2014 ዲሴምበር 30, ማክሰኞ

‹‹ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት መላ ዘመናቸውን አሳልፈዋል›› – የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዜና ሕይወት እና


The Late Accomplished Scholar Lique Kahinat Kinfe Gabriel Altaye
(ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. – ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
  • ከትምህርት ቤትና ከመጻሕፍት ያገኙት ዕውቀት አራት ዓይና ያደረጋቸው ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በተጠያቂነት ደረጃ የሚገኙና አገልግሎታቸውም ሙሉ ነበር፡- ቀዳሽና መዘምር፤ ጋዜጠኛና ሰባኬ ወንጌል፤ ጸሐፊና ተርጓሚ፤ አስተዳዳሪና መምህር፤ የአውራጃ አብያተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ ኤርትራን ጨምሮ የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስምንት መምሪያዎች ምክትልና ዋና ሓላፊ፡፡
  • ሊቁ በሓላፊነት በተመደቡባቸው ቦታዎች ኹሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተማር፤ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፤ ሰበካ ጉባኤያትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር፤ አገልጋዮች ካህናትን በትምህርትና ሥልጠና በማብቃት አስተዳደርን ለማሻሻልና ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ድርጅት በንዋያተ ቅድሳትና በጽ/ቤት መገልገያዎች ለማሟላት እንደነበር ዜና ሕይወታቸው በስፋት አትቷል፡፡
  • የአብነት ት/ቤቶችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎችንና ኮሌጆችን በበላይነት በሚያስተባብረው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ለሦስት ጊዜያት በዋና ሓላፊነት ተመድበው የላቁ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከእኒኽም በመንግሥት የተወረሱ 27 መንፈሳውያንና ዘመናውያን ት/ቤቶችን በተለይም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲመለስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐሳብ በማቅረብና በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነም በኋላ የበኩላቸውን ክትትል በማድረግ መንፈሳዊ ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያናችን ተመልሷል፡፡
  • በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾነው ከተመደቡበት ጥቅምት ወር ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው መዳረሻ ከሌሎች ሊቃውንት ጋራ በመኾን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል÷ ቤተ ክርስቲያናችን የራስዋ የተጣራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት 81 ቅዱሳት መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ መሠረትነት አርመውና አስተካክለው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ለካህናትና ምእመናን በሴሚናር ሲያሰለጥኑበት የቆዩት የቃለ ዐዋዲ ደንብ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሻሻል የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት›› መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በአንድነት አዘጋጅተው ለምእመናን እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡ በርካታ የቅዱሳን ገድላትና የመላእክት ድርሳናት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡
  • የቤተ ክህነት ሥነ ጽሕፈት ኮሚቴ አባል በመኾን በዐበይት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚወጡ ኅትመቶችና በሚሠራጩ የሬዲዮ መግለጫዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና በምርምር የተደገፉ፤ አንባቢንና አድማጭን የሚያረኩ በርካታ ጽሑፎችን በማቅረብ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡ በግል አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን››፤ ‹‹ሳታዩት የምትወዱት›› በሚል ለትምህርትና ለተግሣጽ ባሰራጯቸው ሥራዎቻቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለነገረ ሃይማኖት መጠበቅ ተከራክረዋል፤ ተሟግተዋል፡፡ በተለይም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ክፍል ኾኖ እንዲሰጥ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ መጽሐፉም በኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ለመምህራንና ለተማሪዎች መመሪያና ማጣቀሻ ኾኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
  • የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊም ነበር፡፡ ከግንቦት ፲፬ – ፴ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. የያሬዳዊ ማሕሌትን ዐውደ ትርኢት በምዕራብ ጀርመን ለማሳየት ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ በመኾን የማሕሌታችንን ሥርዐት አሳይተው ተመልሰዋል፡፡ እ.አ.አ ከሐምሌ ፱ – ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ‹‹ክርስቶስን ዛሬ መስበክ›› በሚል ርእስ በእስክንድርያ በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክተኛ በመኾን ጥንታዊ እምነቷንና ሥርዐቷን በቃልም በጽሑፍም በመግለጥ ተሳትፈዋል፡፡ በየመንና በጅቡቲ ለሚኖሩ ምእመናን ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡፡
*           *           *
  • ከደግ ቤተሰብ ተገኝተው በመልካም አስተዳደግ የወጡት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በትዳራቸውም የጋብቻ ጽናት ምሳሌነታቸውን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በተክሊልና በሥርዐተ ቁርባን ካገቧቸው የሕግ ባለቤታቸው ወ/ሮ ድጋፍ ወርቅ ፈቄ ጋራ የ፶ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን ከኹለት ዓመት በፊት አክብረው ነበር፡፡ ስምንት ልጆችንና ዐሥር የልጅ ልጆችን አፍርተውም ለወግ ለማዕርግ አብቅተዋል፡፡
  • ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በሢመተ ክህነት÷ በ፲፱፻፵፩ ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕርገ ዲቁና፤ ሰኔ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሢመተ ቅስና ተቀብለዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው በዜማ፣ በአቋቋም፣ በቅኔና በነገረ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ኾኖ ትርጓሜ መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ከተለያዩ ሊቃውንት በመማር ምስጢር አደላድለዋል፡፡ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ የነገረ መለኰት ትምህርት የቴዎለጂ ዲፕሎማ ተቀብለዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት እና በዳግማዊ ምኒልክ የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
  • ‹‹በዕለተ ሰንበትና በዐበይት በዓላት እየቀደሱና እያወደሱ፣ በሥራ ቀናት በቢሮ እየሠሩ፣ ለምእመናን ወንጌል እየሰበኩ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እያስተማሩና እያሠለጠኑ ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሙሉ አገልግሎት ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡
Lique Kahinat Kinfe Gabriel Funeral
ዕረፍቱ ለሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ (ሚያዝያ 19 ቀን 1929 – ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓ.ም.)
  • በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋት አውራጃ በማፉድ ወረዳ በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም አጥቢያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ስማቸው ክንፈ ገብርኤል፤ ያረፉትም የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዋናው በዓል በሚከበርበት በታኅሣሥ ገብርኤል፤ ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ለነፍሳቸው ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፤ በእርሳቸው እግር ምሁራንን እንዲተካልን ፈጣሪን በጸሎት እንለምነዋለን፡፡››
የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን ዜና ሕይወት ወዕረፍት ከዚኽ በታች ይመልከቱ፡፡

ሰበር ዜና – የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂው ሊቅና ኹለገቡ ባለሞያ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ

Lique Kahinat Kinfe Gabriel Altaye
የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (Liturgical Theology) ተጠያቂው ሊቅ÷ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ
ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና አገራችን ኢትዮጵያን በክህነት፣ በሊቅነት፣ በመምህርነት፣ በአስተዳደር እና በጸሐፊነት ሞያቸው በብቃትና በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ፡፡
የሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ሞተ ዕረፍት የተሰማው÷ ዛሬ፣ እሑድ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ቀበና መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ነው፡፡
በመኖርያ ቤታቸው÷ በቤተ ሰዎቻቸውና በወዳጆቻቸው መካከል ያረፉት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በበርካታ ዘርፎችና በተለያዩ የሓላፊነት ደረጃዎች ሲሠሩ ከኖሩበት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከነበረባቸው ከፍተኛ የደም ግፊትና የነርቭ ሕመም ጋራ በተያያዘ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በጡረታ የተገለሉ ቢኾንም በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባልነታቸው አገልግሎታቸውን ቀጥለው ቆይተዋል፡፡
ከዘመናችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በልዩነት የሚታወቁትና የሚታወሱት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (Liturgical Theology) ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ዘርፍ (discipline) ኾኖ ጎልቶ እንዲወጣና በሥርዐተ ትምህርትም መርሐ ትምህርት ተቀርፆለት እንዲታወቅ÷ በምሁራን አነጋገር የራሱ ጉባኤ እና ወንበር እንዲኖረው÷ ባደረጉበት ጥረታቸውና ድካማቸው ነው፡፡
ለዚኽም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ መጻሕፍት የሚገኙትን የአምልኮ መፈጸሚያ ሥርዓታት በተመጠኑ ገጾች በማስተጋባት ለጥናት እንዲመች አድርገው ያዘጋጁበት ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› የተሰኘው ዝነኛው መጽሐፋቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ባለፉት ዐሥርት ዓመታት፣ በቴዎሎጂ ኮሌጆቻችን፣ በካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና በሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ጸሎተ ቅዳሴውንና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ ተግባራዊውን ትምህርተ መለኰት (Practical Theology) ለማስተማር በመመሪያነትና ማጣቀሻነት እያገለገለ የሚገኘው ይኸው የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› መጽሐፍ ዛሬም በተደጋጋሚ የመታተም ዕድል ማግኘቱም ከፍተኛ ጠቀሜታውን ያሳያል፡፡
ሊቁ መጽሐፉን ከማዘጋጀት ባሻገር በመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን (በቅድስት ሥላሴ፣ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ) በከፍተኛ ደረጃ እንዲኹም በበርካታ መድረኮች ብዙ ሺሕ ምእመናንን ለዓመታት አስተምረውበታል፤ ሳይፋልስ ተጠብቆ እንዲኖርም ሳያሰልሱ መክረውበታል፡፡ በዚኹ መጽሐፍና ከሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ በየጊዜው ባዘጋጇቸው በርካታ ጽሑፎቻቸው ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለመበረዝ በኅቡእም በገሐድም የሚያሤሩ አላውያንና መናፍቃንን ሞግተውበታል፤ ገሥጸውበታል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር የሚመራው ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደ ተቋም መደራጀት በጀመረባቸው ዓመታት አገልግሎታቸውን የወጠኑት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል÷ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ‹‹በእሑድ ትምህርት ቤት›› በየአጥቢያው አሰባስቦ በማስተማር ሰንበት ት/ቤቶች አኹን በሚገኙበት መልክ እንዲቋቋሙ የማድረጉን ጅምር ከወሰዱት፣ ስብከተ ወንጌልን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች (በጽሕፈትም በቃለ ስብከትም) በማስፋፋት ከሚታወቁት መምህራን ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የቀሳውስትና የመምህራን ማሠልጠኛ በተለይም በቅኔ፣ በአቋቋም እና በመጻሕፍተ ሊቃውንት በጉባኤ ያካበቱትን ሞያቸውን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በጀመሩት አገልግሎታቸው በብዙ አትርፈውበታል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅን በምክትል ዲንነት መርተዋል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰው ኃይል አስተዳደርና የአስተዳደር መምሪያ በሓላፊነት ተመድበው በምስጉንነት ሠርተዋል፡፡
በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂነታቸውና ጠበቃነታቸው እንደ ዓምድ የሚታዩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ በመድረክ ትምህርትና በቢሮ ሓላፊነት ብቻ ሳይወሰኑ በቤተ መቅደሱና በቅኔ ማሕሌቱ ክህነታዊ አገልግሎት ሕመማቸውን ታግሠው ጭምር እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው የጸኑ ብርቱ አባት ነበሩ፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የቀብር ሥነ ሥርዐት ነገ፣ ታኅሣሥ ፳ ከቀኑ በ9፡00 ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል እና በአባትነት ትጋት ሲያገለግሏቸው የኖሩት ምእመናን ልጆቻቸውና ወዳጆቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጦአል፡፡
የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የአባታችንን ነፍስ ያሳርፍልን፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...