እሑድ 3 ኦገስት 2014

አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት


አቡነ ዼጥሮስ ምንም እንኩዋ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ ትልቅ ቢሆንም ትውልዱም: መንግስቱም: ራሷ ቤተክርስቲያናችንም ተገቢውን ክብር ሰጥተው እያሰቧቸው አይደለም
ታሪካቸውም ባጭሩ........................
በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩ ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አሔዱ።
ከዚህ በኋላ ልክ በ1900 ዓ.ም. እዚያው ወሎ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ።
በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ከጐሰሙ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተ መቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።
በ1910 ዓ.ም. መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በ1919 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።
የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ አገረ ስብከት ተሾሙ።
ሐምሌ 22 ቀን 1928 ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው።
« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰማዕትነት አለፉ፡፡
"ብፁዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለእርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣልያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ይታይ ነበር።"
የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ እና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደ ሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤ አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡
ለሀገራቸውና ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡ «ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡» /መርሻ አለኸኝ /ዲያቆን/፣ 1986 ዓ.ም፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ ገጽ.80/
ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው «ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ)» ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው በሰማዕትነት አለፉ፡፡ / መርሻ አለኸኝ/ዲያቆን/፣ 1996ዓ.ም፣ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣ገጽ.77/
ፋሺስት ጣሊያን የእርሱ አቋም የራሳቸው አቋም፤ የእርሱ የጭቆና አገዛዝ የእርሳቸው አገዛዝ፣ የእርሱ ተራ ፕሮፓጋንዳ የእርሳቸው እውነት አድርገው እንዲቀበሉ መደለያ /ገንዘብ፣ መኪና በዘመኑ ዘመናዊ የሚባል ቤት/ ልስጦት ሳይላቸው ቀርቶ ነውን) ለሕዝባቸው፣ ለሀገራቸውና ለቤተክርስቲያናቸው ሰማዕት የሆኑት) እርሳቸው ግን መንኖ ጥሪትን ገንዘብ ያደረጉ አባት በመሆናቸው ሌሎቹ የቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ለፋሺስት ጣሊያን ሲያድሩ መደለያው ሳያንበረክካቸው በመንፈሳዊ ወኔ ሰማዕት ሆነዋል፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ሰማዕቱን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ፣ ቀብራቸው በምስጢር መፈጸሙ መዛግብት እንደሚያስረዱ እና የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምስጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምስጢር ቀበሯቸው” ከሚል ጠቅላላ ፍንጭ ያለፈ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቆይቶ ነበር ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ “ለቡ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው “ሙኒሳ ጉብታ” ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ በእርግጠኝነት አስረድተዋቸዋል፡፡
በዚህም በፋሺስት ኢጣሊያ ከ76 ዓመት በፊት ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ የተቀበሩበት ቦታ በአዲስ አበባ በስተደቡብ በለቡ አካባቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አረጋግጣለች፡፡
« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. . . እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰማዕትነት አለፉ፡፡
ከሰማዕቱ በረከት ረድኤት ምልጃ አምላክ ያሳትፈን::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ::

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...