(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኞ ኅዳር 15
ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ
ወዳጆች! እንዴት ዋላችኁ? እንዴት አረፈዳችኁ? እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላምና በጤና አደረሳችኁ፡፡ ዛሬም አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ እጅግ ጣፋጭ የኾነ ስብከቱን ቀጥሏል፡፡ የዛሬውን ስብከት የተረጐምንላችኁ የኦሪት ዘፍጥረትን እየተረጐመ ባስተማረው የአራተኛው
ቀን ስብከቱ ነው፡፡ ምእመናኑ ወደ ጉባኤው መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በየቀኑ ያስቀድሳሉ፤ በየቀኑ ይቈርባሉ፡፡ ቅዳሴውን ካስቀደሱና
ከቅዱስ ቁርባኑ ከተሳተፉ በኋላም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚያስተምራቸው ትምህርት ነፍሳቸውን መግበው ይሔዳሉ፡፡ ይኽን በየቀኑ
እያየ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጣም ይደሰታል፡፡ የምእመናኑ ትጋት እያየ ርሱም ማስተማሩን ቀጥሏል፡፡ በተለይ በሦስተኛው
ቀን ዶፍ ዝናብ እየዘነበባቸው እንኳን ምእመናኑ አለመበተናቸውን አይቶ ቅዱሱን እጅግ በጣም አስደስቶታል፡፡ በመኾኑም በዛሬው ስብከቱ
ይኽን የምእመናኑን ትጋት አይቶ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ምንም እንኳን ከዛሬ 1600 ዓመታት የተሰበከ ስብከት ቢኾንም ዛሬም
አዲስ ነው፤ አይጠገብም፤ ነፍስን ይመልሳል፡፡ እስኪ እኔ ነገር ከማስረዝምባችኁ ከራሱ ከሊቁ አብረን እንማር፡፡ የነቢያትን፣ የሐዋርያትን፣
የሊቃውንትን ጉባኤ የባረከ አምላክ የእኛንም ይባርክልን፡፡ በያለንበት ኾነንም ቃሉን እንድንማር ልቡናችንን ይክፈትልን፡፡ አሜን!!!
እጅግ የምወዳችኁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችኁ
በየቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣታችኁ እያየኹ ነፍሴ ደስ ተሰኘች፤ ዕለት ዕለትም አምላኬን ስለ እናንተ አመሰግነዋለኹ፡፡ ረሃብ
የጤነኝነት ስሜት ነው፤ ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር መጓጓትም በመንፈሳዊ ሕይወት ጤነኛ መኾናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ክብር ምስጋና
ለስም አጠራሩ ይኹንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ፡- “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና” /ማቴ.5፡6/
ያለውም ይኽን የሚያስረዳ ነው፡፡
እንዴት
አድርጌ እንደማመሰግናችኁ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ጽድቅን ከመራባችኁና ከመጠማታችኁ የተነሣ ብፁዓን ኾናችኁ ሳለ አኹንም ይኽን ማድረጋችኁን
አላቆማችኁምና፡፡ ልጆቼ! አባታችን እግዚአብሔር እንዴት እንደሚወደን እያያችኁ ነውን? ከእኛ የሚመጣ ትንሽ መነሣሣት ካለ እግዚአብሔር
ከእኛ መነሣሣት በላይ በኾነ በረከት ነው የሚባርከን፡፡ እኛ ትንሽ ፈቃደኞች ስንኾን ርሱ ግን ከእኛ በላይ ብዙ ጸጋና በረከት ይሰጠናል፡፡
እኔም ይኽን እየተመለከትኩ እናንተን ለማስተማር እጓጓለኹ፡፡ በመንፈሳዊ
ሕይወታችን ለውጥ እንድናመጣ በጣም እጥራለኹ፡፡ ማስተማሬንም እቀጥላለኹ፡፡ እናንተ በመንፈሳዊ ሕይወታችኁ እንድትበረቱ ማንኛውንም
ዓይነት መሥዋዕት እከፍላለኹ፡፡ ምክንያቱም እዚኽ ብቻ እንድታቆሙ አልፈልግምና፡፡ ከዚኽም በበለጠ ወደ መንፈሳዊ ከፍታ እንድትወጡ
እፈልጋለኹ፡፡ ከዚኽ በበለጠ በምትውሉበት የሥራ ቦታ፣ በምትውሉበት የትምህርት ቦታ አስተማሪዎች እንድትኾኑ እፈልጋለኹ፡፡ ቆማችኁ
በማስተማር ሳይኾን መልካም ሥራችኁን አይተው ብዙዎች እንዲማሩ እፈልጋለኹና ትጋቴን ከወትሮው ይልቅ እጨምራለኹ፡፡ ድካሜ በከንቱ
እንዳልቀረ እያየኹ ነውና ከዚኽ የበለጠ ማስተማር እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡
ከምንም
በላይ ደስ ያለኝ ደግሞ የዘራነውን ዘር ቀን በቀን እየጐመራ ነው እየሔደ ያለው፡፡ በወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት እንቅፋት
አላጋጠመንም፡፡ እንደምታስታውሱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘሩ ምሳሌ ባስተማረው ትምህርት ከተዘራው ዘር አንድ አራተኛው ብቻ
ጥሩ ፍሬ ሲያፈራ ሦስት አራተኛው ግን እንደተጠበቀው አልኾነም፡፡ በመንገድ ዳር ላይ የወደቀው ዘር ወፎች መጥተው በልተዉታል፡፡
ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ የወደቀው ፀሐይ ሲወጣ ጠውልጎ ወዲያው ደርቋል፡፡ በእሾኽ መካከል የወደቀውም እሾኹ አንቆታል፡፡
በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ግን መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ አፈራ /ማቴ.13፡3-8/፡፡
እኔም ትምህርቴ
በመንገድ ዳር፣ ወይም በጭንጫ፣ ወይም በእሾኽ መካከል እንዳልወደቀ እየተመለከትኩ ነውና ትጋቴ እንዲጨምር አደረጋችኁኝ፡፡ መልካም
እርሻ ኾናችኋልና በትጋት እንዳስተምራችኁ አድርጋችኁኛል፡፡
እጅግ የምወዳችኁ
ልጆቼ! ይኽን ኹሉ የምላችኁ ግን በውዳሴ ከንቱ ላመሰግናችኁ ፈልጌ አይደለም፡፡ ይኽን ኹሉ እንድል ያደረገኝ አንድ ነገር ስለተመለከትኩኝ
ነው፡፡ ትናንት በዘነበው ኃይለኛ ዝናብ እንኳን አልተበተናችኁም፡፡ ዝናቡ እየዘነበባችኁም ቢኾን ቃሉን ለመማር ቁጭ ብላችኁ ነበር፡፡
ይኽ ለእኔ ትልቅ መልእክት አለው፡፡ እግዚአብሔር በእኔ በባርያው አድሮ የሚያስተምረውን ትምህርት በሙሉ ልባችኁ ኾናችኁ እየተቀበላችኁ
እንደኾነ አሳይቶኛል፡፡ እንድተጋ አድርጋችኁኛል የምለውም ስለዚኹ ነው፡፡
ቃለ እግዚአብሔርን
በማስተዋል የሚያደምጥ ሰው ቃሉ ከልቡናው ትከሻ አይወርድም፡፡ ዘወትር ያስታውሰዋል፡፡ ደግሞም ፈቃደኛ ለኾነ ልብ ማስተማር እንዴት
ደስ ይላል መሰላችኁ፡፡ መጽሐፍስ “ፈቃደኛ ለኾነ ልብ የሚያስተምር ሰው ብፁዕ ነው” ብሎ የለ /ሲራክ 25፡9/፡፡ ከጾም ውጤቶች
አንዱ ይሔ ነው፡፡ ገና ይኽን ስንዠምር ጾም የነፍስ የሥጋ ቁስልን ትፈውሳለች ያልኳችኁ ይኸው ነበር፡፡ ወዮ! ገና ከአኹኑ ይኸን
ያኽል ለውጥ ካየን፥ በሚቀጥሉት ቀናት ትምህርቱን የበለጠ ስንማርና የጾም ወራቱ ሲቀጥልማ እንዴት እንኾን ይኾን? ስለዚኽ የምወዳችኁ
ልጆቼ! ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ፡- “በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ የራሳችኁን መዳን ፈጽሙ” ብዬ እለምናችኋለኹ /ፊልጵ.2፡12/፡፡ ጠላት
ዲያብሎስን በምንም መልኩ ለስንፍና አንጋብዘው፡፡ ከዚኽ የበለጠ እንትጋ እንጂ ከእንግዲኽ ወዲኽ ወደኋላ መመለስ አያስፈልገንም፡፡
ዲያብሎስ አኹን ያፈራነውን ፍሬ እያየ መበሳጨቱ አይቀርም፡፡ ይኽን የያዝነውን ፍሬ ለማስጣልም እንደሚያገሣ አንበሳ ኾኖ በዙርያችን
እንደሚዞር በፍጹም መርሳት የለብንም /1ኛ ጴጥ.5፡8/፡፡ ነገር ግን ጠንቃቃዎችና በእግዚአብሔር ቸርነት የምንደገፍ ከኾነ ዲያብሎስ
ምንም ሊያደርገን አይችልም፡፡ ችግር የሚኾነው እኛው ወደኋላ ማየት ስንዠምር ነው፡፡
አያችኁ
ልጆቼ! ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ደንታ ቢስ ካልኾንን የምንለብሰው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ ብርቱ የኾነ የጦር ዕቃ ነው የሚያለብሰን፡፡
ስለዚኽ ኹለንተናችንን (ንግግራችንን፣ አለባበሳችንን፣ አሰማማችንን፣ ማንኛውንም አካሔዳችንን) በእግዚአብሔር ዕቃ ጦር ማለትም በእግዚአብሔር
ቃል የምናለብሰው ከኾነ ዲያብሎስ የሚወረውረው ጦር እኛን ሊጐዳን አይችልም፡፡ እንደዉም ተመልሶ ርሱን ነው የሚጐዳው፡፡
እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! ብቻ እኛ ፈቃደኞች እንኹን እንጂ፣ ብቻ እኛ
በጾም በጸሎት ቃለ እግዚአብሔርንም በማድመጥ እንበርታ እንጂ የእግዚአብሔር ቸርነት እኛን ከብረት በላይ ጠንካራ ነው የሚያደርገን፡፡
አኹን ከእኛ መካከል አንድን ብረት በቦክስ ቢመታ ማን ነው የሚጐዳው? ብረቱ ወይስ እጃችን? ብረቱ ምንም አይኾንም፤ እጃችን ግን
በእጅጉ ይጐዳል፡፡ የፈለገ ያኽል ጠንካሮች ብንኾንም ብረትን ማቁሰል አንችልም፡፡ ርሱ ነው የሚያቆስለን፡፡ በእግራችን ይኽን ብረት
ብንመታው እኛው ደም በደም ኾነን እንቆስላለን እንጂ ብረቱ ምንም አይኾንም፡፡ ልክ እንደዚኹ እኛም በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣
ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ በመቀበል፣ በመልካም ምግባር ኹለንተናችንን የምንከላከል ከኾነ፥ ዲያብሎስ እኛን ለመጉዳት የሚወረውረው
ጦር መልሶ የሚጐዳው ራሱ ዲያብሎስን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእኛ ጋር ስለሚኾን ጠላት እግዚአብሔርን አልፎ ሊያጠቃን አይችልም፡፡
ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ስለሚኾን ዲያብሎስን ልምሾና ምንም ዓቅም የሌለው ነው የሚያደርገው፡፡
ስለዚኽ
እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! መንፈሳዊ ትጥቅን እንታጠቅ፡፡ ሳንታጠቅ ከጠላት ዲያብሎስ ጋር አንታገል፡፡ ትርፉ መቁሰል አልፎም መሞት
ብቻ ነውና፡፡ ስለዚኽ መንፈሳዊውን ትጥቅ ለመታጠቅ የምናደርገው ትጋት ጨምረን እንቀጥልበት ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ የትም ብንሔድ
ይኽን መንፈሳዊ ትጥቃችንን ትተን መሔድ የለብንም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ብንመጣ፣ ወደ ሥራ ቦታ ብንሔድ፣ ወደ ትምህርት ቤት ብንሔድ፣
ወደ ቤታችን ብንሔድ፣ ብንነቃ፣ ብንተኛ ያለዚኽ ትጥቅ መንቀሳቀስ የለብንም፡፡ ትጥቃችንን ይዘን የትም ብንሔድ ጠላት ያጠቃናል ብለን
አንሰጋም፡፡ ደግሞም ይኽን ተሸክሞ ለመዞር (ክላሽ፣ መትረየስ፣ ሽጉጥ እንሚባሉት) እንደ ምድራዊ ትጥቆች አይከብድ፡፡ እንደዉም
የበለጠ ብሩሃን (ብርሃን የተሞላን) ያደርገናል፡፡ ይኽን ብርሃን እያየም ጠላት ዲያብሎስ ሊያጠቃን አይችልም፡፡ ከእኛ ጋር ያለውን
ብርሃን ለማየት ዓይኑ አይችልምና፡፡ እንዲኽ ከኾነም ደጋግሜ እንደነገርኳችኁ በጾም የሚገኘውን የነፍስ የሥጋ ቁስላችንን እናክማለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ