የምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ትላንት መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ምሽት 2፡00 ገደማ ዐርፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው የስኳር ሕመምተኛ እንደነበሩና እስካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ድረስ በቡሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክሊኒክ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ እንደቆዩ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የደም ማጣራት(ዲያሊስስ) ሲደረግላቸው የሰነበቱ ቢኾንም ጤናቸው መሻሻል ባለማሳየቱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከሆስፒታሉ በአምቡላንስ ወጥተው በኦክስጂን እየተረዱ ወደ ሀ/ስብከታቸው ከተመለሱ በኋላ ትላንት ምሽት 2፡00 ላይ ማረፋቸው ታውቋል፡፡
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፲፱፻፸፭ ዓ.ም. ከተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ የነበሩት ብፁዕነታቸው አኹን ካረፉበት ከምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀ/ስብከት አስቀድሞ በሊቀ ጵጵስና ከመሯቸው አህጉረ ስብከት መካከል የድሬዳዋ እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ አህጉረ ስብከት ይገኙበታል፡፡
በፊት ስማቸው መልአከ ሣህል መዘምር ተገኝ የሚባሉትና በመጻሕፍት ትርጓሜና በቅዳሴ መምህርነታቸው የሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ የቅድስት ሥላሴ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በዲንነት፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምንና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳማትን በበላይ ሓላፊነት አስተዳድረዋል፡፡
ትምህርተ ሃይማኖትን የሚከበውን ቃለ ስብከታቸውንም ‹‹ፍኖተ እግዚአብሔር›› በሚል ርእስ በመጽሐፍ አሳትመዋል፤ በሀ/ስብከታቸውም በቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት በተለይም የመጽሐፍ ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ ሊቃውንትን አግኝቶ ደቀ መዛሙርት አብዝቶ እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በብዙ ደክመዋል፡፡
የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ፣ መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በዚያው በፍኖተ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት እንደሚከናወን ተገልጧል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡
ኦ አባ ንበር በማዕከሌነ
በወርኃ መጋቢት በአዝመራው ወቅት ተጠራ
ለዘመናት ወንጌል ዘርቶ የብዙኃንን ልብ ያበራ
እውነትም ብፁዕ ቶማስ ትጉህ የፍቅር አርበኛ
የመተሳስብ የሰላም የአንድነት አባት ዳኛ
የቀለም ራስ መምህር የመጻሕፍት ቌት ጠንቃቂ
ጎባጣውን የሚያቀና የተጣመመውን ሐራቂ
እንደሰው መጠን ቢፈጠር አዳማዊ ቢኾን ፍጥረቱ
ፍጹም አስደንጋጭ ኾነብን አራደን የቶማስ ሞቱ
ዲያቆን ዘፍጽምና ካህን መናኝ መነኩሴ
መምህር ወጳጳስ ኀሩይ በኀበ ሥላሴ
የቅዳሴው አበጋዝ መራሒ ወንጌል አንደበቱ
እንደምን ድካም ያዛቸው እንደምንስ ተረቱ
የተዋሕዶን ክብር ዝና በዓለም መደረክ ያገዘፈ
በመክሊቱ የሠራበት እልፍ አእላፋትን ያተረፈ
ንዋየ ኀሩይ ቶማስ የታላቅነት ማሳያ
ብርሃን ለምግባር ሠናይ የመልካምነት ገበያ
በመንፈሳዊ ጥበብ የጠለቀ በያሬዳዊ ዜማ የናኝ
እምነትና ፍልስፍናን በዕውቀት ቀንበር ያቆራኘ
ኦ አባ ትጉህ ለጸሎት ኃያል ጽኑ ለተጋድሎ
ያስመሰከረ ማንነቱን በጉባኤ ቤት አውድማ ውሎ
እጨጌ ለመንበረ ፍኖተ ሰላም አቡነ
ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም በታቦተ ጽዮን እምነ
ሥዩመ እግዚአብሔር ወሰብ የፍኖተ ሰላም መሪ
እንደ ፀሐይ ደማቅ እንደ ኮኮብም አብሪ
መዋቲ ሥጋ የለበሰ ሞት ዕጣው ቢኾንም ቅሉ
የአባት ሞት ግን መሪር ነው የማይታመን ለኹሉ
በወርኃ ፍጹም ሱባኤ መጋቢት ሐተታ
እምድኽ ፈለሰ ቶማስ ወደ ላይኛው ቦታ
መከራው ይበልጥ በረታ የሐዘን እንባ ዘነበ
አቡነ መምህር ቶማስ ውስተ መቃብር ሰከበ
ጆሯችንን ጭው ያደረገ ፍጹም ለማመን የከበደ
አባ ሞትኽን ሰማን ልባችን በሐዘን ራደ
እግዚአብሔር ያጽናሽ ቤተ ክርስቲያን
ቅኔ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋስዕት ምዕራፉን
ጠንቅቆ ያወቀ ዝማሬ ድጓውን
የአበውን ትውፊት በደንብ የቀሰመ ልጅሽን ሞት የነጠቀሽ
ሌት እና ቀን ለመምሰል ሳይኾን በመኾን ያቆመሽ
ስምኽ ከመቃብር በላይ ያበራል ጸንቶ እንደፋና
የወንጌል አርበኛው ቶማስ የሔድክ በጽድቅ ጎዳና
የወንጌል ብርሃን ባልበራበት ከአጽናፍ አጽናፍ ዞሮ
ምንኩስና ጵጵስናን በሕይወቱ በእውነት ኖሮ
ነዳያንን በፍቅር ስቦ ምስኪናን በችሮታ
ሰብስቦ ያኖረው ክንድኽ ዛሬስ እንደምን ተረታ
ጸዐዳው የሕይወት መምህር የቀለም ገበሬ
የኹለት ዓለሙን ምሁር ሞት እጁን ያዘው ዛሬ
የአብርሃም እቅፍ ለአንተ የገነት በር ይከፈት
በገድል ትጋት የኖረችው ነፍስም ታግኝ ዕረፍት
ተዋናይ በመንፈስ አባ ንበር በማዕከሌነ
ሳህል ወጸልይ ምሕረት ሀበ ማርያም እምነ
ሊቀ ጳጳሳት ዘሀገረ አባ ኢትዮጵያ
ከአትሮንሱ ላይ ተነሣ ታጠፈ የዕውቀት ገበያ
በትረ ሙሴ ይዞ ሕዝቡን በጥበብ የመራ
ይኽው ወር ተራ ደርሶት እርሱም በመጋቢት ተጠራ
ሕይወታቸው ያለው አይታበልምና ቃሉ
ብፁዕ አቡነ ቶማስ ያክብርህ ከሃሌ ኵሉ፡፡
ከመምህር ሳሙኤል አያልነህ
መታሰቢያነቱ መጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም.
በመሞት ለተለዩን ለብፅዕ አቡነ ቶማስ ሊቀ ጳጳስ
About these ads
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ