የደብረ ዘይት ተራራ የዛሬ ገጽታ |
ደብረ
ዘይት ማለት ቃሉ “ደብር” ሲል ተራራ ሲሆን “ዘይት” ሲል የወይራ ዛፍን ያመለከታል። ባጠቃላይ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ
(የዘይት ዛፍ) የበዛበት ተራራ ማለት ነው። ቦታው የሚገኘው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከጎለጎታ (ቀራንዮ) ተራራ በስተምስራቅ
በግምት ፪ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው። በሁለቱ ተራሮች መካከል ጌቴሴማኒ የሚባለው ለምለም ስፍራ ይኸውም
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመቃብር ስፍራ ይገኛል።
የደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ብዙ ጊዜ የሚያድርበት፣ የሚያስተምርበት፣ ውሎ የሚያርፍበት ሥፍራ ነው። ሉቃ ፳፩፥ ፴፯፣ ሉቃ ፳፪፥ ፴፱፣ ዮሐ ፰፥ ፩ ከዚሁ
ተራራ ላይ ነው ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው። ኋላም በዳግም ምጽአት እዚሁ ተራራ ላይ ነው ለፍርድ የሚመጣው። /ሐዋ
፩፥፲፫/።
በደብረ ዘይት ተራራ ወገብ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚታይ አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም የአይሁድ መቃብር ነው። ይህን ስፍራ
ለመቃብርነት የመረጡበት ምክንያት ወደፊት መሢሑ መጥቶ እስራኤልን ነፃ አውጥቶ ወደ አባቱ ያርጋልና ኋላ ለፍርድ ሲመጣ
በመጀመሪያ የሚፈርድበት ስፍራና ሙታንም የሚነሱበትና የሚሰበሰቡበት ስፍራ ይህ በመሆኑ እኛ መሢሐችንን ለማግኘትና ከሙታንም
ለመነሳት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን ብለው በማመናቸው ነው። አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መሢሕ እርሱ ነው ብለው
አያምኑም። መሢሕ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተቀባ ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ ደግሞ ክርስቶስ ማለት ነው። እግዚአብሔር ሕዝበ
እስራኤልን ለመጠበቅ ከመሃላቸው የሚመርጣቸውን ሰዎች በቅዱሳን ነቢያቱ አማካኝነት በተቀደሰ ዘይት (በቅብዓ ቅዱስ) እየቀባቸው
ካህናትንና ነገሥታትን ይሾምላቸው ስለነበር ሕዝቡም እግዚአብሔር ለቀባውና ለመረጠው እየታዘዙ ይኖሩ ነበር። በመሆኑም እስራኤል
ወደፊት አንድ ታላቅ መሢሕ እግዚአብሔር እንደሚልክላቸው ባላቸው ተስፋ መሠረት ገና አሁንም ድረስ መሢሐችንን እንጠብቃለን
ይላሉ። ይሁንና እግዚአብሔር እስራኤልን ብቻ ሳይሆን ዓለሙን ሁሉ እንዲያድን አንድ ልጁን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን ልኮልን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶልን በእርሱ ቁስል እኛ ተፈውሰናል፣ በእርሱ ሞት እኛ ሕይወትን
አግኝተናል። /ኢሳ. ፶፫፥፬-፮/። ከዚህ በኃላ ሌላ መሢሕ ሌላ አዳኝ ፈጽሞ የለም። አይሁድ በዚህ በትልቁ ነገር ላይ ወደኋላ
ቀርተው ተበድለዋል።
እንግዲህ
በቤተክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም እኩሌታ ደብረ ዘይት በመባል ተሰይሟል፤ ይኽውም በዚሁ ሰንበት ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ስለዓለም ጥፋትና ስለዳግም ምጽአቱ ምልክቱን
ነግሯቸዋል። ይኸውም /ማቴ. ፳፬፥ ፫-ፍ/ እንደተገለጸው፤
• ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ
• ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ
•
ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰማላችሁ
• ሕዝብ
በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ
•
በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል
• በዚያን
ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል፤ ስለ ስሜም በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
• በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ
• ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ
• በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ
• ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ
•
ከዐመፅም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች
• የጥፋት
ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ታያላችሁ
• በዚያን
ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል ካለ በኋላ እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል
በማለት ገልጾላቸዋል።
ክብር
ምስጋና ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ሁልጊዜም የምንድንበትን መንገድ ሳያሳውቀን
ቀርቶ አያውቅም። አሁንም ከላይ የተዘረዘሩትን የመሰናከያ አይነቶችና የመከራ ብዛቶችን ብቻ ጠቅሶ አላለፈም። ይልቁንም ጭንቅ
ሲመጣ ማቅለያውን፣ መከራ ሲገጥም መውጫውን፣ ፈተና ሲከብደን ማለፊያውን ጭምር አሳይቶናል፣ ነግሮናል። ይኸውም፦
«ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» /ማቴ. ፳፬፥፬/
አዎ
በየጊዜው ፍልስፍና የተጠናወታቸው፣ ኃይማኖት መኖሩን የሚያውቁ እንጂ ዕምነት የሌላቸው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን
«እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን የሚመስላቸው»። /፩ ጢሞ. ፮፥፭/ ሐሰተኛ መምህራንና ሐሰተኛ ነቢያቶች አሉ። አዎ
ጥሩ ምዕመን መስሎ መታየትን፣ ጥሩ ዘማሪ፣ ጥሩ ሰባኪ፣ ጥሩ ካህን፣ ጥሩ አባት፣ መልካም መሪ፣ መስሎ መታየትን እንጂ ፈጽሞ
ያልሆኑም አሉ።
ቅዱስ ጳውሎስ /በ፩ ቆሮ. ፯፥፳፫/ ላይ «የሰው ባሪያዎች አትሁኑ» እያለ ብዙዎች ግን የጥልና መለያየት ባሪያዎች፣ የክፋትና የኃጢአት እስረኞች ሆነው በተቀደሰው ሥፍራ በመቆም እነሆ የጥፋት ርኩሰቶችን፣ ቀኖና አፍራሾችን፣ ሥርዓት ገርሳሾችን፣ የጥፋት ኃይሎችን እያየናቸውና እየሰማናቸው እንገኛለንና እንግዲህ አንባቢ ያስተውል። ከእነዚህ በመራቅ እንዳይስት ይጠንቀቅ። ጌታችንም «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» ያለን ለዚህ ሲሆን እንዴት መጠንቀቅም እንዳለብን ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ኛ ተሰ. ፫፥፮ ላይ «ወንድሞች ሆይ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን» በማለት ግዝትም ትምህርትም አስተላልፎልናል። ይሁንና ሥርዓትም የሚያፈርሱ ግዝትም የሚጥሱ እያየን ነው። እንግዲህ ሥርዓት ሲል በጽሁፍ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰጠችንን፣ ወግ ሲል በትውፊት እየወረደ ዛሬ ድረስ የመጣልንን ሲሆን ሌላው ቀርቶ መልካሙ ኢትዮጵያዊ ባሕላችንንና ይሉኝታችንን ሁሉ ጠብቀን ብንይዘው መለያችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ቅዱስ ጳውሎስ /በ፩ ቆሮ. ፯፥፳፫/ ላይ «የሰው ባሪያዎች አትሁኑ» እያለ ብዙዎች ግን የጥልና መለያየት ባሪያዎች፣ የክፋትና የኃጢአት እስረኞች ሆነው በተቀደሰው ሥፍራ በመቆም እነሆ የጥፋት ርኩሰቶችን፣ ቀኖና አፍራሾችን፣ ሥርዓት ገርሳሾችን፣ የጥፋት ኃይሎችን እያየናቸውና እየሰማናቸው እንገኛለንና እንግዲህ አንባቢ ያስተውል። ከእነዚህ በመራቅ እንዳይስት ይጠንቀቅ። ጌታችንም «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» ያለን ለዚህ ሲሆን እንዴት መጠንቀቅም እንዳለብን ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ኛ ተሰ. ፫፥፮ ላይ «ወንድሞች ሆይ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን» በማለት ግዝትም ትምህርትም አስተላልፎልናል። ይሁንና ሥርዓትም የሚያፈርሱ ግዝትም የሚጥሱ እያየን ነው። እንግዲህ ሥርዓት ሲል በጽሁፍ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰጠችንን፣ ወግ ሲል በትውፊት እየወረደ ዛሬ ድረስ የመጣልንን ሲሆን ሌላው ቀርቶ መልካሙ ኢትዮጵያዊ ባሕላችንንና ይሉኝታችንን ሁሉ ጠብቀን ብንይዘው መለያችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ይህ ሊሆን ግድ ነውና
ተጠበቁ አትደንግጡ /ማቴ. ፳፬፥፮/
በአሁኑ
ወቅት በዓለማችን የተለያየ ክፍል እየተሰማና እየታየ ያለው የሰላም መጥፋት፣ የፍቅር መቀዝቀዝና የጦርነት ወሬ ነው። ሕዝብ
በሕዝብ ላይ ወንድም በወንድም ላይ፣ ወገን በወገኑ ላይ፣ ልጆች በልጆች፣ ወላጆች በልጆች፣ ባል በሚስቱ፣ ሚስትም በባል፣
መንግሥትም በመንግሥት ላይ ወዘተ ተነስቷል። ሌላው ቀርቶ ሰው ራሱን በራሱ ላይ የሚያነሳሳበት፣ የሚያምጽበት፣ የሚጣላበት ጊዜ
በመሆኑ እነሆ በዓመጻ ብዛት ፍቅር የቀዘቀዘበት፣ ቢወጡ ቢወርዱ በረከት የራቀበት፣ ባገኘ ቁጥር ሰው የሚጎድልበት ፣በሰበሰበ
ቁጥር የሚበተንበት፣ ቢበሉ የማይጠገብበት፣ ቢጠጡ የማይረካበት፣ ቢለብሱ ድምቀትና ሙቀት የማይገኝበት፣ ጤና ቢባል የጠፋበት፣
ሰላም ቢባል የታጣበት፣ እምነት ቢባል የማይገኝበት ዘመን ውስጥ አለን። ይሁንና ከዚህ ለመራቅና ለመጠበቅ እስከመጨረሻው የጸና
እርሱ ይድናል ነው የተባልነው።
“እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” /ማቴ. ፳፬፥፲፫/
እስከመጨረሻውስ
የምንጸናው በምንድን ነው? የመጀመሪያው በሃይማኖት ነው። ለዚሁም ቅዱስ ጳውሎሰ /በ፪ቆሮ. ፲፫፥፭/ ላይ «በሃይማኖት ብትኖሩ
ራሳችሁን መርምሩ» ብሎናል። በሃይማኖት መኖር ማለት ሃይማኖታችን የሚያዘንንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትነግረንን ንስሐ
በመግባት፣ ጾሙን በመጾም፣ ጸሎቱን በመጸለይ፣ ስግደቱን በመፈጸም፣ ምጽዋቱን፣ አስራቱን በማውጣት፣ ሥጋ ወደሙን በመቀበል እና
የዕለት ሕይወታችን የዕለት እንጀራችን አድርገን በትህትና በመታዘዝ በመልካም አርዓያነት እስከ መጨረሻው ብንፀና ከመዓቱና
ከመቅሰፍቱ እንድናለን ፡፡
ስለዚህ ሃይማኖታችንን መጠበቅ የራሳችንን ሕልውና መጠበቅ በመሆኑ /ዕብ.
፫-፲፬/ «የመጀመሪያ እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናል» ተብለናልና የመጀመሪያይቱን፣
የጥንቷን፣ ያልተበረዘችውን፣ ያልተከለሰችውን፣ በዘመን ብዛት ቄንጥና ጌጥ ያልወጣላትን የማይወጣላትን አባቶቻችንና እናቶቻችን
የተጠቀሙባትን ኢትዮጵያ ሃገራችን በዓለም የታወቀችባትን እጆቿን ዘርግታ ከፈጣሪዋ በመቀበል ከእግዚአብሔር መገናኛችን ቋንቋ ሆና
መግባቢያችን ዜማ ሆና መዝሙራችን መለያ ሆና ክብራችን ወኔ ሆና ብንርቅ የምንቀርብባት ዳር ድንበር
አስጠባቂያችን ብንጣላ የምንታረቅባት ብናጣ የምናገኝባት ብንደኸይ የምንከብርባት ብንታመም የምንድንባት ብንሞትም
በሕይወት የምንነሳባት የመጀመሪያይቱ የተዋሕዶ እምነታችን ናትና እስከመጨረሻው በእርሱ የጸና እርሱ ይድናል።
ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና /ማቴ. ፳፬፥፳፬/
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ ከሚመጡ ሐሰተኞች መምህራንና ሐሳዊ መሢሕ እንድንጠነቀቅና እንድንጠበቅ ያስተማረናል::
እነዚህ ሐሳውያን በተዓምራትና በፈውስ ስም ሰውን የሚያምታቱ “ጌታ እኛጋ እየተሰበከ ነውና ኑ በመንፈስ ተሞሉ ጌታ በዚህ አለ
ምድርን የሚከድኑ አገልጋዮች በኛ ዘንድ አሉ” በሚሉና የራሳቸውን የሥጋ ፈቃድና ፍላጎት የተመላ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆነ
ትምህርት የሚያስተምሩ ናቸው:: ኢሳ ፵፬፥ ፳፭ ሕዝ ፲፫፥፫ ኤር ፳፫፥፲፮
እውነተኞቹ
ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታን ሲከተሉ ሁሉን ትተን ተከተልንህ /ማር. ፲፩፥፳፮/ ቢሉት ኢየሱስም መልሶ እውነት እላችኋለሁ ስለ እኔና
ስለወንጌል ቤቱን፣ ወንድሞቹን፣ እህቶቹን፣ አባት እናቱን፣ ሚስት ልጆቹን፣ እርሻ ሀብቱን የተወ መቶ እጥፍ የማይቀበልና
በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም ብሎ ከምድራዊ ክብር ይልቅ የሚያገኙትን ሰማያዊ ጸጋ
ገልጾላቸዋል::
የዛሬዎቹ
ሐሳውያን መምህራን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማርንና የመዝሙር አገልግሎት መነገጃ መንገድ በሀብትና በዝና መክበሪያ መሰላል
ለማድረግ ሲሮጡ ይታያል:: ። የሐዋርያት ሕይወትና መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚያስተምረን ብርና ወርቅን ለመሰብሰብ ሳይሆን
እግዚአብሔርን በሚያከብር ሕይወት እንድንመላለስ ነው:: /ሐዋ. ፫፥፮/ ጌታም በቅዱስ ወንጌል “ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ነገር
ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ” ብሎናል ዮሐ ፮፥ ፳፯ ስለዚህ ሁላችን በማስተዋል እንድንጓዝና
በእምነታችን ጽኑ እንድንሆን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ባሕል እንዳንወጣ ባዕድ ሥርዓት ባዕድ የአነጋገር ዘይቤ የመዝሙር ዝማሬ
እንዳንቀላቅል የሰው ስሜት እየተከተልን እንዳንጎዳ ሳናውቀው በጥፋት ርኩሰት የድፍረትን ስሕተት በተቀደሰው ስፍራ ላይ
እንዳናሰለጥን ነው የሚያስጠነቅቀን ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!
በተለይ
ምእመናንን ለመጠበቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማክበር እግዚአብሔር ፤ አደራ የጣለብን የምድር ጨው የተባልን ካህናት
Ä
አልጫውን ዓለም ካላጣፈጥነው፣
Ä
የዓለሙ ብርሃን ተብለን ጨለማ ኃጢአትን በንስሐ ትምህርት ካላበራን፣
Ä
የእግዚአብሔር ዓይኖች ተብለን ሁሉን በእኩልና በርህራሄ
ካልተመለከትን፣
Ä
የቤተ ክርስቲያን መብራት ተብለን ሕጓ ሲጣስ ሥርዓቷ ሲፈርስ የጨለማ
ኃይል ሲከባት ከእንቅብ በታች እያበራን ጭራሽ የምናቃጥላት ከሆነ፣
Ä
የመላዕክት ምሳሌ እየተባልን እንደ ቅዱስ ገብርኤል «ንቁም በበሕላዌነ
እስከንረክብ ለአምላክነ» ብለን ባለንበት በጥንቷ በቀደመችው ሃይማኖታችን ጸንተን እንጠብቅ የማንል ከሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ /፩
ጴጥ. ፭፥፫/ ላይ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ ያለውን ቃል ለእርሱ የተሰጠችውን ክህነት ይዘን ቃሉን ግን የማንጠብቅ ከሆነ ለመሆኑ
ከኃያሉ ከእግዚአብሔር ክንድ የሚያድነን ማነው? «መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት!» ተብለናል።/ዘካ. ፲፩፥፲፯/።
ይልቁንስ
እኛ በኑሮም በቃልም በርትተን ቤተ ክርስቲያናችንን ብንጠብቃት ስለ አንድነቷ ጸንተን ብንቆምላት ሕጓን አስከብረን ሥርዓቷን
ብንፈጽምና ብናስፈጽምላት የምድራዊውን አስተሳሰብና የመናፍቃኑን ማዕበል በአንድነት ብንቋቋምላት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
“ያለሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጿቸው” /፩ ተሰ. ፭፥፲፬/ እንዳለ ይህን በተግባር በየቦታው ብንፈጽምላት በዚህ የተነሳ መከራ
ቢመጣ መቀበላችን ተቃውሞ ሲነሳ መቋቋማችን የሚገባን ክብራችን ይሆናል። ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ /በፊሊ.፩፥፳፰/ ላይ «በአንድም
ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ ይህም ለነርሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው ይህም ከእግዚአብሔር ነው ይህ
ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለእርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም» በማለት እንኳንስ ለኛ
ለካህናቱ ምእመናንም እንኳ በዚህ በረከት እንዲጠቀሙ ገልጿል።
ስለዚህ
ሁላችንም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ስለተዋሕዶ ሃይማኖታችን፣ ስለወገናችን፣ ስለውዲቷ ሃገር ኢትዮጵያችን፣ ስለመልካሙ ኢትዮጵያዊ
ባሕላችን ጭምር መጨነቅ፣ መጠበብ፣ መጸለይ፣ መበርታት ይጠበቅብናል ግዴታችንም ነው። ይህን በማስከበር ሂደት ውስጥ ምንም
ዓይነት ፈተና ቢገጥመን ተዋጊው እግዚአብሔር ይሆናል። ዓለም አብሮ ተነባብሮ ቢገፋንም አንጨነቅም፣ ብናመነታም ተስፋ አንቆርም፣
ብንሰደድም አንጣልም፣ ብንወድቅም አንጠፋም። /፪ ቆሮ. ፬፥፱-፲/ ምክንያቱም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ጌታችን ስለዓለም
ምጽአት ከተናገረው የመከራ ምልክት ሁሉ መዳኛ መንገዱ «እስከመጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናልና» /ማቴ. ፳፬፥፲፫/
ብሎናል።
በአጠቃላይ
የደብረ ዘይት በዓል የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት የምናስብበት፣ የመምጫው ምልክት የሆኑትን ነገሮች
እየመረመርን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት የምናዘጋጅበትና ከዘላለም ፍርድ ኩነኔ ለመዳን እንደ ቃሉ መመላለስ እንዳለብን
የምናስብበት ነው። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁም ተብለናልና ሁልጊዜ ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንደቃሉ ለመኖር እስከመጨረሻው ጸንተን
ለመዳን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበ አዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት፡፡
ትርጉም:- ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ተዘጋጅታችሁም ኑሩ፤ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ።ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላቸው፡፡ጌታችንም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ በመለከት ድምፅ ከአእላፍ መላእክት ጋር በግርማ መለኮቱ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርደል፡፡ በዚች ዕለትም ከሞተ ኃጢአት አብ ይማረን የሕይወት ባለቤት የሰንበትም ጌታ ነውና፡፡
ምንባባት መልዕክታት
(1ኛተሰ.4÷13-ፍጻ.) ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡
.......
(2ኛ ጴጥ.3÷7-14) አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡
ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ. 24÷1-21) በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፡፡ ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ÷ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስተመሰገን አግኝተናታል፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ምስባክ
መዝ. 49÷2 እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፡፡ ወአምላክነሂ ኢያረምም፡፡ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
ትርጉም፦ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡ አምላካችንም ዝም እይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡
ወንጌል
(ማቴ.
24÷1-25) ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡” (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ: - ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
በአጠቃላይ የደብረ ዘይት በዓል የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት የምናስብበት፣ የመምጫው ምልክት የሆኑትን ነገሮች እየመረመርን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት የምናዘጋጅበትና ከዘላለም ፍርድ ኩነኔ ለመዳን እንደ ቃሉ መመላለስ እንዳለብን የምናስብበት ነው። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁም ተብለናልና ሁልጊዜ ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንደቃሉ ለመኖር እስከመጨረሻው ጸንተን ለመዳን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ