ሰኞ 27 ጃንዋሪ 2014

በዐረብ ፔኒዙኤላ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትታነጽ ነው


 click here for pdf

በመካከለኛው ምሥራቅ ከእሥራኤልና ቤይሩት ቀጥሎ ሦስተኛዋ፣ በዐረቢያ ፔኑዙኤላ ደግሞ የመጀመሪያዋ የምትሆነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በኳታር ምድር ልትታነጽ ነው፡፡ 
በኳታር ምድር የዛሬ አሥር ዓመት ለጸሎትና ለትምህርት መሰባሰብ በጀመሩ ወንድሞችና እኅቶች የተጀመረችው የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወደ አካባቢው ለሥራ የሚጓዙ ምእመናንን በማሰባሰብና በማገናኘት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና ክርስቲያናዊ ማኅበራዊ ኑሮን በማጠናከር የምትታወቅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ አገልግሎቷን የምትፈጽመው በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን በዓረቡ ዓለም እንደተለመደውም ዘወትር ዓርብ ከሰዓት በኋላ የቅዳሴና የትምህርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ምእመናን የሥራ ጫናውን ሁሉ ተቋቁመው ተግተው በማገልገል ብቻ ሳይሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅም የሚታወቁ ናቸው፡፡
በአብዛኞቹ የዓረበ ሀገሮች እንዳሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በኳታር ለነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ዋና ፈተና የነበረው የራስዋ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አለመኖር ነው፡፡ ይህም አገልግሎቷን በሳምንት ወደ ተወሰኑ ቀናትና ሰዓታት ከማሳነሡም በላይ፣ ምእመናን የሚፈልጓቸውን ሁሉን አገልግሎቶች ለመስጠት እንዳትችል አድርጓት ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያንዋ የራስዋ ሕንጻ መሥሪያ ቦታ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት በዐረቡ ዓለም የመጀመሪያ የምትሆነውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያስችል መሬት ተረክቧል፡፡ 
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየመን፣ በዓረብ ኤምሬትስ፣ በባሕሬን፣ በኩዌት፣ በሊባኖስና በግብጽ የራስዋ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሯትም በራስዋ ገንዘብ የተሠራና ንብረትነቷ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግን ከእሥራኤልና ቤይሩት በቀር አልነበራትም፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከተሠራ በመካከለኛው ምሥራቅ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን› ይሆናል፡፡
በኳታር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በአንድ በኩል የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ከሳምንት እስከ ሳምንት የማያቋርጥ እንዲሆን ሲያደርገው በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላሉት ሌሎች አጥቢያዎችም አርአያነት ይኖረዋል፡፡ ከኳታር በፊት እንቅስቃሴ የጀመሩት እንደ አቡዳቢ መድኃኔዓለም ያሉትን አጥቢያዎች የጀመሩትን በርትተው እንዲፈጽሙ ያነሣሣቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት ታሪክ በዐረቢያ ፔኒዙኤላ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ከ1400 ዓመታት በፊት በየመን ናግራን ታንጾ የነበረው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ እርሱ ከጠፋ ከ1600 ዓመታት በኋላ በዓረቢያ ፔኑዚኤላ ሁለተኛው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ ስም እንደገና በኳታር መታነጹ የታሪኩ ተገጣጣሚነት የሚያስደንቅ ነው፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ወደ አንድ ምዕራፍ የሚያሸጋግር፣ ሲሠልስም ለሌሎች አርአያነት ያለው በመሆኑ ሥራ በኳታር ለሚገኙ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ግብጻውያን እንደዚህ ባሉ አካባቢዎች የሚታነጹ የተለየ ታሪክና ጠቀሜታ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት በመተጋገዝ እንደሚገነቧቸው ሁሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እያንዳንዷን የሕንጻዋን ብሎኬት ተካፍለው በመገንባት በታሪክ ምዕራፍ ላይ አሻራቸውን ማስቀመጥና በረከት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
 በሀገር ቤት፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራልያ የሚገኙ ምእመናን በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ባይኖር ነድተውም ሆነ ተሳፍረው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ቤተ ክርስቲያን መገልገል ይችላሉ፡፤ በዐረቡ ዓለም ግን በአንድ አካባቢ አንድ አጥቢያ ብቻ ስለሚገኝ ወጣ ብሎ በሌላ አጥቢያ መገልገል አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኳታር ባሉ ሀገሮች ያለው ቤተ ክርስቲያን አንድ ነው፡፡ ይህን ቤተ ክርስቲያን ማነጽና አገልግሎቱን ማጠናከር፣ በዐረቡ ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን በመንፈሳ ሕይወታቸው በርትተው፣ ከመንፈስ ጭንቀት ተላቅቀው፣ የሚደርስባቸውን ፈተናም አሸንፈው ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም በመላው ዓለም የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚታነጸው የራሳቸው አጥቢያ መሆኑን አስታውሰው ልባቸው ኳታር ሊሆን ይገባል፡፡ 
 
የገባው ክርስቲያን እግዚአብሔር ሲሠራ አብሮ ይሠራል፡፡ 
         ዶሃ፣ ኳታር

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...