ማክሰኞ 1 ጁላይ 2014

=>+"+ እንኩዋን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+



Dn Yordanos Abebe

=>ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ): ሐጋይ (በጋ): ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

+በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ብሎናልና (ማቴ. 24:20) ልንጸልይ ይገባናል:: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ: አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ:-



"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)

=>ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን:: ተረፈ ዘመኑንም የንስሃ: የፍሬና የበረከት ያድርግልን::

=>በዚሕች ዕለት እነዚህ ቅዱሳን ይከበራሉ:-

+" ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ "+

+በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር:: እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች:: አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር::
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከ72ቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል:: ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል:: (ዮሐ. 14:22)

+ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር 3 ዓመት ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል:: አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል:: አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው:: ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል::

+" ቅዱሳን ዺላጦስና አብሮቅላ "+

=>ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን:: የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል:: የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም::

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል:: ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል:: በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል::

+ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው:: ጌታችንን ተከትላ: ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ: ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች:: ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ::

=>ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ: ከዺላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን::

=>ሰኔ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ሰማዕቱ ዺላጦስ መስፍን
3.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
4.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት
5.የጸደይ መውጫ / የክረምትመግቢያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ /አባ ቡላ/
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

=>+"+ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:1)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...