2014 ኖቬምበር 24, ሰኞ

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ሦስት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ ወዳጆች እንዴት ናችኁ? ዛሬም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስብከቱን ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ትምህርቱ ሊቁ ብዙ ነገር አስተምሮናል፡፡ በጾም ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እንደምንቀርብ፣ ምሥጢራተ እግዚአብሔርን ለማወቅና ለመረዳት ልቡናችን ብሩህ እንደሚኾን፤ ከዚኽ በተጨማሪ በጾም አዳም ከመደበሉ በፊት በገነት የነበረውን ሕይወት እንደምንለማመደው አስተምሮናል፡፡ ምክንያቱም አዳም ከመበደሉ በፊት የእንስሳት ተዋጽኦዎችን አይበላም ነበር፤ ይኽን መብላት የዠመረው ከበደለ በኋላ ነው፡፡ ሥጋውን የሚያስወፍሩና ነገረ እግዚአብሔርን ከማሰብ የሚያርቁ ተግባራትን አይፈጽምም ነበር፡፡ እኛም በመጾማችን ሥጋችንን እየቀጣን ሳይኾን በገነት የነበረውን አዳምን መስለን የበለጠ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንፈሳዊ መንገድ እንደኾነ አስተምሮናል፡፡ ዛሬስ ምን ብሎ ነፍሳችንን ይመግባት ይኾን? የሊድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም ይክፈትልን አሜን!!!

ዛሬ ብሩህ የኾነ ፊታችኁን እያየኹ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ደስታዬ ግን ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ እንደሚያመጡት ዓይነት ደስታ አይደለም፡፡ የእኔ ደስታ ከዚኽ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ቃለ እግዚአብሔር የተራበችውን ነፍሳችኁን ለመመገብ እንዴት ተጠራርታችኁ እንደመጣችኁ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ኹሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ የተናገረውን ቃሉን በተግባር ለመፈጸም /ማቴ.4፡4/ ይኽንን በዓል ለማክበርም እንዴት ጓጕታችኁ እንደመጣችኁ ዐይቼ ደስታዬ ልዩ ነው፡፡
 ስለዚኽ ኑ እንደ ገበሬዎች እንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ ገበሬዎች እርሻቸው እንደለሰለሰ፣ ምንም ዓይነት አረምም እንደሌለ ሲያረጋግጡ እኽል ይዘሩበታል፡፡ እኛም ኑ እንደገበሬዎቹ እንኹን፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት የልቡናችን እርሻ ከለሰለሰ፣ በዚኹ በልቡናችን እርሻ የሚዘራውን ቃለ እግዚአብሔር የሚያንቁትን እንደነ ስልቹነትና ግዴለሽነት የመሰሉ አረሞች ከተነቀሉልን፣ ልቡናችን ሰማያዊ ምሥጢራትን ለመመርመር ብሩህ ከኾነልን፣ ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊ ነገርን ማስቀደም ከዠመርን ከዛሬ ዠምረን ጠለቅ ባለ መልኩ መማማር እንዠምራለን፡፡ ልቡናችን እንዲኽ በቃለ እግዚአብሔር ከለሰለሰ በኋላ ቃሉን የበለጠ ብንዘራበት ፍሬ ማፍራት የሚችል ይኾናልና፡፡ ጾሙም እየገባ ስለኾነ ስለ ምድራዊ መብልና መጠጥ ማሰብ ስለቀነስን ቃሉን ለማድመጥ ምቹ ነው፡፡ አብዝቶ የበላና የጠጣ ሰው ቃሉን ተማር ብንለው እንዴት ሊሰማን ይችላል? ስለበላው ምግብና ስለጠጣው መጠጥ የሚያስብና ሥጋው ወፍሮ የሚያስቸግረው ሰው እንባችን እንደ (አባይ) ወንዝ እየፈሰሰ ብንነግረውም ደንታ አይሰጠውም፡፡
ስለዚኽ አኹን ቃሉን ለመማር ምቹ ጊዜ ነው፡፡ በቤታችን ውስጥ አንድን ነገር ለቤተሰባችን ማሳመን የምንፈልግ ከኾነ ከቤት ሠራተኛዋ ዠምሮ ኹሉም ሰው ሰላማዊና ለማድመጥ ዝግጁ የኾነበትን ሰዓት መምረጥ አለብን፡፡ ጾም ደግሞ የነፍስ ዕረፍትን የምትሰጥ፣ ሽማግሌዎችን ደስ የምታሰኝ፣ ለወጣቶች ቀና መንገድን የምታስተምር፣ ሰውን ኹሉ ጠንቃቃና አርቆ አሳቢ የምታደርግ፣ በየትኛውም ዕድሜ የሚገኘውን ሰው የምታስጌጥ፣ ኹሉንንም እንደ ዕንቁ ፈርጥ የምታሳምር ናት፡፡ ስለዚኽ ከዛሬ ዠምሮ በከተማችን ምንም ዓይነት ሁካታ አይኑር፤ ዳንኬራ ቤቶች የሚሔድ አይገኝ፤ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ቸልተኛ ሰው አይገኝ፤ እኅቶች አለባበሳቸውን ያስተካክሉ፡፡ ኹሉም ሰው ክርስቲያን ክርስቲያን ይሽተት፡፡ ከትናንትናው ጉባኤ በኋላ ዛሬ ላይ ሳያችኁ ይኽን እመለከታለኹ፡፡ በዚኽም ጾም ምን ያኽል ኃይል እንዳላት አስተዋልኩኝ፡፡ ጾም የሰዎችን አስተሳሰብ እንዴት እንደምትቀይር፣ የገዢዎች ብቻ ሳይኾን የተገዢዎችም፣ የአሠሪዎችም የሠራተኞችም፣ የወንዶችም የሴቶችም፣ የሀብታሙም የድኻውም፣ በአጠቃላይ የሰውን ልቡና እንዴት የማንጻት ኃይል እንዳላት ተገነዘብኩኝ፡፡ ገዢውም ተገዢውም ሲጾም ራሱን ዝቅ ማድረግ ይለማመዳል፡፡ ጾም ድኻውም ሀብታሙም እኩል የምታደርግ መሣሪያ ናት፡፡ በሚጾም ልቡና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ምንም ዓይነት ቦታ የለውም፡፡
 በዚኽ ጉባኤ ላይ የታደማችኁ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! ጾም ለየትኛውም ዓይነት መንፈሳዊና ሥጋዊ በሽታ እንዴት ዓይነት ፍቱን መድኃኒት እንደኾነ ተገነዘባችኁን? ይኽን ከእናንተ እየተመለከትኩ ትጋቴ ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ እጅግ ጨመረ፤ በመኾኑም ልቤ እናንተን ለማስተማር ተነሣሣ፡፡ እግዚአብሔር በእኔ በባርያው አድሮ የሚዘራው ቃል በጭንጫ ላይ ሳይኾን በመልካም እርሻ እየበቀለ እንደኾነ ዐየኹ፡፡ በአጭር ጊዜም ፍሬውን ማየት ችያለኹ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከዚኽ በኋላ እዚያ ለታደሙት ምእመናን በኦሪት ዘልደት (ዘፍጥረት) ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ እስከ ኹለት ያለውን ኃይለ ቃል ነው የሚተረጕምላቸው፡፡ በነገራችን ላይ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በዐቢይ ጾም በብዛት የሚተረጐመው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ነው፡፡ ከስሙ መረዳት እንደምንችለው መጽሐፉ ስለ ብዙ ልደታት የሚናገር ነው፡፡ የሰማይና የምድር ልደት፣ የሰው ልጅ ልደት፣ የሰንበት ልደት፣ የጋብቻ ልደት፣ የኃጢአት ልደት፣ የመሥዋዕት (የድኅነት) ልደት /3፡15/፣ የትንቢት ልደት /3፡15/፣ የሰው ሥልጣን ልደት /9፡1-6/፣ የሀገራት ልደት /11/፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ልደት /12፡1-3/፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ ክርስትና ይመጡ የነበሩት አዳዲስ አማንያንም በፋሲካ ነበር የሚጠመቁት፤ ማለትም ዳግም የሚወለዱት፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ጳውሎስ ጥምቀት ማለት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የምንተባበርበት ዳግም አዲስ ልደትም የምናገኝበት እንደኾነ ያስተማረውን ትምህርት በተግባር ለመፈጸም ነው /ሮሜ.6፡4-6/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የኦሪት ዘፍጥረትን በዚኽ ጊዜ የሚተረጕምላቸው ስለዚኹ ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ካስተማረው ትምህርት የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች እናገኛለን፡-
·        እግዚአብሔር ከመዠመሪያ አንሥቶ ለሰው የተናገረው በሰውኛ ቋንቋ እንደኾነ፤
·        ሰው ቢበድልም እንኳ ፍቅሩ አላስችል ብሎት ፍቅራችንን እናድሰው እያለ ከነ አዳም፣ ከነ ቃየን፣ ከነ ኖኅ፣ ከነ አብርሃም (በተለይ ከአብርሃም ጋር በቤቱ እንግዳ ኾኖ በመግባት) ዝቅ ብሎ እንደተጨዋወተ፤
·        ከእስትንፋስ ይልቅ ለሰው ልጆች ቅርብ ኾኖ ሳለ ሰዎች አላስተውል ቢሉት የበለጠ እንዲያውቁት ፈልጐ በሙሴ በኩል ደብዳቤ እንደላከላቸው፤
·        ሙሴም የተቀበለውን ደብዳቤ ለሕዝቡ በየጊዜው ያነብላቸው (ይነግራቸው) እንደነበረ፤
·        ሙሴ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር መኾኑን እንደነገራቸው፤ እኛም ይኽን አሜን ብለን ልንቀበል እንደሚገባን፤
·        የእግዚአብሔር አሠራር ከሰው አሠራር ልዩ እንደኾነ፡፡ ለምሳሌ ሰው አንድን ቤት ሲሠራ ከመሠረት እንደሚዠምር ቀጥሎም ጣርያና ግድግዳ እንደሚሠራ፤ እግዚአብሔር ግን ከሰማይ ማለትም ከጣርያው ዠምሮ ቀጥሎም ምድርን ማለትም መሠረቱን እንደፈጠረ፤
·        ሰው ከምድር አፈር ተፈጥሮ ሳለ አፈሩ እንዴት ብሎ ነርቭ፣ አጥንት፣ የደም ቧንቧ፣ ጡንቻ፣ ፀጉር፣ ምላስ፣ ሳንባ፣ ልብ እንደኾነ ስናስብ ልቡናችን ተደንቆ ተደንቆ ዝም ብለን እግዚአብሔርን ማድነቅ ብቻ ሊኾን እንደሚገባና ይኽን ላደረገ ጌታ ምስጋና ብቻ ማቅረብ እንደሚገባን፤
 ይኽንና ይኽን የመሰለ ጣፋጭ ትምህርት ካስተማራቸው በኋላ ሊቁ የሚከተለውን ይነግራቸዋል፡-
እጅግ የምወዳችኁና እዚኽ ጉባኤ ላይ የታደማችኁ ቃሉንም ያዳመጣችኁ ምእመናን ሆይ! አኹን ለጊዜው የትርጓሜው ትምህርታችን ገታ እናድርግና አንድ ነገር ታደርጉ ዘንድ እለምናችኋለኹ፡፡ ወደየቤታችን ስንሔድ ቃሉን ለመተግበር እንጣጣር፡፡ ቃሉን በልቡናችን ጽላት እንቅረጸውና ዘወትር እንደ እንጀራ እንመገበው፡፡ አባቶች ለቤተሰቦቻችኁ ዛሬ የተማርነውን ትምህርት ድገሙላቸው፡፡ እኛቶችም ይኽን ከባሎቻቸው ያድምጡ፡፡ ልጆች ከእናቶቻቸው ይኽን ያድምጡ፡፡ ልጆች ብቻ አይደለም፤ ከቤት ውስጥ ያሉት እንስሳትም ይኽን ያድምጡ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ፣ በዚኽ ጉባኤ የተማርነውን ትምህርት ከቤታችን ሔደን በተግባር የምንኖረውና ቃሉን ደጋግመን የምንበላው ከኾነ ቤታችን ቤተ ክርስቲያን ትኾናለች፡፡ ዲያብሎስም ወደ ቤታችን መግባት አይቻለውም፡፡ የነፍሳችን ጠላት የኾነው ርኵስ መንፈስ ተኖ ይጠፋል፡፡ በርሱ ፈንታም ወደቤታችን መንፈስ ቅዱስ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ ሰላምና ፍቅር፣ አንድነትና መስማማት ወደ ቤታችን ከነጓዛቸው ሰተት ብለው ይገባሉ፡፡ ይኽን ያደረጋችኁ እንደኾነ እኛንም የበለጠ ታተጉናላችኁ፡፡ የቃሉን ምሥጢር የበለጠ እንድናስተምራችኁ ታበረቱናለችኁ፡፡ ገበሬ የዘራውን እኽል ፍሬ ሲያፈራለት አይቶ እጅግ ደስ እንደሚሰኝ ኹሉ እኛም ደስ እንሰኛለን፡፡ ተደጋግፈንም ክርስቲያን ክርስቲያን የምንሸት እንኾናለን፡፡
ስለዚኽ ደጋግሜ እንደነገርኳችኁ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የትም ብንኾን ቸልተኞችና ደንታ ቢሶች ልንኾን አይገባንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “መልካሙን ሥራችኁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችኁን እንዲያከብሩ ብርሃናችኁ እንዲኹ በሰው ፊት ይብራ” /ማቴ.5፡16/፡፡ የተማርነውን ትምህርት በተግባር የምንፈጽም ከኾነ በዚኽ ጉባኤ የተማርነው ትምህርት ግቡን መትቷል ማለት ነው፤ ፍሬ አፍርተናል ማለት ነው፤ በእውነት ክርስቶስን መስለነዋል ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ያዕቆብ እንደነገረን እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው፤ ሥራም ያለ እምነት እንደዚኹ የሞተ ነው /ያዕ.2፡26/፡፡ የፈለገ ያኽል በእምነታችን ምንም እንከን የሌለን ብንኾን፣ ነገር ግን በተግባራዊ ሕይወታችን ሰነፎችና በኀጢአት ሕይወት የምንኖር ከኾነ ስሕተት የሌለው እምነታችን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ልክ እንደዚኹ እውነተኛ እምነት ውስጥ ሳንኖር የፈለገ ያኽል መከራ ብንቀበልም፣ የምድር መልአክ ብንመስልም አይጠቅመንም፡፡ ስለዚኽ በየጊዜው የምንማረው ትምህርት ጊዜአዊ ስሜታችንን የሚያረካ ሳይኾን ሕይወታችንን የሚቀይረው ሊኾን ይገባል፡፡ ጌታችን ሲናገር፡- “ይኽን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ኹሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል” ብሏል /ማቴ.7፡24/፡፡ ይኽ ሰው ልባም የተባለው ቃሉን ስለሰማ ብቻ አይደለም፤ ቃሉን ሰምቶ እንደ ዓቅሙ ለመተግበር ስለሚጣጣር እንጂ፡፡ ቃሉን ሰምቶ ለጊዜው የሚደሰትና “አቤት የዛሬው ጉባኤ ሲያስደስት” ብሎ የማይተገብር ሰው ግን ሰነፍ ሰው ነው፡፡ ይኽ ሰነፍ ሰውም ቤቱን በአሸዋ እንደሠራ ሰው ነው፡፡ ቤቱን በአሸዋ የሠራ ሰው ነፋስ ወይም ጐርፍ ሲመጣ ይፈርሳል፡፡ ፈተና ባጋጠመው ሰዓት ዐለት በተባለው ክርስቶስ ስላልቆመ ይሸነፋል፡፡ ልባም ሰው ግን በእነዚኽ ፈተናዎች የበለጠ ይፈካል፡፡ ክርስቶስን እየመሰለ ይሔዳል፡፡ ልባሙ ሰው ፈተና ባጋጠመው መጠን ከክርስቶስ ጋር ስለሚኾን መልካም ሥራው የበለጠ እየታየ ይሔዳል፡፡ ሰነፍና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ደንታ የሌለው ክርስቲያን ግን የፈለገ ያኽል እዚኽ ጉባኤ መጥቶ ቁጭ ብሎ ቢማርም ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ ይወድቃል፡፡ ፈተናው ከብዶት ሳይኾን እርሱ ሰነፍ ስለኾነ (ክርስቶስ አብሮት ስለሌለ)፡፡
ስለዚኽ የጦር ዕቃችንን እናንሣ፡፡ የአንድ ሳምንት ጿሚዎች ሳንኾን ዘወትር ብርቱዎች እንኹን፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ በፈተና እንጸናለን፡፡ ትዕግሥተኞች እንኾናለን፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ከምናገኘው ደስታ ጋር ስናነጻጽረው የአኹኑ ሕይወታችን ፈተና ምንም እንዳልኾነ እናውቃለን፡፡ አኹን ትዕግሥተኞችና በፈተና የምንጸና ከኾነ 30፣ 60፣ 100 ያማረ ፍሬ ማፍራት እንችላለን፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር በፈተና እንድንጸና ይርዳን፡፡ የይምሰል ሳይኾን የእውነትና እግዚአብሔር የሚወደው የጾም ወራት ያድርግልን፡፡ ዳግም በመጣ ጊዜ የሕይወት ቃል እንዲያሰማን ፈቃዱ ይኹን፡፡ ምስጋና፣ ክብር፣ አኰቴት ለአብ፣ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ይኹን፡፡ አሜን!!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...