠረቱ እንደሚወገድና በዘመናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ትንሣኤ እንደቀረበ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
ሙስናንና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የሚካሔደው እንቅስቃሴ በእነርሱም በወላጆቻቸውም ጽኑ እምነት እንደተያዘበት የጠቀሱት ወጣቶቹ፣ ጥረቱን ከግቡ ለማድረስ ከፓትርያርኩ ጎን ቆመው በታዘዙበት መሥመር ለመሰለፍ ዝግጁዎች መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
Sunday School Students of Holy Trinity Cathedral headind to Jan Meda,2004E.CTimket
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ወደ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ሲያመሩ
‹‹የፀረ ሙስና እንቅስቃሴውን እንደግፋለን ብላችኁኛል፤ እኔም እንደምትደግፉኝ አምናለኹ፤›› በማለት ተስፋቸውን የገለጹት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው÷ ‹‹ዘመኑ የእምነት ጉድለትና የኑፋቄ ነው፤ ሐቅ፣ መልካም አስተዳደር፣ እውነተኝነትና ሓላፊነት ጠፍቷል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል፤›› ሲሉ አምርረው ተናግረዋል፡፡ ስለ ሙስናና ብክነት ከሚሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ጋራ ተያይዞ ‹‹ኹላችንም ሌቦች ተብለናል›› የሚል ቅሬታ ያቀረቡላቸው ወገኖች መኖራቸውን ያልሸሸጉት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹የሚያመው ያመው ይኾናል፤ ኹላችኁም አማሳኞች ናችኹ የሚል አልወጣኝም፤ የሚያማስኑ እንዳሉ ግን ሐቅ ነው፤›› ሲሉ የችግሩ አስከፊነት ሊካድ እንደማይገባው አረጋግጠዋል፡፡
ሙስና ማለት ጥፋት ነው ሲሉ የቃሉን ትክክለኛ ንባብና ገላጭነት ያብራሩት ፓትርያርኩ፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ያለው የሙስና ሙስና›› መኾኑን በመግለጽ በፀረ ሙስና ቅስቀሳው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ በይበልጥ እንዲዘምቱበት አሳስበዋቸዋል፡- ‹‹ተይዞ ባለው የፀረ ሙስና ቅስቀሳ እናንት የሰንበት ት/ቤት አባላት በይበልጥ ብትዘምቱበት፤ በተጠናከረ ኃይል ይህን ብትረዱኝና ከዳር ብናደርሰው አመሰግናችኋለኹ፡፡››
በተያያዘ ዜና÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ የሚበዙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንደሚደግፉት እየተገለጸ ቢሰነብትም ‹‹ምእመናን በእኛ ሕግ ምን ያገባቸዋል፤›› የሚሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ቅሬታቸውን ለፓትርያርኩ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
እንደምንጮቹ መረጃ፣ ቅሬታ አቅራቢ አስተዳዳሪዎቹ የመዋቅር ለውጡን የሚቃወሙ ሲኾኑ ከእነርሱም መካከል ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጡ በተከታታይ የተካሔዱት የድጋፍ መግለጫ ስብሰባዎች ምእመናኑን በእነርሱ ላይ ኾነ ተብሎ ለማነሣሣት የታለሙ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ከፓትርያርኩ ጋራ ባካሔዱት ውይይት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በግልጽ በመቃወማቸውና በማጋለጣቸው ያሳሰሯቸውና ያስደበደቧቸው አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡
የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅም በማዋልና ለባዕድ አሳልፎ በመስጠት አላግባብ በልጽገዋል የሚሏቸውን አማሳኝ አስተዳዳሪዎች ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ፣ እንደ ሕጉ አግባብም ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማመልከትም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አባላት ተጠቁሟል፡፡
YeTimket Lijoch
ዉሉደ ጥምቀት
የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥቅምት ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ዕንከን ሳይኖርባት፣ ሞያ ሳያንሳትና ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት እንዳለበት የገለጸ ሲኾን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አፈጻጸም እሴቶችና መርሖዎች የሚገልጸው መሪ ዕቅድ ከገመገመ በኋላ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ በሚያስችል አኳኋን ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...