2014 ዲሴምበር 30, ማክሰኞ

የትልቁ ዋርካ ትልቁ ቅርንጫፍ



ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓም በቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከታወቁት ሊቃውንት መካከል አንዱን አጥተናል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን፡፡ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመቆርቆር፣ በማስተማርና በመጻፍ የምናውቃቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያገለገሉ፤ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ጥያቄዎቹን በመመለስና አስረግጠውም በማስረዳት የምናደንቃቸው ነበሩ፡፡
ዜማ፣ አቋቋም፣ የአማርኛ ሰዋስው፣ ቅኔና የግእዝ አገባብ፣ ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ነገረ መለኮት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በዘመናዊ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን ስናይ፤ በአንባቢነታቸው ጥንታውያንና ዘመናውያን መጻሕፍትን የሚያገላብጡ ብቻ ሳይሆኑ በላዔ መጻሕፍት እንደነበሩ በሌሎቹ ሊቃውንት ሲመሰከርላቸው፤ በምሥራች ድምጽ ሬዲዮ ትምህርት በመስጠት፣ በታሪክና ድርሰት ክፍል ለዐሥር ዓመታት በማገልገል፤ የመዝሙር ክፍልን በመምራት፣ የዜና ቤተ ክርስቲያንን በምክትልና በዋና አዘጋጅነት  በማገልገል፣ እንዲያውም ጋዜጣውን የጋዜጣ መልክ በማስያዛቸው በ1962 ዓም መሸለማቸውን  እያዘከርን የተጓዙበትን የዕውቀት ጎዳና ስንመረምር ያጣነው አንድ ሰው ብቻ ባለመሆኑ፡-
አራት ሰው ሞተ ተቀበረ ዛሬ
ድጓ ጾመ ድጓ መዋሥዕት ዝማሬ
ተብሎ ለሊቁ የተገጠመው ሙሾ ለእርሳቸውም ይስማማቸዋል እንላለን፡፡ 

የየረርና ከረዩ አውራጃ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸሐፊ፣ የቀበና አቦ አስተዳዳሪ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ጸሐፊ፣ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የከፋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ የቁጥጥር አገልግሎት ኃላፊ፣ የበጀትና ንብረት መምሪያ ኃላፊ፣ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህት ቤት ምክትል ዲን፣ እየሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ማገልገላቸው ስንመለከት፡-
ቀባሪዎቹን
አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ
የቀለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ
እንላቸዋለን፡፡
በ1977 በምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ዜማ ለማሳየት ከተጓዘው ልዑክ አንዱ ነበሩ፤ በ1995 የዓለም አብያተ ክርስቲያናት በእስክንድርያ ከተማ ባደረገው ጉባኤ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ነበር፣ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መልክ ሲዘጋጅ በብርቱ ካገለገሉት ሊቃውንት አንዱ ነበሩ፣ የመንና ጅቡቲ የሚገኙ ምእመናንን ለማስተማር በየዓመቱ ይጓዙ ነበረ፡፡ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ሆነው ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ይህንን ስንመለከትም
እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር
ዕውቀት ተሸክሞ መጣልህ መምር
እንለዋለን፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሚያዘጋጁት ጉባኤ ልጆችን ሳይንቁ፣ ክፍለ ሀገር በሚዘጋጅ ጉባኤ ለመንገዱ ሳይሰቀቁ በመጓዝ ያስተማሩ የዘመናችን ሐዋርያ ናቸው፡፡ ክህነትን፣ ትምህርትንና ጽሕፈትን አንድ አድርገው የያዙ፤ በተለይም ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን›› እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ እንዲወጣ በብርቱ የደከሙ ሊቅ ናቸው፡፡ ድካማቸው ፍሬ አግኝቶ በየጊዜው ያዘጋጇቸው መጣጥፎችና መጻሕፍት ዛሬ ከኮሌጆች እስከ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ድረስ የማስተማርያ ዋና መሣሪያዎች ሆነዋል፡፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንድ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ሚያዝያ 19 ቀን 1929 ዓም  ይፋት ውስጥ  ደብረ ምሥራቅ ሾተል አምባ በኣታ አጥቢያ ተወልደው፣ በ1941 ዓም ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዲቁና፣ በ1959 ዓም ቅስና ተቀብለው፤ አራት ወንዶችና አራት ሴቶች ወልደው፣ አሥር የልጅ ልጆች አይተው በ78 ዓመታቸው የተለዩን ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ በዕለተ ዕረፍታቸውና ቀብራቸው ብዙዎችን ያስደነቁ ሁለት ነገሮች ተከስተዋል፡፡ የመጀመሪያው ክንፈ ገብርኤል ተብለው ተጠርተው በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል(ታኅሣሥ 19 ቀን) ወደ ፈጣሪያቸው መጠራታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን የሕይወት ታሪካቸው በሚነበብበት ጊዜ ከትልቅ ዋርካ ላይ ማንም ሳይነካው አንድ ትልቅ ቅርንጫፍ ተገንድሶ መውደቁ ነው፡፡
ቦታው የነበሩ፣ ይህንንም ነገር የተመለከቱ ሁሉ ታሪኩን በካሜራቸው ሲቀርጹና ከታላቋ ዋርካ ከቤተ ክርስቲያን ብዙዎችን የያዘው አንዱ ታላቅ ቅርንጫፍ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ዛሬ መሰናቱን በኀዘን ሲተረጉሙ ነበር፡፡ የቅርንጫፉን ቅጠልም ብዙዎቹ ተሻምተው ወስደውታል


በረከታቸው ይደርብን፡፡  

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...