እሑድ 23 ኖቬምበር 2014

.ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ሦስት ገዳማት የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ


•ለፕሮጅክቶቹ ማስፈጸሚያ ከ3 ሚሊዮን 180 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡
ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.


በእንዳለ ደምስስ
gundagundi 02ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡


በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት እነዚህ ፕሮጅክቶች ከኅዳር 3/2007 ዓ.ም. - ኅዳር 8/2007 ዓ.ም. ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለየገዳማቱ አስረክቧል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ፅብላ ወረዳ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም በ630 ሺሕ ብር የተሠራ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ 150 ሺሕ ሊትር መያዝ ይችላል፡፡ ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በገዳሙ ውስጥ ተገንብቶ በመጠናቀቁ ማኅበረ መነኮሳቱ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በቀን ከ4-5 ሰዓት በመጓዝ የሚባክንባቸውን የአገልግሎትና የጸሎት ጊዜያቸውን እንደሚያስቀርላቸው የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡

abune tomas zehayda 02 1ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ገዳሙ ጥንታዊና ገዳማዊ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ የሚገኝበት ሲሆን፤ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

gundagundi 03በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡

ሕንፃው በ416.49 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ማኅበሩ የሠራው የምድሩን ወለል ብቻ ነው፡፡ መሠረቱ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃን መሸከም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ገዳሙ ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ይገነባል፡፡

ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ቀድሞ በርካታ መነኮሳት የነበሩባት ቢሆንም በደርግ መንግሥት የነበራት ሰፊ ይዞታ በመነጠቋ የመነኮሳቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በችግር ምክንያት እየተመናመነ ሄዶ ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ እነሱም በገዳሟ ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ገዳማት የማይገኙ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ለማን ጥለን እንሔዳለን በማለት ችግሩን ተቋቁመው ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡

ወደ ገዳሟ ለመድረስ መንገዱ አስቸጋሪና መኪና የማይገባ በመሆኑ የአንድ ቀን ሙሉ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ለመመለስም እንዲሁ የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ገዳሟ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሲሆን፤ የሁለገብ ሕንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመነኮሳቱ ቁጥር ከሁለት ወደ ሰባት ከፍ ለማለት ችሏል፡፡

dibo 02በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡

የሽመና ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው በገዳሟ ውስጥ ለሚገኙት መነኮሳይያት ሲሆን፤ መነኮሳይያቱ ቁጥራቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የሽመና ውጤቶችን ማምረት ያስችላቸዋል፡፡

ደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ ከሚባሉ ገዳማት መካከል የምትመደብ ስትሆን በውስጧም ጥንታዊ ሥዕላትን ጠብቃ ለትውልድ በማቆየት ትታወቃለች፡፡ ለትኅርምት እና ለጽሞና የምትመረጥም ገዳም ናት፡፡

ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍሉ አማካይነት ለበርካታ ገዳማትና አድባራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ገዳማት የልማት ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...