- ከ1300 በላይ አዲስ አማንያን በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተጠመቁ
- በዓመቱ 17‚000 አዲስ አማኞችን ለማፍራት በመርሐ ግብር የተያዘው ዕቅድ አካል ነው
- ከተጠማቂዎቹ፣ ከባዕድ አምልኮ የተመለሱ አርብቶ አደሮች እንደሚገኙበት ተመልክቷል
* * *
በዲዛይን ሥራው የማኅበረ ቅዱሳን ሞያዊ አስተዋፅኦ ከተገለጸበት አዲሱ የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት (ምረቃ) ጋራ ጥምቀተ ክርስትና የተፈጸመላቸውና ከሰባት የስብከት ኬላዎች የተውጣጡት 1350 ምእመናን ጂንካ የደረሱት ከየስብከት ኬላዎቻቸው (ሼፒ ጋኢላ፣ አልጋ ኪለት፣ ዛቢ፣ ጉርጨት፣ ሰንሰለት፣ አይዳ እና ጋራ) ለሰዓታት በእግራቸው ተጉዘው ነው፡፡የሀገረ ስብከቱን ነባር አብያተ ክርስቲያን በመደገፍና አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማነፅ ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰው የደቡብ ኦሞ የስብከተ ወንጌል፣ የልማት እና ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ለጥምቀተ ክርስትናው መከናወን የገንዘብና ከፍተኛ የቁሳቁስ እገዛ አድርጓል፡፡
ኮሚቴው በጂንካ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በ45 ሚልዮን ብር ወጪ ለሚያሠራው የአብነት ት/ቤት ግንባታ እና ለሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ፓትርያርኩ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠዋል፡፡
* * *
በጠረፋማ የአገራችን አካባቢዎች አተኩሮ በሚካሔደውና ከ፳፻፫ – ፳፻፲፩ ዓ.ም. የተዘረጋው የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተጨመሩት አዲስ አማኞች ጠቅላላ ቁጥር ከ26 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገልጧል፡፡በ፳፻፭ ዓ.ም. የአገልግሎት ዓመት መርሐ ግብሩ በሸፈናቸው የጉምዝ፣ ካፋ(ጫራ) እና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች በተከናውነው ጥምቀት ክርስትና 8,744 አዲስ አማኞች የቅድስት ሥላሴ ልጅነት እንዲያገኙ የተደረገ ሲኾን በተያዘው የ፳፻፯ ዓ.ም. የአገልግሎት ዓመት በአምስት ቦታዎች 17‚000 አዲስ አማንያንን ለማፍራትና የተጨመሩትን ምእመናን ለማጽናት ከብር አምስት ሚልዮን በላይ በጀት በመርሐ ግብሩ ተይዟል፡፡
ሀብተ ውልድና ጥምቀተ ክርስትና አግኝተው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱትን ምእመናን የሚያጸኑ የትግበራ ዕቅዶች ከአህጉረ ስብከት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንና ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ በመቀናጀት ይፈጸማሉ፡፡
ተጠማቅያኑ የሚገለገሉበት ቤተ ክርስቲያን መትከል፣ በቋንቋቸው የሚያስተምሯቸውን ሰባክያንና ካህናት ማሠልጠን፣ በቋንቋቸው የሚማሩባቸውን ጉባኤያት እና ሐዋርያዊ ጉዞዎች ማካሔድ፣ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን (የትምህርት መጻሕፍትንና በራሪ ጽሑፎችን፣ የስብከት እና የመዝሙር ካሴቶችንና ሲዲዎችን) ማዘጋጀትና ማሰራጨት ተጠቃሽ የመተግበርያ ስልቶች ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ባልተተከለባቸው የገጠር ቀበሌዎች የሚቋቋሙት የስብከት ኬላዎች÷ በቅድመ ጥምቀት የተጠማቂ ምእመናን ቅስቀሳና ሥልጠና፤ በጊዜ ጥምቀት የተጠማቂ ምእመናን ዝግጅት እና በድኅረ ጥምቀት ተጠማቂ ምእመናንን በተከታታይ ትምህርትና የአብነት ትምህርት የማጽናት አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ የስብከት ኬላዎች/ምዕራፈ ስብከት/ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያስፈልጓቸው የትግበራ ቁሳቁሶች በማስፋፊያ መርሐ ግብሩ ወጪ የሚሸፈን ሲኾን አዲስ ምእመናን እንዲጨመሩና የተጨመሩትም እንዲጸኑ በየቋንቋው የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልም የገንዘብ ድጎማ ይደረግላቸዋል፡፡አዲስ አማኞችን በማጥመቅ፣ ያሉትን በማጽናትና የካዱትን በመመለስ ላይ ባተኮረው የማስፋፊያ መርሐ ግብሩ÷ የምእመናንን ቁጥር ጨምሯል፤ በቋንቋ የሚያገለግሉና ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑ ካህናትን ለማፍራትና የሰባክያንን ቁጥር ለማሳደግ ተችሏል፤ የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት ተጠናክሯል፡፡ በቋንቋ የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርት እጥረት፣ የገንዘብ አቅም ማነስና በቂ መጓጓዣ አለመኖር የፕሮግራሙ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡
* * *
ይህ ያለእግዚአብሔር ርዳታ ከፍጻሜ አይደርስም፡፡ በክንዳችን ውስጥ የእግዚአብሔር ክንድ ስላለ በኻያ ዓመት የማያልቀውን ይህን ሕንፃ በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ የረዳን እግዚአብሔር ነው፡፡
ሌላም ብሥራት አለ! የሚገርመው ነገር፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በሚመረቅበት በዚኽ ዕለት 1350 ሕንፃ ሥላሴ በዛሬው ዕለት ተጠምቀው የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ኾነዋል፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ ሕንፃ ሥላሴን ሊባርኩ፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ሊመርቁ የመጡት ቅዱስ አባታችን ከዚኽ የበለጠ ደስታ የላቸውምና እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡
እንደምታውቁት ስብከተ ወንጌሉን በዞኑ[በሀገረ ስብከቱ] ኹሉ ለማዳረስ ሀገረ ስብከታችን አቅም የለውም፤ ነገር ግን የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል ከብፁዕነታቸው[አቡነ ኤልያስ] መመሪያ በመቀበልና ከሀገረ ስብከቱ ጋራ በመተባበር ከ፳፻፬ – ፳፻፯ ዓ.ም. 16‚630 ሰዎች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተጠምቀዋል፡፡ ደስ ይበላችኹ! በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከ፳፻፬ – ፳፻፯ ዓ.ም. የዛሬውን ጨምሮ 16‚630 ሰዎች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጨምረዋል፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡
/የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ/
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ/
በዛሬው ዕለት ሀብተ ውልድና ጥምቀተ ክርስትና የተቀበላችኹ ወገኖች ኹሉ፣ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ትብብር ስላለ ነው ለዚኽ ውጤት የበቃችኹት፡፡ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ደስታዋ የተፈጸመበት ቀን ነው፡፡ ይኸውም አንደኛ፡- ገንዘባችኹን፣ ዕውቀታችኹን፣ ጊዜአችኹንና ጉልበታችኹን መሥዋዕት አድርጋችኹ ግሩም ድንቅ የኾነ ቤተ ክርስቲያን በመሥራታችኹ ደስ ብሎናል፤ ደስ ሊላችኹ ይገባል፡፡ ከዚኽ በላይ ደግሞ 1350 አዲስ ክርስቲያኖች ተጨምረዋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ እንዲኹ እያለ ያድጋል ማለት ነው፡፡ በእውነቱ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ እናንተን ይዘው ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ትጉህ አባት፣ ትጉህ ሐዋርያ ናቸው፤ በእናንተ ፊት ላመሰግናቸው እወዳለኹ፡፡
ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋራ የሚገናኙበት ቤተ ክርስቲያን አምሮ ሠምሮ በመሠራቱ አዲስ ምእመናን መጨመራቸው ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሰባክያን፣ መምህራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሕዝቡን ጠንክራችኹ ማስተማርና ወደ ክርስቶስ ጉባኤ እንዲጨመሩ ማድረግ አለባችኹ፡፡ ትልቁ ሥራችኹ ስብከተ ወንጌል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ሥራዋ ስብከተ ወንጌል ስለኾነ በስብከተ ወንጌል ኹላችን መጠንከር አለብን፡፡ ሕዝብን ኹሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት የመሳብ፣ የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ዜጎች እንዲኾኑ የማድረግ ሓላፊነት አለብን፡፡ ሃይማኖታችኹ ጸንቶ ምግባራችኹ ቀንቶ ስናይ ለእኛ ሕይወት መድኃኒት ነው፤ በየጊዜው እንዲጨመሩ ማድረግም ሓላፊነታችን ነው፡፡
የሠራችኹት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለእናንተ ብቻ ሳይኾን ለልጅ ልጆቻችኹ የሚተላለፍ ሥራ ስለኾነ እንኳን ደስ አላችኹ፡፡ ከዚኽ በኋላ ሐሳባችኹ ትምህርት ቤት ወደ መሥራት መኾን አለበት፡፡ ልጆቻችኹ ቋንቋቸውን አጥንተው የጸናችውንና የቀናችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምልኮቷን፣ ሥርዐቷን፣ ቀኖናዋን፣ ምስጢሯን እንዲጠይቁና እንዲያውቁ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡
/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከስድስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ተገኝተው የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤትና የ1350 ምእመናን ጥምቀተ ክርስትና በተፈጸመበት ወቅት ከተናገሩት/
About these ads
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ